Monday, June 24, 2013

ኔልሰን ማንዴላ እየተጠበቁ ነው

ቪኦኤ ዜና

የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ኔልሰን ማንዴላ ጤና እጅግ አሳሳቢ በሆነ ሁኔታ መዳከሙን የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ፅሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡



የፀረ-አፓርታይድ ትግሉ አውራና ባለገድል፣ የዓለም የኖቤል የሰላም ሽልማት ባለቤት ኔልሰን ማንዴላ በሳምባ ሕመም ምክንያት ወደ ፕሪቶሪያ ሆስፒታል ከተወሰዱ ሁለት ሣምንት አልፏቸዋል፡፡

የማንዴላ ጤንነት ባለፉት ሃያ አራት ሰዓታት ውስጥ እጅግ እየተበላሽ መሆኑን የፕሬዚዳንቱ ቢሮያሣወቀ ሲሆን የሃገሪቱ ፕሬዚዳንት ጃከብ ዙማ እና የገዥው ፓርቲ የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ ምክትል ሊቀመንበር ሲሪል ራማፎሣ ማንዴላን ዛሬ ዕሁድ፣ ሰኔ 16/2005 ዓ.ም ምሽት ላይ የተኙበት ሄደው ጎብኝተዋቸዋል፡፡

ኔልሰን ማንዴላ ሚስተር ማንዴላ ለመርዳት ሃኪሞቹ የተቻላቸውን ሁሉ እያደረጉ ናቸው
ሲሉ ፕሬዚዳንት ዙማ ማምሻውን መግለጫ የሰጡ ሲሆን ሃኪሞቹ ለማዲባ ተገቢውን ክትትል እያደረጉላቸው መሆኑንና አሁን ተመቻችተው የሚገኙ መሆኑን እንዳረጋገጡላቸው ተናግረዋል፡፡


የማንዴላ ጤና ሁኔታ ከባድ ቢሆንም ለጊዜው አጣዳፊ አስጊነት የለውም ሲል የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ከትናንት በስተያ መግለጫ አውጥቶ እንደነበር ይታወሣል፡፡

የ94 ዓመት ዕድሜ አዛውንቱ ሚስተር ማንዴላ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ለአጣዳፊና የቅርብ ክትትል ወደ ሆስፒታል ሲወሰዱ ላለፉት አሥራ አምስት ቀናት የተኙበት የአሁኑ ለአራተኛ ጊዜ መሆኑ ነው፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በነገው ሣምንት ውስጥ በአፍሪካ በሚያደርጉት ጉብኝት ከሚረግጧቸው ሃገሮች አንዷ ደቡብ አፍሪካ እንደሆነች ይታወቃል፡፡

የማንዴላን ጤንነት አስመልክቶ ዋይት ሃውስ ጉዳዩን በቅርብ እየተከታተለ መሆኑን አመልክቶ “ሃሣባችንና ፀሎታችን ከእርሣቸው፣ ከቤተሰቦቻቸውና ከደቡብ አፍሪካ ሕዝብ ጋር ነው” ብሏል፡፡

No comments:

Post a Comment