Monday, August 17, 2015

“ላምባ” ፊልም መሰረቁ ከሰብዓዊ ዓላማው አስተጓጎለው ተባለ (አለማየሁ አንበሴ)

 ሌብነት እንኳ አይነት አለው !
 
 በእውነት በ”ላንባ” ፊልም ላይ የተፈጸመው ዝሪፊያ ህሊናችን ከውዴት ነው ያሰኛል፡፡
በአንድቤት ውስጥ አንድና ከዚያ በላይ በኩላሊት ህመም እየተሰቃዩ ባሉ ህማን ላይ እንደመቀለድ ነው፡፡  ….እንኳንስ ድሀው
ምንም የሌለው ገንዘብ ያለውን እያደኸየ ያለ ፤ ድንገት ማንንም የሚጥል ህመም ፤ እድሜና ጾታን የማይለይ ህመምን
ለመዋጋት የሚደረግን ጥረት የሚያኮላሽ ተግባር ….. በአውነት ያማል ፡፡ ሌብነት እንኳ አይነት አለው ፡፡
ይህን አንብባቹ ፍረዱ !!!!!!!!!!!
“ላምባ” ፊልም መሰረቁ ከሰብዓዊ ዓላማው አስተጓጎለው ተባለ

“25 ተመልካቾች ራሳቸውን ስተው ወድቀዋል”
               ፊልሙ የተመልካች አድናቆትን አትርፏል 
                                
      በመጋቢት ወር መጨረሻ ላይ ተመርቆ ለዕይታ የበቃው “ላምባ” ፊልም ተሰርቆ በኢንተርኔት በመለቀቁ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከሲኒማ ቤት የወረደ  ሲሆን ከተነሳለት ሰብዓዊ ዓላማም እንዳስተጓጎለው ተገለፀ፡፡ በእውነተኛ ታሪክ ላይ ተመስርቶ የተሰራው ፊልሙ፤ በአንድ ኩላሊት ህመምተኛ ላይ የሚያጠነጥን ሲሆን ለእይታ በቀረበባቸው ጊዜያት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተመልካች እንደነበረው ታውቋል፡፡ 
ፊልሙ በዘውዲቱ ሆስፒታል ውስጥ ለሚገነባው የኩላሊት ህክምና ማዕከል በሚሊዮን ብር የሚገመት ገቢ ለማሰባሰብ ታቅዶበት የነበረ ቢሆንም ማንነታቸው ባልታወቀ ሰዎች ተሰርቆ በኢንተርኔት በመለቀቁ ዓላማው እንደከሸፈ የፊልሙ ፕሮዱዩሰሮች ይገልፃሉ፡፡ 
ፊልሙ ከሲኒማ ቤት በምን ሁኔታ ተሰርቆ እንደወጣ ያልታወቀ ሲሆን ፕሮዱዩሰሮቹ፣ “በበርካቶች እጅ መግባቱን በማረጋገጣችን ወደ ክስ ለመሄድ እምብዛም ጥረት አላደረግንም” ብለዋል፡፡ ፊልሙ ከአብዛኞቹ ሲኒማ ቤቶች የወረደ ቢሆንም በአሁኑ ሰዓት በላፍቶ ሞልና በአምባሳደር ሲኒማ እየታየ እንደሆነ ታውቋል፡፡ 
የተመልካቹ ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ እንደነበር የጠቆሙት የፊልሙ ደራሲና ዳይሬክተር አቶ አንተነህ ኃይሌ፤ በኩላሊት ህመምተኛ ላይ የሚያጠነጥነው ፊልም እጅግ አሳዛኝ በመሆኑ የተነሳ በተለያዩ ሲኒማ ቤቶች 25 ተመልካቾች ራሳቸውን ስተው እስከመውደቅ መድረሳቸውን ተናግረዋል፡፡ 
800ሺ ብር ገደማ እንደፈጀ የተነገረለት “ላምባ”፤ በሸገር 102.1 ሬዲዮ የ“ለዛ” ፕሮግራም “የዓመቱ ምርጥ ፊልም” ሽልማትን በሶስት ዘርፎች በመመረጥ እየመራ እንደሚገኝ አዘጋጁ ጋዜጠኛ ብርሃኑ ድጋፌ ለአዲስ አድማስ ገልጿል፡፡ 
“ፊልሙን የሰራነው ለምናከናውነው የበጎ አድራጎት ስራ ማነቃቂያ እንዲሆን ነበር” ያለው የፊልሙ ፀሐፊና ፕሮዱዩሰር አንተነህ ኃይሌ፤ በ4 ወራት የሲኒማ ቤት ቆይታው ለኩላሊት ህክምና ማዕከል ማሰሪያ ድጋፍ (በአጭር የስልክ መልዕክት) ወደ 300ሺ ብር የሚጠጋ ገቢ ማሰባሰብ እንደተቻለ ጠቁሟል፡፡ 
በአሁን ሰዓት በዘውዲቱ ሆስፒታል  የኩላሊት ህክምና ማዕከል ህንፃ ግንባታ ተጠናቆ የህክምና መሳሪያዎችን ለመግዛት የሚያስችለውን ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለማግኘት ፊልሙን ማሳየት ጨምሮ የተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሞች ታቅደው  እንደነበር አቶ አንተነህ ለአዲስ አድማስ አስረድቷል፡፡ 
ፊልሙ ባይሰረቅ ኖሮ ዩኒቨርሲቲዎችን ጨምሮ በተለያዩ የ2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች በማሳየት እስከ ግማሽ ሚሊዮን ብር ገቢ ለማሰባሰብ ታስቦ እንደነበር ፕሮዱዩሰሮቹ ገልፀዋል፡፡ በተለይ በመጪው መስከረምና ጥቅምት ወራት የመንግስት ባለስልጣናትን ጨምሮ ለተለያዩ ባለሀብቶችና በውጭ አገር ለሚገኙ ኢትዮጵያውያንም በማሳየት ላቅ ያለ ገቢ ለማስገኘት ታስቦ ነበር፡፡
ከፊልሙ ይገኛል የተባለው ገቢ ከዚህ በኋላ የሚሳካ ባይሆንም የኩላሊት ማዕከሉን ግንባታ ለማስፈፀምና ቁሳቁሶችን ለማሟላት ህብረተሰቡ በስፋት የሚሳተፍበት የቴክስት መላኪያ ቁጥር ከቀጣይ ሳምንት ጀምሮ ይፋ እንደሚደረግ ታውቋል። 
ከጀርመን ሃገር በተገኘ ብድር የተገዙ 20 ያህል የኩላሊት ህክምና ማሽኖች በቅርቡ ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው ይተከላሉ ያሉት አቶ አንተነህ፤ ሌሎች ማሽኖችን ለማስገባት ለሚያስፈልገው 60 ሚሊዮን ብር ደግሞ የተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሞች እንደታቀዱ ገልፀዋል፡፡
በተመልካቾች ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነትን ያተረፈው “ላምባ” ፊልም መሰረቁ በአገሪቱ የፊልም ኢንዱስትሪ ዕድገት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር የፊልም ባለሙያዎች ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡ በ“ላምባ” ፊልም ላይ በመሪ ተዋናይነት የሚሰራውን ዕውቁን አርቲስት ግሩም ኤርሚያስ ጨምሮ ሌሎች በርካታ አርቲስቶች ተውነውበታል፡፡
http://www.addisadmassnews.com/

No comments:

Post a Comment