Wednesday, June 26, 2013

የኢትዮጵያ የሙዚቃ ሸክላ 100ኛ ዓመት በዓል ለምን እንዲቋረጥ ተደረገ?





 መታሰቢያ ካሳዬ
የኢትዮጵያ የሙዚቃ ሸክላ 100 ዓመት በዓል ለምን እንዲቋረጥ ተደረገ?
በአውሮፓ የሚቸበቸበው የነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ሲዲ በአገር ውስጥ ገበያ ላይ የለም
ብትይኝ መጣሁ ብመጣ አንቺ የለሽ፣
ያመትባል ቤተስኪያን ሆኖ ቆየኝ ደጅሽ፡፡
ያመትባል ቤተስኪያን ሆኖ ቢቆይ ደጄ፣
ቆመህ አስቆርበህ ስመህ ሂድ ወዳጄ፡፡
 

ድምፃቸውን በሸክላ ለማስቀረፅ በአገራችን የመጀመሪያው የሆኑት የነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ግጥም ለዚህ ፅሁፍ መነሻ የሆነበት ምክንያት፣ 100 ዓመታትን ያስቆጠረው የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ሸክላ አስመልክቶ የተዘጋጀው በዓል ለምን ተቋረጠ
የሚለውን ጉዳይ ለማንሳት ነው፡፡ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ የመጀመሪያው ሸክላ በነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ተዚሞ፣ .. 1910 . በጀርመን አገር የተቀረፀው ሸክላ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ዘለሰኛና መዲና ዘፈኖች በአስራ ሰባት አይነት ስልት በመጫወት ድምፃቸውን በዲስክ ለማስቀረፅ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ የሆኑት ነጋድራስ ተሰማ፣ በዘፈኖቻቸው የአገርና የባንዲራ ፍቅርን፣የተቃራኒ ፆታን ፍቅር ፣ስልጣንን፣ጀግንነትን አውድሰውበታል፡፡ ነጋድራስ ተሰማ፣ የመኪና ሹፍርናና የመካኒክነት ሙያን እንዲሰለጥኑ በአፄ ምኒልክ ተመርጠው ወደ ጀርመን አገር በተላኩ ጊዜ ከተላኩበት ሙያ ውጪ በስዕል፣ በቅርፃ ቅርፅና በሙዚቃ ሙያ በርካታ ስራዎችን ሲሰሩ ቆይተው ወደ አገራቸው ተመልሰዋል፡፡ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ቀራፂ፣ ፎቶግራፈር፣ አዝማሪ፣ ባለቅኔ፣ ሰዓሊ፣ የፖለቲካ ሰው፣ ነጋዴና የመኪና ጠጋኝና ሹፌር የሆኑት ነጋድራስ ተሰማ፣
በዘመናቸው በርካታ አዳዲስ ነገሮችን ለመጀመር ከፍተኛ ፍላጎትና ጉጉት የነበራቸው ሰው ነበሩ፡፡ ከዘፈን ችሎታቸው በተጨማሪ የተለያዩ ስዕሎችንና ቅርፃቅርፆችን በመስራት ለአዳዲስ ሙያዎች ፈር ቀዳጅ እንደሆኑም ይነገራል፡፡ ሃሳባቸውን በነፃነት ለመግለፅና ፊት ለፊት ለመጋፈጥ ደፋር ነበሩ የሚባሉት ነጋድራስ ተሰማ፣ የቅርፃ ቅርፅ ስራዎች፣ ስዕሎችና ዘፈን ከቤተክርስቲያን ውጪ ሀጢያትና ክፉ ስራ እንደሆነ ይታመን በነበረበት በዚያ ዘመን፣ የፍቅረኛቸውን ምስል በቅርፅ ሠርተውና የተለያዩ የፍቅር ዜማዎችን በማዜም ዘመናቸውን የቀደሙና ሃሳባቸውን በነፃነት ለመግለፅ የደፈሩ ሰው ናቸው፡፡
እነዚህን ከአንድ መቶ አምስት አመት በፊት በሸክላ ተቀርፀው የወጡትን የነጋድራስ ተሰማ እሸቴ የዘፈን ሥራዎች ለማግኘትና በቅርስነት ለመጪው ትውልድ እንዲተላለፉ ለማድረግ፣ የነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ልጅ የነበሩት ታዋቂው የስፖርት ሰው አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ለአመታት ደክመው ሊሣካላቸው ባይችልም አደራውን ለልጃቸው ለአቶ ታደለ ይድነቃቸው አውርሰው
አልፈዋል፡፡ አቶ ታደለም እነዚህን ጥንታዊ የሙዚቃ ሸክላዎች ለማግኘትና በቅርስነት እንዲያዙ ለማድረግ አመታትን የፈጀ ድካምና ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ጥናት ኢንስቲትዩት ወዳጆች ማህበር፣ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪክ ላይ ባዘጋጁት አንድ ፕሮግራም በክብር እንግድነት የተጋበዙት አቶታደለ ይድነቃቸው፣ ስለ መጀመሪያዎቹ የኢትዮጵያ ሸክላዎች በመናገር ዘፈኖቹን ለታዳሚዎቹ አሰሙ፡፡ ይህ ጉዳይ የመሰጣቸው የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት፣ ለጀርመኑ የማይንዝ ዩኒቨርሲቲ የሙዚቃ ታሪክ ተመራማሪ ለዶክተር ዎልፍ ጋንግ ቤንዳር በማሳወቅ የዲስኮቹ ፍለጋ
ተጀመረ፡፡ ፍለጋው ተሣክቶም 1994 . 16 አልበሞችን የያዘ ሸክላ በኢትዮጵያ ጥናት ኢንስቲትዩት ዕቃ ማከማቻ መጋዘን ውስጥ ተገኘ፡፡ በዕድሜ ብዛትና በግዴለሽ አያያዝ የተጐዱትን ዲስኮች በመጠገን እንደገና እንዲቀረፁ ለማድረግ
ዶክተር ዎልፍ ጋንግ ቤንደር፣ አቶ ተሾመ ደስታ ተባሉትን ሰው የቀጠሩ ሲሆን ዲስኮቹም ለመጀመሪያ ጊዜ .. ፌብሪዋሪ 2002 . ተቀረፁ፡፡ ይህ ቀረፃ ከተጠናቀቀ በኋላ አቶ ታደለ ድምፁ ጥራት እንዲኖረው በማሰብ ከአቶ ተሾመ ጋር
በድጋሚ እንዲቀረፅ አደረጉት፡፡ የኢትዮጵያን የጥንት ሙዚቃዎችና ዜማዎች በዘመናዊ ዘዴ በማስቀረፅ ዕውቅና ያላቸው
ፈረንሳዊው የሙዚቃ ሰው ሚስተር ፍራንሲስ ፋልሴቶ፣ .. 2007 . በጃንዋሪ 2007 . ዲስኮቹን አስቀርፀው ለማሣተምና በአገር ውስጥም ሆነ በውጪ አገራት ለማሰራጨት ፍላጐት በማሳየታቸው በጉዳዩ ዙሪያ ከአቶ ታደለ
ይድነቃቸው ጋር ይነጋገራሉ፡፡ አቶ ታደለም በጉዳዩ ይስሙማና በቅጂ መብትና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ስምምነት አድርገው ተጨማሪ የታሪክ ሰነዶችንና ፎቶግራፎችን ለሚስተር ፍራንሲስ ይሰጧቸዋል፡፡ ለሥራው የሚሆን የገንዘብ ድጋፍም ከዩኔስኮ ተገኝቶ የፈረንሳይ ኤምባሲ፣ ገተ ኢንስቲትዩት እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ባደረጉት ትብብር ሥራው ተሠርቶ ይጠናቀቃል፡፡ የምረቃ ፕሮግራም ወጥቶ የምረቃ ጥሪ ወረቀቶች ከተበተኑ በኋላ ፕሮግራሙ እንዲሰረዝ በመደረጉ፣ ታሪካዊ ሲዲ ምረቃው እንዳይካሄድና በአገር ውስጥም እንዳይሰራጭ ሆነ፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ታሪካዊ
ሲዲዎች በተለያዩ የአውሮፓ አገራት በገበያ ላይ ቀርበው እየተቸበቸቡ ይገኛሉ፡፡ ታሪካዊ ዲስኮቹ የታሪካዊነታቸውና የቅርስነታቸው ባለቤት በሆነች አገር ውስጥ እንዳይሰራጭ ተደርገው፣ በውጭ አገራት እንደተራ የሙዚቃ ሲዲ እንዲቸበቸቡ
የሆነበት ምክንያት ምንድነው የሚለውን ጥያቄ ለጉዳዩ ባለቤት ለአቶ ታደለ ይድነቃቸው አቅርበንላቸው ነበር ... 2007 . ሚስተር ፍራንሲስ ፋልሴቶ ዲስኮቹን ለማሳተም ሲጠይቀኝ ፍቃደኝነቴን የገለፅኩለት በደስታ ነበር፡፡ የነጋድራስ
ተሰማ ቤተሰቦች ምንም አይነት የገንዘብ ጥቅም እንደማይፈልጉ፣ ሥራዎቹ ግን የኢትዮጵያ ህዝብ ንብረትና ቅርሶች በመሆናቸው የእኔ ነው ማለት እንደማይችል ተነጋግረንና ተስማምተን በህጋዊ ሠነዶች ላይም ይህንኑ ገልፆና ፈርሞ መረጃዎችንና ሠነዶችን ሰጠሁት፡፡ ሠነዶቹን ከወሰደ በኋላ፣ ከዩኔስኮ የገንዘብ ድጋፍ አግኝቶ ሥራውን ሠርቶ አጠናቀቀ፡፡ ሲዲውን ለማስመረቅና ወዲያውም የመጀመሪያውን ኢትዮጵያዊ ሸክላ አንድ መቶኛ አመት ለማክበር ፕሮግራም ለማዘጋጀት ማሰቡን ሲነግረኝ ሲዲውን እንዲልክልኝና እንዳየው ጠየቅሁት፡፡ ሲዲውን ሲልከው በጀርባው ላይ የቅጂ መብቱንና የባለቤትነት መብቱን የራሱ አድርጐ አሣትሞታል፡፡ በሁኔታው አዝኜ የሠራኸው ሥራ ከውልና ከስምምነታችን ውጪ በመሆኑ፣ የቅጂና የባለቤትነት መብቱን በአስቸኳይ አንሣ ብዬ ፃፍኩለት፡፡ ይቅርታ ጠይቆኝ እንዳነሣው ገልፆ በድጋሚ ላከልኝ፡፡ ሣየው በጀርባው ላይ ያለው ነገር ተነስቷል፡፡ ደስ ብሎኝ ፕሮግራሙ እንዲቀጥል ነገርኩት፡፡ ፕሮግራሙ በጐተ ኢንስቲትዩት
እንዲሆን ተስማምተን በምረቃው ላይ መገኘት ይገባቸዋል ለተባሉ ሰዎች የጥሪ ወረቀት እንዲደርስ ተደረገ፡፡ እኔም በፕሮግራሙ ላይ በክብር እንግድነት እንድገኝና ንግግር እንዳደርግ ተጋበዝኩ፡፡ እሺ ብዬ በዕለቱ የማደርገውን ንግግር ለማዘጋጀት ማጣቀሻ የሚሆን መረጃ ፈልጌ ሲዲውን ስከፍተው፣ የሲዲው የቅጂ መብትና ሙሉ ባለቤትነቱ የቡድሃ ሚዩዚክ
መሆኑን የሚገልፅ ፅሁፍ በሲዲው ላይ በግልፅ ተፅፏል፡፡ ሲዲውን ከቡድሃ ሚዩዚክ ፍቃድ ውጪ ማንም ሰው ማሣተም፣ ለህዝብ ማሠማት አይችልም ይላል፡፡ ምን ማለት ነው? ንብረቱ እኮ የኢትዮጽያ ህዝብ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት እኔ በፕሮግራሙ ላይ እንደማልገኝ አሣወቅሁኝ፡፡ በጉዳዩ የፈረንሳዩ አምባሳደርና ሌሎች ሰዎች ገብተው ሊያነጋግሩን ሞክረው ነበር፡፡ እኔ የቅጂ መብቱን በማንኛውም መልኩ በየትኛውም ስም አላስመዘገብኩትም ብሎ ከፈረመልኝ ምረቃው ሊቀጥል ይችላል አልኩ፡፡ ሚስተር ፍራንሲስ ግን ለዚህ ፈቃደኛ አልነበረም፡፡ ይህ ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ በኢትዮጵያ የሙዚቃ
ሥራዎች ላይ ጥናት የሚያደርጉትን ተመራማሪዎች በነፃነት እንዳይሰሩ የሚያደርጋቸውና ምርምራቸውን ለማቆ የሚያስገድዳቸው ጉዳይ ነውና እኔ በዚህ ፈፅሞ ልስማማ አልችልም፡፡ ከሚስተር ፍራንሲስ ጋር በተደጋጋሚ የተነጋገርን ቢሆንም ልንስማማ
አልቻልንም፡፡ በአውሮፓ የተለያዩ አገራት ስዘዋወር ሲዲዎቹ እንደማንኛውም ተራ ሲዲ በየሙዚቃቤቶቹ መደርደሪያ ላይ ተደርድረው እየተሸጡ ነው፡፡ ይህ በጣም የሚያሣዝን ተግባር ነው፡፡ ሥራዎቹ እኮ ቅርስ ናቸው፡፡ እኔ አሁን ሥራዎቹን
በስሜ ለማሣተምና የቅጂ መብቱን ወስጄ ለሌሎች በሥራዎቹ ላይ ጥናትና ምርምር ለሚያደርጉ ሁሉ በነፃ ለመስጠት ወስኛለሁ፡፡ የእኔ ፍላጐት ጥናቱ እንዲቀጥል ነው፡፡ ሸክላዎቹ የአገር ቅርስ ናቸውና፡፡ ሚስተር ፍራንሲስ ፋልሴቶ እነዚህን ሲዲዎች በሌላ ሰው (ድርጅት) የቅጂ ባለቤትነት መብት ለማስመዝገብ ምን መብት አላቸው? ከውልና ከስምምነቱ ውጪስ ለመሥራት ለምን ተነሳሱ
የሚሉና ሌሎች ጥያቄዎችን ለመጠየቅ ሚስተር ፍራንሲስ ፋልሴቶን ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ በአገር ውስጥ የሉምበሚል ምክንያት ሳይሳካልን ቀርቷል፡፡ ሚስተር ፍራንሲስ ምላሻቸውን በሰጡን ጊዜ ልናስተናግዳቸው ዝግጁ መሆናችንን
በዚሁ አጋጣሚ ለመግለፅ እንወዳለን፡

No comments:

Post a Comment