Written by
ግሩም ሠይፉ
አዲስ አድማስ ጋዜጣ
ታላቁ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ወደ ፖለቲካ ለመግባት ፍላጎት
እንዳለውና የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ለመሆን እንደሚያስብ በመናገሩ ትኩረት ሳበ፡፡ በሳምንቱ መግቢያ ላይ አሶስዬትድ
ፕሬስ አትሌቱን በማነጋገር ያሰራጨውን ዘገባ በመንተራስ በርካታ የዜና አውታሮች እና መረቦች ጉዳዩን በተለያየ
አቅጣጫ በመተንተን ዘግበውታል፡፡ ፎክስ ኒውስ አዲስ አይነት ፉክክር ውስጥ መግባቱን በርእሱ ሲገልፅ፤ የኬንያው
ዴይሊ ኔሽን ኃይሌ ፖለቲካ ሊገባ ነው በሚል ዜናውን አናፍሷል፡፡
ዘ አፍሪካን ሪፖርት በበኩሉ አትሌቱን ከጆርጅ ዊሃ በማነፃፀር
ባሰራጨው መጣጥፍ ኃይሌ ከስፖርት ወደ ፖለቲካ ዓለም በመዞር የአገር ፕሬዝዳንት ለመሆን የሚያበቃ የተሻለ ስትራቴጂ
እንዳለው ደምድሟል፡፡ ምንም እንኳን ቤተሰቡ ያሰበውን ስለማሳካቱ እርግጠኛ ባይሆኑም ኃይሌ ፖለቲካን የፈለገው የብዙ
ወገኑን ጥቅም ለማስጠበቅ እንደሆነ ለአሶስዬትድ ፕሬስ የገለፀ ሲሆን ህዝብን የበለጠ የሚረዳበት እድል ማጣት
እንደማይፈልግ ተናግሯል፡፡ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ የፓርላማ ተመራጭ ሆኖ ለመወዳደር እቅድ እንዳለው በትዊተር
ማስታወሻው እንደፃፈም በርካታ የዓለም ሚዲያዎች ገልፀዋል፡፡ ምርጫ እንደሚወዳደር እና ኢትዮጵያ በእድገት ወደፊት
እንድትራመድ ልረዳት አፍለጋለሁ ማለቱ ተዘግቧል፡፡
ዘ አፍሪካን ሪፖርተ ኃይሌ ገብረስላሴ እና ጆርጅ ዊሃን
ያነፃፀረበትን መጣጥፍ ያቀረበው የስፖርት ስኬት የአንድ አገርና ህዝብን የወደፊት እጣ ፋንታ ለማስተዳደር ይበቃል
ወይ በሚል ጠያቂ ርእስ ነበር፡፡ በአፍሪካ አህጉር በስፖርት ስኬት እና ዝናው ወደ ፖለቲካ በቀጥታ በመግባት ብቸኛው
የላይቤሪያው ጆርጅ ዊሃ እንደነበር ያወሳው ዘ አፍሪካን ሪፖርት ከስፖርት ወደ ፖለቲካ ዓለም መግባት በአውሮፓ እና
በአሜሪካ የተለመደ መሆኑን በማመልከት ነው፡፡ ከስድስት ዓመት በፊት ጆርጅ ዊሃ ከስፖርቱ ዓለም በቀጥታ ወደ
ላይቤርያ ፖለቲካ በመግባት አገሪቱን በፕሬዝዳንትነት ለመምራት የወሰነው በተሟላ ስትራቴጂ አልነበረም የሚለው ዘ
አፍሪካን ሪፖርት በወቅቱ ተፎካካሪው የነበሩትን ሄለን ጆሴፍ ሰርሌፍ ማሸነፍ ሳይሆንለት መቅረቱን አስታውሷል፡፡
እንደ ዘ አፍሪካን ሪፖርት ማብራርያ ኃይሌ ከስፖርቱ ወደ
ፖለቲካው ዓለም በቀጥታ አልገባም፡፡ በስፖርቱ ባገኘው ስኬት እና ዝና፤ በማህበራሰባዊ ግልጋሎቶች፤ በኢንቨስትመንት
መስክ ባገኛቸው ውጤቶች በኢትዮጵያውያን ክብርና አድናቆት አግኝቷል በብሄራዊ ጉዳዮች ባለው የአገር አዋቂነት ሚና
እና የአገር ሽማግሌነት አስተዋፅኦ የተመሰገነበት ተግባራቱ ናቸው፡፡ በርካታ የተቃዋሚ መሪዎችና ፖለቲከኞች
በመንግስት ጥፋተኛ ሆነው ከታሰሩበት ቅጣት በይቅርታ ምህረት ተደርጎላቸው እንዲፈቱ ካአገር ሽማግሌዎች ዋናው ተፅእኖ
ፈጣሪ እንደነበር በዘ አፍሪካን ሪፖርት ሃተታ ተጠቅሷል፡፡
በሌላ በኩል ኃይሌ ገብረስላሴ በኦሎምፒኳ ከተማ ሉዛን ውስጥ በ‹ዘ አሶሴሽን ኢንተርናሲዮናሌ ዴላ ፕሬስ ስፖርትስ› ልዩ ክብር ሽልማት ተሰጥቶታል፡፡ ሽልማቱ AIPS Power of Sport Award ተብሎ ይጠራል፡፡ በየዓመቱ በስፖርቱ ዓለምን፤ አገርንና ማህበረሰብን የሚለውጥ አስተዋፅኦ ላበረከቱ የስፖርት ሰዎች የሚሰጥ ልዩ የክብር ነው፡፡ 86 ዓመታት እድሜ ያለው ዓለም አቀፉ ተቋም “ኤአይፒኤስ” የሽልማት ስነስርዓቱን ዘንድሮ ያዘጋጀው ለሶስተኛ ጊዜ ሲሆን የዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ጃኩዌስ ሬጌ እና አሜሪካዊቷ የቀድሞ ዋናተኛ ዶና ዴሳሮና ሌሎቹ ተሸላሚዎች ናቸው፡፡ ሽልማቱ በአትሌት ምስል የተዘጋጀ ቅርፅ ሲሆን በቻይናው የኦሎምፒክ ምርቶች አምራች እና አከፋፋይ ኩባንያ ሆናቭ የተዘጋጀ ነው፡፡
ኃይሌ ገ/ስላሴ ለዚህ ክብር ለመመረጥ የበቃው በአትሌቲክስ
ስፖርት ለረጅም ጊዜ በከፍተኛ ውጤት በመቆየቱ፤ በስፖርቱ ያለው ተወዳጅነት በአገሩ ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም
በመሆኑ፤ በጂ4ኤስ ታዳጊዎች ፕሮግራም 14 ወጣት አትሌቶች በ2012 የለንደን ኦሎምፒክ ተሳትፎ እንዲያገኙ በፈጠረው
መነቃቃት እና በሰጠው ድጋፍ፤ በፀረ ኤድስ ዘመቻ ለአመታት ባበረከተው አስተዋጽኦ፤ በአፍሪካ ትልቁ የሆነውና እስከ
37ሺ ስፖርተኞችን በማሳተፍ የሚታወቀውን የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድር በመመስረትና በዚሁ ስር የሚካሄዱ
ውድድሮችን በተለያዩ የተባበሩት መንግስታት እና የበጎ አድራጎት ተቋማት ብሄራዊ መልዕክቶች አያይዞ የፈፀማቸው
ተግባራት እውቅና በማግኘታቸው ነው፡፡ ኃይሌ ገብረስላሴ ተመሳሳይ ሽልማት ሲያገኝ የመጀመርያው አይደለም፡፡
ከ2 ዓመት በፊት በስፔን ትልቅ ክብር የሚሰጠውን‹ፕሪንስ
ኦስተሪዬስ አዋርድስ ፎር ስፖርትስ› ተቀብሏል፡፡ ሽልማቱ በስፖርት የሰው ልጅን የላቀ ብቃት እና ችሎታ ያሳደገ
አትሌት በመባል ከስፔን ንጉሳውያን ቤተሰብ እጅ የተረከበው ነው፡፡ ኃይሌ በወቅቱ ይህን ሽልማት የወሰደው ከታዋቂው
ኳስ ተጨዋች ራውል ጎንዛሌዝ ጋር በመፎካከር ነበር፡፡ ‹ፕሪንስ ኦስተሪዬስ አዋርድስ ፎር ስፖርትስ› የተባለው
የክብር ሽልማት በጆኖ ሚር የተባለ ቀራፂ የተሰራ ቅርፅ፤50ሺዩሮ፤ ዲፕሎማና የሽልማቱ አዘጋጅ ፋውንዴሽን አርማ
የተቀረፀበት ስጦታን የሚያካትት ነው፡፡
No comments:
Post a Comment