Tuesday, July 30, 2013

“የፊልም ኢንዱስትሪው ወደፊትም ወደኋላም እየተጐተተ ነው”

ላለፉት 15 አመታት በፊልም ሙያ ላይ የተሰማራው ቴዎድሮስ ተሾመ፤ በፊልም ፅሁፍ ደራሲነት፣ በተዋናይነት፣ በዳሬክተርነትና በፕሮዲዩሰርነትም ሰርቷል፡፡ በሙያ ዘመኑ አምስት ፊልሞችን ሰርቶ ለእይታ ያበቃው አርቲስቱ፤ ስድስተኛውን ፊልሙን “ሦስት ማዕዘን” በሚል ርዕስ የሰራ ሲሆን የነገ ሳምንት ሐምሌ 21 ያስመርቃል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ መልካሙ ተክሌ በአዲሱ ፊልሙ ላይ በማተኮር ከአርቲስት ቴዎድሮስ ጋር ያደረገውን ቃለምልልስ እነሆ፡፡

“ቀይ ስህተት” የተሰኘው ፊልምህ ሲወጣ የቀይ ሽብር ሰማእታት ታሰቡ፡፡ “አባይ ወይስ ቬጋስ” ሲታይ አባይን መገደብ ተጀመረ፡፡ አሁን ደግሞ የስደተኞች ጉዳይ ትኩረት ሲይዝ በስደት ዙርያ የሚያጠነጥነው “ሦስት ማእዘን” የተሰኘ ፊልምህ ሊወጣ ነው፡፡ ፊልሞችህ ወቅት ተኮር ሆኑሳ?
የ“ሦስት ማእዘን” ቀረፃ ያለቀው ከአንድ ዓመት በፊት ነው፡፡ የተፃፈው ከሦስት ዓመት በፊት ነው፡፡ በተለይ በሙያው ውስጥ ያሉ እንደዚህ ሊያስወሩ ይችላሉ፡፡ በትግል የማትጥለውን ሰው ለመጣል እንዲህ አይነት ስትራተጂ ትቀይሳለህ፡፡ የዚህን ፊልም ማስታወቂያ ከጀመርን አስራ አንድ ወር ሆኖናል፡፡ የሕገወጥ ስደት ወሬ ሰፊ ሽፋን ማግኘት የጀመረው ከስድስት ወር ወዲህ ነው፡፡ “አባይ ወይስ ቬጋስ” ፕሮጀክት ሁለት ዓመት ፈጅቷል፡፡ ይኼ ፊልም መታየት ከጀመረ በኋላ ነው የግድቡ አዋጅ የታወጀው፡፡ “አበድኩልሽ” ከሚል የገበያ ሥራ ስታልፍ ችግሮች ቀድመው ሊታዩህ ይችላሉ፡፡
“ሦስት ማእዘን”ን በልደትህ ቀን ለገና ለማስመረቅ አስበህ እንደነበር ሰምቻለሁ፡፡ ለምን እስካሁን ዘገየህ?
ፊልሙ አልደረሰልኝም፡፡ ፊልሙን በልደቴ ቀን ለማስመረቅ አስቤ ነበር፡፡ ይኼ መረጃ እንዴት እንደደረሰህ አላውቅም፡፡
ማትያስ ሹበርት የፊልሙ የፎቶግራፊ ዳይሬክተር እንደሆነ ተገልጿል፡፡ አንዳንድ ወገኖች ግን ባለሙያው ሙሉ ቀረፃውን እንዳልሰራ ይናገራሉ፡፡
ዘጠና ዘጠኝ በመቶውን ቀረፃ የሰራው እሱ ነው፡፡ እዚህ የቆየው ለስልሳ ቀናት ነው፡፡ ቀረፃው በሰባ አምስት ቀናት ተጠናቀቀ፡፡ እሱ ከሄደ በኋላ አስራአምስት ቀን ሙሉ ተቀረፀ ማለት አይደለም፡፡ ከሱ መሄድ በኋላ የሦስት ቀን ቀረፃ ብቻ ነው የነበረው፡፡

ፊልሙን በውጭ ሀገር ፊልም ዘርፍ ለኦስካር ሽልማት እንዲታጭ ለማድረግ አስባችኋል፡፡ ከምን ተነስታችሁ ነው?
ሥራችን ለኦስካር ይመጥናል ብለን ስለምናስብ ነው፡፡ ካሁን በፊት የሰራኋቸው ፊልሞች እዚህ ውድድር ውስጥ አልገቡም፡፡ የኦስካር ፈተና ከባድ ነው፡፡ ውጤቱን አብረን እናያለን፡፡ የእኛ መዝገበ ቃላት ሁልጊዜ “አይቻልም” የሚል ነው፡፡ አይቻልም ስለሆነ ሁሌም አንችልም፡፡ “ሦስት ማእዘን” ግን ይችላል ብለን እናስባለን፡፡ ስለዚህ የሚከፈለውን መስዋእትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን፡፡ ኦስካር መግባታችን ግን ከማትያስ ሹበርት ጋር አይገናኝም፡፡
ሀገር ውስጥ ፍጆታ በተሰራ ፊልም ለዓለም አቀፍ ሽልማት መታጨት ይቻላል?
የሚያጨው ሌላ አካል ነው፡፡ እኛ እንደማንኛውም ተወዳዳሪ እንወዳደራለን፡፡ ስራችንን ለውድድር አቅርበን ዘመቻ እናደርጋለን፡፡ ይህ ራሳችንንና ፊልሙን ለማሳደግ ያለን ፍላጐት አካል ነው፡፡ እኛ ብቻ ሳንሆን የሀገራችን የፊልም ኢንዱስትሪ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆን ሙከራ እናደርጋለን፡፡
በፊልሙ ውስጥ ለተሳተፈ ለእያንዳንዱ የውጪ አገር ዜጋ ተዋናይ 40ሺ ዶላር ከፍለሃል ተብሏል…
ውሸት ነው፡፡ በነፃም አልሠሩም፣ የተጠቀሰውን ያህል ገንዘብም አልተከፈላቸውም፡፡
“ሦስት ማእዘን” ከሌሎቹ ፊልሞችህ በተለየ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መቀረፁን ፊልሙን ለጋዜጠኞች ባሳየህ ወቅት ተናግረሃል፡፡ እስቲ ስለእሱ አብራራልኝ…
በ49 ሴ.ግሬድ ሙቀት በበረሀ መቀረፁ ይመስለኛል፡፡ እያንዳንዱ ፊልም የራሱ ተግዳሮት አለው፡፡ የባለሙያ፣ የበጀት…ችግር አለ፡፡ ይኼን የተለየ የሚያደርገው በረሃው ነው፡፡ ከቤት ውጭ ነው የተቀረፀው፡፡ የውሃ ጥሙ ስቃይ ነው፡፡ ቀዝቃዛ ውሃ አፍ ከመድረሱ በፊት ይሞቃል፡፡ በእርግጥ ሁላችንም ተሰዳጅ ሆነንበታል፡፡ ሌላው ደግሞ ውጭ ሀገር ሲቀረጽ የገጠመን የውጭ ምንዛሬ ችግር እና የቋንቋ መሠናክል ነው፡፡
ወደ ፊልም ሙያ በገባህበት የጀማሪነት ጊዜህ ታዋቂው የፊልም ባለሙያ ሚሼል ፓፓታኪስ ያመቻቹልህን የውጭ ሀገር የትምህርት እድል ሳትጠቀምበት እንደቀረህ ሰምቻለሁ፡፡ ለምን ይሆን?
ከጀመርን የባህል ተቋም ጋር በመሆን ጋና እንድሄድ ነበር የታሰበው፡፡ አጋጣሚው ጥሩ ነበር፡፡ ግን በዚያ ሰዓት ለአራት ዓመት እዚያ ሄጄ ቢሆን ኖሮ አሁን ላለሁበት ደረጃ አልደርስም ነበር፡፡ የራሴ ራእይ ነበረኝ፡፡ የአሁኑን ጊዜ ያለመ፡፡ የባህል ተቋም ኃላፊዋን ለአራት ዓመት ከምትልኪኝ የሦስት ወር ካለ ላኪኝ ብያት ነበር፡፡ እናቴ በህይወት ስላልነበረችና የቤተሰብ ሃላፊነት እኔ ላይ በመውደቁ፣ ለረዥም ጊዜ ውጭ ሀገር መቆየቱን እምቢ አልኩ፡፡ ወንድሞቼንና እህቶቼን ሜዳ ላይ በትኜ መሄድ አልችልም ነበር፡፡
ከዚያ በኋላስ የፊልም ትምህርት የመማር እድል ገጠመህ ወይስ በልምድ ብቻ ቀጠልክ?
ሎስ አንጀለስ የፊልም ትምህርት ቤት ተምሬአለሁ፡፡ ዲግሪዬን በሚቀጥለው ወር እወስዳለሁ፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ውጭ የነበርኩት ለዚህ ነው፡፡
በልጆችህ ላይ ወዳንተ ሙያ የመግባት አዝማሚያ አይተህባቸዋል?
ሦስተኛ ሴቷ ልጄ በተለይ ሙዚቃ ላይ ክንፍ ትላለች፡፡ ያልተለመደ ነገር አላት፤ አካሄዷን እናያለን፡፡ ልጆቼ ምርጫቸውን የሚወስኑት በራሳቸው ጊዜ እንጂ በእኔ ምርጫ አይደለም፡፡ ድራማ እና ፊልም ያያሉ፡፡
“ሦስት ማእዘን” ሲመረቅ መግቢያው 300 ብር መሆኑ “ራስን ማዋደድ ነው” ብለው የሚተቹ ወገኖች አሉ…
ይሄ በዛብን የሚሉ በሌላ የምርቃት ቦታ በመቶ ብር መግባት ይችላሉ፡፡ ከበዛ በሚቀጥለው ቀን በመደበኛ ዋጋ ይታያል፡፡ አምስት መቶ ብር እና አንድ ሺህ ብር ለማድረግም አስበን ይበዛል ብለን ነው የተውነው፡፡ የምርቃት ፕሮግራሙ ልዩ ሥነ ሥርአት ስላለው እኮ ነው፡፡
ለ15 ዓመታት በፊልም ኢንዱስትሪው ውስጥ እንደቆየ ባለሙያ የአገራችንን የፊልም እድገዘ እንዴት ትገመግመዋለህ?
የሁሉም ሀገር የፊልም ኢንዱስትሪ የራሱ ዝግመተ ለውጥ አለው፡፡ ይወለዳል፡፡ ይድሃል፡፡ ያድጋል፤ ትልቅ ኢንዱስትሪ ይሆናል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ እያለፍን ነው ያለነው፡፡ በዚህ ውስጥ የሚፈጠሩ ችግሮች የሁሉም ኢንዱስትሪ ገጽታዎች ናቸው፡፡ የሀገራችን የፊልም ኢንዱስትሪ ከሁለት አቅጣጫ እየተጐተተ ነው፡፡ የሚለፋ ሰዎች አሉ፡፡ ወደ ፊት ያራምዱታል፡፡ ወደ ፊት ሄደ ብለህ ስታስብ ደግሞ አሸር ባሸር የሚሰሩ ሰዎች አሉ፡፡ ወደ ኋላ ይጐትቱታል፡፡ ስለዚህ መሀል ላይ ተወጥሮ ነው ያለው - ወደ ፊትም ወደ ኋላም እየተጐተተ፡፡
የኢትዮጵያ የፊልም ኢንዱስትሪ የግሎባላይዜሽን ተፅእኖ ያሰጋዋል የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ አንተ ምን ትላለህ?
ኢንዱስትሪውን ኢንዱስትሪ ለማድረግ ሦስት ግብአቶች ያስፈልጋሉ፡- ተመልካች፤ ፕሮዲዩሰር እና አከፋፋይ፡፡ አከፋፋይ ሲኖር የጥራት ደረጃ ይመጣል፡፡ ይኼንን ደረጃ ለማምጣት ፕሮዲዩሰርም ተጠንቅቆ ይሰራል፡፡ ተመልካችም ጥራት ምን እንደሆነ ስለሚገባው ያንን መጠየቅ ይጀምራል፡፡ እኛው እንሰራለን፣ እኛው እናስተዋውቃለን፣ እኛው እናከፋፍላለን፡፡ “ሦስት ማእዘን” የራሱ ዓለም አቀፍ አከፋፋይ አለው፡፡
አሁን ሰዎች በፊልም ገቢ ብቻ መተዳደር ጀምረዋል፡፡ ስለዚህ ፊልም እንደ ኢንዱስትሪ ቆሟል ማለት ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠር ብር ለመንግስት ቀረጥ እየተከፈለበት ነው፡፡ የፊልሞች በዓለምአቀፍ የባህልና ቋንቋ ተጽእኖ ሥር መውደቅ እንደፊልም ሰሪዎቹ የአእምሮ ዝግጅት የሚወሰን ነው፡፡ ሁሉም ፊልም ግሎባላይዝድ ሆኗል ማለት ይከብዳል፡፡
ዘንድሮ ከወጡ የአማርኛ ፊልሞች መካከል የወደድከው አለ?
“የመጨረሻዋ ቀሚስ” ጥሩ ነው፡፡ “ኒሻን” የተለፋበት ቆንጆ ፊልም ነው፡፡ ኮሜዲ የሆነው “ኢምራን” ጥሩ ነው፡፡ “ሰምና ወርቅ” በጣም ቆንጆ ነው፡፡ ሁሉንም ፊልም አያለሁ፡፡ ግዴታም አለብኝ፤ በሲኒማ ቤቴ ምክንያት፡፡ ዘንድሮ የወጡትን ፊልሞች ሁሉ ለመዘርዘር ጊዜም የለንም፡፡ ልቤ ውስጥ የቀሩትን ፊልሞች ከሞላ ጐደል ጠቅሼልሃለሁ፡፡
ድርጅትህም ስምህም ከዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ጋር የተገናኘ ነው፡፡ ስለ ሴባስቶፖል መድፍ ፊልም ለመስራት አስበህ ታውቃለህ?
ሴባስስቶፖል ለኔ የመጀመርያው የቴክኖሎጂ ሙከራ ነው፡፡ መድፍ ነው፡፡ እኔ የምመራው የፊልም ድርጅት የእኔ መድፍ ነው፡፡ እስካሁን ስድስት ተኩሼበታለሁ፡፡ ሰባት፣ ስምንት፣ ዘጠኝ አስር እያልኩ እተኩሳለሁ፡፡ ታሪክን አጣቅሼ የራሴን አርማ ለማውጣት ከሴባስቶፖል የበለጠ የለም፡፡ አፄ ቴዎድሮስና ገብርዬ ያሉዋቸውን ታሪኮች ፊልም የማድረግ ህልም አለኝ፡፡ አንድ ቀን ይሰራል፤ ግን ጥናት ይፈልጋል፡፡
ከ”ሦስት ማእዘን” ቀጥሎ ምን እንጠብቅ?
“ሦስት ማእዘን” ቁጥር ሁለት ይከተላል፡፡ ቀረፃው ተጠናቋል፡፡ “ሦስት ማእዘን” ቁጥር ሦስትም አለ፡፡ ምንአልባት ይኸው ፊልም እስከ አስር ሊቀጥል ይችላል፡፡ መፅሔት ተፈራ የምትባል ልጅ ያመጣችው “ሀገር” የሚል የፊልም ፅሁፍም አለ፡፡ የሷን ቆንጆ ድርሰት እንደገና እያዋቀርኩት ነው፡፡ እሱን የመስራት እቅድ አለኝ፡፡ ዳግማዊ ፈይሳ የፃፈው “የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልጅ” የሚል ፅሁፍም በፕሮጀክት እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ ከዚያ “ግድብ” የሚል ሃሳብ አለኝ፡፡ ያስፈልጋል አያስፈልግም የሚለውን ግን እወስናለሁ፡፡
ለኢትዮጵያ ምን አደረግህላት፣ ኢትዮጵያስ ምን አደረገችልህ?
ኢትዮጵያ ወለደችኝ፤ አሳደገችኝ፡፡ እኔ ምን እንዳደረኩላት አላውቅም፡፡ ምክንያቱም የማደርገው ነገር በሙሉ ለመኖር፣ ለራሴ ደስታ ለማግኘት፣ ህይወት ጣፋጭ እንድትሆንና ልጆቼን ለማሳደግ በማደርገው ሩጫ ውስጥ የሚካተት ስለሆነ፣ ለኢትዮጵያ ይህን አደረግሁላት ልል አልችልም፡፡

No comments:

Post a Comment