ከቶታል 1433
ከ10 አመት በፊት ፈረንሳይ ፓሪስ ውስጥ በተካሄደው ዘጠነኛው
የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ጥሩነሽ ዲባባ የምትባል እድሜዋ 17 አመት ከ 333 ቀናት የሆነ ታዳጊ ወጣት በ5 ሺህ
ሜትር ተሳትፋ ርቀቱን 14 ደቂቃ ከ51.72 ሰከንድ በሆነ ጊዜ አሸንፋ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት በመሆን
በሻምፒዮናው ታሪክ በግል ውድድር የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘች በድሜ ትንሻ አትሌት ስትሆን በጊዜው ውድድሩን በተለያዩ
መገናኛ ብዙሀን ሲያስተላልፉ የነበሩ የዘርፉ ባለሞያዎች በጋራ የተናገሩት “የዚችን ታዳጊ ልጅ ስም አእምሯችሁ ውስጥ
አስቀምጡ፤ ለወደፊት የአለም የረጅም ርቀት ሩጫ ውድድሩን ትቆጣጠራለች” የሚል ነበር።
እውነትም አልተሳሳቱም። ከሁለት አመት በኋላ እ.አ.አ በ2005 ዓ.ም በፊንላንዷ ሄልሲንኪ ከተማ አስተናጋጅነት በተካሄደው 10ኛው የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ10 ሺህ እና 5 ሺህ ሜትር የተካፈለችው ጥሩነሽ በሻምፒዮናው የመክፈቻ ቀን በተካሄደው የሴቶች 10 ሺህ ሜትር የፍጻሜ ውድድር ርቀቱን 30:24.02 በሆነ ጊዜ አጠናቃ የሀገሯን ልጆች ብርሀኔ አደሬን እና ታላቅ እህቷ እጅጋየሁ ዲባባን አስከትላ በመግባት አሸንፋ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት በመሆን ከሁለት አመት በፊት ፓሪስ ላይ የአለም ሻምፒዮን መሆኗ ድንገት የተፈጠረ ክስተት እንዳልሆነ አሳየች።
ሄልሲንኪ ላይ ከ1-4 የጨረሱት ኢትዮጵያዊያን |
በዚሁ የሄልሲንኪ ሻምፒዮና የጥሩነሽ ዲባባ ቀጣይ አላማ በ5 ሺህ
ሜትር አሸንፋ ማንም ኢትዮጵያዊ አትሌት በአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና አድርጎት የማያውቀውን የ10 ሺህ እና 5 ሺህ
ሜትር የወርቅ ሜዳሊያዎች ባለቤት በመሆን ታሪክን መጻፍ ነበር። ታዲያ አራት ኢትዮጵያዊያን በተሳተፉበት በዛ
የሄልሲንኪው የአለም ሻምፒዮና የሴቶች 5 ሺህ ሜትር ውድድር ከድንቋ መሰረት ደፋር፣ ከእህቷ እጅጋየሁ ዲባባ እና
ከጠንካራ ተፎካካሪዋ መሰለች መልካሙ ቀድማ በመሄድ ርቀቱን የስፍራውን ክብረወሰን በሰበረ 14፡38.59 ጊዜ
በማጠናቀቅ በአንድ የአለም ሻምፒዮና የጥንድ ወርቅ ሜዳሊያዎች ባለቤት ለመሆን የቻለች የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊ
አትሌት ሆነች። ቀነኒሳ በቀለ እ.አ.አ በ2009 ዓ.ም በርሊን ላይ በተካሄደው የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና
ተመሳሳይ ድል በማግኘት የጥሩነሽን ታሪክ ለመጋራት መቻሉ ይታወሳል።
በጃፓኗ ኦሳካ ከተማ አስተናጋጅነት የተካሄደው 11ኛው የአለም
አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ የመክፈቻ ውድድሮችን ለማየት እ.አ.አ ነሀሴ 25 ቀን 2007 ዓ.ም በናጋይ ስታዲዬም
የተገኘው ተመልካች ምናልባትም በአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ታሪካ ተአምር የሚመስለውን የረጅም ርቀት ሩጫ ብቃት
ለማየት ታድሏል። በሴቶች 10 ሺህ ሜትር ምንም እንኳን ቅድሚያ የአሸናፊነት ግምቱ ለጥሩነሽ ዲባባ ቢሰጥም በወቅቱ
የኦሳካ አየር ሁኔታ እጅግ በጣም ሞቃታማ እና ወበቃማ መሆኑ “ለኢትዮጵያዊያኖቹ አትሌቶች ላይመቻቸው ይችላል” የሚል
ግምት ስለነበረ አንዳንዶች የጥሩነሽ የአሸናፊነት ግምትን ይጠራጠሩት ጀመር።
የሴቶች 10 ሺህ ሜትር ውድድሩ ተጀምሮ ሁለት ኪሎ ሜትር ያህል
እንደተጓዙ አራት ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ከፊት ሆነው መሪነቱን ሲረከቡ አለም የኢትዮጵያዊያን ከአንድ እስከ አራት
ውጤትን መተንበይ ጀመረ። ግማሽ ያህል ድረስ አትሌቶቹ አብረው ከተጓዙ በኋላ 6 ሺህኛው ሜትር ላይ ያልተጠበቀ
ክስተት ትርምስ ተፈጠረና ኢትዮጵያዊያኖቹ ጥሩነሽ ዲባባ እና መስታወት ቱፋ የመሮጫው ትራክ ላይ ወደቁ። መስታወት
ከእግሯ የወለቀው ጫማዋን እንደገና ካጠለቀች በኋላ ሩጫዋን ብትጀምርም የደረሰባት ድንገተኛ ክስተት አቅሟን ወስዶት
ነበር እና ውድድሩን አቋርጣ ለመውጣት ተገደደች።
ጥሩነሽ ዲባባ ከወደቀችበት ተነስታ ሩጫዋን እንደገና ብትጀምርም
ፊቷ ላይ እና አጠቃላይ አሯሯጧ ላይ ምቾት አይታይም ነበር። ሆዷን ህመም ተሰምቷት ስለነበር በእጇ ማሸትን ከመጀመሯ
በተጨማሪ በሙቀቱ አትሌቶች ሊያጡት የሚችሉትን ሀይል ለመተካት በሚል ከመሮጫው ትራክ አጠገብ ወደተዘረጋው ጠረጴዛ
ሮጥ ብላ ውሀ አንስታ እየሮጥች እግረ-መንገዷን ከተጎነጨች በኋላ ትተዋት ወደፊት የሮጡት ተፎካካሪዎቿን የመያዝ
ትግሏን ቀጠለች። በአስደናቂ ሁኔታ ታዲያ ከወደቀችበት 6 ሺህኛው ሜትር በኋላ አንድ ኪሎ ሜትር ያህል ተጨማሪ
እንደሮጡ ጥሩነሽ መሪዎቹን ተቀላቀለች።
ከዛ በኋላ የጥሩነሽ ስራ ከሁለት አመት በፊት ፊንላንድ ሄልሲንኪ
ላይ አሸንፋው የነበረውን የ10 ሺህ ሜትር ወርቅ ሜዳሊያ እንደገና ለመድገም መፎካከር ነበር እና ቀዳሚ ስራዋ
የቅርብ ተፎካካሪዋ የነበረችው ከኢትዮጵያ ወደቱርክ ዜግነቷን የቀየረችው ኤልቨን አብይለገሰን የምትቀድምበትን
የአሯሯጥ ስልት መፈለግ ነበር።
ልክ ውድድሩ ሊያበቃ አንድ ዙር እንደቀረው የሚያበስረው ደወል
ሊደወል ጥቂት ሜትሮች ሲቀሩት ጀምራ ጥሩነሽ የተለመደው ፍጥነት የመቀየር ብቃቷን ተጠቀመች እና ኤልቨን አብይለገሰን
አልፋት ግስጋሴዋን የወርቅ ሜዳሊያውን ለማንሳት በማድረግ 10 ሺህ ሜትሩን 31 ደቂቃ ከ55.41 ሰከንድ በሆነ
ጊዜ አጠናቃ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ሆነች።
ከድሏ በኋላ ሩጫው መሀል ላይ መውደቋን እና የተሰማትን ህመም አስመልክታ ጥሩነሽ ስትናገር፦
“ሌላ ውድድር ቢሆን ኖሮ አቋርጬ እወጣ ነበር። የሆድ ህመሜን ችዬ ለመሮጥ የወሰንኩት ለሀገሬ ክብር ስል ነው። ከወደኩ በኋላ ራሴን ስታዲዬም ውስጥ በተሰቀለው ትልቅ ስክሪን አየሁት እና እንደገና ጥርሴን ነክሼ ሩጫዬን ለመሮጥ ወሰንኩ” አለች።
ከዚህ በኋላ ግን ጥሩነሽ እና የአለም ሻምፒዮና የተለያዩ መስለው
ነበር። እ.አ.አ በ2009 ዓ.ም ጀርመን በርሊን ላይ፣ በ2011 ዓ.ም ደግሞ ደቡብ ኮሪያ ዴጉ ውስጥ በተካሄዱት
12ኛው እና 13ኛው የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች በአሳዛኝ ሁኔታ በጉዳት ያልተሳተፈችው ጥሩነሽ እንደገና
ወደታላቁ የአትሌቲክስ ስፖርት መድረክ የተመለሰችው በሞስኮ አስተናጋጅነት እየተካሄደ ባለው 14ኛው የአለም
አትሌቲክስ ሻምፒዮና ነው።
የአለም ሻምፒዮናው እየተካሄደበት ያለው የሉዝናኪ ስታዲዬም ከዚህ
በፊት ታላላቅ ስፖርታዊ እና የሙዚቃ ዝግጅቶችን በማስተናገድ የታወቀ ሲሆን በአውሮፓ ክለቦች ቻምፒዮንስ ሊግ
የማንቼስተር ዩናይትድ እና ቼልሲን የፍጻሜ ጨዋታ፣ የአውሮፓ ማህበረሰብ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ፣ የማይክል ጃክሰን፣
U2፣ ማዶና፣ የሮሊንግ ስቶንስ እና የሬድ ሆት ቺሊ ፔፐርስ የሙዚቃ ኮንሰርቶችንም ቢያስተናግድም፣ በ14ኛው የአለም
አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሁለተኛ ቀን ውሎ ያሸበረቀው ግን በምንጊዜም ታላቋ የረጅም ርቀት ሩጫ ንግስት ጥሩነሽ ዲባባ
የሚያምሩ የእግር አጣጣሎች፣ አስደናቂ የአሯሯጥ ጥበቦች፣ አስገራሚ የአጨራረስ ብቃት እና በፈገግታ የታጀበ የታላቅ
አትሌትነት ማረጋገጫ ድል ነበር።
ጥሩነሽ ዲባባ 10 ሺህ ሜትሩን 30፡43.35 በሆነ ጊዜ
በማጠናቀቅ በአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ታሪክ በርቀቱ ሶስተኛው በአጠቃላይ ደግሞ አምስተኛዋ የሆነው የወርቅ ሜዳሊያ
አግኝታለች። ኬኒያዊቷ ግላዴስ ቺሮኖ የብር፣ ኢትዮጵያዊቷ በላይነሽ ኦልጂራ የነሀስ ሜዳሊያዎች ባለቤት ሆነዋል።
በ10 ሺህ ሜትር ርቀት ባደረገቻቸው 11 ተከታታይ ውድድሮች አንድም ያልተሸነፈችው ጥሩነሽ ዲባባ በድጋሚ የረጅም ርቀት ሩጫ ንግስት መሆኗን አረጋግጣለች።
በሞስኮ አስተናጋጅነት እየተካሄደ ባለው የ14ኛው የአለም
አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሁለተኛ ቀን ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በተሳተፉባቸው ሌሎች ውድድሮች በሴቶች 1500 ሜትር
የማጣሪያ ውድድር የጥሩነሽ ዲባባ ታናሽ እህት እና በርቀቱ የአለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮን የሆነችው ገንዘቤ ዲባባ
ወደ ግማሽ ፍጻሜ አልፋለች።
በወንዶች 800 ሜትር የግማሽ ፍጻሜ ማጣሪያ ኢትዮጵያዊው መሀመድ አማን ምድቡን አሸንፎ ለፍጻሜ በማለፍ ለወርቅ ሜዳሊያ እንደሚፋለም አረጋግጧል።
No comments:
Post a Comment