አውግቸው ተረፈ የብዕር ስሙ ነው። ወላጆቹ ያወጡለት ስም ኅሩይ ሚናስ ነው። የብዕር ስሙ ግን ይህ ብቻ እንዳልሆነ ደራሲ እንዳለ ጌታ ከበደ ለቢቢሲ ይናገራል።
በአጫጭር ልብወለድ፣ በትርጉም፣ እንዲሁም በአርታኢነት የሚታወቀው ኅሩይ ሚናስ ውልደቱ አዲስ አበባ አይደለም። ከጎጃም ደጀን ነው፤ ወደ አዲስ አበባ መጥቶ አይነ ስውራንን ይመራ ነበር።
ወደ አዲስ አበባ እንደመጣ ራሱን ለማኖር በረንዳ ላይ አድሯል። ቀስ በቀስ የፀሎት መጻህፍትን ወደ መሸጥ ከዚያም በሂደት የትምህርትና የልብ ወለድ መጻህፍትን ሸጧል።
መጻህፍት ንግድን ያስተማራቸው እነ አይናለም ዛሬ በጥሩ ሁኔታ የሚንቀሳቀሱ መጻህፍት ሻጮና አከፋፋይ ሆነዋል ይላል እንዳለ ጌታ ከበደ።
አውግቸው መጻህፍት ሻጭ በነበረበት ወቅት እርሱ እያነበበ ተመሰጦ ሳለ የመግዛት ፍላጎት ያለው ሰው ሲመጣ ውሰደው ብሎ በነጻ እንደሚሰጥ ይነገርለታል።
ለደራሲ አበረ አዳሙ ከአውግቸው ስራዎች "ወይ አዲስ አበባ"ን የሚያክል የለም። "ወይ አዲስ አበባ" የአውግቸው የራሱ ታሪክ ነው ይላሉ።
ለአቶ አበረ አውግቸው ጭምት ደራሲ ነው። በዚህ ሀሳብ የ"አለመኖር" ደራሲው ዶ/ር ዳዊት ወንድማገኝም ይስማማሉ።
ሁለቱም ደራሲያን ብዙ ማውራት አይወድም። በጥልቀት ያስባል ሲሉ አቶ አበረ አክለው የመርህ ሰው ነው ብለዋል።
አቶ አበረ ለአውግቸው የመርህ ሰውነት የሚጠቅሱት በ19 87ና 88 ዓ.ም አካባቢ የሆነውን በማስታወስ ነው "በዚህ ዓመት የማነበው መዝገበ ቃላት ነው ካለ አመቱን ሙሉ ቃሉን ጠብቆ የሚያነበው ያንኑ ነው።"
አቶ አበረ "እንደው ለመሆኑ አውግቸው ጓድ መንግሥቱን ትግል እገጥማለሁ ብሎ ቤተ መንግሥት መሄዱን ታውቃላችሁ?" አሉን።
"አረ በጭራሽ" የኛ መልስ ነበር። አውግቸው አንድ ዕለት ወደ ብሔራዊ ቤተ መንግሥት ሄዶ ኮሎኔል መንግሥቱን ጥሩት አለ። "ለምን?" ሲሉት "ትግል እገጥመዋለሁ መልሱ ነበር።
"ይህንን ... "ብሎም እላፊ ተናገረ።
እኔን ትግል ገጥሞ መጣል ሳይችል አገር መግዛት ይችላል መከራከሪያው ነበር።
ወታደሮቹ አፈፍ አድርገው ደበደቡት። ከዚያም እስር ቤት ወርውረውት ለበርካታ ጊዜ ታስሮ ነው የወጣው ይላሉ አቶ አበረ።
"ይህ መቼ ነው የሆነው አልናቸው?" ሰባዎቹ መጀመሪያ ይመስለኛል አሉ በመጠራጠር።
"ኅሩይ ርትዑነት ያረበበበት ቀና ሰው ነበር የሚለው" እንዳለጌታ አሮጌ መጻህፍትን እየሸጠ የጻፋቸው አጫጭር ልብ ወለዶች የካቲት መጽሔት ላይ ታትመው መነበብ መጀመራቸውን ይናገራል። ለዚህ ደግሞ ምክንያት የሆነው መፅሐፍት ከእርሱ እየገዛ ያነብ የነበረው ስብሀት ገብረ እግዚያብሄር እንደሆነ እንዳለ ጌታ ያስታውሳል።
ያኔ አሮጌ መጻህፍት እየሸጠ ሲጽፍ ጓደኞቹ አንተን ብሎ ደራሲ ብለው እንዳይዘባበቱበት ስለፈራ በብዕር ስም ነው ትረካው መጽሔት ላይ እንዲወጣ ያደረገው።
አውግቸው ብዙ የብዕር ስሞች አሉት የሚለው እንዳለጌታ፣ ራሱ ነገረኝ በማለት አዳነ ቸኮል የእርሱ የብዕር ስም መሆኑን አጫውቶናል።
በዚህ የብዕር ስም፣ በአዳነ ቸኮል 'የአማልክትና የጀግኖች አፈ ታሪክ' የሚል ሥራ ታትሞ ለንባብ በቅቷል፤ አዳነ ቸኮል የአያቱ ስም ነው።
የአውግቸውን በርካታ ሥራዎች ከተመለከተና ካነበበ በኋላ "የአደፍርስ ደራሲ ዳኛቸው ወርቁ አውግቸውን ኩራዝ አሳታሚ ወስዶ በአርታኢነት አስቀጥሮታል" የሚለው እንዳለጌታ ኩራዝ አሳታሚ በርካታ ሥራዎችን ሰርቷል ሲል ምስክርነቱን ይሰጣል።