በመጀመሪያ፤ ይህ ፅሁፍ ቀድሞ የተዘጋጀ የነበረው፣ለአዲሰ አድማሰ ጋዜጣ ነበር፡፡ሳይወጣ በመቆየቱ ወደዚህ አምተነዋል፡፡እናም ወደኋላ መለስ ብላችሁ አንብቡልኝ፡፡ እሱ በማያይበት መፃፌ ብቻ ሀሜት እንዳይመስልብኝ ሰጋሁ፡፡ ቢሆንም ጀመርን……
.
.
ሰላም ላንተ ይሁን ሠራዊት ፍቅሬ! እንደምን አለህ! የሕይወት ‹‹ግራ እና ቀኝ እንዴት ይዞሃል?? ይህችን ፅሁፍ (ደብዳቤ) የምጽፍልህ ‹‹ርዕዩት›› በተባለው የሬድዮ ፕሮግራም ላይ እንግዳ ሆነህ በቀረብክ ጊዜ ‹‹ታነባለህ ወይ›› ተብለህ ለቀረበልህ ጥያቄ ‹ግዴታ ሆኖብህ› እንደምታነብ ስትገልጽ በመስማቴ መልዕክቴ ባክኖ አይቀርም በሚል የፀና እምነት ነው፡፡ ታዲያ ስታነባት ግልጽ የሆነችና በቅን ልቦና የተፃፈች መሆኗን ተገንዘብልኝ፡፡
የፅሁፌም ሙሉ ትኩረት ፣ ግራ እና ቀኝ የተሰኘው ፕሮግራምህ ነው፡፡ በየሳምንቱ በፕሮግራሙ ላይ የሚስተናገዱ ‹‹ሃሳብ አልባ›› ርዕሰ ጉዳዮች ናቸው ሃሳብ እንድሰነዝር ያስገደደኝ፡፡ እንደውም እንደውም ሳስበው እስካሁን ድረስ ርዕሱ እንጂ ፕሮግራም አልጀመራችሁም ባይ ነኝ ፣ ርዕሱ እየመራችሁ እንጂ ፕሮግራሙን እየመራችሁ አይደለም፡፡ እስካሁን በተላለፉት ፕሮግራሞቻችሁ ያየሁትም ‹‹ግራ እና ቀኝ›› ሊቀመጡ የማይችሉ ሃሳቦችን ጭምር በግብታዊነት እያነሳችሁ አቆማችኋቸው እንጂ ፣ እንኳን በአንድ ትልቅ የአገሪቱ ሚዲያ ቀርቶ ለእርስ በእርስ የወዳጅ ጨዋታ እንኳ የሚበቁ አይደሉም፡፡……. ሠራዊት ፣ የፕሮግራሙ ታላቁ ችግር ምን መሰለህ …. ያገኛችሁትን ማምጣታችሁ ፣ ያመጣችሁትን መወርወራችሁ፡፡ ይህንን የምለው ከምንም ተነስቼ አይደለም ፣ ከራስህ አባባል ተነስቼ ነው፡፡ በሊያ መጽሄት ቅፅ2 ቁጥር 17 የታህሳስ እትም ላይ በሰጠኸው ቃለ ምልልስ አንድ ቦታ እንዲህ አልክ ፤ ‹‹…. ሃሳብህ ምንም ይሁን ምን ወርውረው››…አየህ ሠራዊት ‹‹ምንም ይሁን ምን›› እያላችሁ የምትወረውሩዋቸው ፣ ምንም ያልሆኑ ርዕሶች ናቸው የፕሮግራሙ ስብራቶች፡፡
ሠራዊት! ሃሳብ እኮ ጠጠር ያለ ፅንሰ ሃሳብ ነው፡፡ ‹‹ምንም ይሁን ምን›› ብለን የምንወረውረው አይደለም፡፡ ‹‹አባይን አትንኖ የማዝነብ›› ያህል ቀላል አይደለም፡፡ ወዴት እንደሚያደርስ የማናውቀው (ግብ አልባ)፣ ወንዝ ዳር ቆመን እየወረወርን የምንዝናናበት ጠጠር አይደለም፡፡ በትክክል ሃሳብ ከሆነ አልሚ ፣ የተኮላሸም ከሆነ አጥፊ ነው፡፡ አትቀየመኝና የናንተም ፕሮግም እንደሁለተኛው ነው ብዬ ነው የማምነው፡፡
ከጥቂት ጊዜያት በፊት በማስተምርበት ትምህርት ቤት ምን ሆነህ መሰለህ? የአምስተኛ ክፍል ተማሪዎች ናቸው፡፡ ታዲያ በማስተምራቸው ትምህርት መሃል ክርክር ማድረግ አስፈላጊ ሆነና በእነሱ ደረጃ የሆነ ርዕስ እንዲመርጡ ዕድል ሰጠኋቸው በመጀመሪያ የመረጡት ርዕስ ምን እንደነበር ታውቃለህ ‹‹እውቀት ይበልጣል ወይስ ገንዘብ››
ነገር ግን በዚህ ርዕስ ላይ እንዲወያዩ አልፈቀድኩላቸውም፡፡ የከለከልኩበትንም ምክንያት ነግሬያቸው ሌላ ርዕሰ ጉዳይ ቀየሩ፡፡ ታዲያ እኔ ለአምስተኛ ክፍል ተማሪዎች የከለከልኩትን ርዕሰ ጉዳይ አንተ ለሕዝብ ይዘኸው መጣህ፡፡ እኔን ግራ የገባኝ ሠራዊት የአምስተኛ ክፍል ተማሪዎች እንደናንተ አሰቡ ወይስ እናንተ እንደ አምስተኛ ክፍል ተማሪዎች አሰባችሁ?
እስቲ በሞቴ ራስህ መለስ እያልክ ተመልከታቸው፡፡ የቡና አፈላል ያስፈልጋል ወይስ አያስፈልግም? ፣ ገንዘብ ወይስ እውቀት? … ህፃናት ይገረፉ ወይስ አይገረፉ? ... ቢያንስ ቢያንስ እንኳን ‹ይቀጡ ወይስ አይቀጡ› ማለት የአባት ነው፡፡ እንደምን ያለ ቸልተኝነት ነው ቅጣትን ግርፊያ ብቻ አድርጎ እንድታዩ አይታችሁን የዘገባችሁ?
‹‹ትምህርት ያለ ሃሳብ ፣ ብክነት ነው›› ይልሃል ኮንፊሽየስ ፤ ‹‹ፕሮግራም ያለ ሃሳብ ብክነት ነው›› እልሃለው እኔ፡፡ ትውልድ ይበክላል፡፡ አዕምሮ ይበክላል፡፡ ሃሳብ ይበክላል፡፡ ማህበረሰቡን ይበክላል፡፡… ደግሞ ይበልጥ ምን እንደሚያስደነግጠኝ ታውቃለህ በቅርፅና በይዘት ያለፉትን የመሰሉ ሰላሳ የሚሆኑ ፕሮግራሞች እጃችሁ ላይ አለ የሚል ተባራሪ ወሬ መስማቴ!.... ‹‹የበላችው ያቅራታል ፣ በላይ በላይ ያጎርሳታል›› ሆነብን እኮ ሠራዊት!
የሚገባኝ ነገር፣ ግን ትንሽ እውቀት ብዙ ድፍረት ነው!
ሠራዊት! ይህ ፅሁፍ ጫን ያለ ቁጣ መስሎ ብታገኘው (ነው ብዬ ባላምንም!) እንዳትቀየም ፣ ቢያንስ ‹ማንኛውንም ሃሳብ እንወርውር› በሚለው ሃሳብህ ትረዳኛለህ ብዬ በማሰብ ነው፡፡
….ምናልባት ከቀረቡት ውስጥ ስለሰው ‹ያገባኛል አያገባኝም› የሚለው ርዕሰ ጉዳይ በመጠኑ የተሸለ ይመስለኛል፡፡ ሌሎቹ ግን በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ድሮ ልጅ ተማሪ ሳለን ፣ በትምህርት ቤት የክርክር ጊዜያቶች የተከራከርንባቸው ናቸው፡፡ እስቲ አንተም ለማስታወስ ሞክር ብዙዎቹ እንደውም ከዛ ትውስታ የመዘዛችኋቸው ሳይሆኑ እንደማይቀሩ እገምታለሁ፡፡ እናም እጠይቃለሁ ፣ ወደልጅነታችን ልትመልሱን ነው ወይስ ወደልጅነታችሁ ልትመለሱ የፈለጋችሁት?!
ሠራዊት! ውይይትና ክርክር የአዕምሮ ጉዳይ ነው፡፡ የዝና ፣ የአጀብ ፣ የስፖንሰር ፣ የአይነ ግቡ ጌጦች ጋጋታ አይደለም! ይሄ የእናንተ (የአንተ ፕሮግራም) ግን ስማቹህን ከዘራ አድርጎ የቆመ ፣ ቆሞ መሄድ የማይችል እግር አልባ ፕሮግራም ነው፡፡
አዎ! ይህ ዝግጅት ምንም አልተዋጣልህም፡፡ ርዕሰ ጉዳዩ እሱ ስለሆነ እንጂ ሌሎቹ ተዋጥተውልሃል ማለቴ አይደለም ታዲያ፡፡ ካለንበት የሚያወርድ እንጂ ካለንበት ከፍ የሚያደርግ አይደለም፡፡ ሃሳብ አልባ ነው፡፡ ሀሳብ አልባ ሆኖ ፣ አደባባይ ከዋለ ርዕሰ ጉዳይ ደግሞ ፣ አደባባይ ሳይውሉ ሃሳብ! የሆኑት የእኛው ሃሳቦች በስንት ጣዕማቸው፡፡ ሃሳብ ህውስታ አይደለም ፣ መተርጎም ነው፡፡ እናንተም ይዛችሁልን ስትመጡ የከረማችሁት ግን ህውስታ እንጂ ሃሳብ አይደለም፡፡ ስሜት እንጂ ስሌት አልባ ነው፡፡ የሚያስፈልገን ሃሳብ ነው፡፡ እናንተ ይዛችሁ የመጣችሁትን በማየት ‹‹የመድሃኒት መደብር›› በሚያስፈልገን ሰዓት ፣ ‹‹የመርዝ መደብር›› እንደከፈታችሁል(ብ)ን ለማሰብ ተገደድኩ፡፡
… ያው እንደ ሚታወቀው ኢቲቪም ቢሆን ያው ኢቲቪ ነው፡፡ ይህ የእናንተ ፕሮግራም ሲታከልበት ደግሞ ‹‹በደንባራ በቅሎ ፣ ቃጭል ተጨምሮ›› ሆኖብን አረፈው፡፡
ሠራዊት ሆይ! በአጠቃላይ ፕሮግራማችሁ ፣ ወርዶ የሚያወርድ ነው፡፡ ዝሎ የሚያዝል ነው፡፡ ይህን የምለው በስሜት አይደለም! በቁጣ አይደለም! ከትናንት ዛሬ ፣ ከዛቴ ነገ ትሻሻላላችሁ ከሚል ‹‹ባዶ ጥበቃ›› በኋላ ፣ ከረዥም መብሰል በኋላ ነው፡፡
በመጨረሻም ፣ በእናንተው የርዕሰ ጉዳይ ቅርጽ አንድ ሃሳብ ላንሳና አቋሜን በመግለጽ ፅሁፌን ልደምድም፡፡ አዎን… እስቲ እኔም ራሴ ግራ ቀኝ ይኑረኝ… ሃሳቡ ምን መሰለህ… ‹‹ግራ እና ቀኝ ይቁም ወይስ ይቀጥል›› የሚል ነው፡፡ የኔም አቋም እነሆ - ይቁም! ለምን ብለህ ብትጠይቅ ይሄ ፅሁፍ ከሚሰጥህ መልስ በላይ ፣ አንተ እራስህ ፣ ቆም ብለህ ‹‹ለሕዝቡ ምን አደረስኩ? ምላሹ ምን ይመስላል?›› ብለህ ብትጠይቅ ፤ በአስተውሎት ብትመረምር በማህበራዊ ድህረ ገጽ (በፌስ ቡክ) ስለ ፕሮግራሙ የሚባለውን ጎራ ብለህ ብታይ ፣ ፕሮግራሙን የማቆም ጉዳይ ከእኔ በላይ ያንተ ይሆን ነበር፡፡ ዘርዓያቆብ ‹‹ሰዎች በልባቸው ካለው በስተቀር ምን ይነግሩኛል›› ይላል ፤ እኔ ፕሮግራሙ ይቁም ስል ፣ እስካሁን ያሉትን ከልባችሁ አውጥታችሁ እንዳመጣችሁ ሁሉ ፣ በቀጣዩም እንደዚሁ ከማድረግ ልትመለሱ ስለማትችሉ ነው፡፡ በውስጣችሁ ካለው በስተቀር ሌላ አዲስ ልታመጡልን አትችሉማ!! እናም ሌላ ‹‹ባዶ ጥበቃ›› ለማድረግ ስለማልወድ ነው፡፡ ‹‹የማያጠግብ እንጀራ…›› መሆኑን ስለማውቅ ነው፡፡ ከአያያዛችሁ ፣ አዘላለቃችሁን ማወቅ ስለማያዳግት ነው፡፡ ላንተም በየቦታው እየገቡ ፣ ያለውን ከማጉደል ፣ የሞላውን ይዞ መዝለቁ ይሻላል ብዬ በማመን ነው፡፡ በዚህና በሌሎች ብዙ ምክንያቶች ‹ቢቆም ይሻላል› እላለሁ፡፡ እኔም እዚሁ ጋር ለማቆም ወደድኩ….፡፡
ከታላቅ አክብሮት ጋር!
https://www.facebook.com/agegnehu.asegid/posts
No comments:
Post a Comment