አውግቸው ተረፈ የብዕር ስሙ ነው። ወላጆቹ ያወጡለት ስም ኅሩይ ሚናስ ነው። የብዕር ስሙ ግን ይህ ብቻ እንዳልሆነ ደራሲ እንዳለ ጌታ ከበደ ለቢቢሲ ይናገራል።
በአጫጭር ልብወለድ፣ በትርጉም፣ እንዲሁም በአርታኢነት የሚታወቀው ኅሩይ ሚናስ ውልደቱ አዲስ አበባ አይደለም። ከጎጃም ደጀን ነው፤ ወደ አዲስ አበባ መጥቶ አይነ ስውራንን ይመራ ነበር።
ወደ አዲስ አበባ እንደመጣ ራሱን ለማኖር በረንዳ ላይ አድሯል። ቀስ በቀስ የፀሎት መጻህፍትን ወደ መሸጥ ከዚያም በሂደት የትምህርትና የልብ ወለድ መጻህፍትን ሸጧል።
መጻህፍት ንግድን ያስተማራቸው እነ አይናለም ዛሬ በጥሩ ሁኔታ የሚንቀሳቀሱ መጻህፍት ሻጮና አከፋፋይ ሆነዋል ይላል እንዳለ ጌታ ከበደ።
አውግቸው መጻህፍት ሻጭ በነበረበት ወቅት እርሱ እያነበበ ተመሰጦ ሳለ የመግዛት ፍላጎት ያለው ሰው ሲመጣ ውሰደው ብሎ በነጻ እንደሚሰጥ ይነገርለታል።
ለደራሲ አበረ አዳሙ ከአውግቸው ስራዎች "ወይ አዲስ አበባ"ን የሚያክል የለም። "ወይ አዲስ አበባ" የአውግቸው የራሱ ታሪክ ነው ይላሉ።
ለአቶ አበረ አውግቸው ጭምት ደራሲ ነው። በዚህ ሀሳብ የ"አለመኖር" ደራሲው ዶ/ር ዳዊት ወንድማገኝም ይስማማሉ።
ሁለቱም ደራሲያን ብዙ ማውራት አይወድም። በጥልቀት ያስባል ሲሉ አቶ አበረ አክለው የመርህ ሰው ነው ብለዋል።
አቶ አበረ ለአውግቸው የመርህ ሰውነት የሚጠቅሱት በ19 87ና 88 ዓ.ም አካባቢ የሆነውን በማስታወስ ነው "በዚህ ዓመት የማነበው መዝገበ ቃላት ነው ካለ አመቱን ሙሉ ቃሉን ጠብቆ የሚያነበው ያንኑ ነው።"
አቶ አበረ "እንደው ለመሆኑ አውግቸው ጓድ መንግሥቱን ትግል እገጥማለሁ ብሎ ቤተ መንግሥት መሄዱን ታውቃላችሁ?" አሉን።
"አረ በጭራሽ" የኛ መልስ ነበር። አውግቸው አንድ ዕለት ወደ ብሔራዊ ቤተ መንግሥት ሄዶ ኮሎኔል መንግሥቱን ጥሩት አለ። "ለምን?" ሲሉት "ትግል እገጥመዋለሁ መልሱ ነበር።
"ይህንን ... "ብሎም እላፊ ተናገረ።
እኔን ትግል ገጥሞ መጣል ሳይችል አገር መግዛት ይችላል መከራከሪያው ነበር።
ወታደሮቹ አፈፍ አድርገው ደበደቡት። ከዚያም እስር ቤት ወርውረውት ለበርካታ ጊዜ ታስሮ ነው የወጣው ይላሉ አቶ አበረ።
"ይህ መቼ ነው የሆነው አልናቸው?" ሰባዎቹ መጀመሪያ ይመስለኛል አሉ በመጠራጠር።
"ኅሩይ ርትዑነት ያረበበበት ቀና ሰው ነበር የሚለው" እንዳለጌታ አሮጌ መጻህፍትን እየሸጠ የጻፋቸው አጫጭር ልብ ወለዶች የካቲት መጽሔት ላይ ታትመው መነበብ መጀመራቸውን ይናገራል። ለዚህ ደግሞ ምክንያት የሆነው መፅሐፍት ከእርሱ እየገዛ ያነብ የነበረው ስብሀት ገብረ እግዚያብሄር እንደሆነ እንዳለ ጌታ ያስታውሳል።
ያኔ አሮጌ መጻህፍት እየሸጠ ሲጽፍ ጓደኞቹ አንተን ብሎ ደራሲ ብለው እንዳይዘባበቱበት ስለፈራ በብዕር ስም ነው ትረካው መጽሔት ላይ እንዲወጣ ያደረገው።
አውግቸው ብዙ የብዕር ስሞች አሉት የሚለው እንዳለጌታ፣ ራሱ ነገረኝ በማለት አዳነ ቸኮል የእርሱ የብዕር ስም መሆኑን አጫውቶናል።
በዚህ የብዕር ስም፣ በአዳነ ቸኮል 'የአማልክትና የጀግኖች አፈ ታሪክ' የሚል ሥራ ታትሞ ለንባብ በቅቷል፤ አዳነ ቸኮል የአያቱ ስም ነው።
የአውግቸውን በርካታ ሥራዎች ከተመለከተና ካነበበ በኋላ "የአደፍርስ ደራሲ ዳኛቸው ወርቁ አውግቸውን ኩራዝ አሳታሚ ወስዶ በአርታኢነት አስቀጥሮታል" የሚለው እንዳለጌታ ኩራዝ አሳታሚ በርካታ ሥራዎችን ሰርቷል ሲል ምስክርነቱን ይሰጣል።
ከአሮጌ መጽሐፍ ሻጭ ወደ ደራሲነት
አውግቸው መርካቶ አሮጌ መጽሐፍትን ከመሸጥ ተነስቶ፣ ከ20 በላይ መጽሐፍት በድርሰት እና በትርጉም ለአንባቢዎች አበርክቷል።
እንዳለ ጌታ ከበደ ስለ ሥራዎቹ ሲጠቅስ 'ወይ አዲስ አበባ' ይጠቀሳል። በ1974 ዓ.ም ገደማ ከነሲሳይ ንጉሡ ጋር በጋራ በመሆን ያሳተመው 'ጉዞው' የተሰኘው የአጭር ልብ ወለድ ስብስብ "እያስመዘገብኩ ነው" የሚልው የኅሩይን ሥራ ይዟል።
ይህ የአውግቸው ሥራ በበርካታ የሥነ ጽሑፍ ባለሙያዎች ይጠቀሳል። እንደ እንዳለ ጌታ ከበደ ከሆነ ደግሞ ይህ ሥራ ለዛሬው 'እያዩ ፈንገስ' ደራሲም መሰረት እንደሆናቸውም ይጠቅሳል።
ከ'ወይ አዲስ አበባ' ውጪ በዓለም ላይ የታወቁ ደራሲዎችን ሥራዎች በመተርጎምም ይታወቃል ኅሩይ ሚናስ። 'የአንገት ጌጡ' በዓለም ላይ የሚታወቁ ደራሲዎች ሥራ ስብስብ ነው የሚለው እንዳለጌታ የባልዛክ ሥራ የሆነውን 'ምስኪኗ ከበርቴ'ን በመተርጎምም ዝናን ማትረፉን ይናገራል።
"አውግቸው ክላሲካል የሆኑ ሥራዎችን ማስነበብ ላይ ያተኩራል" ያለው እንዳለ ጌታ በኋላ ላይ ያሳተመው "እብዱ" የተሰኘው መፅሐፍም ተጠቃሽ ነው።
በኢትዮጵያ ውስጥ የአእምሮ ህመም ችግር ካጋጠመው በኋላ ያንን በመጻፍ ያስነበበ አንድም ሰው የለም የሚለው እንዳለጌታ አውግቸው ግን ያንን በማድረግ ቀዳሚ ነው ይላል።
በዚህ ሥራው የተነሳ የአማኑኤል ሆስፒታል አንዱን የህክምና ክፍሉን በእርሱ ስም ሰይሞ ምስሉን ቀርጾ በግድግዳው ላይ አኑሮታል።
የአእምሮ ህመምና ኅሩይ
አውግቸው በ70ዎቹ ውስጥ አእምሮው ታውኮ ነበር። እርሱም ለምን እንደሆነ አያውቅም። ወዳጆቹም በእርሱ አይነት ችግር የገጠማቸው ሰዎች የመትረፍ እድላቸው በጣም የመነመነ ነው ይላሉ።
የአእምሮ ሐኪሙ ዶ/ር ዳዊት በዚህ ሀሳብ ባይስማሙም ለደራሲ አውግቸው "እብዱ" ስራ ግን ያላቸውን አድናቆት አልሸሸጉም።
አውግቸው ስለ ህመሙ ሲናገር ለበርካታ ጊዜያት በር ዘግቶ መፅሐፍ ስለሚያነብ፣ ስለሚቆዝም እንዲሁም ያለማቋረጥ ይቅም ስለነበር መታመሙን የእነዚህ ነገሮች ሁሉ ድርብርብ ውጤት ይሆናል ብዬ እገምታለሁ ይል እንደነበር እንዳለጌታ ይናገራል።
አውግቸው አእምሮው በታወከበት ወቅት የሆነች ሴቴ መንፈስ ታዝዘው እንደነበር ይናገራል። ያቺ መንፈስ ማሪያም ነኝ ትለኛለች። ጩቤ ይዘህ ዙር ራስህን ተከላከል እንደምትለው ይናገር ነበር።
ይህንንና በወቅቱ ያለፈበትን በማስታወሻው ላይ አስፍሮ ካቆየ በኋላ ነበር ያሳተመው። ለእንዳለጌታ ይህ ሥራ ልብ ወለድ ኤይደለም ማስታወሻ ነው። የኅሩይ የግል ሕይወት ገጠመኝ ነው።
"ይህንን የአውግቸው ተረፈ ሥራ የሥነ ጽሑፍ ባለሙያዎች ብቻ ሳይሆኑ የሥነ ልቦና ባለሙያዎችም ያጣቅሱታል" ይላል እንዳለ። ለዚህም በዋቢነት የሚጠራው የ'አለመኖር' ደራሲን ዶ/ር ዳዊትን ነው።
ዶ/ር ዳዊት በዚህ ሀሳብ ይስማማሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲህ አይነት የተኖረ ህይወት በአእምሮ ሕክምና ዘርፍ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም መስኮች ተፅፎ አይገኝም ይላሉ።
"እብዱ" የተሰኘው የአውግቸው መጽሐፍ ለስነ ልቦና ባለሙያዎች ለማስተማሪያም ሆነ ለማጣቀሻ ያገለግላል ሲሉ ይመሰክራሉ። መጽሐፉ ከአእምሮ ህክምና ውጪ ያሉ ባለሙያዎች፣ በማህበራዊ ዘርፍም ሊጠቀስ የሚገባው ነው ሲሉም ይከራከራሉ።
ስራው ለእኔ ክላሲካል ነው ሲሉ የሚየያስረዱት ዶ/ር ዳዊት ዘመን ተሻጋሪ ስራ መሆኑን ሲጠቅሱ የአእምሮ ህመምን፣ የአእምሮ ህክምናንና ሥነጽሑፍን የሚያጠና ቢኖር ይህ ስራ ከፊት እንደሚቀመጥ ጥርጥር የለኝም በማለት ነው።
የአውግቸው የመጨረሻ ዘመናት
እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ መርካቶ መሳለሚያ ይኖር የነበረው አውግቸው ኮንዶሚኒየም ደርሶት ቃሊቲ ገላን ኮንዶሚኒየም ይኖር ጀመረ።
የፕሮፌሰሩ ልጆች የሚል ቤሳ ልብወለድ፣ አረቢያን ናይት ሦስተኛውን ክፍል እንዲሁም እብዱን አሻሽሎ ለማሳተም በዝግጅት ላይ ነበር።
ከቤቱ መራቅ ከጤንነትም ሁኔታ ጋር በተያያዘ ብዙ መንቀሳቀስ እና ከሰዎች ጋር መገናኘት ያዳግተው እንደነበር ያስታወሰው እንዳለጌታ አውግቸው ባለትዳርና የልጆች አባት እንደሆነ ይናገራል።
አውግቸው አንገቱ ሊታዘዝለት አይችልም ነበር፤ ያለው እንዳለ ጌታ ይህ ህመሙ ከምን እንደመነጨ አይታወቅም በማለት የነበረበትን የጤና እክል ያስታውሳል።
አውግቸው በ2008 ዓመተ ምህረት የበጎ ሰው ሽልማት ተሸላሚ ነበር።
No comments:
Post a Comment