Monday, May 9, 2016

“የሌላውን አስመስሎ የዘፈነን አላደንቀውም”

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
ድምፃዊው 150ሺ ብር ለበጐ አድራጐት ድርጅት ለገሰ

የትዝታው ንጉስ በሚል የሚታወቀው አንጋፋው ድምፃዊ (ዶ/ር) አርቲስት ማህሙድ አህመድ ባለፈው ሳምንት በማሪዮት ኢንተርናሽናል ሆቴልና በያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት በተለያዩ
ዝግጅቶች የ75ኛ ዓመት የልደት በዓሉን አክብሯል፡፡ የልደት በዓሉን ምክንያት በማድረግም ከልጅነት እስከ እውቀት ከተነሳቸው በርካታ ፎቶግራፎች መካከል 75 ያህሉ ተመርጠው
ለእይታ ቀርበውለታል፡፡ የፎቶ ኤግዚቢሽኑ በተከፈተበት ወቅት ባደረገው ንግግርም፤ “ብዙ የሙያ ጓደኞቼን በሞት አጥቻለሁ፤ እኔ እስካሁን በጤናና በሰላም እዚህ በመድረሴ
እግዚያብሔርን አመሰግናለሁ” ሲል የለቅሶ ሳግ ንግግሩን አቋርጦታል፡፡ አርቲስቱ ባለፈው እሁድ “ሲንደርታ ዴቨሎፕመንት ኢትዮጵያ” በተሰኘ የበጐ አድራጐት ድርጅት ውስጥ
በመገኘት ከ45 ወላጅ ያጡ ህፃናት ጋር የፋሲካን በዓል ሲያጫውታቸውና ሲዘፍንላቸው ያሳለፈ ሲሆን ውሎ ምሳ አብሯቸው ከተመገበ በኋላ ለድርጅቱ 150ሺህ ብር ለግሶ
አምባሳደራቸው እንደሚሆን ቃል ገብቶላቸዋል፡፡ በፎቶ ኤግዚቢሽኑ መክፈቻ ላይ የተገኘችው የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ከአንጋፋው ድምፃዊ ማህሙድ አህመድ ጋር
አጭር ቃለምልልስ አድርጋለች፡፡ እነሆ፡-


75 ዓመታት በህይወት መቆየት… ሶስት መንግስታትን ማየት… በሙያ ለረጅም ጊዜ በሰው ተወድዶ መቆየት ምን ስሜት ይሰጣል?
እ…ም…ምን ስሜት ይሰጣል ነው ያልሺኝ? ከባድ ጥያቄ ነው፡፡ ስሜት እንደ ምግብ… እንደ መጠጥ ጣዕሙ በቃላት የሚገለፅ ባለመሆኑ ጥያቄው ከባድ ነው፡፡ የሆነ ሆኖ የማልዋሺሽ በጣም ደስታ ይሰማኛል፡፡እግዚአብሔር ዕድሜና ጤና ሰጥቶ ለዚህ ስላበቃኝ ደስተኛ ነኝ፡፡ 
እስካሁን በጤናህ ላይ ያጋጠመህ ችግር የለም? እድሜን ተከትለው የሚመጡ የጤና ችግሮች ይኖራሉ ብዬ ነው?
እግዚአብሔር ይመስገን እስካሁን ምንም የጤና እክል አላጋጠመኝም፤ ከዚህ በኋላ ቢያመኝም እችለዋለሁ፡፡ እንዳልሽው የሰው ልጅ እድሜው ሲገፋ የማያመው ነገር የለም፤ ከእነምሳሌው  አባቶች፣ “እርጅና ብቻህን ና” ይላሉ፡፡ እርጅና ብቻውን አይመጣም፤ ብዙ ጓዝ ያስከትላል፡፡ ቢሆንም እኔ እስካሁን ጤነኛ ነኝ፤ ከዚህ በኋላ የሚመጣውን ነገር አላውቅም፡፡ 
ለልደትህ የዛሬ ሳምንት ከአሜሪካ መምጣትህን ሰምቻለሁ፡፡ ኑሮህ ጠቅላላውን አሜሪካ ሆኗል ማለት ነው?
ኑሮዬን ጠቅልዬ አሜሪካ አላደረግሁም፡፡ እዚያ የምሄደው ለስራ ነው፡፡ እዚያ የሚያሰሩኝ ሰዎች ረጅም ቀጠሮ እየያዙ ነው የሚወስዱኝ፡፡ የተለያዩ ኮንሰርቶች እየሰራሁ ስራዬ ሲያልቅ ወደ አገሬ እመለሳለሁ፡፡ ከዛም ወደ ኢትዮጵያ ስመጣ በቀጠሮ ነው፡፡ አሁንም ለዚህ የልደት በዓል በ “አሻራ ፊልምስ” ሃላፊዎች ቀጠሮ ተይዞልኝ ነው የመጣሁት፡፡ 
ከድምፃዊ ጐሳዬ ተስፋዬ ጋር “አይባባም ሆዴ” የተሰኘ ተተኪ ማፍራትህን የሚገልጽ ነጠላ ዘፈን አውጥታችኋል፡፡ በእርግጥ ተተኪ አፍርቼአለሁ ብለህ ታስባለህ?
ማፍራቴን እርግጠኛ ነኝ፤ እንደውም ከሚጠበቀው በላይ ተተኪዎች አሉ፡፡
በምሳሌነት የምትጠቅስልኝ ይኖራሉ?
በድምፅ፣ በግጥም፣ በዜማና በአጠቃላይ ሁኔታዎች የተሻለ ነገር እየመጣ እንጂ ወደ ኋላ አልተጐተተም፡፡ ይህን ያህል ነው ብዬ ልናገረው በማልችለው ሁኔታ በቂ ተተኪ አለ፡፡ አዲሱ ትውልድ በጣም ፈጣንና ጥሩ ጥሩ የሙዚቃ ስራ እየሰራ ነው፡፡ እድገታችሁን በኔ መጠን አድርጉ ማለት አልችልም፤ ከኔ የተሻለ ይሰራሉና፡፡ አሁን ጊዜው ሙዚቃን የተሻለ አድርጐ ለመስራት አመቺ ነው፡፡ 
የአንተን ድምጽ በማስመሰል የሚዘፍኑ ወጣቶች አሉ፡፡ የተደነቅህባቸውና ያስደመሙህ ድምፃውያን አሉ?
በመጀመሪያ እኔ እኔ ነኝ፤ ማንም የእኔን አስመስሎ ሊጫወት አይችልም፡፡ ምክንያቱም መቶ በመቶ አስመስሎ መዝፈን ቀላል አይደለም፡፡ ደግሞ ቢያስመስልም አላደንቀውም፡፡ 
ለምን?
በቃ አላደንቀውም፡፡ ያ ወጣት ራሱን ማውጣት ነው ያለበት፡፡ አንድ ዘፋኝ የሌላውን አስመስሎ ሲዘፍን አላጨበጭብለትም፡፡ የእከሌን ዘፈን የሚጫወተው፣ ያ የማህሙድን ድምጽ የሚያስመስለው፣ ያ የጥላሁንን ዘፈን የሚዘፍነው እየተባለ ጣት መጠቋቆሚያ እንዲሆን አልፈልግም፡፡ ይሄ ሰው ራሱን መፍጠርና ከሌላ ሰው ድምጽ ተፅዕኖ መውጣት አለበት፡፡ እንዲህ አይነቱን ዘፋኝ ባደንቀው ምንም ስለማላመጣ ከማደንቀው ብመክረው ይሻለኛል፡፡ ምክር ብዙ ውጤት ያመጣል፡፡ 
ግን እኮ አንዳንድ ድምፃዊያን እነሱን አስመስለው ለሚዘፍኑ ወጣቶች ሽልማት እስከ መሸለም ሁሉ ይደርሳሉ?
እኔ ሌላውን ወክዬ መናገር አልችልም፤ ያ የእነሱ ስሜትና ፍላጐት ነው፡፡ የእኔን ተናግሬያለሁ፤ እንኳን መሸለም አይደለም አድናቆት አልቸርም፡፡ ጥሩ የሚሆነው ማስመሰልን ማበረታታት ይሁን ራሱን ፈልጐ እንዲያገኝ መርዳት ሁሉም የራሱን ፍርድ የሚሰጥበት ይሆናል፡፡ 
ወደፊት ከአንተ ምን አዲስ ነገር እንጠብቅ? ምን ለመስራት አስበሀል?
በቅርቡ አዲስ ነገር ብትጠብቁ ደስ ይለኛል፡፡ ምክንያቱም አዲስ ዘፈን ሰርቼ ጨርሻለሁ፡፡ 
በቅርቡ ማለት መቼ ነው?
በዚህ ቀን ነው ለማለት አልችልም፡፡ ያ ጊዜ ለእኔም ይደንቀኛል፡፡ እግዚአብሄር ያለ ቀን ብቅ ይላል፡፡ ዋናው አዳዲስ ዘፈኖች ተሰርተው መጠናቀቃቸውን አድናቂዎቼ እንዲያውቁ እፈልጋለሁ፡፡ 
የ “አሻራ ፊልምስ” ባለቤቶች በህይወት እያለህ ልደትህን ለማክበር ሲታትሩ ምን ተሰማህ?
እውነት ለመናገር በጣም ነው ደስ ያለኝ፡፡ በደስታ ነው ጥያቄያቸውን የተቀበልኩት፡፡ እነሱ እኔን ለማክበርና ልደቴን ለማሰብ ደፋ ቀና ሲሉ፣ እኔ እንዴት በደስታ አልቀበልም?! በዚህ አጋጣሚ የ“አሻራ ፊልምስ” ዳይሬክተርና ፕሮዲዩሰርን ታጠቅ ተ/ማሪያምንና የስራ ባልደረቦቹን በጣም አመሰግናለሁ፡፡ 
ዝግጅታቸውን እንዴት አገኘኸው? 
በጣም ጥሩ አድርገው ነው ያዘጋጁት፤ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡
ልደትህን አስመልክቶ በቀረበው የፎቶ ኤግዚቢሽን ላይ 75 ፎቶዎች ለእይታ ቀርበዋል፡፡  እንደው በአጠቃላይ ምን ያህል ፎቶዎች አሉ? 
ከ200 በላይ የተዘጋጁ ፎቶዎች ይኖራሉ፤ ይህ የእኔ ግምት ነው፡፡ ለስራ በየሀገሩ ስሄድ የተነሳኋቸው ፎቶዎች አልቀረቡም፡፡ በርካታ ፎቶዎች ናቸው ያሉኝ፡፡ 
በህይወትህ ይህን ሳላደርግ ቀርቻለሁ ብለህ የሚቆጭህ ነገር አለ?
በፍፁም!! እኔ ከጫማ ጠራጊነት ተነስቼ ወደ ዕውቅና ደረጃ የደረስኩ ሰው ነኝ፡፡ ተወዳጅነትና የሰው ፍቅር ተቀዳጅቻለሁ፡፡ በጣም ብዙ ነገር ያየሁና እግዚአብሔርን የማመሰግን ሰው ነኝ፤ ምንም የሚቆጨኝ ነገር የለም፡፡ በሰው ተወዶ በሰው ተከብሮ፣ ጤናና እድሜ አግኝቶ መኖር ትልቅ ፀጋ ነው፡፡ 
ከዚህ በኋላ ምን ያህል እድሜ ብትቆይ ደስ ይልሃል?
ወቸ ጉድ! ደግሞ በፈጣሪ ስራ ልግባ፣ ስንት አመት መኖር ትፈልጋለህ ትያለሽ? እሱ እንደፈቀደ ነዋ! ፈጣሪ እንደወደደ፡፡ እስከ ዛሬስ ይህን ያህል እድሜ የሰጠኝ አምላክ አይደለም እንዴ?! የኔ ታላቆችም ታናሾችም የነበሩ ብዙ ጓደኞቼ እኮ አልፈዋል፡፡ ይህ የእግዚአብሔር ስራ ነው፡፡ ስለዚህ እሱ የፈለገውን የወደደውን ያህል እድሜ ይስጠኝ፤ አለቀ፡፡
http://www.addisadmassnews.com/