Sunday, November 3, 2013

ስብሐት ገ/ እግዚአብሔር ስንት አይነት ገጸ-ባህሪ ነው


ከበፍቃዱ አባይ

አመቱ ምንም እንኳን 2005 ዓ.ም ላይ ቢሆንም በቅርቡ ልንለው በምንችለው መልኩ ላንባብያን የደረሰውንና ስብሐት ገ/እግዚእብሔርን የተመለከተውን መጽሐፍ አነበብኩት፡፡ስለመጽሕፉና በውስጡ ስለተካተቱ የተለያዩ መልከ-ስብሐት ሐሳቦችን አስመልከቶም በተለያዩ የህትመት ውጤቶች ላይ የቀረቡ ክርክሮችንም ሳነብ ቆይቻለሁ፡፡ በመጽሐፉ ላይ ከተካተቱት የስብሐት መልኮች ውስጥ ግዝፍ ነስቶ የበርካታ አንባብያንን ቀልብ ለመሳብ የቻለው የአርክቴክቱ ሚካኤል ሽፍራው ስብሐትን ከሌላ ማዕዘን የተሰኘው እይታ ነው ለማለት ይቻላል፡፡ በዚህ ሐሳብ ዙሪያ ታድያ የቀረቡት በርካታ ክርክሮችም ውሐ የሚያነሱ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ፡፡ እኔም ስለ መልክአ-ስብሐት ያለኝን አተያይ ለመከተብ ጊዜ ያላጠፋሁ ቢሆንም ለአደባባይ መብቃቱ ላይ ግን ሰንፌ ቆይቻለሁ ዛሬም ሰዓቱ ባለመርፈዱ ስለ መጽሐፉ ጥቂት ለማለት ወድጃለሁ፡፡
መልክዐ ሰብሐት የሚል ስያሜ ያለው ይህ መጽሐፍ በ30 ጸሐፍት፤ደራስያንና ሰዓሊያን እንደተጻፈ የጀርባ ሽፋኑ ላይ የተገለጠ ቢሆንም እኔ ግን በቆጠራ የደረስኩበት 27 ባለሙያዎች የተሳለፉበት መሆኑን ነው፡፡ያም ሆነ ይህ ግን ስበሐት በሐገራችን ካሉ በጣት ከሚቆጠሩ ስመ ጥር ደረስያን/ት/መሐከል እጅግ እድለኛውና በተለያዩ ጸሀፍት ሊዘክር የበቃ ደራሲና ተርጓሚ ነው ለማለት እችላለሁ፡፡በህይወት በነበረበት ወቅት በተለያዩ ወጣቶች ልደቶቹ የተከበሩለት፤በታላላቅ መደረኮች ለመታደም የቻለ፤ከህልፈቱም በኋላም ሆነ በፊት በስሙ ጥቂት የማይባሉ ስነ-ጽሑፋዊ በረከቶች የተለገሱለት ኢትዮጽያዊ ነው፡፡ሰሞነኛው መልክአ ሰብሐትም አንግዲህ የዚህ የሰውየው ስም መነሻ ለመሆን የበቃ መጽሐፍ ነው፡፡ለስብሐት ከፍ ያለ ፍቅርና አክብሮት ያላቸው ጸሐፍት፤ገጣምያንና ሰዓሊያን የታደሙበት መጽሐፍ ታድያ በአብዛኛው ወደ መወድስ ስብሐት ያደሉ ናቸው ለማለት ይቻላል፡፡ጸሐፍቱ ለስብሐት ያላቸውን ክብርና ፍቅር ለመግለጽም የክብር ዶክትሬት የሚገባው ስለመሆኑም ጭምር በስራዎቻቸው ላይ ወትውተዋል፡፡ ከዳኛቸው ወርቁ እስከ ሲግመንድ ፍሩድና ቻርልስ በግዴይር፤ከሄሚንጉዌ አስከ ሆቺሚኒ ደረስ ስማቸው በተወሳበት በዚህ መጽሐፍ ላይ የተለያዩ ሐሳቦች ሰፍረዋል፡፡ከዚህ በተለየ መልኩ የስብሐትን መልክ ፍጹም በማጠየምና በድፍረት ሌላ የተጠየቃዊ ሐሳበ ትንታኔ ይዞ ለመምጣት የደፈረው አርክቴክቱ ሚካኤል ሽፈራው ብቻ ነው፡፡ይህ የሚካኤል ስራ መኖርም ነው የመጽሐፉን ርዕስ ሙሉ ይሆን ዘንድ ያስቻለው፡፡እንደሌሎቹ የስብሐት መልክ ገለጻ ቢሆን ኖሮ የመጽሐፉ ርዕስ ከመልከአ ስብሐት ይልቅ ለመወድሰ ሰብሐት የቀረበ ይሆን ነበር፡፡ይህ መጽሐፍ ሰሞኑንም በጣይቱ ሆቴል ጃዝ አምባ ላውንጅ በርካታ የስብሐት አድናቂዎችና የአርታኢው አለማየሁ ገላጋይ ተጠረዎች በታደሙበት ተመርቋል፡፡በዕለቱም ከቱባ የስነ-ጽሁፍ ሰዎች እስከ ወጣቶቹ ጭምር በመድረኩ ላይ ስለ መልክአ ሰብሀት መጽሀፍ ምረቃ ሲሉ ስለ ስብአት ለአብ የተለያዩ ስራዎቻቸውን አቅርበዋል፡፡49 የኢትዮጽያ ብር የተተመነለትንና 277 ገጾችን በጉያው የሸከፈውን መልክአ ስብሀት ብዙዎች እንደሚያነቡት ተስፋ አድርጋለሁ፡፡
ከንባባችን በመለስም መጽሀፉን አንብበን ስናበቃ የምንነጋገርባቸው የሐሳብ ሰበዞችን ማቀበሉ እንደማይቀርም እገምታለሁ፡፡ይህንን መንደርደሪያ ምርኩዝ በማድረግም መጽሐፉ ለገበያ መቅረቡ በፊትም ሆነ ከረበ በኋላ ስብሐት ገ/እግዚአብሔርን አስምልከቶ ለራሴ ስጥይቃቸው የነበሩ ጥያቄዎቼን ይበልጥ ያቀጣጠሉ መግፍኤ ሐሳቦችን አነሳ ዘንድ አነሆ አልኩ፡፡
ግለ-ምልከታ
በኔ የግንዛቤ ልኬትመሰረት በመልክአ ስብሐት ላይ ከወጡት ጽሑፎች ውስጥ የተለየና ጠለቅ ባለ ሐሳብ ላይ እይታዎቻቸውን መግለጽ የቻሉት ቴዎድሮስ ገብሬና ሚካኤል ሽፈራው ናቸው፡፡ሌሎቹ ገጣምያን፤ጸሐፍትና ሰዓሊያን የሰጡንን አበርክቶዎች በማክበር ምን አዲስ ነገር ጨመሩልን ስል ለመጠየቅ እገደዳለሁ፡፡እንደውም አብዛኛዎቹ በተለያዩ የህትመት ውጤቶች ላይ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ቀደም ባሉት ጊዜያት ያነበብናቸውና ስብሀት ገ/እግዚአብሄር በህይወት በነበረበትም ሆነ በአጸደ ሰጋ ከተለየን በኋላ የምናውቃቸውን ታሪኮች ዳግም በመልክአ ስብሐት ላይ አቅርበውልናል፡፡ ያም ሆኖ ታድያ የእነዚህን ባለሙያዎች አስተዋጽኦ የመዘንጋትና የማንኳሰስ ስሜት እንዳልተጫነኝ መግለጽ ይገባኛል፡፡ያም ሆኖ ታድያ ስብሐት ስንት ነው እንድል የሚያስገድዱኝን የሐሳብ መጣረሶች ማንሳት የዚህ ሐቲት ዋንኛ ግብ ይሆናል፡፡
ሚያዝያ 27 ቀን1928 ዓ.ም ተውልዶ የካቲት 12 ቀን 2004 ዓ.ም ይህቺን አለም የተሰናበተው ስብሐት በስነ-ጽሑፋዊ ስራዎቹም ሆነ በግለሰባዊ ማንነቱ ዙሪያ የሚነሱ ክርክሮች የሰውየውን መልክ አጠይሞታል፡፡አነዚህ የሰውኛ ግብሩ እና ስነ-ጹፋዊ መለያዎቹ አከራካሪዎች የመሆናቸው ጉዳይም ከባለቤቱ የትኛውንም ወገን ደግፎ ጎራ
ካለመለየቱ ጋር ተዳምሮ የደራሲውን ስንትነት እጠይቅ ዘንድ አስገድዶኛል፡፡ይህ መጠይቅም እርስ በእርስ በተጣረሰ መልኩ ስለ ደራሲው ከተጻፉት የመልክአ ሰብሐት መጽሐፍ ላይ የሚወሰዱ ይሆናሉ፡፡ቀዳሚው የቴዎድሮስ ገብሬ ሐሳብ ነው፡፡
ቴዎድሮስ ገብሬ /ሰብሐትና ወሲብ/
በበይነ-ዲስፒለናዊ መጽሐፉ በሚገባ የተዋቅሁት ቴዎድሮስ ገብሬ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የሰብሐት የመጫወቻ ካርዶች፤ፍትወት፤ልቦናና ታሪክ በሚል ርዕስ ሰፋ ያለ የስብሐት እይታዎቹን ያቀረበበትና ለሰብሐት ስራዎች ጥብቅና ለመቆም የሞከበት ስራ ነው፡፡በዚህ አብይ ርእስ ስር የተለያዩ ንዑስ ርእሶችን ያነሳሳል፡፡ከእነዚህ ወስጥም በተራ ቁጥር 2 ላይ ሥነ-ጽሑፍና ነገረ ወሲብ የተሰኘው ንዑስ ርዕስ ቀልቤን ወሰዶታል፡፡ተዎድሮስ ገብሬ በዚህ ርዕስ ስር የሰብሐትን ስራዎች ነጻ ለማውጣትና ከማህበረሰባዊ እምነቶች፤እሴቶች፤ሰነ-ጽሑፋዊ ግንዛቤዎች ……ወዘተ ያሳደሩትን ተጸዕኖዎች በማለዘብ ለመከላከል ሞክሮአል፡፡ቴዎድሮስ የስብሐትን ስራዎች ከፖሮኖግራፊነት ይልቅ ወደ ሮማንቲክ ሐሳብነት ዝቅ በማድረግ ታቡ የሚሰኙ ማህበራሰባዊ ዋጋዎችን በመጻጻረር ረገድም ስሱ ስለመሆኑ ለማሳየት ሞክሮአል፡፡ለዚህም የአዲስ ባሻገርን መጽሀፍ የዘመን ምልከታና የአሁንን ጊዜ መድረሻ በማሳየት ስራዎቹን ከፍ…ከፍ ለማድግ ሞክሮአል፡፡ለዚህም የፖሮኖግራፊና የአሮቲካን ትንታኔ በማሳየት የሰብሐት ስራዎች ከፖርኖግራፊነት ይልቅ ወደ ሮማንቲክ ፋይዳነት ያጠጋጋዋል፡፡ነገር ግን በትንታኔ ረገድ የቴዎድሮስ የስብሐት ስራዎች ትንታኔ ወደ ፖርኖግራፊነት እየተጠጉበት ሲቸገር ይስተዋላል፡፡ይህንን የትርጉም መመሳስል ለማስታረቅም የስብሐት ስራዎች ፖርኖ ያለመሆናቸውን ለማስተባበል ደጋግሞ ይሞክራል፡፡ አርግጥ ነው፤በዘይቤዎቻቸው ልቅነት እና በጉዳዮቻቸው ባህል ገፍነት በሚታወቁት የስብሐት ልብ ወለዶች ውስጥ የወሲብ ኮክቴል ይገጥመናል፡፡በየዓይነት በየዓይነቱ፡፡ይህን ማለት ግን ሥራዎቹ ፖርኖግራፊ ናቸው ማለት አይደለም፤በፍጹም፡፡ ፖርኖግራፊ ወሲብን በመተንኮስና ስሜትን በማንቃት፤በማስፈንደቅ እርካታ ከመስጠት ያለፈ ፋይዳ የሌላቸው፤በኪናዊ እሴቶቻቸው እምብዛም የሆኑ፤ብዙም ጊዜም በተወሰኑ ገጽታዎችና ነጥቦች ላይ ብቻ ተመስረተው የሚበጁ ስራዎች መጠሪያ ነው፡፡ ሲልም ስብሐትንና ፖርኖግራፊን ለማራራቅ የሚያስችል ርቀቶችን ይጓዛል፡፡ነገር ግን ከዚህ ሐሳብ በመነሳት ብቻ ጥያቄዎችን ማንሳት እፈልጋለሁ፡፡እንደ አቶ ቴዎድሮስ ገለጻ ፖርኖግራፊ መለያዎቹ ከሆኑት ነጥቦቹ መሐከል ስሜትን መተንኮስና ስሜትንመቀስቀስ ስለመሆኑ ሲገልጹ እነዚህ የስሜት መቀሳቀሶች በቃልም ሆነ በተግባር የሚገለጹ ስለመሆናቸው የሚያስማማ ይመስለኛል፡፡የሰብሐት ስራዎች እነ ትኩሳት፤ሌቱም አይነጋልኝም በመሳሰሉትስራዎቹ ውስጥ እነዚህ የስሜቶች መጋራቶች በጋራ የሉም ወይ፡፡የስብሐት ወሲባዊ ስነ-ጽሑፎች በጽሑፍ መልክ ተቀንብበው በመቅረባቸው ኪናዊ ፋይዳ አላቸው ወደሚል ድምዳሜ ካለቀረበን በቀር በስራዎቹ ውስጥ የምናገኛቸው ወስባዊ ተራክቦች የተለየ ጥበባዊ መጠበብና መሰህብን ስብሐት አሳይቶናል ለማለት አያደፋፍረኝም፡፡ምኪኒያቱም በመጽሐፉ ላይ በአብዛኛዎቹ መወድስ አቅራቢዎችም ሆነ በቀደሙት ጊዜያት እንደሚታመነው ሰብሐት የተፈጥሮአዊነት ፍልስፍና አራማጅ ከመሆኑ አንጸርና ህይወትን ከነቡግሯ ለማይት ካለው ጽኑ አምንት አንጻር እንዚህን የመጽሐፌ ሁነቶች መቀባባትና መኳኳልን ስለማይሻ ነው፡፡የጥበባዊ ፋይዳ አንደኛ መገለጫውም ይህ የፖርኖግራፊ ትርጓሜ ለስብሐት አለብ ቅርብ አይሆንም፡፡ ሌላውና ለጥያቄ የሚያነሳሳኝን ሐሳብ ከዚሁ የርሳቸው ትርጓሜ በመነሳት ለመፈተሸ እቀጥላለሁ፡፡ፖርኖግራፊ በኪናዊ እሴቶቻቸው እምብዛም መሆኑን ሲገልጹ የስብሐት ስራዎች ውስጥ እነዚህን ኪናዊ ጉልበቶች ስለማግኘታቸው የነገሩን ነገር ያለመኖሩ ትርጓሜያቸውንና የሰብሐትን ስራዎች እፈትሽ ዘንድ ያነሳሳኛል፡፡ ሰብሐት ስንት ነው እል ዘንድ ከሚያደፋፍሩኝ ጉዳዮች መሐከልም በዚሁ መጽሐፍ ላይ በአቶ ቴዎድሮስ አማካይነት የቀረበው የሐሳበቸው ማሰሪያ የሰብሐት ገ/እግዚአብሔር ቅንጭብ ማድመቂያ ይገኝበታል፡፡
ፖርኖ ማለት ሆን ተብሎ በምርጥ ባለጌ ቃላት የሚጻፍ አንባቢው የሚያቅፈው ሲያጣ ለብቻው የሚደሰትበት ነው፡፡ሊሲዝ ግን የህይወትን ሰዕል የሚያሳይ የስነ-ጥበብ ሥራ ስለሆነ ፖርግራፊ አይደለም፡፡…….
-ዝኒ ከማሁ ገጽ 214
ይህ ሌላኛው የፖርኖጋረፊ ትርጓሜ ለኔ ከማናቸውም ኢትዮጽያውያን እይታ አንጻር ለጋሽ ስብሐት የተገባ ይመስለኛል፡፡ይህም የሰውየውን ስንትነትነት የሚያስማማ ይሆናል፡፡
ጌታቸው ወርቁ/ስብሐትና አጠያየሙ/
በቀጣይ የምመለከትወና ላነሳሁት ጥያቄ መጠንከሪያ የሚሆነኝን የስብሐት ሌላኛውን ገጽ ያገኘሀበተን ሐሳብ የማገኘው ደግሞ በጌታቸው ወርቁ አማካይነት የቀረበው ስብሐት ከአመሻሽ ውብ ገጸ-በከቶች ጋር በሚል ርዕስ ያቀረበው ጽሑፍ ነው፡፡እንደ ጌታቸው ገለጻ ለማጉላትና ለማሳየት የተነሳበት ዋንኛ ማጠንጠኛም በስራም ሆነ በግል የነበሩአቸውን ትውውቆች በማንሳት ስለስብሐት ያሉትን ትውስታዎችና የሰብሐትን ስብዕና ለማጉላት ባደረገው ጥረት ውስጥ የሰውየውን ስንትነት ያሳይችኝን ስስ መሰል ሐሳብ ነገር ግን የዋዛ የማትባል ጉዳይ ነች፡፡ጌታቸው ስብሐትና ወጣቱ ባለቤቱቃላኪዳንን በአጋጣሚ ያገናኘች አንዲት እሁድ ጠዋት የምታወጋ ነች፡፡ጌታቸውና ስብሐት በድንገት የተገኛኙባት ሰንበት ታድያ ስብሐትና ባለቤቱአንዲት ከሱስ ለማገገም በአማኑኤል ሆስፒታል ውስጥ በመታከም ላይ የነበረችን ወጣት ለመጠየቅ ሲያዘግሙ ነበር፡፡ጌታቸውም ድንገት ካገኛቸው ወዳጆቹ ጋር አብሮወደ አማኑኤል ሆስፒታል ይጓዛል፡፡ ቀጣዩ ታሪክ እንዲህ ይተረካል፡፡ስራው በአማኑኤል ሆስፒታል ውስጥ መሆኑን አትዘንጉ፤
………..ቃልኪዳንን በጆርዋ የሆነ ነገር ሹክ አላትና ግማሽ ሊትር የውሐ ላስቲክ ከቦርስዋ አውጥታ ወደኔ ጠጋ በማለት ከሆስፒታሉ ፊት ለፊት ካለው የአበሻ አቄ ቤት ጎራ ብዬ አረቄ ገዝቼላት በኮፋ በርዤ ይዤለት እንድመጣ ተማጸነችኝ፡፡ለመግዣ ልትሰጠኝ የነበረውን 10 ብር አልቀበልም በማለቴ አበይ ተቀብሎ ለባልቴቷ የአእምሮ ታማሚ ሰጣቸው፡፡…………ገጽ 86
ይታያችሁ አንግዲህ ሰብሐት ጌታቸውን የሚልከው ከሱስ ለመላቀቅ ሰዎች ህክምና በሚሰጣቸው ሆስፒታል ወስጥ ሆኖ ነው፡፡ይህንን አረቄ እዚህ ውስጥ ተገዝቶ እንዲመጣ ማዘዝ ደግሞ መዘዙ ምን ሊሆን እንደሚችል የሚያመለክት ነው፡፡ታሪኩ በዚህ ብቻ የሚያበቃም አይደለም፡፡ጌታቸው አረቄውን እንደታዘዘው ገዝቶ ከመጣ በኋላና ከሚጠይቋ ወጣት ጋር ከተገናኙም በኋላ ይቀጥላል፡፡

…………. የሱስ ማገገሚያ ታካሚዎች የሚተኙበት ክፍል ገብተን የተባለችን ብስል ቀይ (በአንድ ወቅት በጣም ቆንጆ እንደነበረች ላሕይዋ የሚመሰክርላት)ልጅ ከበራፉ አቅራቢያ ባለ አልጋ ላይ አገኘናት፡፡ልክ አንደተመለከተችን አቦይ ብላ አቅፋው ስቅስቅ ብላ ማልቀስ ጀመረች፡፡ከቃልኪዳንም ጋር ተቃቅፈው ተላቀሱ፡፡ልጅቱ ሁኔታው የተመቻት አትመስልም፡፡ታሳዝናለች፡፡…………አቦይ በረንዳው ጋ ወጣ ብሎ ቁጭ ካለ በኋላ አረቄ-ፔፕሲውን መጎንጨት ጀመረ፡፡ሲጋራም አጤሰ፡፡ቃልኪዳን ለልጅቱ የሆነ ነገር ሰጠቻትና ሁለቱ ተያይዘው ወደ ውጭ ሲወጡ እኔና አቦይ ወደ ውስጥ ገባን፡፡………..ገጽ 86
እንግዲህ አነዚህ ሐሳቦች ምንን ያመለክታሉ፡፡በሱስ ማገገሚያ ሆስፒታል ውስጥ አረቄ ይ ይዞ መግባትና ከሱስ ለመታከም በሆስፒታል የተኛችን ወጣት መጠየቅ ምንና ምን ናቸው፡፡ከዚያ ባለፈም ቃሊኪዳን ለወጣቷ ያቀበለቻት ምንድን ነው መልሱ መቼም ከዘመዶቿ የተላከላትን ደብዳቤ ሊሆን አይችልም፡፡ግልጽ ነው አደንዛዥ ዕጽ ነው፡፡ምክኒያቱም ስብሐት እጽ ተጠቃሚነቱ የአደባባይ ምስጢር ስለሆነ፡፡ቃሊኪዳንና ወጣቷ ተያይዘው የወጡትም አደንዛዥ ዕጹ በጋራ ለማጤስ ነው፡፡ጌታቸው ሳይነግረን ቀረ እንጂ ወጣቷ ወደ ክፍሏ ስትመለስስ ከያዘው አረቄ ስላለመጎንጨቷ ምን ማስተባበያ ልንሰጥ እንችላለን፡፡ይህ እንግዲህ በስብሐት መወድስ ውስጥ የገባች የሰውየውን ስንትነት የምታጠይቅ ምርጥ ማሳያ ነች፡፡

ሌላው በዚህ መጽሀፍ ወስጥ ያገኙት የሰብሐትን ስንትነት እንዳጸና የገፋፋኝ ሐሳብ የተገኘው ደግሞ ከኃይለ ጊዮርጊስ ማሞ ነው፡፡ሰብሃት አከራካሪው ገጸ-ባህርይ በሚል ርአስ ስር ውዳሴውን አበርከቷል፡፡ከአነዚህ ውዳሰሴ ዘ ስብሐት መዘርዝሮች ውስትጥ ሁለቱ ሐሳቦች አሸንፈውኛል፡፡
እኔ የማህበረሰቡ አዛውንት፤በእነሱ ወርማ የወጣትነት ዓለም የጠፋሁ፤እኔ እንዴት እና ለምን በዚህ እንደባከንኩ እግጠኛ አይደለሁም፡፡
ይህ ሐሳብ ስብሐትን በደንብ የሚገልጸው ይመስለኛል፡፡እርሱም አንዳለው ርዕሴም እንደሚጠይቀው የስብሐት ስንትነት መልስ እንደማይኖረው ማሰሪያም ይመስለኛል፡፡እንደጠፋ፤እንባከነ የሚሰማው በዚህ ትወልድ ብቻ ስለመሆኑ ማጣየቅም ያስፈልጋል፡፡ስብሐት ስንት እንደሆነ የማይታወቅባቸው ክርክሮች በዚህ በኛ ዘመንም ብቻ ሳይሆን በእርሱም ዘመን የነበረ መጥፋትና መባከን ይመስለኛል፡፡በጣልያን ሰማዕታት ሐውልት አሳየ የተባለው ጸያፍ ድርጊት፤የውቤ በረሐ ተረኮች፤ከወጣቶች ጋር ያለው አግባብ፤ለአጠ ፋሪስና አረቄ ያለው ወዳጅነት፤ለፍቅር ያለው ትርጉም፤ለንባብ ያሳየው ትጋት፤ስለ ወሲብ ያለው አቀቋም…….ወዘተ ሰብሐት ስንት ነው እንድል የሚያስገድዱኝ መለያዎች ናቸወ፡፡ይህ ስለ ሰብሐት ያሉትን መምታታችና ጥርት ያለ ማንነቱን ለማወቅ መክበድ በመልክዐ ሰብሐት ጽሁፎች ላይም ብቻ ሳይሆን በመጽሐፉ ላይ በተካተቱትም የስዕል ንድፎች ላይም አስተውያለሁ፡፡አንደኛው ሰዓሊ ስብሐትን ተወዳጅ ሲያደርገው ሌላኛው ደግሞ በራሱ አምሳል ሌሎችን ጠፍጥፎ እንደሚሰራ ቀራጺ ያደርገዋል፡፡በቃራኒው ሰብሐት በብዙ እይታዎች ተወጥሮ ማንነቱን ያጣ ሲያደርገው፣ባንጻሩ ደግሞ በኮረዶች ዳሌ ዙሪያ የቆመውን ሰብሐት ያሳየናል……… ሳይከብዙ በጥቂቱ፡፡
የመጨረሻ መጨረሻ
ለዚህ ሃሳብ መብላላት መንስኤው መልክአ ስብሐት ነው፡፡ያም ሆኖ ደራሲው በማህበረሰቡ ውስጥ ያለውን ትክክለኛ ዋጋ ለማወቅ አልተቻለም ስል ብዙ ራሴን ጠይቄ ነው ፡፡አብዛኛዎቹ የመጽሐፉ ግብአቶች ስለ ስብሐት ዋጋ መነፈግና የሚገባውን ክብር ያለማግኘት ላይ የሚያተኩሩና በዚህም የሚንገበገቡ ናቸው፡፡ስራው ላይ ያተኮረ ባይሆን እንኳን አንድ ጸሐፊ ብቻ ነው በጠንካራ ትችት ስበሐትን የነካው፤ያም ሆኖ ግን የሚካኤል ሽፈራው ድምዳሜ የሁሉንም መወድሶች ክብደት በሚገባ የሚነቀንቅ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ለኔ ስብሐት በእውን ከኖረው ስብሐትነቱ ይልቅ ልክ በመጽሐፍ እንደሚያወቀው ገጸ-ባህሪ ይሆንብኛል፡፡ከዚህ እምነቴ ጋር እንዳልኖር ደግሞ በተሰጠው ገጸ-ባህሪያዊ ውክልና ልክ ልጨብጠው አይቻለኝም፡፡አንዳንዴ ጎበዝ ደራሲ በሚገባ የሳለው ጥሩ ገጸ-ባህሪ ሲሆን ሌላ ጊዜ ደግሞ ጀማሪ የሳለው አብስትራክት ሰዕል ይሆንብኛል፡፡ስራዎቹ እርሱን ሲግልጡ፤እርሱ ደግሞ ስራዎቹን መግለጥ የማይችል ደራሲ ይንብኛል፡፡ስብሐት በእነዚህ መተላለፎች መሀከል ያለ በማህበረሰብ እና በስነ-ጽሑፍ መሐከል በግልጽ ያልተሰመረ የሐሳብ መስመር ሆኖብኛል፡፡ ለዚህ ይሆን ከላይ ለማሳያነት የወስደኳቸው ስራዎች በማድነቅና በመውቀስ መሀከል የተቀመጡት:: መልስ ያለው ወዲህ ይበል፡፡በቀጣይም የሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህንና በዓሉ ግርማ ዝክሮችን ለማቋደስ እንደሚጥር ያወጋን አለማዩሁ ገላጋይን ግን ቃልህ ይጽና ማለት እፈልጋለሁ፡፡

No comments:

Post a Comment