“ጥበብ ለእኔ እንደ ሱስ ነው፤ ከጥበብ ተለይቼ መኖር አልችልም”
ዓለምፀሐይ ወዳጆ
ሕይወቴን በሙሉ ያሳለፍኩት በኪነ ጥበብ ውስጥ በተዋናይነትና በገጣሚነት ሙያ ነው:: ወደ አሜሪካ ከመጣሁ በኋላ ኑሮን ለማሸነፍና ቤተሰቤን ለማስተዳደር ያልሰራሁት ሥራ የለም፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን ከምወደው ሙያ አልተለየሁም፡፡ ጥበብ ለእኔ እንደ ሱስ ነው፤ ከጥበብ ተለይቼ መኖር አልችልም፡፡ በዚህ ዓለም ላይ ዳግም የመኖር ዕድል ቢሰጠኝ፣ የምመርጠው የአሁኑን ሙያዬን፣ መሆን የምፈልገውም የአሁኗን ዓለምፀሐይን ነው፡፡
እኔ በተወለድኩ ጊዜ፣ እናቴ 16 ዓመቷ ነበር፡፡ ወዲያው አባቴ በግሪክ አገር ሥነ መለኮት የመማር ዕድል አግኝቶ ስለሄደ ያደግሁት፣ ፍቅር በተሞላበት የአያቶቼ ቤት፣ የጠየቅሁት ሁሉ እየተሟላልኝ ነበር:: የልጅነት አርአያዬ የሆነችው ማራኪዋና ከሰው ተግባቢዋ ሴት አያቴ፤ ተግቶ መስራትንና ለጋስነትን አስተምራኛለች፡፡ ሁሌም “መኖር ብቻውን ትርጉም የለውም፤ ሌሎችንም መርዳት አለብሽ” ትለኝ ነበር፡፡ ጥበብን እንደ ነፍሷ ነበር የምትወደው፡፡ ታንጎራጉራለች፡፡ በአሮጌ ቴፕዋም ሙዚቃ ታዳምጥ ነበር፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ወስዳ ተውኔት ያሳየችኝ እሷ ናት፡፡ የግጥምና የድራማ ፍቅር የተጋባብኝም ከእርሷ ነው ማለት እችላለሁ፡፡
አስተማሪዎቼ ለኪነ ጥበብ ያለኝን ፍላጎትና ተሰጥኦ የተረዱት ገና ታዳጊ ሳለሁ ነበር፡፡ በ13 ዓመቴ እኔን ለሌሎች ምሳሌ በማድረግ የአማርኛ አስተማሪዬ፣ ግጥሜን ለተማሪዎች ድምጹን ከፍ አድርጎ አንብቦልኛል፡፡ በዚያው ዓመት በየክፍለ ሀገሩ እየዞረ ለሚያሳየው ቲያትር፣ ተማሪዎችን ይመለምል የነበረው የሙዚቃ አስተማሪዬ መላኩ አሻግሬ፤ በሀገር ፍቅር ቴያትር መድረክ ላይ እንድተውን ዕድል ሰጠኝ፡፡ እዚያው ቲያትር ቤት በነበረ የአማተር ክበብ ውስጥም አባል ሆንኩኝ፡፡ ይህ የቲያትር ፍላጎቴ ግን ቤተሰቤ ውስጥ አከራካሪ ጉዳይ ነበር፡፡ አባቴ ከግሪክ እንደተመለሰ በትምህርቴ አንደኛ እንድወጣ ብቻ ሳይሆን ሐኪም ወይም ጠበቃ መሆን እንዳለብኝ ቁርጤን ነገረኝ፡፡ መድረክ ላይ ቢያየኝ እግሬን መስበር ብቻ ሳይሆን እንደሚገድለኝም ጭምር አስጠነቀቀኝ:: አያቴ ግን እንድተውን ፈቀደችልኝ፡፡ በእርግጥ እሷም ብትሆን ቅድመ ሁኔታ አስቀምጣልኝ ነበር:: ትምህርቴን ማጠናቀቅ እንዳለብኝና ምስሌ በፖስተር ወይም በበራሪ ወረቀት ላይ እንደማይወጣ ቃል አስገባችኝ፡፡ ትያትር የምሰራው ሕዝብ ፊት እንደመሆኑ ትወናዬን ከአባቴ መደበቁ አስቸጋሪ ነበር:: ሁልጊዜ መድረክ ላይ ስተውን ድንገት አባቴ ከተፍ ቢልብኝ በማለት፣ ሁሌም ተክቶኝ የሚሰራ ተዋናይ አዘጋጅ ነበር፡፡
በ18 ዓመቴ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ካጠናቀቅሁ በኋላ፣ በብሔራዊ ቴአትር ለሁለት ዓመት ይሰጥ በነበረው አዲስ የሥልጠና ፕሮግራም ውስጥ ከተካተቱት 12 እጩዎች መካከል አንዷ ሆኜ ለመመረጥ በቃሁ፡፡ ይህንንም የስልጠና ፕሮግራም በበላይነት ይመራ የነበረው፣ አስደማሚው ባለቅኔ ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድኅን እንደነበር አስታውሳለሁ:: ሥልጠናውን እንዳጠናቀቅሁ ነበር፣ በብሔራዊ ቲያትር፣ በከፍተኛ ተዋናይነት ተቀጥሬ፣ የረዥም ጊዜ ሕልሜን እውን ማድረግ የጀመርኩት፡፡ ከሥልጠናው በተጨማሪ ከአገሪቱ ድንቅና ምርጥ ተዋናዮች፣ ጸሐፌ-ተውኔቶችና አዘጋጆች ጋር በመሥራት ያገኘሁት ልምድ፣ የትያትር ተሰጥኦዬንና ችሎታዬን በማጎልበት ረገድ በእጅጉ አግዞኛል፡፡ ለቀጣዮቹ 17 ዓመታትም በተዋናይነትና በጸሐፊነት መሥራቱን ገፋሁበት፡፡ በኢትዮጵያ ትያትሮች ብቻ ሳይሆን ዘመን አይሽሬ በሆኑ የጥንት የውጪ ደራሲያን ተጽፈው በሀገራችን ሰዎች በተተረጎሙ ትያትሮችም ላይ ድንቅ ገጸ ባሕርያትን በመወከል ተጫውቼአለሁ፡፡ በ“የቬኑሱ ነጋዴ” ፖርትያን፣ በ “ሐምሌት” ኦፌሊያን እንዲሁም በኒኮላይ ጎጎል “ዋናው ተቆጣጣሪ” ማርያን ሆኜ ለመተወን በመቻሌ፣ ነፍሴ በሐሴት ጮቤ እረግጣለች፡፡ “መድረክ ላይ ባይሽ እግርሽን እሰብረዋለሁ” ሲል ያስጠነቀቀኝ አባቴ፤ ለ14 ዓመት ከተወንኩ በኋላ ነበር በ “ሐምሌት” ትያትር ላይ አፌሊያን ሆኜ ስተውን ለመጀመሪያ ጊዜ ያየኝ፡፡ ይሄን ጊዜ ግን እሱም ሐሳቡን ቀይሮ ነበር፡፡ በሙያዬ በእጅጉ ኮራብኝ፡፡ ለእኔ የጥበብ ጣኦቴ፣ በአስገራሚ የትወና ብቃቷ የማመልካት አንጋፋዋ ተዋናይት አስናቀች ወርቁ ነበረች፡፡
የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሆኜ ነው፣ የንጉሡን አገዛዝ በመቃወም በተጀመረው የተማሪዎች እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳታፊ የሆንኩት፡፡ 11ኛ ክፍል ሳለሁ ለአዲስ አበባ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በተዘጋጀ የጽሑፍ ውድድር፣ ትምህርት ቤቴን መድኃኔ ዓለምን ወክዬ ተወዳድሬ ነበር፡፡ ሌሎች ተወዳዳሪዎች፤ በንጉሳውያን ቤተሰብ አባላት ስም ከተሰየሙ ት/ቤቶች የመጡ መሆናቸውን ካስተዋወቁ በኋላ፣ ተራዬ ሲደርስ “እኔ ግን የመጣሁት ሰዎች ከየት መጡ ወይም ከማን ተወለዱ ሳይል ሁሉንም በእኩል ከሚያይ፣ ያሻውን ሁሉ የማድረግ ኃይል ካለው፣ ነገር ግን በኃይሉ ከማይመካውና ከማይታበየው ኃያሉ ፈጣሪ፣ መድኃኔ ዓለም ስም ከተሰየመ ትምህርት ቤት ነው” ብዬ ራሴን ሳስተዋውቅ፣ አስተማሪዎቼ በድንጋጤ የሚገቡበት ቢጠፋቸውም፣ ታዳሚው ግን በሚያስገመግም ድምጽ አድናቆቱን ገለጸልኝ:: የተወዳደርኩበት ግጥም የንጉሰ ነገሥቱን አገዛዝ የሚተች ነበር፤ እንዲያም ሆኖ ግን በውድድሩ አሸናፊ ሆንኩኝ፡፡ ይህንንም ተከትሎ፣ የትምህርት ቤቴ የተማሪዎች ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት ሆኜ በመመረጤ፣ ከሁለተኛ ደረጃና ከዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መሪዎች ጋር ትስስር የመፍጠር ዕድል አገኘሁ፡፡ ለዲሞክራሲና ለሴቶች መብት የመሟገት የዕድሜ ልክ ትግሌ የጀመረው በዚህ መልኩ ነበር:: ለአጭር ጊዜ፣ በንጉሡ አገዛዝ ታስሬም ነበር፡፡ ነገር ግን ዕድሜ ለአያቴ ጎረቤት! ወህኒ ቤት ከመክረም አትርፈውኛል፡፡ አባቴም የአገዛዙ ተቃዋሚ ስለነበረ በዚህ ረገድ እኔና አባቴ ልዩነት አልነበረንም፡፡
የንጉሡ አገዛዝ በደርግ ወታደራዊ ኃይል ተገርስሶ እንደወደቀ፣ የኢትዮጵያ ሴቶች አደራጅ ኮሚቴ (በኋላ የአብዮታዊ ኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበር የተባለው) የብሔራዊ ቴአትር ተወካይ በመሆን ተሾምኩ:: የማኅበሩም ሥልጣንና ኃላፊነት፣ የአዲሲቱን ሶሻሊስት አገር ሴቶች ማደራጀት እንዲሁም በመብታቸውና ነጻነታቸው ዙሪያ ንቃተ ኅሊናቸውን ማሳደግ ነበር፡፡ የማኅበሩ ተወካይ ብሆንም ቅሉ፣ በምሥጢር ኢሕአፓ የተባለውን ተቃዋሚ ቡድን እደግፍ ነበር፡፡ በዚያን ሰሞን የብሔራዊ ቴአትር ከያኒያን፣ የጡረታ ጥቅማጥቅሞች ጥያቄያቸው ምላሽ እንዲያገኝና የሙያ ማኅበር የመመስረት መብታቸው እንዲከበር ሰላማዊ ሰልፍ ባደረጉበት ጊዜ፣ ይህንን አጋጣሚ በመጠቀምም፣ የኢሕአፓ አባላት መንግስትን የሚቃወም ወረቀት በማሰራጨታቸው፣ ፖሊስ ተኩስ ከፍቶ 11 ከያኒያን ተይዘው ታሰሩ፡፡ በዕለቱ አያቴ ሞታ ስለነበር እኔ በሰልፉ ላይ ለመሳተፍ ባልችልም፣ “ምን ያለበት ዝላይ አይችልም--” እንዲሉ፣ የሥራ ባልደረቦቼ ከተቃዋሚ ቡድን ጋር ግንኙነት አንዳለኝ ይጠረጥሩኝ ስለነበር፣ ወደ ሥራ ለመመለስ ክፉኛ ፈራሁ፡፡ በዚህም የተነሳ ከቤት ወጥቼ ዘመዶቼ ጋ ለስድስት ወር ያህል ተሸሸግሁ፡፡ የማታ ማታም ከተሸሸግሁበት ወጣሁና የታሰሩትን 11 ከያኒያን ይቅርታ ጠይቄ ሥራችንን ቀጠልን፡፡
ከዚያ በኋላ ነው ለመንግሥት የሶሻሊስት መርሐ ግብሮች የሰራሁት፡፡ በተለይም ሴቶችና ሕጻናትን በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ በማተኮር፡፡ ወላጆቻቸው የጦርነት ሰለባ የሆኑባቸው ሕጻናት በነበሩበት የዝዋይ ሕጻናት አምባ ውስጥ የኪነ ጥበብ ፕሮግራምን ለሕጻናት እየቀረጽኩ አቀርብ ነበር:: ይሄንንም ፕሮግራም በየ15 ቀኑ በበጎ ፈቃደኝነት እያካሄድኩ እስከ 1982 ዓ.ም ድረስ ዘልቄአለሁ:: በባህል ሚኒስቴር የሕጻናት የቲያትር ክፍልን አቋቁሜም በኃላፊነት መርቻለሁ፡፡ የትያትር ክፍሉን የመሰረትኩት ምሥራቅ ጀርመንን በጎበኘሁበት ወቅት ያየሁትን ምሳሌ በማድረግ ሲሆን ክፍሉን በባህል ሚ/ር ሥር ለሰባት ዓመት አስተዳድሬያለሁ:: ከሙያ ባልደረቦቼ ጋር በመተባበር ደግሞ የኢትዮጵያ ተዋናዮች ማኅበርን መሥርቼአለሁ:: ማኅበሩን በሊቀ መንበርነት ባገለገልኩባቸው 14 ዓመታት ውስጥ የተዋንያን ደሞዝ እንዲሻሻል ስኬታማ ቅስቀሳ አድርገናል፡፡ ሌላው ስኬታማ እንቅስቃሴያችን፣ ስለ ወሲብና በግብረ ሥጋ ግንኙነት ስለሚተላለፉ በሽታዎች ማውራት ነውር በነበረበት ዘመን፣ በአዲስ አበባ ያዘጋጀነው ለሳምንት የዘለቀ የጸረ - ኤድስ ፌስቲቫል ሲሆን በፌስቲቫሉ ላይ በርካታ ዕውቅ ከያኒያን ስራቸውን አቅርበዋል፡፡ ፌስቲቫሉ በተካሄደበት ስታዲየም ውስጥ “በጥንቃቄ ተጠቀሙ” የሚል ጽሑፍ በሰፈረበት የክብሪት ቤት ውስጥ ኮንዶም ጨምረን ለታዳሚው አሰራጭተናል:: ከዚህም ባሻገር፣ በኅብረተሰቡ ዘንድ ስለ ኮንዶም የነበረውን የኃፍረት ስሜት ለመስበር፣ ኮንዶሙን እንደ ፊኛ በመንፋት ለማዝናናት ሞክረናል፡፡
በብሔራዊ ቴአትር ተውኔቶችንና ግጥሞችን ከመተወንና ከመጻፍ ጎን ለጎን፣ የሕዝብ ግንኙነት ሥራዎችን እንዲሁም ፕሮግራሞችንና ዝግጅቶችን መምራቴን ገፋሁበት፡፡ ምንም እንኳን ወታደራዊው መንግሥት የከያኒያንን ሥራ በሳንሱር መቀስ ይጎማምድ የነበረ ቢሆንም፣ ጥበባዊ ፈጠራዎች እንዲስፋፉ የተገኘችውን ቀዳዳ ሁሉ ተጠቅመናል:: “ደማችን” ከተሰኘው የመጀመርያ የሙሉ ሰዓት ትያትሬ (የመጀመርያው ባለቤቴ ታደሰ ወርቁ፣ ስብሐት ተሰማና እኔ በጋራ የጻፍነው ነበር) በኋላ መንግስትን ክፉኛ የሚተች “በሩ” የሚል ተውኔት የጻፍኩ ሲሆን በራስ ትያትር ለአምስት ጊዜ ያህል ከታየ በኋላ፣ የባህል ሚኒስትሩ ጠርተውኝ በትያትሩ ላይ አንዳንድ ማሻሻያዎችን እንዳደርግ ጠየቁኝ፡፡ እኔ ግን አሻፈረኝ አልኳቸው፡፡ በዚህም ሳቢያ ትያትሬ እንዳይታይ እገዳ ተጣለበት፡፡
ከወደቀው አገዛዝ ጋር በቅርበት ሥሰራ በመቆየቴ ደርግ ሊወድቅ አንድ ዓመት ሲቀረው፣ ሁለት ልጆቼን (ተወለድ ታደሰና አይናለም ደጀኔን) ይዤ ወደ አሜሪካ ተጓዝኩ፡፡ ባለቤቴ ደጀኔ ገረመው ከስድስት ወር በኋላ እኔን ተከትሎ አሜሪካ ገባ:: በአሜሪካ ኑሮን ለማሸነፍ የተለያዩ ሥራዎችን ለመስራት ብገደድም፣ ልቤ ግን መቼም ቢሆን ከጥበብ ተለይቶ አያውቅም፡፡ ከልቤ የምወደውን የኪነ ጥበብ ስራ በስፋት የመስራት ዕድል ያገኘሁት ግን በ1992 ዓ.ም በዋሺንግተን ዲሲ፣ ጣይቱ የባህል ማዕከልን በማቋቋም፣ በዋና አስተዳዳሪነት መምራት ስጀምር ነበር፡፡ ማዕከሉ ላለፉት 13 ዓመታት ያለ ብዙ የውጭ ድጋፍ፣ በርካታ የኢትዮጵያ ባህላዊ ዝግጅቶችን ሲያስተናግድ ቆይቷል፡፡ እስካሁን ከ35 በላይ ተውኔቶችን ሰርተን ያቀረብን ሲሆን ከ150 የሚበልጡ የዓርብ የግጥም ምሽቶችን አዘጋጅተናል:: ከዚህም በተጨማሪ በየዓመቱ በአሜሪካ 17 ግዛቶችና በአውሮፓ እየተጓዝን፣ በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ የኪነጥበባዊ ዝግጅቶችን እናቀርባለን፡፡ ወጣት የኪነጥበብ ባለሙያዎችን ለማሰልጠን በየጊዜው ዐውደ ጥናቶችን እናዘጋጃለን:: ግጥም በኢትዮጵያ ባህላዊና መንፈሳዊ ሕይወት ውስጥ ጉልህ ድርሻ በመያዝ ለዘመናት የዘለቀ ጥበባዊ ኃይል ነው፡፡ ፕሮግራማችን በስደት ላይ ያለን ኢትዮጵያውያን ሁሉ ባህላችን ህያው ሆኖ እንዲቀጥል ብቻ ሳይሆን ከአገራችን ጋር ያለን መንፈሳዊ ቁርኝት እንዲጠናከር፣ የመጪው ዘመን ተስፋችንም እንዲለመልም አስተዋጽኦው ቀላል አይደለም፡፡ በቅርቡ በአሜሪካ የመጀመርያውን የአማርኛ ቤተ መጻሕፍት በዋሺንግተን ዲሲ ከፍተናል፡፡ የአገሪቱን መዲና በመቆርቆር ጉልህ ድርሻ የነበራቸው የእቴጌ ጣይቱ ብጡልን ሐውልት በአዲስ አበባ ከተማ ቆሞ ማየት ትልቁ ህልሜ ነው፡፡
ኢትዮጵያ የበርካታ ሴት መሪዎችና ንግስቶች አገር ብትሆንም፣ ለብዙኃኑ ሴቶች ግን ተመችታ አታውቅም፡፡ ሴቶች በሥራቸው ላይ ለመቆየት፣ ደሞዝና ዕድገት ለማግኘት እንዲሁም ሐሳባቸው እንዲከበርና ተቀባይነት እንዲያገኝ፣ ከወንዶች እጥፍ ተግተው መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ወንዶች ፊት ስለ ሴቶች እኩልነትም ሆነ በሥራ፣ በቤትና በአጠቃላይ በኅብረተሰቡ ውስጥ ስለሚደርስባቸው በደልና ኢ-ፍትሃዊነት ማውራት አይሞከርም፡፡ ወንዶች እንዲህ ያሉ ነገሮችን ለመስማት አይፈልጉም፡፡ እኔን የገጠሙኝ ፈተናዎች፣ ለራዕዬ ወይም ለሙያዬ ያለኝን ፍቅር ለማደናቀፍ አቅም ያላቸው አልነበሩም፡፡ ሰዎች “ብረቷ እመቤት” እያሉ ይጠሩኛል፤ እኔም እራሴን መንፈሰ ጠንካራና የምወደውን ሥራ ለመስራት ፈጽሞ የማይታከተኝ ሰው አድርጌ ስለምመለከት፣ ይህን መጠሪያዬን እወደዋለሁ፡፡
ለወጣት ሴቶችና ልጃገረዶች የማስተላልፈው ምክር ግልጽና ቀላል ነው፡- “በራሳችሁ እምነት ይኑራችሁ፣ ትልቅ ነገር አልሙ፣ መንፈሳችሁን አጠንክሩት፣ በምንም ሁኔታ ቢሆን ተስፋ አትቁረጡ” የሚል ነው፡፡
http://www.addisadmassnews.com

No comments:
Post a Comment