ዮሐንስ አንበርብር
- ሁዋዌና ዜድቲኢ ፕሮጀክቱን ተካፈሉት
- የውጭ ቴሌኮም ኩባንያዎች እየገቡ ነው
ኢትዮ ቴሌኮም በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ መሠረት የተጣለበትን ግብ ለማሳካት የቀረፀውን የ1.6 ቢሊዮን ዶላር የማስፋፊያ ፕሮጀክት እንዲያከናውኑለት ከዓመት በፊት ሁለቱን የቻይና ኩባንያዎች ከመረጠ በኋላ፣ ሁለቱ ኩባንያዎች በፕሮጀክቱ ላይ የበላይነትን ለማግኘት በፈጠሩት ፉክክር ምክንያት አንድ ዓመት የፈጀ ውጥረትና ሥጋት የተሞላበት ድርድር በማካሄድ በዚህ ሳምንት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡
ውሳኔውንም ተከትሎ ኢትዮ ቴሌኮም ሁዋዌ ቴክኖሎጂ ከተባለው የቻይና ኩባንያ ጋር የ800 ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ውል ስምምነት ባለፈው ሐሙስ ምሽት በሸራተን አዲስ ተፈራርሟል፡፡ በዚህ የስምምነት ሥነ ሥርዓት ላይ በኢትዮ ቴሌኮም የተበተነው ጋዜጣዊ መግለጫ የውል ስምምነቱ የሚፈጸመው ከሁለቱ የቻይና ኩባንያዎች ከሁዋዌና ከዜድቲኢ ጋር መሆኑን ቢገልጽም፣ ስምምነቱን የፈረመው ግን ሁዋዌ ብቻ ነው፡፡ ዜድቲኢ ከተባለው የቀድሞውን የማስፋፊያ ፕሮጀክት ካከናወነው የቻይና ኩባንያ ጋር የሚቀር ድርድር ስላለ ቀሪው የ800 ሚሊዮን ዶላር ስምምነት ለጊዜው አልተፈረመም፡፡
ዜድቲኢ በዚህ የኮንትራት ስምምነት ላይ ያልተገኘው በኢትዮ ቴሌኮም ውሳኔ ቅር በመሰኘት መሆኑን የኢትዮ ቴሌኮም ምንጮች ለሪፖርተር የገለጹ ቢሆንም፣ በኮንትራት ስምምነቱ ላይ የተገኙት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የኢኮኖሚ ዘርፍ አስተባባሪና የኢንፎርሜሽንና ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ደብረ ፅዮን ገብረ ሚካኤል ከሞላ ጐደል ከሁለቱም ኩባንያዎች ጋር በመርህ ደረጃ ስምምነት ላይ ተደርሷል በማለት፣ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ነገር ግን ዜድቲኢ ቅሬታ ከሌለበት ኮንትራቱን ለምን እንዳልፈረመ እንዲያብራሩ ሲጠየቁ፣ ስምምነቱ በመርህ ደረጃ በመሆኑ ቀሪ መጠናቀቅ የሚገባቸው ጉዳዮች መኖራቸውንና እነሱን ለማጠናቀቅ ተጨማሪ ውይይት እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡
ሙስና በኢትዮ ቴሌኮም
በኢትዮጵያ ከፍተኛ የሙስና ወንጀል ለመፈጸም ከሚመቹ ተቋማት አንዱ ኢትዮ ቴሌኮም መሆኑን የተለያዩ ጥናቶች የሚያረጋግጡ ሲሆን፣ በተግባርም የተደረሰባቸው የሙስና ወንጀሎች በዚህ ተቋም ውስጥ መፈጸማቸው ይታወቃል፡፡
የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ የሙስና ወንጀል ድርጊትና ተጋላጭነት ላይ ያደረገውን ጥናት ባለፈው ጥር ወር በሒልተን ሆቴል ይፋ ባደረገበት ወቅት፣ በከፍተኛ የሙስና ተጋላጨነት ስማቸው ከተጠቀሱ የመንግሥት ተቋማት አንዱ ኢትዮ ቴሌኮም ነው፡፡
የባንኩ የጥናት ውጤት እንደሚያስረዳው ኢትዮ ቴሌኮም በቢሊዮኖች ዶላር ግዥ የሚፈጽም ተቋም ቢሆንም፣ በተቋሙ ወጥ የሆነ የግዥ ሥነ ሥርዓት አለመኖሩን ይገልጻል፡፡ ይህ ደግሞ ዋነኛው ለሙስና ምቹ የሆነ አሠራር መሆኑን የሚያብራራው የባንኩ ሪፖርት፣ እ.ኤ.አ. በ2006 ለመጀመርያው የማስፋፊያ የ1.5 ቢሊዮን ዶላር ፕሮጀክት የሚያስፈልጉ የቴሌኮም መሣሪያዎች ግዥ በጨረታ ሥነ ሥርዓት የተገዙ መሆናቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችል መረጃ ማግኘት አለመቻሉን ያስረዳል፡፡
‹‹ይህ የጥናት ውጤት በሙስና ወንጀል ላይ የተደረገ ምርመራ ወይም ሙስና በዚህ የ1.5 ቢሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ላይ ተፈጽሟል የሚል የተሳሳተ ትርጓሜ እንዳይሰጠው፤›› ሲል የሚያሳስበው የዓለም ባንክ ሪፖርት፣ በጥናቱ ወቅት ከተጠየቁ ባለድርሻ አካላትና ነፃ ታዛቢዎች በኢትዮ ቴሌኮም ሙስናን ለመቆጣጠር የሚያስችል ሥርዓት እንደሌለ መገንዘቡን ያስረዳል፡፡
በመጨረሻም ኢትዮ ቴሌኮም ባከናወናቸው ትልልቅ ግዥዎች ላይ መንግሥት ኦዲት ሊያደርግ እንደሚገባው፣ እንዲሁም የቬንደር ፋይናንሲንግ (ኩባንያዎች ለሚወዳደሩበት ፕሮጀክት ወጪ ራሳቸው ገንዘብ በማቅረብ ካጠናቀቁ በኋላ በረዥም ጊዜ የሚከፈሉበት የብድር ሥርዓት) ሥርዓት በከፍተኛ ደረጃ ለሙስና የተጋለጠ በመሆኑ፣ ሊያስወግድ እንደሚገባ አስተያየቱን ለመንግሥት ለግሷል፡፡
ይህ የዓለም ባንክ ሪፖርት በቀረበበት ወቅት ግን መንግሥት በቬንደር ፋይናንሲንግ ሥርዓት የ1.6 ቢሊዮን ዶላር የቴሌኮም ማስፋፊያ ለማድረግ ከመረጣቸው ዜድቲኢና ሁዋዌ ኩባንያዎች ጋር በድርድር ላይ ነበር፡፡ ከሁለቱ ኩባንያዎች ጋር የተደረገው ድርድር ዓመት የፈጀ ሲሆን አሰልቺ አንደነበርም ተሳታፊ የነበሩ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በዚሁ ሁኔታ ውስጥ ወደትግበራ ሊሸጋገር የደረሰው የ1.6 ቢሊዮን ዶላሩ የማስፋፊያ ፕሮጀክት ከሙስና ጭጋግ የፀዳ ይሆን የሚለው አሁንም ጥያቄ ያስነሳል፡፡
የሙስና ድባብ በአዲሱ ፕሮጀክት
በዓለም ባንክ ጥናት መሠረት ኢትዮ ቴሌኮም ከሚያንቀሳቅሰው ከፍተኛ ሀብትና የመሠረተ ልማት ፕሮጀክት ግዝፈት ያልተናነሰ የሙስና ተገላጭነት አለ፡፡ ይህ ተቋም ለሙስና ተጋላጭ ካደረጉት ሥርዓቶች ደግሞ የቬንደር ፋይናንሲንግ የግዥ ሥርዓት አንዱ ነው፡፡ ይህ ሥርዓት ለሙስና ምቹ ከመሆኑ ባሻገር ሊፈጸም የሚችለው ሙስና ጉዳቱ ሁለት መሆኑን የባንኩ ሪፖርት ያስረዳል፡፡ አንድም አገሪቱን ለከፍተኛ ወጪ የሚዳርግ ሌላው ደግሞ በሚከናወነው የመሠረተ ልማት ላይ የሚያስከትለው የጥራት ጉድለት ነው፡፡
የኢትዮ ቴሌኮም የማስፋፊያ ፕሮጀክቱን ለማከናወን ጨረታ ያወጣው ከዚህ የዓለም ባንክ ሪፖርት በፊት ቢሆንም፣ ሥርዓቱ ግን ያው ቬንደር ፋይናንሲንግን የተከተለ ነው፡፡
በዚህ ጨረታ ላይ ለመሳተፍ ፍላጐት ያሳዩ ድርጅቶች ውስን በመሆናቸው ጨረታው ተሰርዞ በዚሁ የቬንደር ፋይናንሲንግ ሥርዓት መሠረት ሁለቱ የቻይና ኩባንያዎች ባቀረቡት ፕሮፖዛል መሠረት፣ ከዓመት በፊት የመንግሥትን ይሁንታ ማግኘታቸውን መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡
ኩባንያዎቹ የማስፋፊያ ፕሮጀክቱ የሚጠይቀውን ወጪ በመሸፈን ለመሳተፍ ፍላጐት ማሳየታቸው መንግሥት ከኩባንያዎቹ ጋር ድርድር ማድረግን እንዲመርጥ መንገድ ከፍቶለታል፡፡ ይህም በፕሮጀክት ማስፋፊያ ዕቅዶቹ ላይ የፋይናንስና የቴክኒክ ፕሮፖዛሎቻቸውን እንዲያቀርቡ በማድረግ ኩባንያዎቹ ውድድር ውስጥ እንዲገቡ፣ በዚህም መንግሥት በተሻለ ወጪ ጥራት ያለው የቴሌኮም መሠረተ ልማትን መዘርጋት ዓላማው ያደረገ መሆኑን መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡
ይሁን እንጂ ይህ መንግሥት የመረጠው መንገድ ውጥረት የተሞላበትና እልህ አስጨራሽ የሆነ የአንድ ዓመት የድርድር ጊዜን እንዲያሳልፍ አስገድዶታል፡፡ በዚህ ወቅትም ሁለቱ ኩባንያዎች የፕሮጀክቱን አንበሳ ድርሻ ለመያዝ ፉክክር ውስጥ መግባታቸውንና ይህን ውጥናቸውን ለማሟላትም ካቀረቡት የገንዘብና የቴክኒክ ፕሮፖዛል ባለፈ ተጨማሪ ጥረቶችን ሲያደርጉ መቆየታቸውን፣ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
የኢትዮ ቴሌኮም ከፍተኛ አመራሮችን እንዲሁም በኢትዮ ቴሌኮም ቦርድ ውስጥ የሚገኙና ከውጭ ያሉ የፖለቲካ አመራሮችን በመቅረብ ፍላጐታቸውን ለማሳካት ጫና ሲያደርጉ እንደነበርም ምንጮቹ ገልጸዋል፡፡
በዶ/ር ደብረፅዮን የበላይነት የተቀየሰው መንገድ ግን ኩባንያዎቹ በኢትዮ ቴሌኮም ገምጋሚዎች ላይ ጫና እንዳያደርሱ ከለላ የሰጠ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
በዋናነት የሚጠቅሱት ኩባንያዎቹ የሚያቀርቡትን ፕሮፖዛል የሚመረምር የኢትዮ ቴሌኮም የቴክኒክ ባለሙያዎች ቡድን እንዲዋቀር ማድረጋቸውንና ቡድኑም ግምገማውን በሚያካሂድበት ወቅት የሌሎች አካላት ጣልቃ ገብነት እንዳይኖር ጥረት ይደረግ ነበር ብለዋል፡፡ ከእነዚህ መካከልም የቴክኒክ ቡድኑ ግምገማውን የት እያደረገ መሆኑ እንዳይታወቅ በሚስጥር መያዙን፣ አልፎ አልፎም ከአዲስ አበባ ውጪ ግምገማውን እንደሚያደርግ፣ በግምገማ ወቅትም የቡድኑ አባላት ተንቀሳቃሽ ስልክ ይዘው መግባት እንደማይፈቀድላቸው ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ኩባንያዎቹ የሚኖራቸው ድርሻ በእነዚህ የባለሙያዎች ቡድን የግምገማ ውጤት ላይ የተመሠረተ መሆኑን የሚገለጹት ምንጮች፣ ከአራት ወራት በፊት በግምገማ ውጤቱ መሠረት የኢትዮ ቴሌኮም አመራር ሁዋዌ የተባለው ኩባንያ 60 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ እንዲወስድ ወስኖ እንደነበር፣ ነገር ግን ከፍተኛ ተቃውሞ በዜድቲኢ በኩል በመነሳቱ በድጋሚ ወደ ውድድር መገባቱን ያስረዳሉ፡፡
ከዚህ ውጥረት የተሞላበት ድርድር በኋላ ኢትዮ ቴሌኮም የመጨረሻ ውሳኔውን በማሳለፍ ሁለቱ ኩባንያዎች የ1.6 ቢሊዮን ዶላር ፕሮጀክቱን 50 በመቶ እኩል እንዲካፈሉ ተወስኖ ተጠናቋል፡፡
የሁዋዌ የኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሚስተር ጆኒ ዱዋን ስለ ድርድሩ ተጠይቀው እጅግ አስቸጋሪ ወቅት እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ‹‹በመጨረሻም ሁላችንም ጥቅም የምናገኝበት ውሳኔ በመተላለፉ ወደ ስምምነት መጥተናል፡፡ ድርድሩ ለኢትዮ ቴሌኮም ጥሩ ዕድልን የፈጠረ ነው፡፡ ምክንያቱም ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ማቅረብ ውድድሩን ለማሸነፍ መሠረታዊ በመሆኑ ኢትዮ ቴሌኮም ተጠቃሚ ሆኗል፤›› ብለዋል፡፡
ድርድሩ እንዴት አንድ ዓመት ሊፈጅ ቻለ በሚል የተጠየቁት ዶ/ር ደብረ ፅዮንም በተመሳሳይ የኢትዮ ቴሌኮምን ጥቅም ለማስከበር መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ በስምምነቱ መሠረት የሚካሄደው የማስፋፊያ ፕሮጀክት የአገሪቱን የሞባይል አገልግሎት ወደ 50 ሚሊዮን የሚያሳድግ ሲሆን፣ አገልግሎቱም በተለይ በአዲስ አበባ ዓለም የደረሰበትን የ4G ቴክኖሎጂ የሚያካትት ነው፡፡ በተጨማሪም አሁን በተወሰኑ አካባቢዎች ብቻ ያለውን የ3G አገልግሎት በመላው አገሪቱ ያዳርሳል፡፡
ይህንን ማስፋፊያ ለማከናወን ፕሮጀክቱ የኔትወርክ ዘርፍና የኢንፎርሜሽን ሲስተም ዘርፍ በሚል ለሁለት ተከፍሎ የተለያዩ ዝርዝር ሥራዎች በየሥራቸው ተካትተዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል በደንበኞች አገልግሎት አቅርቦት የተመለከቱ ፕሮጀክቶችን እንዲያከናውን የተመረጠው ሁዋዌ ነው፡፡ ዜድቲኢ ደግሞ በኦፕሬሽን ድጋፍ መስጫና በደኅንነት ሥርዓት ዝርጋታ መስክ ያሉ ተግባራትን ያከናውናል፡፡
በአጠቃላይ ሁዋዌ ተመራጭ የሆነባቸው መስኮች ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የሚጠይቁ የሞባይልና ኢንተርኔት አገልግሎቶችን የሚያካትት እንደሆነና የአዲስ አበባው የ4G ፕሮጀክትም በዚሁ ሥር እንደሚሆን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
የኢትዮ ቴሌኮም አመራሮችና የሁዋዌ ሥራ አስፈጻሚ ግን የአዲስ አበባው የ4G ፕሮጀክት ገና አልተወሰነም ይላሉ፡፡
ዜድቲኢ በኮንትራት ስምምነቱ ላይ ለምን እንዳልተገኘ በተደጋጋሚ ቢጠየቅም ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም፡፡ ምንጮች ግን የአዲስ አበባው የ4G ፕሮጀክት ለሁዋዌ በመሰጠቱ ቅር ተሰኝቶ ነው ይላሉ፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም ወዴት?
መንግሥት የዓለም የንግድ ድርጅትን በ2007 ዓ.ም. ለመቀላቀል እየሠራ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ የዓለም የንግድ ድርጅት አሠራር ደግሞ የመንግሥት ሞኖፖሊን የሚከለክል መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህም ማለት ኢትዮ ቴሌኮምን ወደ ግል ሳያዘዋውር የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን አዳጋች ነው፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ታዋቂ ዓለም አቀፍ የቴሌኮም ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ መሆናቸው መንግሥት ኢትዮ ቴሌኮምን ወደ ግል የማዞር የቅርብ ጊዜ ዕቅድ አለው የሚሉ መላምቶች እንዲጐሉ ምክንያት ሆኗል፡፡ ዶ/ር ደብረ ፅዮን ግን መንግሥት ኢትዮ ቴሌኮምን ወደ ግል የማዞር የቅርብ ጊዜ ዕቅድ እንደሌለው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
‹‹የደቡብ አፍሪካው ኤምቲኤን በኢትዮጵያ ቢሮውን የከፈተ ሲሆን፣ ሌሎች ኩባንያዎችም እያነጋገሩን ነው፡፡ ይህ ግን ኢትዮ ቴሌኮምን ከማዞር ጋር አይገናኝም፤›› ብለዋል፡፡
እየገቡ ያሉት ኩባንያዎች ዋና ዓላማ ተጨማሪ እሴት እየጨመሩ የቴሌኮም አገልግሎቶችን ለመስጠትና የኢትዮጵያን ገበያ እያጠኑ ለመቆየት ነው የሚሉት ዶ/ር ደብረ ፅዮን፣ መንግሥት ኢትዮ ቴሌኮምን ወደ ግል የማዞር ዕቅድ ባይኖረውም ለዘለዓለም ይዞት ይኖራል ማለት ግን አይደለም ብለዋል፡፡
http://www.ethiopianreporter.com/

No comments:
Post a Comment