Tuesday, July 3, 2018

“ዶ/ር ዐቢይ፤ የርዕዮተ ዓለምና የቀኖና እስረኛ አይደለም” Written by አለማየሁ አንበሴ

Dr .Dagnachew Asefa 


ዩኒቨርሲቲ የመወያያ መዲና እንጂ ከመንገድ የመጣን ሃሳብ ሁሉ መቀበያ አይደለም

    ከሦስት ዓመት በፊት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርነታቸው የተባረሩትና ሰሞኑን በራሳቸው ጥያቄ፣ ወደ ማስተማር ሥራቸው የተመለሱት የፍልስፍና ምሁሩ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ፤ እንዴት ወደ ዩኒቨርሲቲ እንደተመለሱ፣በሃገሪቱ እየታየ ስላለው የፖለቲካ ለውጥና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርገዋል፡፡

    አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማስተማር የጀመሩት እንዴት ነው?
ለብዙ ዓመታት አሜሪካን ሃገር ነው የኖርኩት፡፡ በቆይታዬ ብዙ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ስለመመለስ ነበር የማስበው፡፡ ወደ ሃገሬ ተመልሼ ማስተማር ነበር የምፈልገው፡፡ ለኔ ማስተማር የህይወት ጥሪ ነው፤ ሌላ ነገር መስራት አልችልም፡፡ እዚያም ሃገር የምሠራው አስተማሪነት ነበር፡፡ በዚህ መነሻ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና ትምህርት ክፍል አቅንቼ፣ “እናንተ ጋር ማስተማር እፈልጋለሁ፤”አልኩኝ፡፡ በወቅቱ ያነጋገርኳቸው ሓላፊም”ታዲያ አንተ ከፕ/ር አንድርያስ ጋር ትግባባለህ፣ ለምን ከሳቸው ጋር አትነጋገርም?” አሉኝ፡፡ “አይ እንደሱ አልፈልግም፤ በመተዋወቅ ሳይሆን በህጋዊ መስመር መጥቼ ነው መግባት የምፈልገው” አልኩ፡፡ በኋላም የዲፓርትመንቱ ሃላፊ ጋ ማመልከቻዬን አቅርቤ ተቀበሉኝ፤ በዚህ ሁኔታ ነው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን የተቀላቀልኩት፡፡ መግባቴን ፕ/ር አንድርያስ የሰማው በኋላ ነው፡፡  
ዩኒቨርሲቲ እያስተማሩ፣ በተለያዩ የፖለቲካ መድረኮች ላይ ሃሳብዎን ያቀርቡ ነበር…?
አሜሪካን ሃገር ለ10 ዓመታት ያህል አስተምሬያለሁ። በዚህ ቆይታዬ፣ ለሰው ልጅ፣ ነፃነት ሁለተኛው ተፈጥሮው መሆኑን አውቄያለሁ፡፡ አካዳሚክ ነፃነት ማለት ምን እንደሆነ ጠንቅቄ አውቃለሁ፡፡ ለምሳሌ፡- በ1919 በሁለት ፕሮፌሰሮች ተረቅቆ፣ አሁን ድረስ እውቅና ያለው የአካዳሚክ ነፃነት ምሶሶዎች (መርሖዎች) አሉ፡፡ አንደኛው፤ በትምህርት ክፍል ውስጥ በመረጠው ርእሰ ጉዳይ ለማስተማር የመቻል ገደብ የለሽ ነፃነት ነው፡፡ ሁለተኛው፤ በምርምር ያካበተውን እይታና ሐሳብ በመጽሐፍ የማሳተም ነፃነት ነው፡፡ ሦስተኛው፤ ዩኒቨርሲቲውን በሚመለከት ከአስተዳደርና አትክልተኛ እስከ ፕሬዚዳንቱ ጽ/ቤት ድረስ የመማር ማስተማር አሠራሩን የመተቸት መብት ነው፡፡ አራተኛው ምሶሶ፤ ስለ ሃገርህ ሁኔታ እንደ አንድ ዜጋ የፈለግኸውን ነገር የመናገር መብት ነው፡፡ እነዚህ ናቸው የአካዳሚያዊ ነፃነት ምሶሶዎች፡፡ ይሄን ይዤ አስተምራለሁ፤ በዚያው ልክ የምሁራዊ መብቴን ተጠቅሜ እተቻለሁ፡፡ 
እኔ በየመድረኩ ስናገር፣ እተች የነበረው፣ ይህን ተፈጥሮአዊ መብቴን ተጠቅሜ ነው፡፡ ልክ ኮንትራቴን አቋርጠው፣ “አታስተምር” ሲሉኝ፤ “አሁን ገና ኢትዮጵያዊ ሆንኩ” ነው ያልኳቸው፡፡ ምን ማለት ነው ተብዬ በብዙኃን መገናኛ ተጠየቅሁ፡፡ በወቅቱ የመለስኩላቸው፤”ኢትዮጵያዊ ማለት መብቱ የተረገጠ ነው፤የኔ መብት እስክባረር አልተረገጠም ነበር፤ አሁን ተረግጧል፤ ስለዚህ ኢትዮጵያዊ መሆኔን አረጋግጫለሁ፤” በማለት ነው፡፡ በርግጥም የሆነው እንደዚያ ነው፡፡ 
በዩኒቨርሲቲ ቆይታዎ ምንድነው  የታዘቡት?


እኔ መጀመሪያ ስገባ ያስተዋልኩት ነገር ዝምታ መስፈኑን ነው፡፡ ሁሉም ጭጭ ያለ ነገር ነው፡፡ እኔ እንኳ ስናገር፣ ከመስመር የወጣ አድርገው ነበር የሚያዩኝ። “ይሄ ገና ሃገሩ አልገባውም፤ ቆይ ዋጋውን ያገኛል” የሚሉም ነበሩ፡፡ የኔ አመለካከት ደግሞ ዩኒቨርሲቲ የዝምታ መድረክ አይደለም፡፡ ዩኒቨርሲቲ የመወያያ፣ የመተቻቻ፣ ሃሳብ የመፈተሻና የማፍታቻ፣ ትልልቅ ሃሳቦች የሚነሱበት የሚወድቁበት ቦታ ነው፡፡ ነገር ግን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለዚህ የተመቸ አይደለም፡፡ ዝም ብሎ በመንገድ ያለፈ ሃሳብ መቀበል ነው ልማዱ፡፡ ከዚህ አንፃር፣ የኔ አካሄድ አልተመቻቸውም ነበር፡፡ በነገራችን ላይ ፀባቸው ከኔ ጋር አይደለም፤ ከአስተሳሰብ ብዝሃነት ጋር ነው፡፡ በእኔ እይታ ዩኒቨርሲቲው ትችትን ማስተናገድ አቃተው፤ ፍልስፍናን ማስተናገድ አቃተው፡፡ ስለዚህ እኔ መባረር ነበረብኝ፡፡ ልክ አቴናውያን ፍልስፍናን ማስተናገድ አቅቷቸው፣ ሶቅራጥስን እንደገደሉት፡፡ ልክ አክሱማውያን ፍልስፍናን ማስተናገድ ሲያቅታቸው፣ ዘርአያዕቆብን እንዳባረሩት ነው፡፡ እኔ ፈላስፋ ነኝ እያልኩ አይደለም፡፡ ነገር ግን ዩኒቨርሲቲው የተለየ ሃሣቤን ማስተናገድ አልቻለም፡፡ እንደውም ለ7 አመት ታገሰኝ ማለት ይቻላል፡፡
ለምንድነው ዩኒቨርሲቲው የሃሳብ ብዝሃነትን  ማስተናገድ የተሣነው?
በዩኒቨርሲቲው እኮ የአካዳሚክ የበላይነት ያላቸው አይደሉም እያስተዳደሩት የነበረው፡፡ ከአካዳሚያዊ የበላይነት ይልቅ ካድሬያዊ የበላይነት የነበራቸው ናቸው፡፡ እንኳን አመራር አስተማሪ መሆን የሚቻለው እኮ ግለሠቡ ባለው የፖለቲካ ውግንና ነበር፡፡ የትምህርት ማዕከልነቱ እየተደፈጠጠ እያነሰ፣ ዩኒቨርሲቲው የፖለቲካ መድረክ፣ ያውም የአንድ የፖለቲካ አስተሳሰብ በግድ የተጫነበት ማዕከል ነው እየሆነ የመጣው፡፡ ይሄ ነው የተለየ ሃሣብ ካላቸው ሠዎች ጋር ያጋጨው፡፡
የአካዳሚያዊ ነፃነት ምሰሶዎች ብለው ከጠቀሷቸው አንፃር፣ የዩኒቨርሲቲውን ምሁራን እንዴት ይገመግሟቸዋል?
በደርግ ጊዜ ትንሽ ጫና--- በተለይ እስራትና ግድያ ስለነበር ሁኔታው አስቸጋሪ ነበር፡፡ ከዚያ የተወረሰ ልማድ ይመስለኛል፣ አብዛኛው ምሁር ዘንድ ያለው፣ “አርፌ ልጆቼን ላሳድግ” የሚል አስተሳሰብ ነው። ይህ የምሁራኑ ዳር መያዝ ሳያንስ ደግሞ ካድሬዎች አመራሩን ለፖለቲካ ጥቅም ወሰዱት፤ ምሁሩን አንድ ለአምስት እናደራጅ አሉ፡፡ አንድ ቀጭን መንገድ የነበረችው፣ ማስተማር ብቻ ነች፡፡ 
በእንዴት ያለ ሁኔታ ነው፣ ከዩኒቨርሲቲው የተሰናበቱት?
እውነቱን ለመናገር፣ አሁን እጄ ላይ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማስተማሬን እንኳ ማስረዳት የምችልበት ሰነድ የለኝም፡፡ “ሰባት ዓመት አስተምረሃል፤ አሁን አንፈልግህም” የሚል ወረቀት እንኳን አልሰጡኝም። የሆነው ምን መሠለህ…የዕረፍት ጊዜ ተሰጠኝ። ወደ አሜሪካ ሄድኩ፡፡ ከሁለት ሣምንት በኋላ፣ “ወደ ዩኒቨርሲቲው አልመለስም ብለሃል” በማለት እንዳላስተምር ከለከሉኝ፡፡ በወቅቱ ወደ ፍርድ ቤት ስሄድ፣ “በመጀመሪያ የዩኒቨርሲቲው የቦርድ ሊቀ መንበር ለነበሩት አቶ ካሣ ተ/ብርሃን፣ በሕጉ መሠረት አስቀድመህ አቤቱታ ሳታቀርብ ክሥ መመሥረት አትችልም፤” ተባልኩ፡፡ እርሳቸው ቢሮ ብሔድ ብመላለስ፣ ምንም ምላሽ አጣሁ፡፡ በዚህ ሁኔታ ነው ያለፈውን ሦስት አመት ያሳለፍኩት፡፡ በዚህ መሃል ግን ስራ አልፈታሁም፤ በተለያዩ የሃገር ውስጥ ዩኒቨርሲቲዎች በግል አስተምር ነበር፡፡ 
እርስዎ “የሕግ ጥሰት ተፈጽሞብኝ ነው የተሰናበትኩት” ብለዋል፡፡ እንዴት ነው የሕግ ጥሰት የተፈጸመው?
መምህራኑን በሚመለከት መቅጠርና ማሰናበት የሚችለው የፍልስፍና ትምህርት ክፍሉ ነው፡፡ ይህ መብት ያለው ትምህርት ክፍሉ ነው፡፡ በወቅቱ የነበሩት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ግን ያለቦታቸው፣ በማያገባቸው ጣልቃ ገብተው ነው፣ በውስጥ ትእዛዝ፣ “የዶ/ር ዳኛቸውን ኮንትራት እንዲቋረጥ አድርጉ” ያሉት፡፡ በዩኒቨርሲቲው ህግ ግን ትምህርት ክፍሉ እስከፈለገ ድረስ፣ አንድ መምህር ለምን እድሜው 80 አይሆንም፣ ማስተማር ይችላል፡፡ 
አሁን ወደ ዩኒቨርሲቲው የተመለሱት በምን አግባብ ነው?
እኔ አስቀድሜ እንዳልኩት፣ ማስተማር የምወደው ስራ ነው፡፡ አሁን ባለው የለውጥ ሁኔታ ተበረታትቼ፣ በቀጥታ አሁን ላሉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ነው፣ “መመለስ እፈልጋለሁ” ብዬ የፃፍኩት፡፡ መመለስ የፈለግሁትም አሁን ባለው የፖለቲካ ለውጥ ተበረታትቼ ነው፡፡ አሁን አንድ አንድ የሁለተኛ ድግሪና የሦስተኛ ድግሪ ተመራቂዎችን፣ የመመረቂያ ጥናት እንድገመግም ጠይቀውኛል፤ ወደ ዩኒቨርሲቲው ተመልሻለሁ ለማለት ነው፡፡ 
በፖለቲካ ለውጡ ተበረታትቼ ነው ወደ ማስተማር ለመመለስ የፈለግሁት ብለዋል፡፡ በአጠቃላይ ፖለቲካዊ ለውጡን እንዴት ይመለከቱታል?
እኔ ገንቢ የኾነ ለውጥ እየተደረገ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ በመጀመሪያ ላይ ይህን ለውጥ ብዙ ሰዎች ተጠራጥረውት ነበር፡፡ ምክንያቱም የለመድነው ለውጥ፣ በዐፄ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ የነበረው በግጭት የመጣ ለውጥ ነው፡፡ የኮሎኔል መንግሥቱ ጊዜም ያበቃው፣ በግጭትና ትርምስ ነው፡፡ አሁን የመጣው ዝም ያለ ለውጥ ነው፡፡ አፄው እና ደርግ ሲለወጡ ከነበረው ለውጥ ያሁኑ የተለየ፣ የሠከነ ለውጥ ነው፡፡ እንደውም ጥልቀትና ጥብቀት የሚኖረው፣ እንዲህ አይነቱ ለውጥ ነው፡፡ ዶ/ር ዐቢይ፣ ዞሮ ዞሮ ኢህአዴግ ነው የሚሉ ሰዎች ማጤን ያለባቸው ነገር አለ፡፡ ኢህአዴግ አራት እግር ያለው ድርጅት ነው፡፡ ትግራይ እግር አለው፣ ኦሮሚያ እግር አለው፣ አማራ እግር አለው፣ ደቡብ ላይ እግር አለው፡፡ አሁን የመጣው ለውጥ በኦሮሞ እና አማራ እግር ላይ ነው፡፡ በፊት ትልቁ እግር የነበረው ህወሓት ነው፡፡ አሁን ህወሓት በድሮ መንገድ ልትቀጥል አልቻለችም፡፡ ሰፊ የውስጥ ትግል ተደርጎበታል፡፡ ይህ የውስጥ ትግል ደግሞ የውጪ ትግሉን፣ ደጀን፣ መከታ ያደረገ ነው፡፡ ዶ/ር ዐቢይ ወደ መንበረ ሥልጣን የመጣው፣አራቱ የኢህአዴግ ድርጀቶች ተሰብስበው፤ “አንተ ሁንልን፣ አንተ ምራን” ብለው አይደለም፡፡ከጠረጴዛ ዙሪያ ውጭም ትግል ተደርጎ ነው፡፡ ለዚህ ትግል ደግሞ በተለይ የአማራና የኦሮሞ ትግል ደጀን ነበር፡፡ በብዙ መስዋዕትነት የመጣ መሪ ነው፡፡ እንደ አቶ ኃይለ ማርያም እንዲሁ በህወሓት በጎ ፈቃድ የመጣ አይደለም፡፡ ዶ/ር ዐቢይ፣ይሄን የመጣበትን መንገድ ከረሳ፣ነገር ተበላሸ ማለት ነው፡፡ ይሄ እውነት መኾኑን ማረጋገጫ መጥቀስ ካስፈለገ፣ መጥቀስ ይቻላል፡፡
ያስፈልጋል እንጂ--- እስቲ ይጥቀሱልን?
ሁላችንም እንደምናስታወሰው፤ በሕዝቡም በጠረጴዛ ዙሪያም የተሸነፈችው ህወሓት፣ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁን ይዛ ነው የመጣችው፡፡ የዚህ ዓላማ የነበረው፣ የጠረጴዛውን ዙሪያ የፖለቲካ ጨዋታንም ለመጫን ነበር፡፡ ኦህዴድ ደግሞ ቄሮን ይዛ ብቅ አለች። ብአዴን፤ ከጎንደር እስከ መርሳ ያለውን ሕዝቧን ይዛ ነው ወደ ጠረጴዛው የመጣችው፡፡ በጠረጴዛ ዙሪያ ሲሰበሰቡ፣ እነዚህ ሁሉ ታሳቢ ተደርገው ነው። ህወሓት ምን አለሽ ስትባል፣”ሠራዊቱ አለኝ” አለች፡፡ ኦህዴድ ደግሞ “ቄሮ አለኝ”፣ ብአዴን ደግሞ “ሕዝቡ አለኝ” ነው የተባባሉት፡፡ ይህን እንደተባባሉ መጠራጠር የለብንም። በኋላ ነው ህወሓት፣ ቄሮንና ሕዝቡን፣ ወታደራዊ ሠራዊቱ ሊቋቋመው እንደማይችል ተረድታ፣ ከቦታው ገለል ማለትን የመረጠችው፡፡ በዚህ ነው ዶ/ር ዐቢይ ወደ ሥልጣን የመጣው፡፡
ሁለተኛው ታሳቢ ምን መሰለህ? አስቀድሞ ኦህዴድ፣ የኦሮሞን ህዝብ የሚወክል ድርጅት እንደሆነ ተፈቅዶለታል፤ ግን የተፈቀደለት ህወሓትን በማይገዳደር መልኩ ነበር፡፡ በተመሣሣይ ብአዴንም አማራውን እንዲወክል ተፈቅዶለታል፤ ግን ህወኃትን በማይገዳደር መልኩ ነው፡፡ ይሄን የህወኃት ስሌት ነው እንግዲህ እነ ለማ መገርሳ፣ አሽቀንጥረው የጣሉት፡፡ “እኔ የእናንተ ጉዳይ አስፈፃሚ አይደለሁም፤የምወክለውን ህዝብ እንጂ” ብሎ ነው፣ የእነ አቶ ለማ ቡድን የተነሣው፡፡ ብአዴንም በእነ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው አመራር ወደዚያው ነው እየሄደ ያለው፡፡ የእነሱ (ህወሓት) ጭንቀት የነበረው፣ የኦሮሞና የአማራ ብሄርተኝነትን፣እንዴት የኛን የበላይነት በማይገዳደር መልኩ ማስተናገድ እንችላለን የሚለው ነበር። ያ ቁጥጥራቸው ነው፣ በቄሮና በእነ ለማ መገርሣ የተሠበረባቸው፡፡ ለዚህ ነው ዛሬ ዶ/ር ዐቢይ፣ ብዙ ርቀት ሄዶ፣ በልበ ሙሉነት፣ ያሻውን የሚናገረው፣ ያሻውን የሚያደርገው፡፡ 70 እና 80 ሚሊዮን ህዝብ ከጀርባው እንዳለ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ በቅዳሜው ሠላማዊ ሠልፍም የታየው ይሄው ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት በተጨባጭ የሚታይ  ለውጥ እየመጣ ነው ማለት ይቻላል?
በእኛ ሃገር የተለመደው ለውጥ አንዱ ጉልበተኛ ደካማውን አሽቀንጥሮ ጥሎ፣ በዙፋኑ እርሱ የሚነግሥበት ነው፡፡ ብዙ ሰው ያለቀበት ዐይነት ለውጥ ነው እኛ የለመድነው፡፡ ለዚህ ነው ዝግ ብሎ፣ ነገር ግን ሥር እየሰደደ የሚመጣ ለውጥ የማይታየን። ርግጥ ነው በጥንቃቄ ማየቱ ጠቃሚ ነው፡፡ በዚያው ልክ ከወራት በፊት፣ ይህ ሃገር ሊፈነዳ የደረሰ እንደነበር መለስ ብሎ ማየት ያስፈልጋል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ መምጣት ባያረጋጋው፣ ምን ሊኾን ይችል ነበር? ዶ/ር ዐቢይ፣ ከዚህ ጥግ ላይ ተቀምጠው የነበሩ ግፉዓን፣ ሊቀበሉ የሚችሉትን ነገር ነው ይዞ የመጣው፡፡ ኢትዮጵያዊነትን ነው ይዞ የመጣው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ያለፈ ነገር ነው፣ ትተነዋል ሲሉ ከነበሩ ሰዎች መሃል እነዚህ መጥተው፣ ጭራሽ “ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው” ብለዋል፡፡ በሠላማዊ ሠልፉ ያየሁትም ይሄን ስሜት ነው፤ ይሄ ቀላል አይደለም፡፡ ከዚህ በኋላ አሁን ካለንበት ቡድናዊ ሁኔታ፣ ወደ ዜግነት ላይ የተመሠረተ ፖለቲካ መሸጋገሩ ቀላል ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነትን እየጣሱ ነው፣ ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ ርእዮተ ዓለም አፈንግጠዋል የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?
ዶ/ር ዐቢይ፣ ርእዮተ ዓለም ሳይገድበው፣ ሕግና ቀኖና ሳይገድበው፣ የጊዜውን ጥያቄ በጊዜው መንገድ ለመፍታት የተዘጋጀ ሰው ነው፡፡ የርእዮተ ዓለምና የቀኖና እስረኛ አይደለም፡፡ የእሱ ጥንካሬም እዚህ ላይ ነው፡፡ የተወሰኑ የፓርቲ የርእዮተ ዓለም መመሪያዎች ተቀብሎ፣ “ይሄ ይደረግ፣ ያ ይደረግ” ማለት አልፈቀደም። ለህዝቡ ይበጃል፣ ለሃገሪቱ ይመጥናል ካለ ማድረግ አይከብደውም፡፡ ደፋር ነው፡፡ የአብዮታዊ ዴሞራክሲ እስረኛ አይደለም፡፡ በመሠረቱ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ምን እንደሆነ፣ ጠበቃ እንቆምለታለን የሚሉትም በቅጡ አያውቁቱም፡፡ ሊገልፁትም አይችሉም፡፡ ዶ/ር ዐቢይን ዝም ብለን በርእዮተ ዓለም ጎራ ውስጥ አስገብተን ማየት አንችልም፡፡ ለእነሱ ለራሳቸው ሕክምና ነው እየሰጣቸው ያለው፡፡
ይህን ሐሳባቸውን ወደ ህዝቡ ለማውረድ የተጠቀሙበት መንገድስ?
ሌላው አስገራሚው ነገር እርሱ ነው፡፡ ዶ/ር ዐቢይ ከብዙ ሥረ መሠረት የመጣ ነው፡፡ በሃይማኖትም በብሔርም ብናየው፣ መሠረቱ ሰፋ ያለ ነው፡፡ አዲስ ትውልድ ውስጥ በቀላሉ መግባት የሚችል ሰብእና ያለው ሰው ነው፡፡ በዚያ ላይ በበቂ የተማረ፣ ያነበበ ነው። በመጀመሪያ ቀን ስለ ባለቤቱ፣ ስለ እናቱ አወራ። ሰው መሆኑን አረጋገጠልን፡፡ እንደ ሰው አዝኖ አልቅሶ፣ ሰው መሆኑን አሳየን፡፡ እንደ ሰው፣ ልጆችህን፣ እናትህንና ሚስትህን ስትወድ፣ ሰው ነህ፤ ቢሮክራት አይደለህም፡፡ ዶ/ር ዐቢይ፣ ይሄን ይዞ ነው የቀረበን፡፡
በፖለቲካው ረገድስ ምን ዓይነት መንገድ ነው ይዘው የመጡት?
በአለም ላይ ለውጥ አካሒያጆች ሁለት መንገድ ነው መምጫቸው፡፡ አንደኛው፤ ያቆሠለህን እያቆሠልክ፣ እየገደልክ የምትረማመድበት ነው፡፡ ይሄ የእነስታሊን መንገድ ነው፡፡ ሌላኛው የበደለንን፣ ያቆሠለንን በይቅርታ እያለፉ መምጣት፣ ከዚያም ሲያልፍ እነሡም የለውጡ አካል ናቸው ብሎ በፍቅር ወደ ለውጡ መሳብ ነው፡፡ ይሄ የእነጋንዲ፣ የእነኔልሰን ማንዴላ መንገድ ነው፡፡ አሁን ባለው አካሄድ ዶ/ር ዐቢይ የመረጠው፣ ይሄን የይቅርታና የሁሉን አቃፊነት መንገድ ነው፡፡ 
የእርሳቸው መንገድ ያዛልቃል ብለው ያስባሉ?
ከግለሰብ አልፎ ተቋማዊ መሆን አለበት፤ አሁን ሰው ትልቅ ሸክም ነው ከላዩ ላይ የተነሣለት፡፡ ቦታው ከፈት፣ ከፈት ብሏል፡፡ በዚህ አካሄዱ ዶ/ር ዐቢይ እና የሚመራውን ድርጅት በምርጫ ማንም አይደርስበትም ይሆናል፤ ገና ለምርጫው ሁለት ዓመት ገደማ አለ። በዚህ ጊዜ ውስጥ ብዙ ነገር ሊፈጠር ይችላል፤ ነገሮች ወደ ኋላ ሊመለሱም ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ይህን ሰው መርዳት ያለባቸው፣ ከልባቸው ሊረዱት ይገባል። ይቺ ሁለት አመት በጣም ወሳኝ ናት፡፡ ለውጡን የማይፈልገው ቡድን እኮ አፈገፈገ እንጂ አልተሸነፈም። ለውጡ ወዴት አዝማሚያ ሊሔድ እንደሚችል አናውቅም፡፡
በቅዳሜው የድጋፍ  ሰልፍ ላይ በፈነዳው ቦምብ ምን ተሰማዎት?
ብዙ ጊዜ እንዲህ ዓይነት ለውጦች ሲመጡ መቁነጥነጦች፣ መፍጨርጨሮች ይኖራሉ፡፡ ይህም ክሥተት የዚያ አይነት ባሕርይ ያለው ነው፡፡ ይህ ሰላማዊ ሰልፍ ሁለት አንድምታ ነው የነበረው፡፡ አንደኛ፤ ለውጡን እያመጣ ያለውን ሰው፣ “ቅቡልነት አለህ፣ በርታ” ለማለት ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ እንዲህ ዓይነት ተቁነጥናጮችን “አደብ ግዙ፣ ድጋፍ ያለው ሰው ስለሆነ፣ ያልሆነ ነገር ባትሞክሩ ይሻላል፤” የሚል መልእክት ለማስተላለፍ ነው፡፡ የቦንብ ጥቃቱም የመሸነፍ፣ እየተፍጨረጨሩ፣ አረፋን መጨበጥ ማለት ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት በየቦታው ብሔር ተኮር ግጭቶች እየተከሠቱ ነው፤ ምክንያቱ ምንድን ነው ይላሉ?
ይሄ የፌደራሊዝሙ ችግር ነው፡፡ የቆየ ችግር ነው፣ ነፃ ሜዳ ሲያገኝ ነው የፈነዳው፡፡ ሳስበው ግን ሀገሪቱ ከብሔር ወደ ዜጋ ፖለቲካ ልትሔድ መንገድ ላይ መኾኗን የሚያመላክት ይመስለኛል፡፡ ብሄር፣ ጎሣ የሚሉ ነገሮች አሁን አቅማቸውን እያሟጠጡ፣ ዜጋ ወደሚለው እየሔዱ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ይሄ ለመሆን ግን የዴሞክራሲ፣ የሕግ የበላይነት፣ የሀብት ፍትሐዊ ክፍፍል መስፈን ወሳኝ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ክልል እንሁን ብለው መጠየቃቸው አይደለም ችግሩ፤ የተጠየቀበት የዐመፃ መንገድ ነው ችግሩ፤ ድሮም የሚፈራው ይሄ ችግር ነው፡፡ ዶ/ር ዐቢይ፣ አቶ ለማም ኾኑ አቶ ገዱ፤ ይህ የሃገሪቱ ኹኔታ የገባቸው ይመስለኛል፡፡ አሁን በጎሣዎች መካከል ያለውን ችግር መፍታት፣ በሒደትም ወደ ዜጋ ፖለቲካ የምንሄድበትን መንገድ መፍጠር አስፈላጊ ነው፡፡ አሁን የመጣው ብሔራዊ መግባባት ለዚህ ይረዳናል፡፡ አሁን ኢትዮጵያ ወደራሷ እየተመለሰች ነው፤ እርቅ እየመጣ ነው፡፡ 
በቀጣይ ምን ዓይነት የለውጥ ሒደት ይጠብቃሉ ?
ለምሳሌ፣በቀጣዩ ሁለት ዓመት ውስጥ ወደ ሕግ የበላይነት ለመሔድ ይሞከራል፣ የፖለቲካ ምኅዳሩ ይሰፋል፣ ነፃ እና ተአማኒነት ያለው ምርጫ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይሄን ለማድረግ ብዙ ትግል ይጠይቃል፡፡ በዚህ መሃል ግን ብዙ ተስፋ አለን፡፡

http://www.addisadmassnews.com















No comments:

Post a Comment