Monday, August 18, 2014

የጳውሎስ መልእክት ወደ ኢትዮጵያ ሰዎች !

ርዕስ- ጳውሎስ ኞኞ (1926-1984)፣
የገፅ ብዛት - ከፎቶና ማጣቀሻ ጽሑፎች ዝርዝር ጋር 308፣
የሽፋን ዋጋ - 84 ብር (24 ዶላር)፣
የህትመት ዘመን - 2006 ዓ.ም
ህትመት - አርቲስቲክ ማተሚያ ድርጅት
ጸሐፊ - ደረጀ ትዕዛዙ

በዘመናችን ግለታሪኮችና ታሪኮች በብዛት ባይሆንም በተሻለ መጠን ለህትመት እየበቁ ናቸው፣ ይህ መልካም ጅምር መጠናከር ይኖርበታል፡፡ ምክንያቱም ዓለማችንን የቀየሩዋት ባለ ልዩ አዕምሮ ግለሰቦች ናቸው፤ በእነሱ ጥረትና የድካም ፍሬ ድምሩ ህዝብ ተጠቃሚ ሆኗል፤ ይሆናልም፡፡ እንኳንስ ተፈጥሮ አድልታ ባለ ምጡቅ አዕምሮ ያደረገቻቸው ግለሰቦች ይቅሩና የኔቢጤው በረንዳ አዳሪ ሁሉ ቀርቦ የሚያነበው ቢያገኝ ታላቅ መጽሐፍ ነው፤ ታላቅ መረጃ በውስጡ ይኖራል፡፡
ከነገስታትና ልኡላን ዜና መዋዕሎች በቀር እብዛም ያልተለመደ የነበረው የግለሰቦች ታሪክ በቤተሰቦቻቸው፣ ወይም መልካም ፈቃዱና ችሎታው ባላቸው ግለሰቦች አማካይነት እየተጻፈ ልምዳቸውን እንድንካፈል የላቀ ድርሻ እየተወጡ ናቸው፡፡ በቅርቡ ታትሞ ገበያ ላይ የዋለውና በጳውሎስ ኞኞ የህይወትና ሥራ ታሪክ ላይ የሚያጠነጥነው መጽሐፍም ከእነዚህ የግለሰብ ታሪኮች የሚመደብ ነው፡፡
በዘጠኝ ምዕራፎች የተከፋፈለው የ“ጳውሎስ ኞኞ” መጽሐፍ፤ የተለያዩ ፎቶግራፎችንና ውሱን ሰነዶችንም አካትቷል፡፡ ስለጳውሎስ ልደት፣ ዕድገት፣ ትምህርት፣ ሥራና ባህርይ የሚያትተው ይህ መፅሀፍ፤ ከጳውሎስ ጋር ባላንጣ ስለነበሩት የወቅቱ የማስታወቂያ ሚኒስትር ደጃዝማች ግርማቸው ተክለሐዋርያትም የሚያካፍለን ቁም ነገር አለ፡፡
ጳውሎስ ያልሞከረው ሥራ የለም ማለት ይቻላል፤ ግለሰብ ሱቅ ውስጥ ተቀጥሮ መስራት የጀመረው ገና በልጅነት ዕድሜው ሲሆን ትምህርቱን ከአራተኛ ክፍል ያቋረጠውም በድህነት ምክንያት ነው፡፡ (ገፅ 16) ከግሪካዊው ኞኞ እና ከኢትዮጵያዊቷ ወ/ሮ ትበልጫለሽ ቁልቢ ገብርኤል አካባቢ የተወለደው ጳውሎስ፤ የልጅነት ህይወቱ የተመሰቃቀለ ነበር፡፡ እናቱ ፍጹም ድሃ በመሆናቸው እንደ እመጫት ድመት በየቦታው ይዘውት ስለሚዞሩ በትምህርቱ ላይ ጫና መፈጠሩ የግድ ነበር፡፡