ብዙ ጊዜ ቀልድ የምጠብቀው ከተደላደለ ህይወት፣ከሚጣፍጥ
እንጀራ መሶብ እንጂ ከመረረ የኑሮ ዉጣ ውረድ አይደለም፤ግን ተሳስተናል፡፡ ብዙ ታላላቅ ደራሲያን የተወለዱት
በጦርነትና በሰቆቃ ማህጸን እንጂ በተድላ አበባ እምብርት ላይ አይደለም። ንቦች ናቸው ከጥሩ መዓዛ ማር
የሚጋግሩት፡፡ ንቦች ስል የኛን አገር ንቦች(ኢህአዴግን)ማለቴ አይደለም፡፡ በቅርቡ ያነበብኩት፡፡ ግን ደግሞ ትንሽ
ቆየት ያለ (በ2001) የታተመ መጽሃፍ “ድህነት” በእንግሊዝኛው “poverty”ብሎ የጻፈው ጽሁፍ የሚያሳዝንና
የሚያስቅ ነበረ - ጆ ጉድ ዊን ፓርከር፡፡ “Poverty is being tired. I always been tired.
They told me at the hospital when the last baby came that I had chronic
anemia caused from poor diet, a bad cause of worms, and that I needed a
corrective operation. I listened politely – the poor are always polite.
The poor always listen.”
ድህነት ሁልጊዜ በመከራ ላይ መከራ ያደከመው ነው፡፡ ድሃ ሁልጊዜ
አንገት ደፊ፣ ሁልጊዜ አድማጭ ነው፡፡---ጸሃፊው ብዙ ቀልድ ይቀልዳል፡፡ ምክንያቱም ዘፋኙ እንዳለው መናደድ ሲበዛ
ያስቃልና!... የዛሬው ርዕሰ ጉዳዬ፣ የበኀይሉ ገ/እግዚአብሄር “ኑሮ እና ፖለቲካ” የተሰኘ መጽሃፉ (በቅርብ ቁ-
2 ብሎ ያወጣው) ውስጥ ያሉ ቀልዶች ናቸው፡፡ በ160 ገጾች የተካተቱት የበሃይሉ ቀልዶች ሙሉ በሙሉ ከሃገራችን
ፖለቲካ ጋር የተያያዙ ስለሆኑ ብዙ የረሳናቸውን ነገሮች ያስታውሱናል፡፡ እያዋዙ ታሪክ ይነግሩናል፡፡ በጣም
ያሽሟጥጣሉ፡፡ ከንፈራቸውን እያወዛወዙ፡፡ በተለይ የምርጫ 97 ስህተቶችና ነውሮችን ያሳዩናል፡፡ እስቲ ትንሽ
እንይ፡- አቅመ ደካማዋ ባልቴት ወ/ሮ ልጓሜ በ1997 ዓ.ም የተካሄደውን ብሄራዊ ምርጫ ተከትሎ በተነሳው ብጥብጥ
“ድንጋይ ወረወረ” ተብሎ በጠገበ ቆመጥ በፀጥታ ሃይሎች የተሰባበረ ጎረምሳ ልጃቸውን እያስታመሙ ነው፡፡ ታዲያ በዚህ
መሃል በቴሌቪዥን፣ የህገ መንግስት ጥያቄና መልስ የሞባይል ካርድ የሚያሸልም ጥያቄ ይጠየቃል፡፡ ”በፓርላሜንታዊ
ስርዓት የሃገር መከላከያ ሰራዊት ተጠሪነቱ ለማን ነው” የሚል ነበር፡፡ ይሄኔ በጋቢ ተጠቅልሎ የተኛው ልጅ፣
ጥያቄውን ለመመለስ ሞባይሌን አቀብዪኝ - ይላል እናቱን፡፡ እናትየው “አይ ልጄ ድከም ብሎህ እኮ ነው፤አሁን የዚህ
ጥያቄ መልስ ሰው ይጠፋዋል ብለህ ነው
” ልጁም መልሶ “እስቲ ካወቅሽው መልሱ ምንድነው?” “ጥያቄው
የመከላከያ ሰራዊቱ ተጠሪነቱ ለማነው? ነው አይደል?” “አዎ!” “ለዲያቢሎስ ነዋ ሌላ ለማን ይሆናል?”አሉ እትዬ
ልጓሜ - በፀጥታ ሃይሎች የተሰባበረ ልጃቸውን በብስጭት እያዩ፡፡ ይህ የ1997 ዓ.ም ምርጫ በታሪካችን እጅግ
አስገራሚና ለውጥ የናፈቀ እንደ ነበር ሁላችንም የምናስታውሰው ስለሆነ ይህን ጉዳይ ማንሳቱ የግድ ነው፡፡ ዛሬ ዛሬ
በሚደረጉት ምርጫዎች ላይ በሰላም ተጠናቀቀ፤ ወዘተ ሲባል ያስቀኛል፡፡ ሆዳችን እያወቀው ለምን እንደምንሸዋወድ
አይገባኝም፡፡ መንግስት የምናውቀውን ነገር እየዋሸ ከሚያበሳጨን ምናለ ዝም ብሎ የወደደውን ሳያወራ ቢያደርግ! ...
ለመሆኑ የትኛው መነሳሳት ነው ረብሻ የሚያስነሳው! ... ኢህአዴግ ከራሱ ጋር ሊጣላ ነው! ...... ኩመካ
ይመስላል፡፡ እንደኔ እንደኔ ኢህአዴግ ከራሱ ሰዎች ለመምረጥ ካልሆነ በቀር ምርጫ የሚባል ነገር እየመጣ ባያበሳጨን!
... ኢህአዴግ በፈጠረህ አርፈህ ግድቡን ጨርስ … ባቡሩን ቶሎ ቶሎ አሰራ!...ብሎ የሚነግርልኝ ቢኖር ደስታውን
አልችለውም፡፡
ከበኃይሉ መፅሐፍ ዘና ለማለት ያህል “ውዴ የትም አትጠብቂኝ”
የሚለውን ትንሽ እንየው ይሆን!.. ”ፒያሳ መሃሙድ ጋ ጠብቂኝ ፤ ቦሌ ፒኮክ ጋ ጠብቂኝ ፤ መርካቶ ምዕራብ ሆቴል ጋ
ጠብቂኝ ፤ አራት ኪሎ ጆሊ ባር ጋ ጠብቂኝ ፤ ሽሮሜዳ መዶሻ ጠጅ ቤት ጋ ጠብቂኝ ---- የደላቸው ይባባሉ፡፡ ውዴ
እኔ ግን እላለሁ፤ የትም አትጠብቂኝ! እንድትሰሚ? ምን እንድትጠጪ? ምን እንድትበዪ?… ጉድ እኮ ነው! ውዴ!
እነሱ ወገኞች ናቸው፡፡ ፒያሳ፣ ቦሌ፣ መርካቶ---ሲባባሉ አንዳች የሚታይ ተዐምር አለ ብለሽ እንዳትጠብቂ፡፡ በዛም
ብትሄጂ በዚህ፣ ጠጅ ቤት ገባሽ ድራፍት ቤት፣ ቡቲክ ደጃፍ ላይ ቆምሽ፣ ጫት መሸጫ ሱቅ ፤ ጭድ ተራ ወረድሽ፣ ጎማ
ተራ፤ የሚታየው፣ የሚሰማው፣ የሚተነፈሰው ሁሉ የማያምርበት፤ ከቀልቡ ያልሆነ ህዝብ ወዲያና ወዲህ የሚልበት
ነው፤/አይ ውዴ ቀልብ ከሌለ ቀልብ ከየት ይመጣል አልሽ!?…ሕም!/ “ፒያሳን ያየሽው እንደሆነ…/ለነገሩ ምኑ
ይታያል?/ አካል ጉዳትና እግዜር የቀማውን አካል ወደ ገቢ ማስገኛ ቀይሮ መሬት ላይ ተነጥፎ ሲለምን ማለፊያ
ይነሳሻል፡፡
እናቲቱ ጡቶችዋን ልጆችዋ አፍ ላይ ደቅና ራቁቷን አስፓልት ላይ
ተቀምጣ እንቅፋት ትሆንብሻለች፡፡ ጎረምሳው ከፒያሳ የሚሰፋ እጁን ፊትሽ ላይ ዘርግቶ ዛቻ እና ማስፈራሪያ
በተቀላቀለበት ማጉረምረም፣ “ራበኝ፤ አምስት ብር አምጪ!” ሲል ያስደነግጥሻል፡፡ /እንዴ! ብራችን የሚጀምረው
ከአምስት ብር ሆነ እንዴ/ “ኧረ እኔም ከነጋ እህል በአፌ አልዞረም!” ካልሽው፤ እጅሽን ቀብ አድርጎ፣ “ራበኝ!”
ይልሻል በድጋሚ አይኑን አፍጥጦ፡፡ “ካልሰጠሽኝ ዋ!” መሆኑ ነው፡፡/ በእህል ውሃ የምንቀረጠው አንሶ ለእግዚሃሩ
አየርም ቅረጡ ሊሉን ነው እንዴ፡፡ እግዝኦ! በዚህ ደካማ አቅማችን የተሸከምናቸው አነስተኛና ጥቃቅን መንግስታት
መብዛታቸው!/ በነገራችን ላይ ውዴ፤ ሁለት ልጆችዋ አፍ ላይ ጡትዋን ደግና ወደምትለምነው እናት ልመልስሽና ልጆቹ
ጡት እየጠቡ ይሁን ገቢ ማስገኛ ቴአትር እየተጫወቱ በውል ማወቅ አልቻልኩም፡፡” በዚህ ርዕስ ላይ የጻፈው ትዝብትና
ሽሙጥ ይቀጥላል፡፡ ከላይ የጠቀስናቸውን መጽሃፍት የሚታዘብ፣ ወይም ለቀልድ የመረጣቸው ይመስላል። መጽሃፉ ብዙ ጉድ
አለው፡፡ “ኣያዋጣኝም!” ይህ ታሪክ የኮንዶሚኒየም ዕጣ ሲወጣ ለማየት የፈለገ ጓደኛው፣ ተራኪውን ወደ ቤት አጣድፎ
ከወሰደው በኋላ ያለውን ሁኔታ ነው፡፡ እስቲ እንየው፡- “እዚህ ላይ ሁል ጊዜ የሚገርመኝ የኤርትራ ቴሌቪዥን
፣የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሲሠራ የሚሰራ፣ ሲበላሽ አብሮ የመበላሸቱ ነገር ነው፡፡
ነገሩ በስም እና በአገር ቢለያዩ እንጂ በሚያስተላልፉት
ፕሮግራምስ አንድ አይነት ናቸው፡፡ እዚያም የሚታረስ መንገድ፤እዚህም የሚታረስ መንገድ፤እዚያም ያማረ የገብስ
ማሳ፤እዚህም ያማረ የገብስ ማሳ፡፡ እዚያም “ቶክ ፉት ቦል”፤ እዚህም “ቶክ ፉት ቦል”፡፡ /እንደ አጋጣሚ ሆኖ
በኤርትራ ቴሌቪዥን ያላየሁት የኮንዶሚኒየም ዕጣ በቀጥታ ሲወጣ ብቻ ነው/ እንዲህ ያለ ምስስሎሽ ካላቸው ታዲያ
ለምንድነው እንደ አልቃይዳ አንዱ ጣቢያ አንዱን ይዞት የሚጠፋው?እንጃ! “ውጪ አገር ያለ አንድ ወዳጄ ሲያጫውተኝ፣
“የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እንደ ዕድል ሆኖ ሰርቶ ካየሁት ሁልጊዜ እንዲህ እላለሁ” አለ፤”ግን የልማት ዜና አገሬም
እያለሁ አይቼዋለሁ፡፡ የገብስ እርሻው ታጭዶ ጎተራ ሲገባ የማየው መቼ ነው? እነዚህስ ሣር የሚግጡ የደለቡ በሬዎች
እስካሁን አልታረዱም ካራ ሳይገቡ አረጁ እኮ! ይህስ በአነስተኛ ጥቃቅን ተደራጅቶ አምናም ፣ካቻምናም፣ዘንድሮም
ድንጋይ የሚፈልጠው ወጣት፤ ገቢው አድጎ፣ ስራው ተሻሽሎ የማየው መቼ ነው እስከ መቼስ ቱታውን
እንደለበሰ፣‹መንግስት ባመቻቸልን የስራ ዕድል ተጠቅሜ ካፒታሌ ይህን ያህል ደርሷል‹ ሲል ይኖራል” ትረካው
የኮንዶሚኒየሙ ዕጣ እስኪወጣ ድረስ ያለውን ምጥና ሌሎች ማህበራዊና ፖለቲካዊ ቀውሶቻችንን ያሳያል፡፡ ሌላው ለዛሬ
የመረጥኩት “ኑሮዬን ፓርላማ አድርጎታል” የሚለው ነው፡፡ የአንድ ባልና ሚስት ታሪክ ነው፡፡… ሚስት ከምትለው ገባ
ብለን እንጀምር፡-“በቃ ምን ልበልህ… ቃላት አጥሯት ድንቅፍቅፍ፡፡ አወዛጋቢው ንግግር ይህ ነው፤ ሚስት፣ “ኑሮዬን
ፓርላማ አድርጎታል” ያለችበትን ምክንያት በመጠየቅ ጆሯችንን ለትዳር ብሶት አናጋልጥም፡፡ እንዲህ መጠርጠር ግን
እንችላለን፡፡ የጥርጣሬውን ነጥቦች ልለፋቸውና ልቀጥል፡፡ “በስብሰባ ወቅት በመተኛትና በማንኮራፋት ቀሪውን ተሰብሳቢ
በመረበሻቸው አራት የፓርላማ አባላት የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ደረሳቸው” ይላል - ዐይኔ ያረፈበት የጋዜጣ
ዜና፡፡”አይ ፍትህ! ከፍትህ በታች እንጂ በላይ ማን አለ!? ለመሆኑ ይሄ የሆነው የት ይሆን?”ብዬ በጉምዥት ቁልቁል
ሳነብ ጉዳዩ የሆነው ቬትናም የተባለች አገር እንደሆነ ተረዳሁ፡፡
የዛን ሰሞን የኛዎቹ፣”ነፃ ፕሬሶች” ሽወዳ ትዝ አለኝ፡፡”ጠቅላይ
ሚኒስትሩ ስልጣናቸውን ለቀቁ!” ብለው በትልቅ ርዕስ ፊት ለፊት ጽፈው ያስነበቡንና፣ ወደ ውስጥ ስንገባ ግን የሌላ
እድለኛ አገር ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ ይገኛል፡፡ ኧረ ሌላም አለ፤ለምሳሌ እቤቴ እስካሁን ያለ አንድ የግል ጋዜጣ
፣”ጠቅላይ ሚኒስትራችን በነገው ዕለት ስልጣናቸውን ይለቃሉ” ብሎ ጽፏል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ግን ስልጣናቸው ላይ
ኖረው በቅርቡ ነው በሞት የተለዩን፡፡ የበኃይሉ ሽሙጦችና ቀልዶች ማህበራዊና ፖለቲካዊ ሂሶችን እንዲሁም ስነ
ልቦናዊ ችግሮቻችንን አጣፍጠው የሚያክኩን ናቸው፡፡ መንግስትን…ፕሬሱን …እኛን ሁላችንን እያሳሳቀ ይተቸናል። በተለይ
መንግስት መስማት የተሳነው ባይሆን ፤ ከነዚህ ቀልድ መሰል ጽሁፎች በሽታው ምንና የት እንደሆነ ያውቅ ነበር፡፡
ግን አሁን እየባሰበት መጥቶ ጆሮውን በጠጠር ደፍኗል ማለት
ይቻላል። ህዝቡን የማይሰማ መንግስት መቼም ቢሆን ጥሩ ስራ አይሰራም፤ቢሰራም ብዙ ከስሮ ነው፡፡ እባክህ መንግስት
ሆይ ስማ!! ቅድም ከላይ የጠቀስኳቸው ደራሲ “poverty is asking for help.” ይላል፡፡ መንግስታችን
የድሆችን ድምጽ ካልሰማ ለውጥ ይመጣል ብሎ መጠበቅ አይታሰብም፡፡ ሃሳቤን ከማጠናቀቄ በፊት ኢህአዴግ/ኢህዴን/
ካሳተመው “ሶረኔ” የግጥም መጽሃፍ ላይ “የአርሶ አደሮች እንጉርጉሮ” ከሚለው ልውሰድና እኔም እንደ በኃይሉ
አሽሟጥጬ ልጨርስ ይሆን? የጭቆና ቀንበር ከብዶ በላያችን በግብር በጉቦ አልቆ ጉልበታችን በጦር በሰፈራ አልቆ
ወገናችን መጣልን ኢህአዴግ የነፍስ አባታችን፡፡ ይህንን ግጥም ዛሬ ኢህዴን ሲያነብበው ምን ይል ይሆን?…ታሪክ
ይደገማል?… ለጭቆና ታግሎ ጨቋኝ መሆን ጥሩ ነው ትላላችሁ? ኢህአዴጎች፡፡ ወይስ እኔን ትምክህተኛ ትሉኛላችሁ
? ለማንኛውም ልብና ዕድሜ ይስጠን!!
http://www.addisadmassnews.com/index.php?option=com_k2&view=item&id=12220:%E1%8B%A8%E1%89%A0%E1%88%83%E1%8B%AD%E1%88%89-%E1%88%BD%E1%88%99%E1%8C%A6%E1%89%BD%E1%8A%93-%E1%8D%96%E1%88%88%E1%89%B2%E1%8A%AB%E1%89%BD%E1%8A%95&Itemid=211
http://www.addisadmassnews.com/index.php?option=com_k2&view=item&id=12220:%E1%8B%A8%E1%89%A0%E1%88%83%E1%8B%AD%E1%88%89-%E1%88%BD%E1%88%99%E1%8C%A6%E1%89%BD%E1%8A%93-%E1%8D%96%E1%88%88%E1%89%B2%E1%8A%AB%E1%89%BD%E1%8A%95&Itemid=211
No comments:
Post a Comment