በዓሉ የ«አዲስ ዘመን ጋዜጣ አዘጋጅ ሳለ፣ ከጋዜጠኞቹ አንዱ አስቸገረው፡፡ «ጥጋብ» የሚሉት ዓይነት ማስቸገር፡፡ አንድ ቀን የ«ዘመን» አባላት ሁሉ ተሰብስበው በዓሉ ስብሰባውን ይመራል፡፡ ወይም ለመምራት ይሞክራል እንበል፣ ያ ጋዜጠኛ አጉል እያቋረጠው፣ እንደመስደብም እንደ መዝለፍም እያደረገው አስቸገረው፡፡ በዓሉ በትዕግሥት እንደምንም ስብሰባውን ጨረሰ፡፡
ስብሰባውን ሲበትን ያን ጋዜጠኛ፣ «አንተ ቆይ፣ እማነጋግርህ አለኝ» አለው፤ ቆየ፡፡
በዓሉ ተነሥቶ በሩን ዘጋ፣ ቆለፈው፡፡ ኮቱን አወለቀ፡፡ እና ጋዜጠኛውን በጥፊና በቦክስ አነጋገረው፡፡ ደብድቦት ሲያበቃ በሩን ከፈተለት፡፡ ጋዜጠኛው ወጣ፡፡ ከዚያ በኋላ ማስቸገሩን ትቶ የበዐሉ ዋና ወዳጅ ሆነ፡፡
እንደ ተራ አለቃ ቢሆን ኖሮ ግን በዐሉ ያንን ጋዜጠኛ የሚነቅፍ፣ የሚዘልፍ እና ከደሞዙ ላይ የሚቆርጥ ደብዳቤ ይጽፍለትና፣ ያ ደብዳቤ የሰውየውን ፋይል ይበክለውና፣ ሁልጊዜ የሚከተለው ጥቁር ነጥብ ይጥልበት፣ ለወደፊት እድገቱ እንቅፋት ይሆንበት ነበር፡፡ ይህንንም ተገንዝቦ ነው ያ ሰውዬ ለበዐሉ አድናቆት ያደረበት፡፡
ከስብሐት ገብረእግዚአብሔር
ካቲት መጽሔት
ታኀሳስ፣ 1984 ዐ.ም
No comments:
Post a Comment