Monday, November 4, 2013

“ባህላዊውን ሙዚቃ ወጣቱ እንዲወደው እፈልጋለሁ” አበባየሁ ገበያው


አብዛኛው ሙዚቃ አፍቃሪ የሚያውቀውና ዝነኝነት የተቀዳጀበት ዘፈኑ “ሰላ በይልኝ” የሚለው ቢሆንም በኢትዮጵያ ያልተለቀቁ በርካታ ዘፈኖች ያህል እንዳሉት ይናገራል - ወጣት ድምፃዊ ጐሳዬ ቀለሙ (ጃኪ ጎሲ)፡፡ ወደ ሙዚቃው ህይወት የገባው ገና በ13 ዓመቱ ነበር - በትያትር በኩል፡፡ በታዳጊነቱ ከታዋቂ አርቲስቶች ጋር ትያትር ለማሳየት ወደ ፈረንሳይ ሄዶ ለበርካታ ዓመታት ወደ አገሩ አልተመለሰም፡፡ በጀርመን በሬጌ ባንድ ውስጥ እንግሊዝኛ ዘፈኖችን ሲያቀነቅን የቆየው ጃኪ ጐሲ፤ የመጀመርያ የአማርኛ ነጠላ ዜማውን ኢትዮጵያ መጥቶ እንደሰራ ይናገራል፡፡ ባህላዊ ዘፈኖችን እያዘመነ በመስራት ወጣቱ ባህላዊውን ሙዚቃ እንዲወደው የማድረግ ፍላጐት አለው፡፡ 
በአሁኑ ሰዓት በአዲስ አበባ የመጀመርያ ሙሉ አልበሙን ለማውጣት ተፍ ተፍ የሚለው ጃኪ፤ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አበባየሁ ገበያው ጋር በህይወቱና በሙዚቃ ሙያው ዙሪያ እንዲህ አውግተዋል፡-
ሥራ ላይ ነው እንዴ ያደርከው? የደከመህ ትመስላለህ ?
አዎ ፤አልበም እየሰራሁ ነው፡፡ ሙሉ አልበም የማወጣው ለመጀመሪያ ጊዜ ስለሆነ ጥሩ ስራ ለመስራት ቀን ከሌት እየተጋሁ ነው፡፡ 
ምን ዓይነት ዘፋኝ ነኝ ብለህ ነው የምታስበው? ባህላዊ ወይስ ዘመናዊ ?
አቅሜ ብዙ ነው ብዬ ነው የማስበው። ባህላዊውንም ዘመናዊንም እችላለሁ። ባህላዊ ሙዚቃን ሞደርን ለማድረግ ነው የምፈልገው፤የባህሉን ሙዚቃ ወጣቱ ትውልድ እንዲወደው እፈልጋለሁ፡፡ ባህሌን ስለምወድ ነው ወደ ባህላዊው የመጣሁት፡፡ ውጭ አገር ሬጌ ባንድ ውስጥ እንግሊዝኛ ሙዚቃ ነበር የምጫወተው፡፡ ያ ደግሞ እኔን አይገልፀኝም፤ እኔነቴን አይወክልም ብዬ ስለማምን ነው የተውኩት፡፡ በዘመናዊ ሙዚቃ ውስጥም አለሁኝ፡፡ ባህላዊ ዘፋኝ ብቻ አይደለሁም። በአዲሱ አልበሜ ባህላዊ ዘፈን ብቻ አይደለም ይዤ የምቀርበው፤አቅሜንም ለማሳየት ስለምፈልግ ለአድናቂዎቼ የተለያዩ ነገሮች ነው የማቀርበው፡፡ ኢትዮጵዊ ቀለም ያላቸው ዘመናዊ ዘፈኖችን ነው የሰራሁት፡፡

ወደ ሙዚቃ ህይወት እንዴት ገባህ ?
በ13 ዓመቴ በህፃናትና ወጣቶች ቲያትር ቤት እሰራ ነበር፡፡ በቲያትር ቤቱ ውስጥ አማርኛ መዝፈን ጀመርኩ፤ መነሻዬ ያ ነው፡፡ ከዚያ ለሥራ ወደ ጀርመን አገር ሄድኩ፡፡ በሬጌ ባንድ ውስጥ የሬጌ ሙዚቃ እጫዎት ነበር፡፡ ኳየርም ነበርኩ። ከረጅም ጊዜ በኋላ ነው ወደ አማርኛ ሙዚቃ የተመለስኩት፡፡ ራሴን ካገኘሁ በኋላ ማለት ነው፡፡ ሬጌ ሙዚቃ ዘፍኜ የሚሰጠኝ አስተያየት (ፊድባክ) አሁን እንደሚሰጠኝ አስተያየት አያኮራኝም ነበር። ዛሬ ‹‹ሰላ በይ›› ብዬ ዘፍኜ ከህዝብ የማገኘው ፍቅርና አድናቆት ኩራትና ደስታ ያጎናፅፈኛል፡፡ ራሴን እንደ ባህላዊ ዘፋኝ አድርጌ ብቻ አይደለም የምቆጥረው። በዘመናዊ ሙዚቃ በኩል ትውልዱ ባህሉን እንዲወድ የማድረግ አስተዋፅዖ ለማበርከትም እፈልጋለሁ። ምክንያቱም ትውልዱ ዘመናዊነትን የሚከተል በመሆኑ ዘመናዊውን ቢሰማ ደስ ይለዋል፣ ሁለቱን በመቀላቀል ባህሉንም በዘዴና በጥበብ የበለጠ እንዲወደው ይሆናል፡፡ ወጣቱ ዘመናዊ ሆኗል፡፡ ቴክኖሎጂ ሲቀየር ሁሉም ሰው እያደገ ነው የሚመጣው፡፡ ወደ ኋላ ሄዶ የድሮውን ነገር ከሚያይ፣ የድሮው ዛሬ ላይ መጥቶለት ሲያይ የመቀበል ሁኔታው ይጨምራል፡፡ 
በህፃናትና ወጣቶች ቲያትር ቤት ውስጥ የማንን ሙዚቃ ነበር የምትጫወተው? 
በድምፃዊነት ስሰራ ቲያትር ቤቱ ብቻ የሚያቀርበውን ነበር የምሰራው፡፡ በብዛት “እቴ ሜቴ”፣ “እንዲች እንዲች” የመሳሰሉ የልጆች ዘፈኖችን ነበር የምሰራው፡፡ የፍቅር ከሆነ ደግሞ ስለ እናት ነው፡፡ ለፍቅረኛ ወይም ስለ ፍቅር አልዘፍንም ነበር፡፡ ዕድሜያችን ያንን ለመዝፈን ስለማይፈቅድ፣ የሚመጡትም ወላጆች ከህፃናት ጋር ስለሆነ፣ እነሱን የሚያስተምር ሙዚቃ ነው የምንሰራው፡፡ በዛን ጊዜ በቲያትር ቤቱ ከጎናችን ሆነው ሲያግዙን የነበሩት እነ ሙሉ ገበየሁ፣ ዛሬ እዚህ ለመድረሴ ከፍተኛ አስተዋፅዖ አድርገውልኛል፡፡ 
ፕሮፌሽናል ድምፃዊ ነኝ ብለህ ታስባለህ ?
አዎ፡፡ በርግጥ ድምፃዊነት የእግዚአብሄር ተሰጥዖ ያስፈልገዋል፡፡ ያንን ጨምረሽ ት/ቤት ስትገቢ፣ ቴክኒካል ነገር ትማሪያለሽ፡፡ ለብዙ ነገር ይረዳል። ተሰጥዖ ብቻውን ምንም አይሰራም፤ተጨማሪ በትምህርት የሚመጡ ነገሮች አሉ፡፡ ትንፋሽ አያያዝና ዜማ አያያዝ ላይ ትምህርቱ ይረዳል፡፡ ከሁሉም ግን ተፈጥሮ ይቀድማል፡፡ 
እንዴት ነው ወደ ጀርመን የሄድከው?
በ13 ዓመቴ ነው ለስራ የወጣሁት፡፡ መጀመርያ ከተለያዩ ታዋቂ አርቲስቶች ጋር ቲያትር ልናሳይ ወደ ፈረንሳይ ሄድን፡፡ ስራውን ከጨረስን በኋላ አክስት ስለነበረችኝ ወደ ኢትዮጵያ አልተመለስኩም፡፡ ሌሎች ሁለት ጓደኞቼም አልተመለሱም፡፡ ከዛ ጊዜ ጀምሮ ኑሮዬ ውጪ ሆነ ማለት ነው፡፡ የመጀመሪያ ነጠላ ዜማዬ እስኪወጣ ድረስ ውጪ ነበር የምኖረው፡፡ 
ውጭ ስንት ዓመት ኖርክ ማለት ነው?…
ወደ 13 ዓመት ገደማ ማለት ነው፡፡ 
ለምንድን ነው ጃኪ ጎሲ የተባልከው ?
ስሜ ጎሳዬ ቀለሙ ነው፡፡ ማንኛውም ሰው ለራሱ መለያ ስም ይሰጣል፡፡ የአርት ስሜ ነው ጃኪ ጎሲ፡፡ 
ጀርመንኛ ትችላለሃ ?
አዎ በደንብ እናገራለሁ፡፡ 
በጀርመንኛ መዝፈንስ ?
ጀርመንኛ አልዘፈንኩም፤ ቋንቋቸውን ብዙ አልወደውም፤ አያምርም፡፡ እናገረዋለሁ እንጂ እንኳን ለዘፈን ለምንም አይሆንም፡፡ ድምፅ ያለሽም አይመስል ብትዘፍኝበት፡፡
በቀለም ትምህርት ምን ያህል ገፋህ ?.
እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል ነው የተማርኩት። ትምህርት ላይ ከልጅነቴ ጀምሮ ሰነፍ ነበርኩ። ሙዚቃ ብቻ ነበር የሚታየኝ፤ሌላ ምንም ነገር አይታየኝም፡፡ ውጪም ሳለሁ ሙሉ በሙሉ ፍላጎቴ ሙዚቃ ላይ ነበር፡፡ የሙዚቃ ስሜቴ ስለበለጠ፣ እንደምንም ገፍቼ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ብቻ ነው የተማርኩት፡፡ 
የምትታወቀው በአንድ ዘፈን ነው..በእሱም በዓለም ላይ እየዞረክ ነው…
ወደ አምስት ዘፈኖች አሉኝ፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ያልመጡና ያልተለቀቁ፡፡ እዚህ ይታወቃል ብዬ የማስበው ሶስት ወይንም አራት ዘፈን ሊሆን ይችላል፡፡ ጭራሽ፣ የእኔ አካል፣ ደሞ አፌ፣ ሰላ በይ፣ ባንዲራው የታለ----እነዚህ ዘፈኖች በደንብ ነው የሚሰሙት---ተጨማሪ የመድረክ ስራዎችንም ይዤ እሄዳለሁ፡፡ የምወዳቸውን የታላላቅ አርቲስቶች ዘፈኖች ጨምሬ ነው የማቀርበው፡፡
በኮንሰርት የት የት አገራት ዞረሃል?
በቁጥር አላውቀውም፡፡ አውሮፓ፣ አውስትራሊያ፣ አረብ አገሮች፣ እስራኤል…በቅርብ ደግሞ ወደ አሜሪካ እሄዳለሁ፡፡ ከአሜሪካ በኋላ ሳውዝ አፍሪካ፣ ኬንያ፣ ሱዳን…አድናቂዎቼ እየጋበዙኝ ስለሆነ የምሄድባቸው ብዙ ቦታዎች አሉ- ከዛየን ባንድ ጋር፡፡ አሁን አብሬ እየሰራሁ ያለሁት ከዛየን ባንድ ጋር ነው፡፡ በጣም አሪፎች ናቸው፤ በጣም ደስተኛ ነኝ ከነሱ ጋር በመስራቴ፡፡ ከዛየን ባንድ ጋር የመጀመሪያ ኮንሰርቴን የሰራሁት በዱባይና አቡዳቢ ነው፡፡ ከዚህ በኋላም ከእኔ ጋር ናቸው፡፡ አሜሪካም አብረውኝ ይሰራሉ፡፡ 
ወደ አውሮፓ ስትመለስ በመደበኛነት ምንድነው የምትሰራው?ናይት ክለብ ውስጥ ትሰራለህ ?
ሬጌ ባንድ ውስጥ ነበር፤ አሁን ትቼዋለሁ፡፡ ‹‹ጭራሽ›› የሚለውን ዘፈኔን እስከሰራ ድረስ ከነሱ ጋር ነበርኩ፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ብዙ ታዋቂ የሬጌ ዘፋኞች አሉ..ያ የእኔ ባህል አይደለም፤ የነሱ ባህል ነው፡፡ ብታወቅበትም ሪፕረዘንት አላደርግበትም፤እኔነቴን ስለማይገልፀው ይሆናል። ኢትዮጵያዊነቱን ይዤ የራሳችንን ባህል ትንሽ አሳድጌው ወጣቱ ትውልድም ሆነ ትላልቁ ሰው እንዲወደው ማድረግ ለእኔ አንድ ሃላፊነት ነው፡፡ ናይት ክለብ ላልልሽው አልሰራም፡፡ 
እዚህስ ኮንሰርት አላሰብክም ?
እዚህ ግብዣዎች አሉ፡፡ አልበሜ ሲወጣ ለማቅረብ መቆየትን መርጫለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ኮንሰርት ማድረግ እንዳለብኝ ይሰማኛል፡፡ እስከ አሁን የምጠብቀው አልበሜ ከወጣ በኋላ ከዛየን ባንዶች ጋር እዚህና አፍሪካ ውስጥ በደንብ ኮንሰርት እንሰራለን፡፡ 
“ሰላ በይልኝ” በሚለው ባህላዊ ዘፈንህ ላይ የምታሳየውን ባህላዊና ዘመናዊ የተደባለቀበት እንቅስቃሴ ኦሪጂናሉን እስክስታ እንደመበረዝ የሚቆጥሩ ወገኖች አሉ ---
በባህላዊ ዘፈን ላይ ዘመናዊ ዳንስ ነው የምደንሰው፡፡ ባህሉን ለማበላሸት ወይም ለመበረዝ አይደለም ዓላማዬ፡፡ ቢቱ ትክክለኛ ነው፤ አልቀየርነውም፡፡ ማሲንቆ አለው፡፡ ዜማ አወጣጤ የኢትዮጵያ ቀለም አለው፡፡ የቀየርነው ስታይሌንና አደናነሴን ነው፡፡ ያን ያደረግሁት ደግሞ ትውልዱን በዘመናዊ እንቅስቃሴ ለመሳብና ዘፈኑ ውስጣቸው ገብቶ እንዲወዱት፣እንዲኮሩበት ነው። ነጮች እንዲያዩትም ብዬ አይደለም፡፡ በአሁኑ ጊዜ ባህላዊ ሙዚቃ እየጠፋ ነው፡፡ ትላልቅ ክለቦች ብትሄጂ ..ባህላዊ ሙዚቃ መክፈት ሃጢያት ነው የሚመስላቸው፡፡ ከውጪ መጥቼ አንዳንድ ጊዜ ትላልቅ ክለብ ስሄድ፣ የውጪ ዘፈን ብቻ ነው የሚደመጠው፡፡ አገሬ ላይ ሳይሆን እዛው ያለሁ ነው የሚመስለኝ፡፡ እና ውስጤ ዘመናዊነትም ባህላዊነትም አለ፡፡ ያንን አቀናጅቼ ውጤት ለማምጣት ነው የሞከርኩት፡፡ ያንንም አምጥቼዋለሁ፡፡ 
እስክስታ ላይስ እንዴት ነህ ?
/ሳቅ/ እስክስታ የለመድኩት ከ“ሶራዎች” ነው፡፡ ለ“ሰላ በይ” የሙዚቃ ክሊፕ ለመስራት ገጠር ሄደን ነው የ“ሶራ”ን ባንድ ያየሁት፡፡ በጣም ተደነቅሁኝ። “ሶራ”ን ይዘው ሲመጡ ለእኔ አዲስ ነገር ነበር --- ከተለመደው ውጪ ስለሆነ፡፡ ደስ የሚል የእስክስታ አብዮት (ሪቮሉሽን) ነው የፈጠሩት፡፡ ትልቅ ለውጥ ነው፡፡ የትም ብትሄጂ ደግሞ የእነሱ ተፅዕኖ አለበት። በሁሉም ቦታ እንደዚህ ዓይነት ለውጥ መምጣት አለበት፡፡ .“ሶራ” ባይቀጥልም ሌላ ሪቮሉሽን ያስፈልጋል፡፡
“ሰላ በይ” ምን ማለት ነው?
ፈታ በይ፣ አንቺ ፈታ ካልሽ ፍቅርም ይፍታታል። ሰላ ካልሽ በመካከላችን ፍቅርና ሰላም ይወርዳል---ነገር አለማክረር ማለት ነው፡፡
በቅርቡ ደግሞ ለብሄራዊ የእግር ኳስ ቡድናችን “ትውልዱ ፍም እሳት ነው”የሚል አዲስ የሙዚቃ ክሊፕ ከናቲ ማን ጋር ሰርታችኋል፡፡ እውነት ትውልዱ ፍም እሳት ነው?እንዴትስ ይገለፃል? 
ናቲ ለሶስት ቀን አውሮፓ መጥቶ በሶስት ቀን ውስጥ ነው የሰራነው፡፡ ቃልዋን በአጋጣሚ እሱ ነው ያመጣት - ‹‹ፍም እሳት›› የምትለውን፡፡ ለዚህ ትውልድ ምን እንስራ ብለን እየተነጋገርን ነበር…‹‹ይሄ ትውልድ ፍም እሳት ነው›› የሚለውን ነገር ሲያመጣ እኔም አመንኩበት፡፡ ሙዚቃውን ያቀናበረው ዮኒ ውብ ይባላል፡፡ እዛው ጀርመን ነው፡፡ ጓደኛዬ ነው። የእኔን ክፍል እኔ ፃፍኩት፡፡ ናቲም የራሱን ክፍል ፃፈ- ‹‹ፍም እሳት›› የሚለውን፡፡ 
በፍቅር ያመነ፣ በቃል የፀና፣
ሀረጉን የማይመዝ ይከተለን እና
በእኛው ቅኝት ገብቶ ይህን ሰምቶ
የእውነትን ዘር ዘርቶ
ተማምኖ የሚኖር ተከባብሮ
ጥላቻን አርቆ ሽሮ
‹‹ሃይለኛ ትውልድ›› ማለት ነው፤በአሉታዊ መልኩ ሳይሆን በአዎንታዊ --- ‹‹ማሰብ የሚችል፣ ፈጣን›› እንደማለትም ነው፡፡ አንቺን ለመውደድ ‹‹አማራ ነሽ፣ ትግሬ ነሽ፣ ኦሮሞ ነሽ፣ ከየት ነሽ፣ ወዴት ነሽ፣ የት ነው ያደግሽው?›› ማለት አይገባኝም፡፡ ለእኔ አበባየሁ መሆንሽ ብቻ ይበቃኛል፡፡ ይሄ በአገር ውስጥም በውጪም ያለውን ይመለከታል፡፡ 
እስካሁን ከአገርህ አርቲስቶች ጋር ኮንሰርቶች አቅርበሃል? 
ከአስራ አምስት ቀን በፊት ከሄለን በርሄ ጋር ዱባይና አቡዳቢ ላይ ሰርቻለሁ፡፡ ከጂጂ ጋር ጀርመንና ሆላንድ፡፡ ብዙ ታዋቂ ሳልሆን ደግሞ ከአስቴር አወቀ ጋር ሰርቻለሁ፡፡ ሁሉም አበረታተውኛል፡፡ አስቴር አወቀ ‹‹ልጅ ነህ በርታ፤ጥሩ ነው ያለኸው›› ብላኛለች። ጂጂ እንደውም ከማደንቃት ነገር--- ያኔ እኔ ሃሳቤ ሁሉ በሬጌ ውስጥ ስለነበር---አንድ አማርኛ ሬጌ ዘፍኜላት “በጣም አሪፍ ነው” ብላ እንደውም ማሲንቆ ክተትበት አለችኝ፡፡ ሬጌ ዘፈኑ ላይ እኮ ነው። በጣም አልረሳትም፡፡ ማሲንቆ እዚህ አገር ርካሽ ተደርጎ ነው የሚቆጥረው፤ሰው ዋጋውን በደንብ አላወቀውም። ውጪ አገር ግን አነጋጋሪ ነው፡፡ ማሲንቆ ስሰማ ሊወረኝ ይችላል፡፡ ባህል ሙዚቃ ውስጥ ማሲንቆ ነው ትልቅ ሚና የሚጫወተው፡፡ 
ማሲንቆ መጫወት ትችላለህ?
አልችልም፤ ብችል ደስ ይለኛል፡፡ ኪቦርድ እሞክራለሁ፣ ቦክስ ጊተር እየተማርኩ ነው፡፡ 
በግራና ቀኝ እጅህ ላይ እንዲሁም አንገትህ ላይ የተነቀስከው ነገር ትርጉም አለው ?
አዎ፡፡ ከአንድ ዓመት በፊት ነው ጀርመን የተነቀስኩት፡፡ እጄ ላይ በህይወት የሌሉትን የእናትና አባቴን ስም ነው የተነቀስኩት፡፡ አንገቴ ላይ ደግሞ የሙዚቃ ኖታ ነው፡፡ ሙዚቃ ህይወቴ የሚለውን ለመጠቆም፡፡ በዚች ምድር ላይ የምወዳቸውን ሶስት ነገሮች ነው የተነቀስኩት፡፡ 
ሙዚቃህ በዩቲዩብ ተወዳጅ ሆኗል፡፡ ለመሆኑ ስንት ሰው ጎበኘው? 
አንዱዋን ብቻ ነው የምነግርሽ፡፡ ‹‹ጭራሽ›› የሚለው ለምሳሌ 3 ሚሊዮን ደርሷል፡፡ ‹‹ሰላ በይ›› የሚለው ደግሞ ሁለት ሚሊዮን ይሆናል፡፡ የተለያየ አካውንት ላይ የተለቀቁትን ብታይ ግን አምስት ሚሊዮን ይደርሳል፡፡
የሙዚቃህ አድናቂዎች እነማን ናቸው?
ወጣቱ ትውልድ ነው በደንብ የተቀበለኝ። ትላልቆቹ መጀመሪያ ላይ አልተቀበሉትም ነበር፤እየቆዩ ሲሄዱ ግን እየገባቸውና እየወደዱት መጡ፡፡ አሁን መንገድ ላይ ሲያገኙኝ ያበረታቱኛል። 
ፍቅረኛ አለህ?
የለኝም፡፡ ለጊዜው ፍቅረኛዬ ሙዚቃ ናት፡፡

No comments:

Post a Comment