አለማየሁ ገላጋይ
ፊት ለፊት ስራው፣ ከበስተጀርባ ደግሞ ህይወቱ ይገኛል፡፡ ሥራው የህይወቱ ማጣቀሻ ነው የሚሉ አሉ፡፡ በዚህም ሥራውን እንደ አነፍናፊ ውሻ አስቀድመው ህይወቱን ያንጎዳጉዳሉ፡፡ “እንዲህ ሲል የፃፈው በህይወቱ እንዲያ ስለሆነ ነው፡፡” በማለት ሥራና ህይወቱን ያጋባሉ፣ ያፋታሉ፡፡ ስለዚህ የደራሲ ቤት በሩ ቢዘጋም ከመግባትና ከመውጣት አይከላከልም፡፡ የደራሲ ደጃፍ ውሻ ቢታሰርበትም አያስፈራም፡፡ ቢታጠርም ከዘላዮች አያመልጥም፡፡
እኛ ዘንድ እንዲያ ለማድረግና ለመሆን የሚያስችል ሁኔታ የለም፡፡ ደራሲ የጓዳ ህይወቱ ቀርቶ አደባባይ የዋለው ሥራው እንኳን “በሙሉ አይን” አይታይም። ሀዲስ አለማየሁ፣ በዓሉ ግርማ፣ መንግሥቱ ለማ፣ ከበደ ሚካኤል፣ ፀጋዬ ገብረመድህን… የኖሩት ቀርቶ የፃፉትም የሚታየው በእሽኩርምሚት ነው። ከሥራዎቹ ፊት “ተልመጥማጮች” ያጠሩት የሙዚየም “ክር” አለ፤ አይታለፍም፡፡ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያም አለ፤ “በእጅ መንካት ክልክል ነው” የሚል፡፡ እኔ የሚገርመኝ “የተልመጥማጮቹ” በክር ማጠርና መንገር አይደለም፡፡ የእኛ አክብሮ ሥነ - ፅሁፍን በሙዚየም ህግ መጎብኘት እንጂ …፡፡
“የሀዲስ ዓለማየሁ ፍቅር እስከ መቃብር ተረታማ ነው” ከተባለ “ቱግ” የሚሉ “አንቀራባጮች” አሉ። “በዓሉ ግርማ ልቦለድ ያድፋፋል፤ አጨራረሱ መሰላቸት የሚታይበት የተካለበ ነው” ከተባለ የሥራው “ተሸላሚዎች” ፣ “ሐይማኖት የግል ነው፣ ለምን ይነካብናል?” በማለት ህገ መንግሥት መጥቀስ ይዳዳቸዋል፡፡ “የመንግሥቱ ለማ ግጥሞች ጥብቀትና ፍላት የሌላቸው በተሃ ናቸው” ከተባለስ? ጉዳዩን የቤተሰብ ፖለቲካ አድርገው “አብዬን?” የሚሉና የዛገ ጦር ከራስጌ የሚመዙ ሞልተዋል፡፡ “ከበደ ሚካኤል መከሩ፣ ዘከሩ እንጂ አልተቀኙም” የሚል ካለ፣ “ባባቶቻችን ደም” ይዘፈንበታል፡፡ “ፀጋዬ ገብረመድህን ግጥም እንጂ ዝሩው ያዳግተዋል” ብሎ በህይወት መኖር ያዳግታል …
የእኛ ሥነ - ፅሁፍ መብላላት ሲገባው የሚደነብሸው ለዚህ ሳይሆን ይቀራል? ገንዘብ ያወጣሁበትን መፅሐፍ ለመግዛት፣ ጊዜ ያፈሰስኩበትን ልቦለድ (ለማንበብ)፤ ቦታ የሰጠሁትን ሥራ ለማስቀመጥ … እንዴት በሌሎች እይታ እንድገመግመው እገደዳለሁ? እንዳቅሜ ከቻልኩ “ብበላው”፣ ካልቻልኩ “ብደፋው” ከውይይት ያለፈ ከሳሽና ወቃሽ ሊመደብብኝ ይገባል?...
… እንደውም ከሥራዎቹ አልፈን ደራሲዎቹ ህይወትና ኑሮ ላይ ብንሳፈር “ውረድ!” ባይ እልፍኝ አስከልካይ ሊመደብብን ይገባል? ስለ ሀዲስ ዓለማየሁ ብህትውና፣ ስለ በዓሉ ግርማ ውሎና አዳር፣ ስለመንግስቱ ለማ ሽሙጥ፣ ስለ ከበደ ሚካኤል የኩርፊያ ኑሮ፣ ስለ ፀጋዬ ገብረመድህን የተመላኪነት መንፈስ … ማውራት ግለሰብ ማውሳት ነው?...
ዮሐንስ አድማሱ ስለ ደራሲ ማውሳት ግለሰብ ማማት ተደርጎ እንዳይወሰድ የሚዘክር ተቀዳሚ ገጣሚ ነው፡፡ ስለ ዮፍታሔ ንጉሴ በቀረበው ጥናት ላይ የባለቅኔውን “የቆንጆ ፀርነት” ከማውሳት አልፎ እናቱ “ሒያጅ” እንደነበሩ ይጠቅስና እንዲህ ይላል፤
“ዮፍታሄን እንዲህ ማንሳቴ አለመልኩ እንዳይመለክ፣ አለግብሩ እንዳይወቀስ፣ እንደ ግዑዝ እንዲታይ ነው፡፡”
ዮሐንስ “እንደ ግዑዝ” ሲል ምን ማለቱ ነው? እንደ ዕቃ? እንደ ሀውልት? ወይስ ምን? ብለን እንጠይቅ። ዮሐንስ ማለት የፈለገው ዮፍታሄ እንደ ግለሰባዊ ህልው፣ አድራሻና መዳረሻ እንዳለው ሳይሆን ለመወያያ ወደ ሀሳብነት ደረጃ ከፍ አድርገን፣ የሰው ልጅ ምስጢር ማስተንተኛ ይሁነን ነው፡፡ ደራሲን “ከሰውነት” አውጥቶ ወደ “ሀሳብነት” ማሳደግ፣ ለህብረተሰብ አውጠንጣኝነት የሚበጅ ነው፡፡ እኛ ግን ለዚህ አልታደልንም፡፡
በተለይ ጥቂቶቹ ደራሲዎቻችን ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ በኋላ በሥማቸው የሥነ ፅሁፍ ደብር ይደበርና ጭፍን አምልኮ ይካሄድባቸዋል። አለመልኩ ይመለካሉ፤ አለግብሩ ይዘከራሉ፤ አይመረመሬ ይሆናሉ፡፡
ይሄን አምልኮ ለመሻር በማሰብ ይመስላል ብርሃኑ ዘሪሁን “አዲስ ዘመን” ጋዜጣ ላይ ስለ ደራሲዎች ቁርቁስ ተከታታይ መጣጥፍ አቅርቦ ነበር፡፡ በተለይ መንግሥቱ ለማ እና ፀጋዬ ገብረመድህን ያላቸውን የፉክክር “አተካራ” አጠንክሮ ጠቅሶታል፡፡ ስለዚህ ጉዳይ የተጠየቀው ጸጋዬ ገብረመድህን፤ “ጦቢያ” መፅሄት ላይ እንዲህ በማለት መልስ ሰጥቶ ነበር፡-
“… ወዳጄ ብርሃኑ ዘሪሁን ነበር በተለመደ ቅንነቱ በሥነ - ፅሁፍ ዓለም የደራሲያን መከራከርና መወዳደር ሙያውን ያዳብራል፣ የአንባቢውንም ህዝብ ጣዕምና ግንዛቤ ያካብታል በሚል ትክክለኛ ሀሳብ ተነስቶ፣ በአዲስ ዘመን አምድ ላይ “የደራሲያን ጦርነት” ብሎ ያስቀመጠው መልዕክት፣ እሱም እኛም ወደ አላሰብነው አቅጣጫ ሄዶ፣ ለከተሜው የቧልት ፍጆታ ሆነ፡፡ እስከዛሬ “ጦርነት” እየተባለ “በምሁራን” አካባቢ ይቧለትበታል፡፡ እንጂ ከወዳጄ ከመንግስቱ ለማ ጋር እንኳን ጦርነት ቁርቋዞም አልነበረንም”
ፀጋዬ ይሄን ይበል እንጂ መለስ አድርጎ ስለ መንግስቱ ለማ ቀልድ ለበስ ንግግር ሲገልፅ አንዳች ነገር እንደነበር ለመጠርጠር እንገደዳለን፡፡
“… እኔ ከገጠር ሜጫ ምድር ከገበሬና ከመለስተኛ ነጋዴ ቤተሰብ መጥቼ፣ አዲስ አበባ በምኒልክ ከተማ፣ ብዙ የሥነ ፅሁፍ ታላላቅ ሰዎች በታወቁበት፣ በደረጁበትና ሥር በሰደዱ መሀል ገብቼ፣ ገና በሀያ ዘጠኝ ዓመቴ ስሸለም፣ የነፍሳቸውን መክሊት እንደወሰድኩባቸው ያህል በተለይ ጉምቱዎቹ የሥነ ፅሁፍ አባቶች ያደረሱብኝን የምቀኝነት ቁስል በቁጭት ሳስታውሰው፣ የወዳጄ የመንግሥቱ ለማ ደማም ቅሬታ፣ እንኳንስ ሊያማርረኝ እንደቅድመ ማስጠንቀቂያ ምክር ነበር የጠቀመኝ፡፡ በዛሬው ጊዜ ታዲያን እንደመንግስቱ ለማ ደማም ቀልደኛ፣ ኮሶውን ከማር ለውሶ ማሻር የሚያውቅበት ደራሲ ስለጠፋ ነው፣ የጭቃ ጅራፍ ለጣፊና የጭቃ ጅራፍ “ተለጣፊ” ብቻ የተንሰራፋው፡፡ ያም ሆኖ የመንግስቱም ቀልድ አንዳንድ ጊዜ መራራ ነበር፡፡”
ሥነ ፅሁፋዊው “በደረቁ እጥበት” የደራሲዎቻችንን ህይወት አንፅቶ የአደባባይ ክት - ልብስ አደረገው እንጂ በየስርጉጡ የተነካካከ ነበር። የሚገርመው በላውንደሪ ሥራ መጠመዳችንና በማንፃት ሥራ መለከፋችን የነበረው እንደነበረው የማቅረብን ያህል የሚጠቅመን አልነበረም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ብቅ የሚሉ መረጃዎቻችንን ስንመረምር፣ ፀጋዬ ቁርቁሱን እጅግ አድርጎ እንዳለዘበው ይገባናል። የሥዕልና የሥነ-ፅሁፍ ሀያሲው ስዩም ወልዴ “ኩርፊያ የሸፈነው ፈገግታ” የተሰኘ መፅሀፉ ውስጥ ስለዚሁ የደራሲያን የመሸራደድና የመጠቃቃት ባህርይ ይነግረናል፡፡ ከበደ ሚካኤል የአፄ ኃይለሥላሴ ሽልማት ድርጅት ሲሸልማቸው፣ ደራሲ ዓለማየሁ ሞገስ በዚሁ በሽልማቱ ጉዳይ ስብሰባ ጠሩ፡፡ ወወክማ ለታደመው ሰውም በአደባባይ “ከበደ ደራሲም ተርጓሚም አይደለም፡፡ ከበደ ሌባና ባንዳ ነው” እንዳሉ ስዩም ወልዴ ነግሮናል፡፡
እንኳን የጓዳው ህይወት እንዲህ ያሉ የአደባባይ መግለጫዎችም ያለተፈጥሯቸው ውስጥ ለውስጥ እንዲስለከለኩ እያስገደድናቸው ነው። ለምን? ለማን? … ደራሲዎቻችንን ከህልፈት በኋላም፣ ሲወጓቸው እንደሚደሙ፣ ሲነግሯቸው እንደሚደመሙ ከማሰብ፤ እንደ ዮሐንስ አድማሱ ወደ ሀሳብ ደረጃ አሳድጎ፣ አጠቃላይ የሰው ልጅን ማጥኛ ማድረግ አይበጅም? እኔ ይበጃል ባይ ነኝ፡፡
http://www.addisadmassnews.com/

ጆሲ ኢንዘሀውስ የደሀ ወዳጁ የደሀ ተቆርቋሪ የተባለው ነጋዴ ይሄ ሁሉ ምስኪን በሞት ተቀጥፎ ቴሌቪዥኑ ቀኑን ሙሉ የጭፈራ ሙዚቃ ሲያሰጮህ መዋሉ ብዙም ግር አላለኝም እኔ ምክኒያቱም እምባ ሽጦ አዳሪ መሆኑን ቀድሜ አውቀው ነበር፡፡
ReplyDelete