ሪፖርተር
አበበ መለሰ እንደሚታወቀው በኢትዮጵያ የሙዚቃ ዕድገት ፈር ቀዳጅ የሆነና ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረገ ድንቅ የሙዚቃ ሰው ነው፡፡ ይኼም በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ሥፍራን እንዲይዝ አድርጐታል፡፡ ለአሠርት ዓመታትም ሕዝቡ ከሚያደንቃቸው ሙዚቀኞች ጀርባ ሆኖ የተለያዩ ግጥሞችንና ዜማዎችንም አበርክቷል፡፡ ከነዚህም ውስጥ ጥላሁን ገሰሰ፣ ማህሙድ አህመድ፣ ፀሐዬ ዮሐንስ፣ መሉቀን መለሰ፣ ንዋይ ደበበ፣ ሐመልማል አባተና የመሳሰሉት አርቲስቶችን ይጠቀሳሉ፡፡
ይኼ ስመጥር አርቲስት በማኅበረሰቡ ዘንድ መታወስ የሚችሉ ሥራዎችን ቢሠራም በገጠመው የኩላሊት ችግር ምክንያት ከሚወደው ሙያው ተነጥሏል፡፡ ይኼንንም በማየት የሙያ አጋሮች ውለታ የተሰኘ ኮንሰርት ያካሄዱለት፡፡
ባህር ዳር ተወልዶ ያደገው አበበ መለሰ፣ በሕፃንቱ ነው ግጥም መጻፍ የጀመረው፡፡ ዜማዎቹ አምባሳልን፣ ትዝታን አንቺ ሆዬ፣ ባቲን፣ ያካተቱ ናቸው፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት ጀምሮ በዚህ ችግር እየተሰቃየ ሲሆን፣ በእስራኤልም ሕክምናውን እያደረገ ነው፡፡ ሕክምናው የኩላሊት ዲያሊስስን ያካተተ ሲሆን፣ ዘላቂ መፍትሔ ሊያገኝ አልቻለም፡፡ ይኼንንም በማየት ከአሥር በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ኩላሊት ለመስጠትም ፈቃደኛነታቸውን አሳይተዋል፡፡
ነገር ግን ኩላሊት የመቀየር ሒደት በጣም ውድ በመሆኑ የተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅቶች እየተደረገለት ነው፡፡
ሁለቱም ኩላሊቱ መቀየር እንዲችልና በሙሉ ጤንነት እንዲመለስ የሙዚቃው ዝግጅት ስመ ጥርና ዝነኛ አርቲስቶችን በማካተት ተካሂዷል፡፡
በዚህ የሙዚቃ ዝግጅት ሥራቸውን ያቀረቡ አርቲስቶች ቴዲ አፍሮ፣ ማዲንጐ አፈወርቅ፣ ፀሐዬ ዮሐንስ፣ ፀጋዬ እሸቱ፣ ኃይልዬ ታደሰ፣ አስቴር ከበደ፣ ሐመልማል አባተ፣ ዳዊት መለሰ፣ ኢዮብ መኮንን፣ ይሁኔ በላይና ግርማ ተፈራ ተሳትፈውበታል፡፡
ቅዳሜ ‹‹ውለታ›› የሚለውን ኮንሰርት ለማየት የታደመው ተመልካች 3,000 አካባቢ የሚደርስ ሲሆን፣ በተለያዩ የዕድሜ ክልል ያሉ ታዳሚዎች የተስተዋሉበት ነው፡፡ በዕለቱ በላፍቶ ብሥራተ ገብርኤል አጠገብ በሚገኘው ላፍቶ ሞል ተመልካች የታደመው ከቀኑ 12 ሰዓት ጀምሮ ነበር፡፡ አርቲስቶቹ ሙዚቃዎቻቸው ያቀረቡት ከምሽቱ 3፡15 ሰዓት ጀምሮ ሲሆን፣ በራስ ባንድ አጃቢነት የመጀመርያ የመክፈቻ ሥራ የሠራው ማዲንጐ አፈወርቅ ነበር፡፡ በዕለቱ ምሽቱን ያደመቀው ሁኔታ በጣም ብዙ አድማጭ አላቸው የሚባሉ አርቲስቶች ዝግጅታቸውን ማቅረባቸው፣ አንድ ላይ ሆነውም እንደዚህ ዓይነት ለጥሩ ነገር መሳተፋቸው አድናቂዎቻቸውን ያስፈነደቀ ነው፡፡
ውለታ በሚለው ዝግጅት አንጋፋ ሙዚቀኞች መካከል የተመልካችን ቀልብ ገዝተው ከነበሩት መካከል ፀጋዬ እሸቱ፣ ፀሐዬ ዮሐንስና አስቴር ከበደ ከተመልካቹ ሞቅ ያለ አቀባበል ተደርጐላቸዋል፡፡ በተለይም ከሙዚቃው መድረክ ራቅ ያለችው አስቴር ከበደ ወደ አገር ቤት ከተመለሰች በኋላ ያደረገችው የሙዚቃ ዝግጅት ሲሆን፣ አሁንም የሙዚቃ ተሰጥኦ እንዳላት ያሳየችበት ምሽት ሆኗል፡፡
ሪፖርተር ካነጋገራቸው ተመልካቾች መካከል በ20ኛ ዕድሜዋ ላይ የምትገኘው ዮርዳኖስ ተክሌ እንዳለችው፣ ‹‹የሚገርመው እኔ አበበ መለሰን በግል አይቼው ሁሉ አላውቅም፡፡ ነገር ግን ከተለያዩ ሚዲያዎች ስለ እሱ መታመምና ሥራዎቹን ሲያቀርቡ ሳይ በጣም ተገርሜ ይህን ሰው ለመርዳት በግል የተቻለኝን ለማድረግ ነው ወደዚህ ኮንሰርት የመጣሁት፡፡ ብዙውን ጊዜ እንደዚህ ዓይነት ቦታ መምጣት ብዙም አልወድም፡፡ ነገር ግን የአበበን ሥራዎች ስለሰማሁና ውስጤ በጣም ስለተነካ የተቻለኝን ለማድረግ ነው የመጣሁት፤››፡፡
በመቀጠል ሪፖርተር ካነጋገራቸው ተመልካች መካከል አቶ አንተነህ ፋንታ በ45 ዕድሜ ክልል የሚገኙ ሲሆን፣ ‹‹ይህ በጣም በረጅም ጊዜ ልንጠየቀው የምንችለው የዕርዳታ ጥሪ ነው፡፡ በዚህም መሠረት አበበን ለመርዳት በጣም ትንሿ ነገር ነው ያደረግኩት ብዬ እላለሁ፡፡›› ምክንያቱም ይላሉ አቶ አንተነህ፣ ‹‹አሁን ከምታያት ከባለቤቴ ጋር ቢያንስ ለ20 ዓመት አብረን በፍቅር ኖረናል፡፡ በእያንዳንዱ የፍቅር መጀመርያ ዓመታት ላይ የአበበ መለሰ የሚገርም ሥራዎች በነዚህ የፍቅር ዕድሜ አንጓ ውስጥ ትልቁን ሥፍራ ይይዛሉ፡፡ አቤ በጣም ድንቅ ነው፡፡ መተኪያ ሊኖረው የማይችል ቢኖረውም የሱን ያህል ዘፈን ሊሠራ የሚችል ሰው ይኖራል ብዬ አልገምትም፡፡››
የኮንሰርቱ ማስታወቂያ ላይ ስማቸው ካልነበረ አርቲስቶች መካከል ኢዮብ መኮንንና ይሁኔ በላይ ዝግጅታቸውን ያቀረቡ ሲሆን፣ ለአበበ ያላቸውን ስሜት ለመግለጽ እንደተገኙ በዝግጅቱ አስተዋዋቂ ተገልጿል፡፡
በአዲካ ኮሙዩኒኬሽንና ኢቨንትስና በኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማኅበር ጥምረት የተዘጋጀው ይኼው ኮንሰርት፣ የተለያዩ አስተዋጽኦ ያደረጉ ድርጅቶችና ሚዲያዎች በዕለቱ ሽልማት ተቀብለዋል፡፡ በዚሁ ሥነ ሥርዓት ሽልማቱን የሰጡት አቶ ዳዊት ይፍሩ የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማኅበር ፕሬዚዳንትና የሮሃ ባንድ አባል እንዲሁም የአበበ መለሰ ልጅ ዳግም አበበ ሽልማቱን ለተሸላሚዎች ሰጥተዋል፡፡
ላፍቶ ሞል ለዚህ ዝግጅት ቦታ በመስጠት እንደተባበራቸው በዕለቱም ተገልጿል፡፡ ላፍቶ ከዚህ በፊት ኮንሰርት በማዘጋጀት የሚታወቅ በዕለቱ ተመልካቹን ከዝናብ ለመታደግ የቻለ ቢሆንም፣ ቦታው ላይ የሚገኘው የውኃ መዋኛ ሥፍራ ግን ውኃው እንደተሞላ ክፍት በመሆኑ ለአደጋ በሚያጋልጥ መልኩ መተዉን ግን ታዝበናል፡፡
ኮንሰርቱ ማጠቃለያውን ያደረገው ከሌሊቱ 8፡00 ሰዓት በቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ‹‹ጥቁር ሰው›› ዘፈን ሲሆን፣ በጣም በደማቅ ሁኔታ ተመልካቹንም ያዝናና ነበር፡፡ ምን ያህል ገቢ እንደተገኘ ባይገለጽም በዚህ የሙዚቃ ዝግጅት ሁለት ሚሊዮን ብር ለማሰባሰብ ታቅዶ ነበር፡፡ ከኮንሰርቱ በተጨማሪ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አካውንት የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅትም እየተካሄደ ነው፡፡
http://www.ethiopianreporter.com
No comments:
Post a Comment