ኤልሳቤጥ ወልደ ጊዮርጊስ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር
ዶ/ር ኤልሳቤጥ፡- ዋናው እንግዲህ የመጽሐፌ ንድፈ ሐሳብ ይህ ዘመናዊነት የምንለው ነገር እንዴት እንደምንረዳው ነው፡፡ ዘመናዊነት ማለት ዘምኖና ዘንጦ መሄድ፣ የመሳሰሉትን ነገሮች ለመግለጽ የተለመደ አመለካከት አለ፡፡ ዘመናዊ አለባበስ፣ ዘመናዊ አመጋገብ፣ ወዘተ፡፡ ከእሱ በላይ ግን በመጽሐፌ ዘመናዊ ርዕዮተ ዓለም ወይም ጽንሰ ሐሳብ ላይ ነው መነጋገር የፈለግኩት፡፡ እናም ዘመናዊነት የሚለው ጽንሰ ሐሳብ እኛ አገር ውስጥ እንዴት ሰረፀ? እንዴትስ ሄድንበት? ያ ጽንሰ ሐሳብ የት አደረሰን? መከራ ላይ ጣለን? አብላላነው፣ ተነጋገርንበት፣ ወዘተ የሚሉትን መሠረታዊ የዘመናዊነት ምልከታዎችን ነው ላነሳ የፈለኩት፡፡ ወደ አገር ቤት ከመጣበሁት ጊዜ ጀምሮ የታዘብኩት ነገር፣ ይህ የዘመናዊነት ጽንሰ ሐሳብ በቅጡ ያልተብላላ፣ ብዙ ክርክር የሚያስፈልገው፣ የብሔር ግጭትና የዘመናዊ ትምህርት አካሄድን ጨምሮ እዚህ ደረጃ ያደረሰን ይህ የዘመናዊነት ጽንሰ ሐሳብ ላይ በደንብ መነጋገር አለመቻላችን ነው፡፡ ምሁራኖቻችንም በቅጡ አይወያዩበትም፡፡ እናም ችግር እየሆነ መጥቷል፡፡ ወደድንም ጠላንም ዘመናዊነትን ማሰብ የምንችለው አሁን ያለንበትን አውሮፓዊ ዕይታ ውስጥ ሆነን በተፈጠረው ባህላዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ማዕቀፍ ውስጥ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ጫና ያለበት ቢሆንም፣ ተዋረዳዊ ስለሆነ ሁሉ ነገራችንን አስተሳስሮናል፡፡ ባህሉን፣ አመለካከቱንና ትምህርት አሰጣጡንም፡፡ ስለዚህ ይህ ከምን ጋር ነው የመጣው? ዘመናዊነት ከሚለው ከአውሮፓዊ ጽንሰ ሐሳብ ጋር ነው የመጣው፡፡
ኤልሳቤጥ ወልደ ጊዮርጊስ (ዶ/ር) ለስድስት ዓመታት ያህል የኢትዮጵያ የጥናት ተቋምን በዋና ዳይሬክተርነት መርተዋል፡፡ በመቀጠልም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አለፈለገ ሰላም ትምህርት ቤትና የአፍሪካና ኦሪዬንታል ጥናት ማዕከል መምህር በመሆን በማገልገል ላይ ናቸው፡፡ በቅርቡ ‹‹Modernist Art In Ethiopia›› በሚል ርዕስ ጥናታዊ መጽሐፋቸው በኦሀዮ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ አማካይነት ታትሞላቸዋል፡፡ መጽሐፉ በመጪው ወር በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አማካይነት ይመረቃል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ በውጭ አገር የሚኖሩ በርካታ ኢትጵያውያንም እያነበቡት ነው፡፡ ባሳተሙት አዲስ መጽሐፍ ውስጥ ያሉ ዘመናዊነት፣ የዘመናዊነት ዓለም አቀፋዊና አገራዊ የታሪክ ሒደቶች፣ እንዲሁም ጽንሰ ሐሳቡ ለኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕድገት ያበረከተው አስተዋጽኦና የጎደለውን ነገር አስመልክቶ ነአምን አሸናፊ አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- አዲስ ባሳተሙት መጽሐፍ ውስጥ የተለያዩ የታሪክ ሒደቶችን ከዘመናዊነት አንፃር የተደረጉ ተሞክሮዎችን ለመዳሰስ ሞክረዋል፡፡ ነገር ግን የታሪክ ሒደቶቹን ከመመልከታችን በፊት፣ ዘመናዊነት የሚለው ጽንሰ ሐሳብ በኢትዮጵያውያን ልሂቃን ዘንድ የተለያየ አረዳድና ትርጓሜ ስለሚሰጠው ከብያኔው ለመነሳት ያህል ዘመናዊነት ምንድነው?
ኤልሳቤጥ ወልደ ጊዮርጊስ (ዶ/ር) |
በመጽሐፌ መግቢያ ላይ እንደምገልጸው ደግሞ ይህ ጽንሰ ሐሳብ በቅኝ ግዛት መንገድ ነው የመጣው፡፡ በአንድ በኩል ከኢንዱስትሪ አብዮት በኋላ፣ በሌላ በኩል የአብርሆት ዘመን ሰዎች አመዛዛኝ ምክንያታዊ ነፃነት ሊኖራቸው ይገባል፣ በራሳቸው ነገሮችን እንዲወስኑና እንዲሠሩ ይገባል ከሚለው ተራማጅ አስተሳሰብ ጋር በተያያዘ የመጣ ነው ማለት ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የዘመናዊነት ታሪክ የአመፅ ታሪክ ነው፡፡ አመፁ ምንድነው አፍሪካ ሄዶ ቅኝ ይገዛ ነበር፡፡ ከበርሊን የመቀራመት ስምምነት ጀምሮ ይህ ምዕራባዊ ኃይል አፍሪካን ብቻ ሳይሆን፣ እስያንና ደቡብ አሜሪካን በጭካኔ የገዛበት ሒደት ነው፡፡ ሁለተኛው ባርነት በሰፊው የተካሄደበት፣ አፍሪካውያን አዲስ ዓለም ወደሚባለው በጭካኔ ተሸጠው የሄዱበት ጊዜ ነው፡፡ ስለዚህ ይህ የዘመናዊነት ታሪክ ሁለት ገጽታ ይኖረዋል፡፡ አንደኛው ጭካኔ በተሞላበት አኳኃን በቅኝ ግዛት መንገድ የሚገለጽ ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ የአውሮፓውያን የአብርሆት ዘመን የመጣበት፣ በተለይ ከፈረንሣይ አብዮት በኋላ የመጣው አመለካከት ነው፡፡ እንግዲህ የአመፃውንና የቅኝ ግዛቱን ታሪክ ስንመለከት ለምንድነው ያስፈለገው ሲባል፣ በርካሽ የሠራተኛ ጉልበት አውሮፓን ለማበልፀግ የተደረገ ነው፡፡ አውሮፓን ለማበልፀግ ደግሞ ሀብት የተወሰደበት ነው፡፡ የአውሮፓን ኢኮኖሚ ለማዳበር እነዚህ ሁሉ ጭካኔዎች ተከናውነዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ዘመናዊነት ትርጓሜው በዚያ መንገድ ከሆነ ኢትዮጵያ ደግሞ ቅኝ አልተገዛችምና ይህ ትርክት እንዴት ነው ኢትዮጵያ ላይ የሚሠራው?
ዶ/ር ኤልሳቤጥ፡- ትልቁ ችግራችን ይህ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ነፃ ሆና ኖራ ታውቃለች ወይ? እንግዲህ የዝመና ዘመን ብዬ የምለው ከዓድዋ ድል በኋላ ነው፡፡ ከዓድዋ በኋላ ያልኩበት ምክንያት ዘመናዊነት የታሪክ ሒደት ስላለው ነው፡፡ የዘመን ሒደቱም ከኢንዱስትሪ አብዮት ጀምሮ ከዚያ ሄደ የሚል አለ፡፡ ያ የዘመን ሒደት ግን በእኛ ዓይነት በቅኝ በተገዙ አገሮች ላይ አይሠራም፡፡ ምክንያቱም ሌላ ታሪክ ነው ያለው፡፡ በቅኝ ግዛት ታሪክ የአመፅ ታሪክ ስለሚመጣ የዘመን ሒደቱን የምንለካው በራሳችን ታሪክ ውስጥ ነው፡፡ ይህ የዘመን ሒደት ብያኔ በምዕራባውያንና በሌሎች ምሁራን መሀል ያለው ልዩነት፣ እነዚህኞቹን ከቅኝ ግዛት ነፃነት በኋላ ሲጀምሩ የእኛዎቹ ደግሞ ከየት እንደሚጀምሩ አይታወቅም፡፡ ኢትዮጵያ የሦስት ሺሕ ዓመት ታሪክ አላት ከሚለው ተነስተው ከዚያ ሊወስዱት ይችላሉ፡፡ ዘመናዊነት ልውጠት (Transformation) እስከሆነ ድረስ ላሊበላም፣ አክሱምም ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን የዘመናዊ ቅኝ ግዛታዊና የቅርብ ጊዜ ታሪክን ነው ማወቅ ያለብን፡፡ ያ ታሪክ ደግሞ ከ18ኛው ክፍለ ዘመን እስካሁን ያለውን ነው፡፡ ስለዚህ እኔ ዓድዋ ያልኩት ከዓድዋ በኋላ ብዙ ፈረንጆች ይመጣሉ፣ የዘመናዊ አገር ግንባታ ፕሮጀክት ተጀምሯል ብዬ አምናለሁ፡፡ በዚህ ጊዜ ባንኩ፣ ፖስታው፣ ጋዜጣው አለ፡፡ አንድ ወጥ የሆነ አገር ለመመሥረት ምኒልክ ወደ ደቡብ ያደረጉት ዘመቻ አለ፣ ወዘተ፡፡ ይህ ሁሉ የሚያሳየው የዘመናዊ አገር ግንባታን አንድ ምልከታ የምንወስድበት ነው፡፡
ሁለተኛው ደግሞ የፈረንጆቹ መምጣት የግለሰቡን ወይም የማኅበረሰቡን የመዘመን ፍላጎትና አመለካከቶች የሚመጡበት ስለሆነ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያ ከዓድዋ ድል በኋላ ከአውሮፓዊ ጫና ወጥታ አታውቅም፡፡ ስለዚህ የቀጥታ ቅኝ ግዛት አይኑር እንጂ፣ በእጅ አዙር ከአውሮፓዊው ጫና ጋር የኖርን ሰዎች ነን፡፡ ስለዚህ ከሰፊው የዘመናዊነት ታሪክ ራሳችንን ልናወጣ አንችልም ብዬ እገምታለሁ፡፡ ነገር ግን ታሪካችን የተለየ ነው፡፡ ዘመናዊነትን በጊዜ ሒደት እንዴት ነው የምንገልጸው? ምክንያቱም ቅኝ ስላልተገዛን፡፡ የአገሪቱ የዘመናዊነትን ጽንሰ ሐሳብ አወሳሰድ ይህ ሁሉ ታሪክ አለው፣ ታሪኩ የተለየ ነው፡፡ ነገር ግን ከትልቁ የኢኮኖሚ ጫና ታሪክ ተላቀን አናውቅም፡፡ ስለዚህ የዘመናዊነት ታሪክ እኛንም እዚያ ውስጥ ይከተናል የሚለው የእኔ አመለካከት ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ነገር አልተብላላም፡፡ እኔ ከዚያኛው ከቅኝ ግዛቱ ታሪክ ጋር አንቀላቀል እያልኩ አይደለም፡፡ ታሪካችን ልዩ ነው፡፡ ታሪካችንን የምናይበት መንገድ ግን ከዘመናዊው የቅኝ ግዛት ታሪክ ነፃ አይወጣም የሚል ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የዘመናዊነት ታሪክን ከአጠቃላይ የአገሪቱ ታሪክ ጋር እንዴት ነው የምንመለከተው? ምክንያቱም የሦስት ሺሕ ዓመቱን ታሪክ እንኳን ወደ ጎን ትተን ባለፉት 150 ዓመታት በተከናወኑ የታሪክ ክስተቶች ላይ እንኳን መስማማት አልቻልንም፡፡ ከዚህ አንፃር በአገሪቱ የቅርብ ጊዜ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ታሪክ ሳንግባባ ይህንን ማንነት ይዘን ወደ ዓለም አቀፉ የዘመናዊነት ትርክት መግባት እንዴት ይቻለናል? ከንቱ ልፋትስ አይሆንም ወይ?
ዶ/ር ኤልሳቤጥ፡- አይሆንም፡፡ ዓለም አቀፋዊውን ትርክት ብናውቀው እኮ ነው ይህንን መግባቢያ መንገድ የምንፈጥረው፡፡ ዓለም አቀፋዊውን በጭካኔ የተሞላ የቅኝ ግዛት ውጤት ከሆነ በእኛ አገር ላይ የሚያመጣውን ካላየን ችግር ነው፡፡ አሁን ለምሳሌ እዚህ አገር ውስጥ በብሔር ማንነት እየተቧቀስን ነው፡፡ ትልቁና ኃይለኛ የሆነው ዓለም እኮ እኛን የሚመለከተን በጣም እንደ ትንሽ ሕዝብ ነው፡፡ እንደ ትንሽ ሕዝብ ስለሚያየን እንዴት ነው እነሱ ጋር የምንደርሰው? እዚያ የምንደርሰው እንደዚህ በመቧቀስ ሳይሆን፣ በትብብር ነው የሚለውን ነገር ስላላየን ነው እዚህ የደረስነው፡፡ በእውነት አሁን የምንጣላበት የብሔር ማንነት ወይም ችግር እዚሁ የተፈጠረ ይመስለናል፡፡ እዚህ አይደለም የሚፈጠረው፡፡ ይህን ሁሉ ያመጣው የኢኮኖሚያዊ ልዩነት ጉዳይ ነው፡፡ የእኔ መሬት ከአንተ ይበልጣል ዓይነት ነገር ነው፡፡ ይህን መሬት ስጠኝ ያኛው ድንበር የእኔ ነው የሚልህ የኢኮኖሚያዊ ልዩነት ጥያቄ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የዘመናዊነትን ዓለም አቀፋዊ ሒደት አለመረዳት አሁን ለደረስንበት የብሔር መቧቀስና መፋጠጥ መሠረቱ እዚህ ብቻ የነበረ አይደለም፡፡ የዓለም አቀፍ ልምድ አካል ነው፡፡ ይህ ደግሞ ወዴት ይወስደናል? ዕውቀትን እንዴት ነው የምንረዳው? የምንገመግመው? የምንተገብረው? ወዘተ ወደሚሉ ምልከታዎች ያመራናል፡፡ ከዚህ አንፃር የዚህ አገር ዕውቀት የማምረት (Knowledge Production) ሒደት የነጠፈ ነው የሚመስለው፡፡ ስለሆነም ዘመናዊነትን ተረድተን ከዓለም አቀፉ ትስስር ውስጥ መግባት ቀርቶ ቀላል የሚመስሉ የአገር ውስጥ ችግሮችን እንኳን መፍታት አልቻልንም፡፡ የዚህ ችግር ምንጩ ምንድነው?
ዶ/ር ኤልሳቤጥ፡- ታሪካችን የተለየ ስለሆነ ነው እዚህ ቦታ የገባነው፡፡ ታሪካችን የተለየ የሆነው ቅኝ ባለመገዛታችን ነው፡፡ ቅኝ አለመገዛታችን ምን አደረገን? ይህንን ተዋረድ በደንብ እንዳንመረምረው አደረገን፡፡ እኛ ደግሞ ያንን ማወቅና ማጣጣም ሲገባን አናውቀውም፡፡ ስለዚህ ዘመናዊ በሚለው ጉዳይ ላይ በተለይ ደግሞ የ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመርያ ላይ የሚደረግ ክርክር ነበር፡፡ በመጽሐፉ ላይ እንደገለጽኩት የብርሃንና ሰላም ምሁራን ክርክራቸው የነበረው ዘመናዊነት፣ ጃፓናይዜሽን የሚሉት ላይ ነበር፡፡ ያን ጊዜ ፍራቻም ነበራቸው፡፡ አጠገባቸው የነበሩ አገሮች በአጠቃላይ ቅኝ የተገዙ ስለነበሩ፣ ይመጡብን ይሆን የሚለው ሥጋት ነበር በምሁራኑ በኩል፡፡ ስለዚህ ራሳችንን ማዘመን አለብን ይሉ ነበር፡፡ በወቅቱ ግን ግዴታ አገሪቱን ዘመናዊ ማድረግ አለብን፣ አውሮፓ ግን ዘመናዊ ልታደርገን አትችልም የሚለው መረዳት የለም፡፡ እንችላለን የሚል ወኔ ነው የነበራቸው፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ በእግዚአብሔር የተመረጠች አገር ነች፣ ፈጣሪ ይረዳናል፣ ከተማርንና ቴክኖሎጂውን በደንብ ካጠናን እንወጣዋለን የሚል ዓይነት ክርክር ነበር፡፡ በተለይ ፊታውራሪ ደሬሳ አመንቲ እዚያ ላይ በጣም ያምኑ ነበር፡፡ ይህ ነበር ክርክሩ፡፡
ነገር ግን እስካሁን ያለው ክርክር ዘመናዊነት ላይ ነው እንጂ የዘመናዊነት ፍልስፍና ምንድነው? መርሐ ግብሩ ምንድነው? ዋናው ያቀፈው ነገር ምንድነው? የሚለው ነገር ተወያይተን አናውቅም፡፡ ስለዚህ የዘመናዊነት ታሪክ እንጂ የቅኝ ግዛት ሰብዕና ጥያቄ አልመጣም፡፡ ዘመናዊ መሆን እንዴት ይቻላል የሚል ትንታኔ ውስጥ አልገቡም፡፡ አፍሪካውያን ቢሆኑም ትንታኔ ውስጥ አልገቡም፡፡ ነገር ግን በድርጊት ያውቃታል፡፡ እነርሱ ዘነድ የሰብዕና ጥያቄ አንደኛ ሆኖ ይወጣል፡፡ የእኛን እኮ አላዩትም፡፡ በዚያን ጊዜ ደግሞ ዘመናዊነት እንዲህ ያለ ነው ብሎ ለመፈላሰፍ ከባድ ነበር፡፡ በእርሱ አልበይናቸውም የሚችሉትን ያህል አድርገዋል፡፡ በወቅቱ የሚቀጥለው ትውልድ ነበር ማወቅ ያለበት፡፡ በተለይ በ1960ዎቹ የመጣው ትውልድ፡፡ በተለይ በተለይ የአፍሪካ አገሮች የፀረ ቅኝ አገዛዝ ትግል በሚያከናውኑበት ጊዜ ያ ትውልድ ያንን ማብላላት ነበረበት ብዬ እገምታሁ፡፡ ያንን አላደረገም፣ ይህንም ማድረግ ያልቻለው በታሪክ ልዩነታችን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የ1960ዎቹ ትውልድ አባላት በማርክሳዊ ዓለም አቀፋዊነት በመመራት ዓለም አቀፍ ጭቆናን እንታገላለን የሚሉና ድጋፋቸውንም ለተለያዩ በቅኝ ግዛት ሥር ለነበሩ የአፍሪካ አገሮች ይለግሱ እንደነበር በተለያዩ ጽሑፎች ይታያል፡፡ ሆኖም እነሱም ቢሆን ኢትዮጵያ ቅን ያልተገዛች በመሆኗ ታሪኳ የተለየ ነው የሚል አመለካከት ነበራቸው፡፡ ከዚህ አንፃር የዚያ ትውልድ ዘመናዊነትን የመተንተንና የመተግበር ድርሻስ ምን ነበር?
ዶ/ር ኤልሳቤጥ፡- የእነርሱ ድርሻ አውሮፓዊ የሆነው ዘመናዊነት ወንድማማችነት ላይ ማተኮር ነበር፡፡ ለምሳሌ ፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ እርሱ ላይ ያተኩራል፡፡ ወንድማማችነቱ ላይና የዘመናዊነት መሠረታዊያን የሚላቸው ነገሮች አሉ፡፡ ወንድማማችነት፣ ነፃነትና እኩልነት የሚለው ትውልድ ለፍትሕ የቆመ ትውልድ ነበር፡፡ ያንን ሰፊውን የዘመናዊነት ጽንሰ ሐሳብ ወስዶ ለኢትዮጵያውያን ሁሉ ፍትሕ በሚል ታግሏል ብዬ አስባለሁ፡፡ በመደብ የተከፋፈለን ኢትዮጵያዊ አንድ ለማድረግና ለፍትሕ ታግሏል፡፡ ከዚህ አንፃር ትልቅ ድርሻ ነው የወሰደው፡፡ ነገር ግን ይህ ፍትሕ የሚገኘው እንዴት ነው? ለሚለው የማርክሲስት ፍልስፍናን ይወስዳል፡፡ ማርክሲስት ፍልስፍናውን ሲወስድ ደግሞ ከዓለም ተገንጥሎ አይደለም፡፡ በዚያ ጊዜ በርካታ ማርክሲስታዊ ንቅናቄዎች ነበሩ፡፡ አፍሪካውያን ራሳቸው የቅኝ ግዛት ቀንበር ውስጥ ሆነው ማርክሲዝም ነው የሚያወጣን ብለው የገመገሙበት ነበር፡፡ ይህም ትውልድ ቢሆን ሊፈረድበት አይችልም፡፡ ታሪክ የተለየ ስለነበር በፍትሕ፣ በእኩልነትና በእውነተኛነት ነው የተመለከቱት፡፡ ዛሬ እናጣጥለዋለን፣ ልናጣጥለው አንችልም፣ ያ ታሪካችን ነው እዚህ ያደረሰን፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ስንት ሰው ለዚህ ለፍትሕ አልቋል? ያንንም ማሰብ በጣም ቁልፍ ነው፡፡ ችግሩ ምንድነው የሆነው የተማረ ልሂቅ ይፈጠርና አንደኛው የተማረ ልሂቅ ማርክሲዝምን ለፍትሕ እናምጣ ይላል፡፡ ሌላው በሥነ ጽሑፍ፣ በሥነ ጥበብ የወሰድኩት የተማረ ልሂቅ ደግሞ የቅኝ ግዛት ጭካኔን ስላጣጣመ ዝመና አውሮፓዊ ዝንባሌም አለው፣ አፍሪካዊ ዝንባሌም አለው ይላል፡፡
ሪፖርተር፡- እዚህ አገር የዘመናዊነት ትልም ላይ የተለያዩ ጽንፎችን የያዙ ልሂቃን አሉ፡፡ በአንድ በኩል አገር በቀል ዕውቀቶችን ሙሉ በሙሉ ትተናቸዋል፣ ለዚህም ነው መዘመን ያቃተን የሚሉ አሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አገር በቀል ዕውቀቶችና ተሞክሮዎች ላይ ብቻ በማተኮር ዘመናዊ መሆን አይቻለም የሚሉ አሉ፡፡ ነገር ግን አገር በቀል ዕውቀቶችን በመረዳትና በመንከባከብ ብቻ መዘመን ይቻላል?
ዶ/ር ኤልሳቤጥ፡- በምሳሌ እንመልከተው፡፡ ፍራንዝ ፍኖን የሚለው ለምሳሌ የአውሮፓውያኑን ትተን የራሳችንን እናጥና ነው፡፡ ያንን ግን ሙሉ ለሙሉ እንተወው አይልም፡፡ እንተወው የሚለው ጭቆና ያለውን ሲሆን፣ ጠቃሚ የሆነውን እንውሰድ ይላል፡፡ አብረን የተሳሰርን ሕዝቦች ስለሆንን አገር በቀል የሆነውን ዕውቀት አውጥተን እናዛምደው ነው የፍኖን መከራከሪያ፡፡ የአፍሪካን ዘመናዊነት የገለጹት የአፍሪካ የፈጠራ ሥራዎች በተለይ ከቅኝ ግዛት በኋላ ላለፉት 30 ዓመታት በርካታ ምሁራን ያወጡትና የአፍሪካ ዘመናዊነት ተብሎ የወጣው ላይ ‹‹ዘመናዊ የፈጠራ ሥራ ከአውሮፓዊ ዘመናዊነት ታሪክ ሊገነጠል አይችልም››፣ ምክንያቱም ወደድንም ጠላንም በዘመናዊነትና በቅኝ ግዛት ዘመናዊነት መካከል ይኼ ትስስር መጥቷል፡፡ ስለዚህ መደራደር መቻል አለብን፡፡ ሥነ ጥበብን ስንሠራ የፒካሶን ብቻ ሳይሆን የራሳችንንም እያዛመድን ካልሄድን እንዋጣለን፡፡ ስለዚህ የሆነ ድርድር መደረግ አለበት፡፡ ልትደራደር የምትቸለው ግን ታሪኩን ካወቅክ ነው፡፡ የነበረን የዕውቀት ምንጭም ቢሆን እንዲያድግ አልተደረገም፡፡
ሪፖርተር፡- በመጽሐፉ ላይ እንደሚገልጹት ቢያንስ ቢያንስ የ1920ዎቹ ምሁራንም ሆኑ የ1960ዎቹ ምሁራን ዘመናዊነትን በመበየን ደረጃ እንኳን ባይሆን ምሁራዊ ውይይት ነበራቸው፡፡ በተለያዩ ደረጃ የሚደረጉ ውይይቶችና ጥያቄዎች ነበሩ፡፡ አሁን ደግሞ እንኳን ዘመናዊነት ምንድነው? በሚል ደረጃ ይቅርና የአገሪቷን ህልውና በሚወስኑ ነገሮች ላይ እንኳን ውይይቶች፣ ሙግቶችና ጥያቄዎች ሲካሄዱ አንመለከትም፡፡ ለዚህ ዓይነቶቹ ውይይቶችና ሙግቶች መጥፋት ምክንያቱ ምንድነው?
ዶ/ር ኤልሳቤጥ፡- ንጉሠ ነገሥቱ ከዝመና ጋር በተያያዘ የተቀበሉት ነገር ነበር፡፡ ጠቅላይ አገዛዝ ቢኖርም እኔንም ከእግዚአብሔር ጋር አገናኙን ቢሉም የተወሰኑ የወሰዷቸው የዝመና ፍልስፍናዎች አሉ፡፡ አንደኛው ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ፍፁም የሆነ አካዳሚክ ነፃነት ነበር፡፡ አገር የገለበጠው የተማሪ ማኅበር ከዚያው ነው የመነጨው፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ አገሪቱ ገና ልሂቃን የምትፈጥርበት ጊዜ ነበር፡፡ ሳንሱርና ጫና ነበር፡፡ ነገር ግን ኃይለኛ ነበር የሚባል አይደለም፡፡ ስለዚህ ጊዜው የሚፈቅድ ነበር፡፡ በዚያ ጊዜ ኢትዮጵያ አትነጋገር የሚባልበት ጊዜ ሊሆን አይችልም ነበር፡፡ ዓለም ውስጥም ሆነ እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ ብዙ ንግግር ስለሚካሄድ፡፡ ስለሆነም የመነጋገር መድረኩ በአንፃራዊነት ተከፍቶ ነበር፡፡ ነገር ግን በዓለም የመብት ጉዳይ ያነቃነቀበት ጊዜ ስለነበር፣ ኢትዮጵያ ደግሞ እስከ ዛሬ ድረስ ቅኝ አለመገዛቷ ለእኛ ምልክት ናት የሚል የጥቁር ንቅናቄ ስለነበር፣ ለንጉሠ ነገሥቱም ለራሳቸው መኩሪያና የሥልጣናቸው ምንጭ ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ብዙ አፍሪካዊ ተማሪዎች በስኮላርሺፕ አማካይነት ይመጡ ነበር፡፡ ጊዜው በጣም ይህንን የሚያበረታታ ነበር፡፡ ደርግ ሲመጣ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ይዘጋዋል፣ ብዙ ይሰደዳል፣ ይሞታል፡፡ የተወሰኑ ልሂቃን ያልቃሉ ወይም ይሰደዳሉ፡፡ ከዚያ ኢሕአዴግ ሲመጣ ሌላ ዓይነት ኃልዮት ይዞ ይመጣል፡፡ አመለካከቱ እንዲቀየር አደረጉት፡፡ ዩኒቨርሲቲ መጥተው እኮ ይህን ካልተመለከታችሁ፣ በዚህ ካልሄዳችሁ፣ ልማታዊ ሥነ ጥበብና ልማታዊ ነገር ካልሠራችሁ ትወጣላችሁ ዓይነት ነገር ነበር፡፡ ስለዚህ አንዳንዱ ወጣ፣ እዚህ የቀረው ዳግም እንዲህ ሆነ፡፡ የፖለቲካው መዋቅር ብዙ ጊዜ ምሁራዊ መዋቅራዊ ጋር ግንኙነት አለው፡፡
ሪፖርተር፡- የአገሪቱ የትምህርት አሰጣጥ ሥርዓት መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት በሚያስቀምጡት አቅጣጫ እየተመራ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ትምህርትም ሆነ ሌሎች አገር አቀፍ ትልሞች ብድርና ዕርዳታ በሚሰጡ አካላት ላይ ተመርኩዞ የሚሠራ ከሆነ በአገሪቱ ላይ የሚያመጣው ችግር ምንድነው?
ዶ/ር ኤልሳቤጥ፡- የትምህርት ነገር በጣም አሳሳቢ ነው፡፡ ምክንያቱም ትምህርት ትውልድ ይፈጥራል፡፡ አንድ ትውልድ ደግሞ የአገር ግንባታን ጉዳይም ስለሚያካትት በጣም አሳሳቢ ነው፡፡ የትምህርት መዋቅሩ እንደገና መታየት አለበት፡፡ የትምህርት መዋቅሩ ኢሕአዴግ ከመጣ ጀምሮ ዕውቀትን መሠረት ያደረገ አይደለም፡፡ እ.ኤ.አ. በ1995 የወጣው የመጀመርያው የትምህርት ፖሊሲ ሲተነትን ዕውቀት ሳይሆን የሚለው፣ ክህሎት ነው፡፡ ይህ ደንበኛ የዓለም ባንክ የትምህርት ፖሊሲ ነው፡፡ መንደርደሪያው ራሱ ለዕውቀት ብዙ ትኩረት አይሰጠውም፡፡ ስለዚህ ኢሕአዴግ ከመጣ ወዲህ በተለይ ከትምህርት አሠራረፁ ጀምሮ ችግር አለ፡፡ የትምህርት ክህሎቶቹ ራሳቸው 70 በመቶ ለቴክኖሎጂ፣ 30 በመቶ ለማኅበራዊ ሳይንስና ሒውማኒቲስ ብለን ካልን ብዙውን የምናመርተው ሐሳብ (Idia) የሌለው ሰው ነው ማለት ነው፡፡ ይህ ራሱ መጥፎ ሁኔታ ላይ ይጥለናል፡፡ አሁን ያለንበት ደረጃ ላይ ያደረሰንና በአገሪቱ የሚታዩ ግጭቶችን ያመጣብንም ይህ ይመስለኛል፡፡ ነገሮችን በደንብ ያላጠናንበትና የተወሰነ ፖሊሲ ከውጭ ተቀርፆ መጥቶ በእሱ ተመሥርተን የሄድንባቸው ነገሮች፣ አሁን ያለውን ቀውስ ያመጡብን ይመስለኛል፡ ትውልዱን ሰፋ ያለ አመለካከት እንሰጠዋለን ካልን ይህንን ትልቅ ግንዛቤ ላይ መጣል አለብን፡፡ አንድን ነገር የሚቀይረው ትምህርት ነው፡፡ ለምሳሌ ቄሮ ተነሳ ስንል ቄሮ ለብቻው አልተነሳም፣ የሆነ ልሂቅ አለው፡፡ ያ ልሂቅ በዚህ መንገድ ብቻ አስቡ ካለ መክሰራችንን ነው የሚያሳው፡፡
ሪፖርተር፡- መምህርትና ተመራማሪ በመሆን ይህን መጽሐፍ ለንባብ አብቅተዋል፡፡ በዚህ ሒደቶች ውስጥ ሴት በመሆንዎ የገጠመዎ ተግዳሮቶች እንዴት ይገለጻሉ?
ዶ/ር ኤልሳቤጥ፡- በጣም ከባድ ነው፡፡ እዚህ አገር ውስጥ ሴት ልጅ ሆኖ መሥራት በአጠቃላይ ከባድ ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ሴት ምሁር ሆኖ መሥራት ደግሞ በጣም ከባድ ነው፡፡ እኔ እዚህ አገር ተሹሜ ነው ከአሜሪካ የመጣሁት፡፡ በእርግጥ ከዚያ በፊት ለ17 ዓመታት ባንክ ውስጥ ሠርቻለሁ፡፡ ከዚያ በኋላ በአሜሪካ በደረሰው የ9/11 ጥቃት ሕንፃው ውስጥ ስለነበርኩኝ፣ ይህ የባንክ ሥራ በቃኝ ብዬ ትምህርት ቤት ገብቼ የሙዚየም ጥናት ትምህርቴን ስጨርስ ነው የመጣሁት፡፡ እና በኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ውስጥ ለስድስት ዓመታት ሠራሁ፡፡ አብዛኛው የተቋሙ ሠራተኞች ወንዶች ነበሩ፡፡ ከእነርሱ ጋር መሥራት በጣም ከባድ ነበር፡፡ አሜሪካ ባንክ ውስጥ ስሠራ በሴትነቴ የሚደርሱ ጫናዎች ያጋጥሙ ስለነበር ስመጣ ብዙም አላስጨነቀኝም፣ ታገልኳቸው፡፡ የራሴን ነገር ሠራሁ፡፡ ታጥቀው ያልመጡ ሴቶች ይታይህ እንዴት እንደሚሆኑ፡፡ ተሾሜ ስለመጣሁ መጨረሻ ላይ ዩኒቨርሲቲው ሊቀጥረኝ ይገባ ነበር፡፡ የሥራ ዘመኔ ሲያልቅ እንዲቀጥርሽ ለተቋሙ አመልክቺ ተባልኩ፡፡ ነገር ግን በተቋሙ የነበሩ ስድስት ወንዶች አንቀጥራትም አሉ፡፡ ለምንድነው ተብለው ሲጠየቁ ኃይለኛ ስለሆነች ነው ተባለ፡፡ በትግል ነው አስተዳደሩ እንደገና ያስቀጠረኝ፡፡ ይህን ያህል ነው ተፅዕኖው፡፡ ይህንን መጽሐፍም የጻፍኩት ከዚያ ንዴት በመነሳት ነው እላለሁ፡፡ ንዴት ማለት ፀጥ ነው፡፡ ብዙ ታሪኮች አሉን፡፡ እኛ አገር ውስጥ የዘመናዊነት ታሪክም አንዱ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ እርሱ እንኳን ባለማወቅ ነው፡፡ ነገር ግን የሴቶች ታሪክ ሙሉ በሙሉ ፀጥ ያለ ነው፡፡ በየቦታው የሚያጋጥሙህ አግላይ የሆኑ ነገሮች በጣም ሞራል ይነካሉ፡፡ ሌላው ደግሞ ሴት እናት ናት፣ እህት ናት የሚለው ነገር መቆም አለበት፡፡ አንዲት ሴት እህትም እናትም ላትሆን ትችላለች፡፡ ሰብዕናዋ ነው መታወቅ ያለበት፡፡ በመጽሐፉ እያንዳንዱ ምዕራፍ ላይ ልገልጸው ፈልጌያለሁ፡፡ የተወሰኑ ሴቶችን ታሪኮች ከነበረው ዓውድ ጋር እንዴት ነበር የሚታዩት የሚለውን ለማውጣት ሞክሬያለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- በመጽሐፉ ላይ በርካታ ሐሳቦችን ለማንሳት ይሞክራሉ፡፡ በተለይ ከዘመናዊነት ጽንሰ ሐሳብ አንፃር፡፡ ነገር ግን የአገሪቱን አጠቃላይ የታሪክ፣ የማንነት፣ እንዲሁም እንደ አገር የመቆምና የመገንባት ሒደትን ሙሉ ለማድረግና ትልሞችን ለማሳከት ምን መደረግ ይኖርበታል?
ዶ/ር ኤልሳቤጥ፡- የአስተሳሰብ ለውጥ መምጣት አለበት፡፡ የአስተሳሰብ ለውጥ ከየት ነው የሚመጣው የሚለውን ለመመለስ ደግሞ የተወሰነ የተማረ ልሂቅ መኖር አለበት፡፡ ያንን የሚያነቃንቅ፡፡ ለእኔ የተማረ ልሂቅ ነው ፖለቲካውንም የሚያደራጀው ሰፋ ያለ አመለካከትም የሚሰጠው፡፡ ስለዚህ ያ የተማረ ልሂቅ እንዴት ነው የምንፈጥረው የሚለው ላይ ማተኮር አለብን፡፡ ውይይቶችን ለማስቀጠል መድረኮች መክፈት አለብን፡፡ መድረኩም ስለሌለና ስላልተገናኘ ነው እንጂ በእርግጠኝነት ሰው አለ፡፡ አሁን ካለንበት ውይይት ውጪ ትችት የሚችል ውይይት መፍጠር መቻል አለብን፡፡ ትችት የሚችል ማለት የማይቆጣ፣ የማይቀየም፣ ቡራ ከረዩ የማይል፣ ለምን እንዲህ አልሽ፣ ወዘተ ዓይነት ንግግሮች የሚደረጉባቸው መድረኮች መከፈት አለባቸው፡፡ ችግሮቻችንን ራሳችን ማወቅ አለብን፡፡ ችግራችሁ ይህ ነው የሚለውን የምዕራባውያን አተያይ መሞገት መቻል አለብን፡፡ ፖለቲካችን እንዲህ እንዲህ ነው ብለን ያለ ፍራቻ ትችት የምንፅፍበት ዕድልም መፈጠር አለበት፡፡ www.ethiopianreporter.com
No comments:
Post a Comment