የሞትህን ዜና በምን ሁኔታ ሰማህ?
ረቡዕ ወደ ማታ ቤት ቁጭ ብዬ እየሰራሁ ሳለሁ፣ ባልተለመደ መልኩ ስልኮች በተከታታይ መደወል ጀመሩ፡፡ አስደንጋጭ ነበር፡፡ ብቻ የሆነ ነገር እንዳለ ያስታውቃል፡፡
ዜና እረፍትህን ሰምተው መደወላቸውን እንዴት አወቅህ?
አንዱን ጓደኛዬን በድፍረት ጠየቅሁት፡፡ ምክንያቱም በዚህ ፍጥነት በተከታታይ ሲደወል ለእኔ የተለመደ አይደለም፡፡ “ምንድን ነው ነገሩ? አካባቢው ላይ የተፈጠረ ነገር አለ እንዴ? ብዙ ሰው በተከታታይ እየደወለልኝ ነው” ብዬ ስጠይቅ፤“አይ ሞተሀል ተብሎ በሬዲዮ ተነግሮ ነው” ሲለኝ ክው ብዬ ደነገጥኩኝ፡፡ ደግሞ ያስታውቃል፤ አንዳንዶቹ ልክ ስልኬን አንስቼ “ሀሎ” ስላቸው ቶሎ ይዘጉታል። ብቻ መኖሬን ነው ማወቅ የሚፈልጉት፡፡ እንደዚህ ካደረጉት ውስጥ ጓደኛዬ አርቲስት ሰለሞን ቦጋለ አንዱ ነው፡፡ አማኑኤል መሀሪ እንዲሁም ቤተሰቦቼም ድምፄን ሰምተው ብቻ ስልክ ዘግተዋል፡፡ ምክንያቱም ወደ ቤተሰቦቼም ይደወል ነበር፡፡ ከውጭ አገር ሁሉ የስልክ ጋጋታው ሊያቆም አልቻለም፡፡
ሲደውሉልህ የሰዎች ስሜት እንዴት ነበር?
በጣም ህመም የሆነብኝ እሱ ነው፤ በጣም የሚያለቅሱና ኡኡ የሚሉ ነበሩ (ለቅሶ…) በጣም ያሳዝናሉ፤ እኔም አብሬያቸው አለቅስ ነበር (ረጅም ለቅሶ)…
ሬዲዮ ጣቢያው ጋ አልደወልክም ?
ትንሽ ቆይቶ--- ከዛሚ 90.7 ኤፍ ኤም ደወሉልኝ፡፡ “በስህተት ነው ፈለቀ አበበ ሞተ ያልነው፤ የሞተው ግን አርቲስት ፈለቀ ጣሴ ነው፤ አንተ በጣም ታዋቂ ስለሆንክ ፈለቀ ስንል አፋችን ላይ የገባው የአንተ አባት ስም ነው” አሉኝ፡፡ ነገር ግን ሰው በጣም ያለቅሳል፤ በጣም ያሳዝናል፡፡
ይቅርታ ጠየቁ ወይስ----
እኔን በግሌ ይቅርታ ጠይቀውኛል፡፡ አድማጮችን ይቅርታ ይጠይቁ አይጠይቁ አላውቅሁም፡፡ ነገር ግን በነገሩ በጣም አዝኛለሁ፡፡ ማንም ከሞት አይቀርም ግን እንዲህ ቀላል የሚመስሉ ስህተቶች ከባድ ጉዳት ያመጣሉ፡፡ ለምሳሌ በድንጋጤ ልቡ ቀጥ የሚል ቤተሰብ፤ ወዳጅ ዘመድ ይኖራል፤ መሞት አለ --- ስንት ነገር አለ፡፡
በዚህ ድንገተኛ ክስተት ምን ተረዳህ?
እንዴ… በጣም በጣም ተገረምኩ እንጂ! ይህን ያህል ሰው ይወደኛል ወይ ነው ያልኩት፡፡ በጣም ደነቀኝ፡፡
ዜና እረፍትህ ከተነገረ ጀምሮ ምን ያህል ሰው ደውሎልሀል?
ከ500 በላይ ስልክ ተደውሏል፤ በግምት ወደ 600 ሳይጠጋ አይቀርም፡፡ ከዚህ በስህተት ከተሰራጨ ዜና እረፍት መልካም አጋጣሚ የምትለው ነገር አለ?
እንደውም በጣም እድለኛ ነኝ አልኩኝ፡፡ በቁሜ ይህን ያህል ሰው እንደሚወደኝ ማየት ችያለሁ፡፡ ግርምቴ እስካሁን አልቆመም፡፡
ከዚህ በፊት ያልሞተ ሰው ሞተ ተብሎ የተነገረበትን አጋጣሚ ታውቅ ነበር?
ሰምቼ አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን ብዙዎቹን የሰማኋቸው ዛሬ (ሐሙስ ማለቱ ነው) ነው፡፡ ለምሳሌ ጥላሁን ጉግሳ የሚባል ሌላ አርቲስት ሲሞት፣ በስም መመሳሰል በህይወት ያለው ጥላሁን የመሰለበት አጋጣሚ ትዝ ይለኛል፡፡ ሌላ ጊዜ በቴሌቪዥን አርቲስት ሲራክ ታደሰ ሲሞት፣ የአርቲስት አለሙ ገ/አብን ፎቶ ማሳየታቸው ትዝ ይለኛል፡፡ ያጋጥማል ነገር ግን ሰው የሚያለቅሰው… መንገድ ላይ ሲያዩኝ የሚሆኑት ሁኔታ በጣም ያሳዝናል፡፡
አሁን እንዴት ነው ስልኩ ቀነሰ? አንተስ ተረጋጋህ?
ያው እየተረጋጋሁ ነው፡፡ አንድ ነገር ወደ አዕምሮዬ መጣ፡፡ የህይወት እስትንፋስን የሚሰጠው እግዚአብሔር ነው፡፡ የምንኖረውም እግዚአብሔር የፈቀደልንን ያህል ነው፡፡ ማናችንም ከተቆረጠልን ቀን አናልፍም፡፡ ግን እዛው ቤቴ ውስጥ ቁጭ ብዬ፤ “አሁንስ ለመኖሬ ምን ማረጋገጫ አለ” ብዬ መፈላሰፍ ጀመርኩኝ፡፡ ከዚያ “ኦኬ በቃ አለሁ ማለት ነው…” ማለት ጀመርኩኝ፡፡ አንዳንዶች እኮ “እርግጠኛ ነህ ፈለቀ ነህ የምታናግረኝ” ብለውኛል፡፡ ስለሞት ብዙ ነገር ነው ያሰብኩት፡፡ ከምንወለድበት ቀን ይልቅ የሞት ቀን ይሻላል የሚለውንም አሰብኩኝ፡፡ እንደውም የአዲስ አድማስ ባለቤትና መሥራች አሰፋ ጎሳዬ ሲሞት አዲስ አድማስ ግቢ ሆኜ የፃፍኩት ግጥም ነበር፡፡
ትዝ ይልሃል ---ምን የሚል ነው?
ቢርቅም አይጠፋም ይልቃል ከሽቶ
በሰው ልብ ይኖራል ከመቃብር ሸሽቶ፡፡ የሚል ነበር፡፡ አየሽ --- በዚህ አጋጣሚ ያየሁት የሰው ፍቅር፤ የበለጠ የምሰራበትና መልካም ያልሆኑ ነገሮች ካሉኝም ለማሻሻልና ጥሩ ለማድረግ የምተጋበት ነገር ተፈጥሯል፡፡ የበለጠ መልካም ሆኜ እንዳልፍ የሚያደርግ ጥሪም ነው፡፡ ደጋግሜ የምነግርሽ… ሰው ለእኔ የሆነው ነገር ገርሞኛል… እንዲህ ነው ወይ የምትወዱኝ ነው ያልኩት፡፡
አንዳንዴ ሞት የሚያናድደው ከሞትክ በኋላ ሰው ለአንተ ያለውን ፍቅርም ሆነ ጥላቻ ማየት ባለመቻሉ ነው አይደለ?
እውነት ነው፡፡ እህቴም እንደዚህ ነው ያለችው፡፡ እህቴ ምስጢር ደምሴ ስትነግረኝ፤ መንግስቱ የተባለ ደራሲ “ሞቻለሁ” ብሎ ቀጨኔ መድሀኒዓለም ሰው ተሰብስቦ ዋይ ዋይ ሲል፣ እሱ ተደብቆ ማን ቀብር እንደመጣና እንዳልመጣ፣ ማን ከልቡ እንዳዘነና እንዳላዘነ ይመለከት ነበር፡፡ ይሄ ይገርማል። እሱ አስቦበትና ተዘጋጅቶ ነው፡፡ እኔ ደግሞ ከዚህ በተቃራኒው ሌሎች በፈጠሩት ስህተት፣ የህዝቡን ፍቅር አይቼበታለሁ፡፡ እኔ ልሳቀቅ፣ እኔ ልደንግጥላቸው (ለቅሶ…)
የሞትህ ዜና ሲነገር ስራ ላይ እንደነበርክ ነግረኸኛል፡፡ ምን እየሰራህ ነበር?
የመጽሐፍ ቅዱሱን ዮሐንስ ራዕይን በትረካ መልክ ለማቅረብ እየተረጐምኩ ነበር፡፡ በመተርጐም ላይ ሳለሁ ነው ስልኩ በተደጋጋሚ መደወል የጀመረው። ሀሙስ ጠዋት ከቤት ስወጣ ገርጂ አካባቢ “ዊሽ ስቱዲዮ” የሚባል ፎቶ ቤት አለ፤ ፎቶ ሲያነሱኝ አየሁ፡፡
ለምን እንደሆነ አልጠየቅሃቸውም? አልጠየቅኳቸውም፡፡ እነሱ ማታ ሞቷል መባሉን ሰምተው አድረው ኖሮ፣ ፎቶ ካነሱኝ በኋላ “Fele this morning” ብለው ፌስ ቡክ ላይ ፖስት አድርገውኝ አየሁ፡፡ ሌላም ሰው “Still alive” ብሎ ፖስት አድርጓል --- እና የሚገርም ነው፡፡
እና አሁን ምን ትላለህ?
አለሁ አልሞትኩም፤ ፈጣሪ እስከፈቀደልኝ እኖራለሁ፡፡ የሞተውን ወዳጃችንን ፈለቀ ጣሴንም ነፍሱን ይማርልን፡፡ ማርክ ትዌይን ያለውን እናስታውስና እንጨርስ፤ “ሞቴን በተመለከተ የወጣው ዘገባ ያለቅጥ ተጋንኗል” እናም አልሞትኩም። በዚህ አጋጣሚ አንዱ ጓደኛዬ መኪና እየነዳ “ፈለቀ አበበ ሞተ” ሲባል በድንጋጤ መኪናውን መቆጣጠር አቅቶት ከመስመር ወጥቶ ሊጋጭ ለትንሽ ነው የተረፈው፡፡ እህቴም ቀድማ አልሰማችም እንጂ በልብ ድካም ትሞት ነበር፡፡ ስለዚህ ጋዜጠኝነት ትልቅና የተከበረ ሞያ በመሆኑ በጥንቃቄ ሊያዝና ሊከበር ይገባል እንጂ በቸልታ የሚሰራበት አለመሆኑን ልገልጽ እወዳለሁ፡፡ የኢትዮጵያን ህዝብ እግዚአብሔር ያክብርልኝ፤ እኔም እወዳችኋለሁ፤ ስለተጨነቃችሁ ስላዘናችሁልኝ አከብራችኋለሁ እላለሁ፤ አመሰግናለሁ፡፡
http://www.addisadmassnews.com
No comments:
Post a Comment