ኩርማን መግቢያ
እግዜር ከሞላው ኩሬ ውስጥ ፣ እስቲ እንዋኝ ብለን ገብተን
ሳንጨርሰው ውሃው ደርቆ፣ መካከል ላይ ዋጋ ከፈልን!
ለኩሬ ዋናው ተጥፈን
በውቂያኖሱ ተቀጣን!
***
አለሥራችን ገብተን፣ አንጨቅጭቀው እግዜአብሔርን፤
ይቅርታ እንጠይቅ እንጂ፣ ስለመፈጠራችን፤
ለመኖሪያችንማ፣ “የቀን ውሎ - አበል” አልን!
ተጠባባቂ ቤንች እንጂ፣ ቋሚ ተሰላፊ አደለን!
የካምቦሎጆን ነገር፣ የቀመሰ ያቀዋል
ለካስ ኳስ ሳይሞቁት በፊት፣ ጨዋታው ብርድ - ብርድ ይላል፡፡
***
ጭፈራችንን መልሱልን
ያገር ብርድ ሲቆነድደን
ኳስ ሜዳውን አልቤርጐ አርገን
ድንጋይ ጠርዙን ተንተርሰን
የታክሲ ውስጥ አልጋ አንጥፈን
ሌት በዋዜማ አልመን፣ ነገን በዕውነት ልናበራ፤
ባንዲራ እንደደመራ
ከምረን በየኳስ ጐራ፤
ተውለብልበን አውለብልበን
ላንቃችን እስኪበጣጠስ፣ ሆ ብለን በማታ በቀን፤
በጭለማ ድል ጐስመን
አገር ላዕላይ ነው ብለን፤
የሰው እግር እንደጅረት፣ ጨርቅ ማሊያው እንደጐርፍ
ባንዲራውን እንደ ጅራፍ
ስናጮኸው መኪና አፋፍ፤
በጥሩምባ መለከት አፍ
የሳግ ጩኸት ሞታችንን
ስናንባርቅ ድላችንን፣
ያን መሳይ ዝማሬ ቃና፣ ያን ጭፈራ ታስነጥቁን?!
እግዜር ለድል እያበቃን፣ እኛው “የእግዜር ስተት” ከሆን
ከመዋል ከማደር በቀር፣ ለህይወትም ያው “ቤንች” ነን!!
አዬ መጥኔ ካምቦሎጆ
አድሮ የንፍገት ኮሮጆ!
በሠርግ አጋፋሪ ጥፋት፣ ከፈረሰ ድንኳን ዳሱ
ገና ሜዳ ሳንገባ፣ ከተነፈሰማ ኳሱ፤
ለምን ላገር ይትረፍ ጦሱ?
ጭፈራችንን መልሱ!!
እናንተው ተከሳሰሱ
ብቻ ሳትውሉ ሳታድሩ፣ ጭፈራችንን መልሱ!!
ሰኔ 11/2005 (ለምስኪኑ ህዝባችን)
ነ.መ(ነብይ መኮንን )
http://www.addisadmassnews.com
No comments:
Post a Comment