የዳንኤል ዕይታዎች
ዳንኤል ክብረት
ኢትዮጵያ ከቦትስዋና ጋር ስትጫወት ተገቢ ያልሆነ ተጨዋች አሰልፋችኋልና ሦስት ነጥብ
ታጣላችሁ ብሎ ፊፋ የሚባል ቡዳ አገሩን ቀወጠው፡፡ እንደ አውነቱ ከሆነ እንዲህ ዓይነት ነገር ማድረግ የሌለበት ሁኔታ ነው
ያለው፡፡ ፊፋ ከአድኅሮት ኃይሎች ጋር ካልተሰለፈ በቀር ሌላ ምክንያት ሰጥቶ ኢትዮጵያን መጣል ይችል ነበር፡፡ ለኛ የኢትዮጵያ
ነጥብ መቀነስ አይደለም ችግራችን፤ ነጥቡ መቀነሱን ሕዝቡ መስማቱ ነው፡፡ እኛኮ ቀስ አድርገን ‹ኪራይ ሰብሳቢዎች የሀገራችንን
የስፖርት ራእይ ለማደናቀፍ ከፀረ ሕዝብ ኃይሎች ጋር በመሆን የደቀኑብን ሤራ ነው› ብለን ሕዝቡን ማሳመን እንችል ነበር፡፡
መጀመሪያ ከበላዮቻችን ጋር እንነጋገራለን፤ ሂስ ከተሰጠንም ሂሳችንን እንውጣለን፣
ግምገማችንንም እንቀበላለን፣ ዋናው ይሄ አይደለም፤ አንዴት አድርገን ለሕዝቡ እንንገረው? የሚለው ነው፡፡ ሕዝብ እንደነገርከው
ነው፡፡ እንደ አሰማሙ ነው፡፡ አቀናብረን ከነገርነው አቀናብሮ ይሰማል፡፡ ግን ምን ያደርጋል፣ ፊፋ የሚባል ቡዳ ለሕዝብ መነገር
የሌለበትን ለሕዝብ ተናገረና መከራ አሳየን፡፡
አሁን አዳሜ ዕድል ስታገኝ ጊዜ ‹ለምን ሥልጣን አትለቁም› ትላለች፡፡
እንዲህ በቀላሉ የሚተው መስሏቸው
አለች የሀገሬ ዘፋኝ፡፡ ሥልጣን እንዲህ በቀላሉ የሚተው መስሏቸዋል፡፡ እኛ በቀጣዩ
ምርጫ እንዴት አድርገን ተመልሰን እንደምንመጣ እያሰብን እነርሱ ሥልጣን ልቀቁ ይሉናል፡፡ ‹ከአንድ ሙዚቃ በኋላ ተመልሰን
እንገናኛለን› አሉ የኤፍ ኤም ጋዜጠኞች፡፡
ስለ ሥልጣን መልቀቅ እዚህ ሀገር የሚያስብ ሰው ካለ የመጨረሻው ጅል እርሱ መሆን
አለበት፡፡ ምክንያቱም ስለ ሥልጣን አያውቅምና፡፡ ‹‹አቤቱ የሚናገሩትን አያውቁትምና ይቅር በላቸው››፡፡ እነዚህ ሰዎች
ሥልጣንን ያልቀመሷት ሰዎች ናቸው፡፡ ቢቀምሷት ኖሮ ‹አጥብቃችሁ ያዟት› ይላሉ እንጂ ‹ልቀቋት› አይሉም ነበር፡፡ መንፈሳውያን
ነን፣ ዓለምን ንቀናል የሚሉት አባቶች እንኳን ለሥልጣን በሚታገሉባት ሀገር እኛን ዓለማውያኑን ‹ሥልጣን ልቀቁ› እንደማለት ያለ
የዓመቱ ምርጥ ቀልድ የለም፡፡
ጎበዝ እዚህ ሀገር ባለ ሥልጣን ማለትኮ ትንሽ ፈጣሪ መሆን ማለት ነው፡፡ ሰው
የሚሰግድልህ ሥልጣን ሲኖርህ ነው እንጂ ዕውቀት ሲኖርህ አይደለም፣ ሰው የሚኮራብህ ሥልጣን ሲኖርህ እንጂ ችሎታ ሲኖርህ
አይደለም፡፡ እስቲ የትኛው የአክስትህ ልጅ ነው እገሌ የተባለው ሳይንቲስትኮ ዘመዴ ነው ብሎ የሚኮራው? የባለሥልጣን ግን
እንኳን ዘመዱ ድመቱም አረማመዱ የተለየ ነው፡፡ ጅል- ሥልጣን ልቀቁ ይላል እንዴ፡፡ ሥልጣን የሻሂ ቤት ወንበር መሰላችሁ
እንዴ፡፡
ችሎታ ካለህ አንተ ወደ ሀብት ትሄዳለህ፤ ሥልጣን ካለህ ግን ሀብት ወደ አንተ
ትመጣለች፤ ዕውቀት ካለህ ዕድልን ፍለጋ ትንከራተታለህ፣ ሥልጣን ካለህ ግን ዕድል አንተን ፍለጋ ትንከራተታለች፤ ዕድለኛ ከሆንክ
በዕድሜህ አንድ ጊዜ ሎተሪ ይደርስሃል፣ ሥልጣን ካለህ ግን በየቀኑ ሎተሪ ይወጣልሃል፡፡ ዘመድ ካለህ ውጭ ቤትህ ውጭ ሀገር
ይሆናል፤ ገንዘብ ካለህ መሬት ትገዛለህ፤ ሥልጣን ካለህ ግን መሬት ትሸጣለህ፤ ንግድ ፈቃድ ካለህ ስለ ቀረጥ ታወራለህ፤ ሥልጣን
ካለህ ግን ስለ ቀረጥ ነጻ ታወራለህ፤
ዓይኔን ግንባር ያርገው ብሎ ይምላል ሰው
የቀኑን ጨለማ እንደኔ ባይቀምሰው
አለ ማየት የተሳነው ለማኝ፡፡
ሥልጣን ልቀቅ የሚሉ ሥልጣን የለቀቁ ምን እንዳጋጠማቸው ያላወቁ ብቻ ናቸው፡፡ ወዳጄ
እዚህ ሀገር ሥልጣን ለቅቆ በሰላም የኖረ ሰው ታውቃለህ? እኔ የማውቀው ዐፄ ካሌብን ብቻ ነው፡፡ እርሳቸው ሥልጣናቸውን
ለልጃቸው ለገብረ መስቀል ለቅቀው አባ ጰንጠሌዎን ገዳም ገቡ፡፡ እንደ እርሳቸው አደርጋለሁ ብለው አድያም ሰገድ ኢያሱ
ሥልጣናቸውን ቢለቅቁ አይደል እንዴ የገቡበት ገዳም ድረስ ሄደው የግፍ ሞት የገደሏቸው?
ፈረንጅ በትንሽ በትልቁ ሥልጣን ለቅቄያለሁ የሚለው ለምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? በቀላሉ ነዋ የሚያገኘው፡፡ በየቴሌቭዥኑ ለፍልፈህ፣ ልብ የሚያጓጓ ንግግር ተናግረህ፣ የሰው ካርድ ጠብቀህ የምታገኘው ሥልጣንና ጉቦ ሰጥተህ፣ ደም ተፍተህ፣ ለስንቱ ጉልበተኛ አጎንብሰህ፣ ተለማምጠህና ከሰው በታች ሆነህ የምታገኘው ሥልጣን አንድ ነው እንዴ? ደግሞ ፈረንጅ ምን ችግር አለበት፤ ‹በፈቃዴ ሥልጣኔን ለቅቄያለሁ› ቢል ‹ይህስ ኅሊና ያለው ነው፣ ኃላፊነት የሚሰማው ዜጋ ነው› ተብሎ ያም ያም ይሻማበታል፤ ሥልጣኑ ይቀርብህ እንደሆነ እንጂ ገንዘቡና ክብሩ አይቀርብህም፤ ኧረ እንዲያውም ከባለሥልጣኑ በላይ ልትከበርም ትችላለህ፡፡
እስኪ እዚህ ሀገር ከሥልጣን ውረድና እንኳን ሥራ ቀጠሮ የሚቀጥርህ ታገኝ እንደሆነ
ሞክራት፡፡ እንኳን ሌላ የገዛ ዘመድህ ሊያስጠጋህ አይፈልግም፡፡ እንኳን ዘመድህ የገዛ ሰውነትህ ይሸሽሃል፡፡ ሥልጣን እያለህ
አንተ እንኳን ለዘመድህ ለጎረቤትህ ሁሉ የባንክ አካውንት ስታስከፍት ትኖራለህ፤ ሥልጣንህን ስታጣ ግን እንኳን የዘመድህ የአብሮ
አደግህ አካውንት አይቀራቸውም፤ ይጠረቅሙልሃል፡፡
እና ምን ልሁን ብዬ ነው ሥልጣን የምለቅቀው? እኔ ሥልጣኔን ከማጣ ኢትዮጵያ እንኳን
ሦስት ነጥብ ለምን ኳስ ሜዳዋን አታጣም፡፡ ደግሞስ ውርደት በኛ ነው እንዴ የተጀመረው፡፡ ‹አህያውን ፈርቶ ዳላውን› አለ፡፡
በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ማግስት ባድሜን በፍርድ ቤት ክርክር አግኝተናል ተብሎ ሕዝብ ወጥቶ በአደባባይ ጨፈረ፤ ሚዲያውም
አራገበው፡፡ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ግን ባድሜኮ ለኛ አልተፈረደም፤ በፎርፌ ተበልተናል፤ ያልተገባ ተጨዋች አሰልፈን፣ ባድሜን
አጥተናል ተባለ፡፡ ሕዝብ ኩምሽሽ አለ፡፡
እና ያን ጊዜ ማን ‹ሥልጣን ልቀቁ› አለ፡፡ ማንስ ሥልጣን ለቀቀ? አሁን በኛ ላይ
ነው እንዴ ሁሉም ጥርስ የሚያወጣው፡፡ አስጨፍሮ ድልን መቀማት በኛ ነው እንዴ የተጀመረው፡፡ ባድሜን ያህል ቦታ ያሳጣ ምንም
ሳይደረግ፣ ሦስት ነጥብ ያሳጣን ሥልጣን ልቀቅ ማለት ፍርሃትን እንጂ ጀግንነትን አያሳይም፡፡
ከመስቀል አደባባይ እስከ ሳሪስ ያለው የመሐል መንገድ መቶ ሚሊየኖች ወጥተውበት
ተሠራ፡፡ አቤት አገራችን አለፈላት፤ ሦስት መንገድ በአንድ አቅጣጫ ተገነባ ብለን እልል አልን፣ አደነቅን፤ አዳነቅን፡፡
ቴሌቭዥኑም የዕድገት ማሳያ አድርጎ ደጋግሞ ከሙዚቃ ጋር አሳየን፡፡ ገና ደስታችንን ሳንጨርስ ግን መንገዱ ሲታረስ አገኘነው፡፡
በስሕተት ነው፤ ያልተገባ ተጨዋች ተሰልፎ የገነባው ነውና ለባቡር ይፈርሳል ተባለ፡፡ ሀገሪቱ መቶ ሚሊየኖች ያወጣችበትን መንገድ
አምስት ዓመት እንኳን ሳያገለግል ማረስ ከሦስት ነጥብ በላይ ሀገርን ማሳጣት አይደለም እንዴ፡፡ ግን ያን ጊዜ ማን ተናገረ፡፡
ማን ሥልጣን ልቀቁ አለ፡፡ የትኛው ሥራ አስፈጻሚ ተቀጣ፤ የትኛውስ የጽ/ቤት ኃላፊ ተባረረ፤ የትኛው ምክትል ፕሬዚዳንት ሕዝብ
ፊት ቀርቦ አለቀሰ፡፡ ዝም አይደል እንዴ የተባለው! እኛ ላይ ሲሆን ነው እንዴ ዘራፍ የምትሉት? ‹ጓደኛው
ቢያቅተው ወደ ሚስቱ ዞረ› አሉ፡፡
አንድ ሰውዬ ያሉትን ልንገራችሁማ፡፡
ሰውዬው ሀብት ያካበቱት እየዘረፉ ነው፡፡ ሲነቃባቸው ደግሞ አላደረግኩም ብለው ድርቅ
ይላሉ፡፡ ቢታሠሩም፤ ቢደበደቡም አያምኑም፡፡ ልጃቸውንም እንደ እርሳቸው አድርገው አሳደጉት፡፡ እርሱም ሀብታም ሆነ፡፡ አንድ
ቀን ሲዘርፍ ተያዘና ፍርድ ቤት ቀረበ፡፡ ‹ሰርቀሃል ወይ›› ሲባል ‹አዎ› ብሎ አመነ፡፡ ተፈረደበት፡፡ አባትዬው ይህንን ታሪክ
ሰሙ፡፡ ‹‹ልጅዎኮ ሰርቆ ተፈረደበት›› አሏቸው፡፡ ‹‹በምቀኝነት ነው እንጂ የኔ ልጅ እንዲህ አያደርግም›› ብለው ተሟገቱ፡፡
‹‹እንዴ እርሱ ሰርቄያለሁ ብሎ ያመነውን እርስዎ እንዴት ይክዳሉ›› አሏቸው፡፡ አባትዬውም ‹‹ልጄ ቢሰርቅም ሰርቄያለሁ አይልም››
ብለው ሞገቱ፡፡ ሰዎቹም ‹‹ብሏል በጆሯችን ሰምተነዋል›› አሏቸው፡፡ እርሳቸውም ‹‹ፈጽሞ አይልም›› ብለው ተከራከሩ፡፡
ሰዎቹ ግራ ገባቸው፡፡ ‹‹እንዴት በጆሯችን የሰማነውን እርስዎ ይክዳሉ›› ብለው
ጠየቋቸው፡፡ ‹የኔ ልጅ ሰርቄያለሁ አይልም› አሉ አባት፡፡ ‹‹ለምን›› ሲባሉ ‹‹ያለ አባቱ ከየት ያመጣዋል›› አሉ አሉ፡፡
መስረቅ እንጂ ማመንን አላስተማሩትማ፡፡ አሁንም እኛ ያለ አባታችን ከየት እናመጣዋለን፡፡
እናንተ በሥልጣን ላይ ያሉትን የመንግሥት ባለ ሥልጣናት ብቻ ነው የምታዩት፡፡ እስኪ
በተቃዋሚው መንደር አስሱ፡፡ እነዚያው ሰዎች አይደሉም እንዴ በዙር ሥልጣኑን የያዙት? መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ተመልከቱ፤
መሥራችና ፕሬዚዳንት ራሳቸው አይደሉም እንዴ? ሲቪል ማኅበራቱን እዩ፤ የመሠረቱት ናቸው አሁንም ወንበሯን የተቆጣጠሯት፡፡ ውጡ
ደግሞ ወደ ዲያስጶራው፡፡ በአንዲት መንደር ሃያ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ የሚመሠረተው ለምንድን ነው? ሁሉም ሊቀመንበር መሆን
ስለሚፈልግ አይደለም እንዴ? ፓርቲዎቹ ሲሰነጣጠቁ የሚውሉት በርዕዮተ ዓለም ተለያይተው ነው? ፈጽሞ፡፡ የተለያዩት በወንበር
ነው፡፡ አብያተ ክርስቲያናቱ ሲከፋፈሉ የሚውሉበት ዋናው ምክንያት ምንድን ነው? ሁሉም የደብሩ አስተዳዳሪ፣ ሁሉም ቦርድ፣ ሁሉም
ገንዘብ ያዥ መሆን ስለሚፈልግ ነዋ፡፡
ደግሞኮ አንዳንዶቹ የሚገርሙ ናቸው፡፡ ‹ፌዴሬሽኑ ራሱን ተጠያቂ ማድረግ ሲገባው
ግለሰቦች ላይ አነጣጠረ› ይላሉ፡፡ ፍየል መፈለግ በኛ ነው እንዴ የተጀመረው፡፡ ‹ምን ሹም ቢያጠፋ ባላገር ይክሳል› የሚለውን
አልሰሙም መሰል፡፡ ምን ፌዴሬሽኑ ቢያጠፋ የሆኑ ፍየሎችማ ለእርድ መቅረብና ኃጢአት ማስተሥረያ መሆን አለባቸው፡፡ እንዲሁ ነውኮ
የኖርነው፤ አንተ ታጠፋለህ፣ ፍየልህን ታርዳለህ፡፡ የጦስ ዶሮ ሲባል አልሰማችሁም፡፡ እንተ ትታመማለህ፣ ምንም ባላጠፋው ዶሮውን
አርደህ፣ ሦስት ጊዜ አዙረህ ትወረውራለህ፡፡ ከዚያስ? ‹ጦስህን ይዞ ይሂድ› ትላለሃ፡፡
እና፣ ውረዱ፣ ልቀቁ ምናምን አትበሉ፡፡ እዚህ ሀገር ‹ውረድ› የሚባለው ዛፍ ላይ
የወጣ ሰው፣ ‹ልቀቅ› የሚባለው ሰይጣን የያዘው ሰው ብቻ ነው፡፡ አንድ ሰሞን ተንጫጭቶ ለሚረሳ ሕዝብ መውረድና መልቀቅን ምን
አመጣው፡፡ ገና የባሰ ነገር ታያላችሁ፡፡
እንኳን ሦስት ነጥብ ተቀነሰ ተብሎ ይቅርና ሀገሪቱ ማጣሪያ በተደጋጋሚ ስትወድቅ፣
ከአፍሪካ ዋንጫ 31 ዓመት ስትርቅ፣ የምሥራቅ አፍሪካ ዋንጫ ሲርባት፣ ክለቦቿ ከአፍሪካ ክለቦች ዋንጫ አርባ ክንድ ሲርቁ፣ ማን
ሥልጣን ለቀቀና ነው እኛ ሥልጣን የምንለቀው? አቦ አትቀልዱ፡፡
ጁባ፣ ደቡብ ሱዳን
No comments:
Post a Comment