Wednesday, July 31, 2013

ለቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሐውልት እንዲቆምላቸው ጥሪ ቀረበ

 በ  ታደሰ ገብረማርያም
የደቡብ አፍሪካ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ታቦ ምቤኪ
የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (የአፍሪካ ኅብረት) መሥራች ለሆኑት ለቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የመታሰቢያ ሐውልት እንዲቆምላቸው ተጠየቀ፡፡

ይህንን የጠየቁት የድርጅቱ/የኅብረቱ 50ኛ ዓመት ኢዮቤልዩ ክብረ በዓልን ለማክበርና መሥራቾች አባቶችን ለመዘከር ባለፈው ቅዳሜ በተካሄደው ውይይት ላይ ከተገኙ ተሳታፊዎች መካከል አንዳንዶቹ በሰጡት አስተያየት ነው፡፡

የኮኖጎዋ ብራዛቪል የኢትዮጵያንና ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክን ጨዋታ ልታስተናግድ ነው

(ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያና  ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የሚያደርጉት ጨዋታ ኮንጎ ብራዛቪል ላይ እንዲደረግ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን/ፊፋ/ መወሰኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ገለፀ ።

የሁለቱ አገራት ጨዋታ ጷጉሜ  ወር ላይ በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ዋና ከተማ  ባንጉይ መካሄድ የነበረበት ቢሆንም ፥  በአገሪቱ ያለው  የፀጥታ ሁኔታ ጨዋታውን ለማካሄድ የሚያስችል ባለመሆኑ ተለዋጭ አስተናጋጅ አገር ሲፈላለግ ቆይቷል ።

በፈረንጆቹ መስከረም 7  በብራዛቪል  የሚካሄደውን የኢትዮጵያና  የማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ጨዋታንም የሚዳኙ አራት ዳኞች ከአልጄሪያ  መመረጣቸውንም  ፊፋ  ጨምሮ ገልጿል ።

ስለጨዋታው ያነጋገርናቸው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዋና  አሰልጣኝ አቶ ሰውነት ቢሻው ውደድሩ  የሚካሄድበት ቦታ ሞቃታማ ቢሆንም ጠንከረን በመስራት  ግባችንን  አንመታለን ብለዋል ።

አቶ ሰውነት ጨምረውም ጨዋታው በኬኒያ አልያም በኡጋንዳ ቢካሄድ ኖሮ ለኢትዮጵያ  የተሻለ እንደነበር ነው የተናገሩት ።

EthioJazz performs at Ethiopian Heritage Festival in DC

The rising stars of EthioJazz perform a play from the works of legendary Ethiopian composer Mulatu Astatke. The San Jose based EthioJazz travelled to DC now as honorary members of the Ethiopian Heritage Society in North America. The current 3-day festival is the third since the birth of the Society.

Tuesday, July 30, 2013

“የፊልም ኢንዱስትሪው ወደፊትም ወደኋላም እየተጐተተ ነው”

ላለፉት 15 አመታት በፊልም ሙያ ላይ የተሰማራው ቴዎድሮስ ተሾመ፤ በፊልም ፅሁፍ ደራሲነት፣ በተዋናይነት፣ በዳሬክተርነትና በፕሮዲዩሰርነትም ሰርቷል፡፡ በሙያ ዘመኑ አምስት ፊልሞችን ሰርቶ ለእይታ ያበቃው አርቲስቱ፤ ስድስተኛውን ፊልሙን “ሦስት ማዕዘን” በሚል ርዕስ የሰራ ሲሆን የነገ ሳምንት ሐምሌ 21 ያስመርቃል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ መልካሙ ተክሌ በአዲሱ ፊልሙ ላይ በማተኮር ከአርቲስት ቴዎድሮስ ጋር ያደረገውን ቃለምልልስ እነሆ፡፡

“ቀይ ስህተት” የተሰኘው ፊልምህ ሲወጣ የቀይ ሽብር ሰማእታት ታሰቡ፡፡ “አባይ ወይስ ቬጋስ” ሲታይ አባይን መገደብ ተጀመረ፡፡ አሁን ደግሞ የስደተኞች ጉዳይ ትኩረት ሲይዝ በስደት ዙርያ የሚያጠነጥነው “ሦስት ማእዘን” የተሰኘ ፊልምህ ሊወጣ ነው፡፡ ፊልሞችህ ወቅት ተኮር ሆኑሳ?
የ“ሦስት ማእዘን” ቀረፃ ያለቀው ከአንድ ዓመት በፊት ነው፡፡ የተፃፈው ከሦስት ዓመት በፊት ነው፡፡ በተለይ በሙያው ውስጥ ያሉ እንደዚህ ሊያስወሩ ይችላሉ፡፡ በትግል የማትጥለውን ሰው ለመጣል እንዲህ አይነት ስትራተጂ ትቀይሳለህ፡፡ የዚህን ፊልም ማስታወቂያ ከጀመርን አስራ አንድ ወር ሆኖናል፡፡ የሕገወጥ ስደት ወሬ ሰፊ ሽፋን ማግኘት የጀመረው ከስድስት ወር ወዲህ ነው፡፡ “አባይ ወይስ ቬጋስ” ፕሮጀክት ሁለት ዓመት ፈጅቷል፡፡ ይኼ ፊልም መታየት ከጀመረ በኋላ ነው የግድቡ አዋጅ የታወጀው፡፡ “አበድኩልሽ” ከሚል የገበያ ሥራ ስታልፍ ችግሮች ቀድመው ሊታዩህ ይችላሉ፡፡
“ሦስት ማእዘን”ን በልደትህ ቀን ለገና ለማስመረቅ አስበህ እንደነበር ሰምቻለሁ፡፡ ለምን እስካሁን ዘገየህ?
ፊልሙ አልደረሰልኝም፡፡ ፊልሙን በልደቴ ቀን ለማስመረቅ አስቤ ነበር፡፡ ይኼ መረጃ እንዴት እንደደረሰህ አላውቅም፡፡
ማትያስ ሹበርት የፊልሙ የፎቶግራፊ ዳይሬክተር እንደሆነ ተገልጿል፡፡ አንዳንድ ወገኖች ግን ባለሙያው ሙሉ ቀረፃውን እንዳልሰራ ይናገራሉ፡፡
ዘጠና ዘጠኝ በመቶውን ቀረፃ የሰራው እሱ ነው፡፡ እዚህ የቆየው ለስልሳ ቀናት ነው፡፡ ቀረፃው በሰባ አምስት ቀናት ተጠናቀቀ፡፡ እሱ ከሄደ በኋላ አስራአምስት ቀን ሙሉ ተቀረፀ ማለት አይደለም፡፡ ከሱ መሄድ በኋላ የሦስት ቀን ቀረፃ ብቻ ነው የነበረው፡፡

ፊልሙን በውጭ ሀገር ፊልም ዘርፍ ለኦስካር ሽልማት እንዲታጭ ለማድረግ አስባችኋል፡፡ ከምን ተነስታችሁ ነው?
ሥራችን ለኦስካር ይመጥናል ብለን ስለምናስብ ነው፡፡ ካሁን በፊት የሰራኋቸው ፊልሞች እዚህ ውድድር ውስጥ አልገቡም፡፡ የኦስካር ፈተና ከባድ ነው፡፡ ውጤቱን አብረን እናያለን፡፡ የእኛ መዝገበ ቃላት ሁልጊዜ “አይቻልም” የሚል ነው፡፡ አይቻልም ስለሆነ ሁሌም አንችልም፡፡ “ሦስት ማእዘን” ግን ይችላል ብለን እናስባለን፡፡ ስለዚህ የሚከፈለውን መስዋእትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን፡፡ ኦስካር መግባታችን ግን ከማትያስ ሹበርት ጋር አይገናኝም፡፡
ሀገር ውስጥ ፍጆታ በተሰራ ፊልም ለዓለም አቀፍ ሽልማት መታጨት ይቻላል?
የሚያጨው ሌላ አካል ነው፡፡ እኛ እንደማንኛውም ተወዳዳሪ እንወዳደራለን፡፡ ስራችንን ለውድድር አቅርበን ዘመቻ እናደርጋለን፡፡ ይህ ራሳችንንና ፊልሙን ለማሳደግ ያለን ፍላጐት አካል ነው፡፡ እኛ ብቻ ሳንሆን የሀገራችን የፊልም ኢንዱስትሪ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆን ሙከራ እናደርጋለን፡፡
በፊልሙ ውስጥ ለተሳተፈ ለእያንዳንዱ የውጪ አገር ዜጋ ተዋናይ 40ሺ ዶላር ከፍለሃል ተብሏል…
ውሸት ነው፡፡ በነፃም አልሠሩም፣ የተጠቀሰውን ያህል ገንዘብም አልተከፈላቸውም፡፡
“ሦስት ማእዘን” ከሌሎቹ ፊልሞችህ በተለየ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መቀረፁን ፊልሙን ለጋዜጠኞች ባሳየህ ወቅት ተናግረሃል፡፡ እስቲ ስለእሱ አብራራልኝ…
በ49 ሴ.ግሬድ ሙቀት በበረሀ መቀረፁ ይመስለኛል፡፡ እያንዳንዱ ፊልም የራሱ ተግዳሮት አለው፡፡ የባለሙያ፣ የበጀት…ችግር አለ፡፡ ይኼን የተለየ የሚያደርገው በረሃው ነው፡፡ ከቤት ውጭ ነው የተቀረፀው፡፡ የውሃ ጥሙ ስቃይ ነው፡፡ ቀዝቃዛ ውሃ አፍ ከመድረሱ በፊት ይሞቃል፡፡ በእርግጥ ሁላችንም ተሰዳጅ ሆነንበታል፡፡ ሌላው ደግሞ ውጭ ሀገር ሲቀረጽ የገጠመን የውጭ ምንዛሬ ችግር እና የቋንቋ መሠናክል ነው፡፡
ወደ ፊልም ሙያ በገባህበት የጀማሪነት ጊዜህ ታዋቂው የፊልም ባለሙያ ሚሼል ፓፓታኪስ ያመቻቹልህን የውጭ ሀገር የትምህርት እድል ሳትጠቀምበት እንደቀረህ ሰምቻለሁ፡፡ ለምን ይሆን?
ከጀመርን የባህል ተቋም ጋር በመሆን ጋና እንድሄድ ነበር የታሰበው፡፡ አጋጣሚው ጥሩ ነበር፡፡ ግን በዚያ ሰዓት ለአራት ዓመት እዚያ ሄጄ ቢሆን ኖሮ አሁን ላለሁበት ደረጃ አልደርስም ነበር፡፡ የራሴ ራእይ ነበረኝ፡፡ የአሁኑን ጊዜ ያለመ፡፡ የባህል ተቋም ኃላፊዋን ለአራት ዓመት ከምትልኪኝ የሦስት ወር ካለ ላኪኝ ብያት ነበር፡፡ እናቴ በህይወት ስላልነበረችና የቤተሰብ ሃላፊነት እኔ ላይ በመውደቁ፣ ለረዥም ጊዜ ውጭ ሀገር መቆየቱን እምቢ አልኩ፡፡ ወንድሞቼንና እህቶቼን ሜዳ ላይ በትኜ መሄድ አልችልም ነበር፡፡
ከዚያ በኋላስ የፊልም ትምህርት የመማር እድል ገጠመህ ወይስ በልምድ ብቻ ቀጠልክ?
ሎስ አንጀለስ የፊልም ትምህርት ቤት ተምሬአለሁ፡፡ ዲግሪዬን በሚቀጥለው ወር እወስዳለሁ፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ውጭ የነበርኩት ለዚህ ነው፡፡
በልጆችህ ላይ ወዳንተ ሙያ የመግባት አዝማሚያ አይተህባቸዋል?
ሦስተኛ ሴቷ ልጄ በተለይ ሙዚቃ ላይ ክንፍ ትላለች፡፡ ያልተለመደ ነገር አላት፤ አካሄዷን እናያለን፡፡ ልጆቼ ምርጫቸውን የሚወስኑት በራሳቸው ጊዜ እንጂ በእኔ ምርጫ አይደለም፡፡ ድራማ እና ፊልም ያያሉ፡፡
“ሦስት ማእዘን” ሲመረቅ መግቢያው 300 ብር መሆኑ “ራስን ማዋደድ ነው” ብለው የሚተቹ ወገኖች አሉ…
ይሄ በዛብን የሚሉ በሌላ የምርቃት ቦታ በመቶ ብር መግባት ይችላሉ፡፡ ከበዛ በሚቀጥለው ቀን በመደበኛ ዋጋ ይታያል፡፡ አምስት መቶ ብር እና አንድ ሺህ ብር ለማድረግም አስበን ይበዛል ብለን ነው የተውነው፡፡ የምርቃት ፕሮግራሙ ልዩ ሥነ ሥርአት ስላለው እኮ ነው፡፡
ለ15 ዓመታት በፊልም ኢንዱስትሪው ውስጥ እንደቆየ ባለሙያ የአገራችንን የፊልም እድገዘ እንዴት ትገመግመዋለህ?
የሁሉም ሀገር የፊልም ኢንዱስትሪ የራሱ ዝግመተ ለውጥ አለው፡፡ ይወለዳል፡፡ ይድሃል፡፡ ያድጋል፤ ትልቅ ኢንዱስትሪ ይሆናል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ እያለፍን ነው ያለነው፡፡ በዚህ ውስጥ የሚፈጠሩ ችግሮች የሁሉም ኢንዱስትሪ ገጽታዎች ናቸው፡፡ የሀገራችን የፊልም ኢንዱስትሪ ከሁለት አቅጣጫ እየተጐተተ ነው፡፡ የሚለፋ ሰዎች አሉ፡፡ ወደ ፊት ያራምዱታል፡፡ ወደ ፊት ሄደ ብለህ ስታስብ ደግሞ አሸር ባሸር የሚሰሩ ሰዎች አሉ፡፡ ወደ ኋላ ይጐትቱታል፡፡ ስለዚህ መሀል ላይ ተወጥሮ ነው ያለው - ወደ ፊትም ወደ ኋላም እየተጐተተ፡፡
የኢትዮጵያ የፊልም ኢንዱስትሪ የግሎባላይዜሽን ተፅእኖ ያሰጋዋል የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ አንተ ምን ትላለህ?
ኢንዱስትሪውን ኢንዱስትሪ ለማድረግ ሦስት ግብአቶች ያስፈልጋሉ፡- ተመልካች፤ ፕሮዲዩሰር እና አከፋፋይ፡፡ አከፋፋይ ሲኖር የጥራት ደረጃ ይመጣል፡፡ ይኼንን ደረጃ ለማምጣት ፕሮዲዩሰርም ተጠንቅቆ ይሰራል፡፡ ተመልካችም ጥራት ምን እንደሆነ ስለሚገባው ያንን መጠየቅ ይጀምራል፡፡ እኛው እንሰራለን፣ እኛው እናስተዋውቃለን፣ እኛው እናከፋፍላለን፡፡ “ሦስት ማእዘን” የራሱ ዓለም አቀፍ አከፋፋይ አለው፡፡
አሁን ሰዎች በፊልም ገቢ ብቻ መተዳደር ጀምረዋል፡፡ ስለዚህ ፊልም እንደ ኢንዱስትሪ ቆሟል ማለት ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠር ብር ለመንግስት ቀረጥ እየተከፈለበት ነው፡፡ የፊልሞች በዓለምአቀፍ የባህልና ቋንቋ ተጽእኖ ሥር መውደቅ እንደፊልም ሰሪዎቹ የአእምሮ ዝግጅት የሚወሰን ነው፡፡ ሁሉም ፊልም ግሎባላይዝድ ሆኗል ማለት ይከብዳል፡፡
ዘንድሮ ከወጡ የአማርኛ ፊልሞች መካከል የወደድከው አለ?
“የመጨረሻዋ ቀሚስ” ጥሩ ነው፡፡ “ኒሻን” የተለፋበት ቆንጆ ፊልም ነው፡፡ ኮሜዲ የሆነው “ኢምራን” ጥሩ ነው፡፡ “ሰምና ወርቅ” በጣም ቆንጆ ነው፡፡ ሁሉንም ፊልም አያለሁ፡፡ ግዴታም አለብኝ፤ በሲኒማ ቤቴ ምክንያት፡፡ ዘንድሮ የወጡትን ፊልሞች ሁሉ ለመዘርዘር ጊዜም የለንም፡፡ ልቤ ውስጥ የቀሩትን ፊልሞች ከሞላ ጐደል ጠቅሼልሃለሁ፡፡
ድርጅትህም ስምህም ከዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ጋር የተገናኘ ነው፡፡ ስለ ሴባስቶፖል መድፍ ፊልም ለመስራት አስበህ ታውቃለህ?
ሴባስስቶፖል ለኔ የመጀመርያው የቴክኖሎጂ ሙከራ ነው፡፡ መድፍ ነው፡፡ እኔ የምመራው የፊልም ድርጅት የእኔ መድፍ ነው፡፡ እስካሁን ስድስት ተኩሼበታለሁ፡፡ ሰባት፣ ስምንት፣ ዘጠኝ አስር እያልኩ እተኩሳለሁ፡፡ ታሪክን አጣቅሼ የራሴን አርማ ለማውጣት ከሴባስቶፖል የበለጠ የለም፡፡ አፄ ቴዎድሮስና ገብርዬ ያሉዋቸውን ታሪኮች ፊልም የማድረግ ህልም አለኝ፡፡ አንድ ቀን ይሰራል፤ ግን ጥናት ይፈልጋል፡፡
ከ”ሦስት ማእዘን” ቀጥሎ ምን እንጠብቅ?
“ሦስት ማእዘን” ቁጥር ሁለት ይከተላል፡፡ ቀረፃው ተጠናቋል፡፡ “ሦስት ማእዘን” ቁጥር ሦስትም አለ፡፡ ምንአልባት ይኸው ፊልም እስከ አስር ሊቀጥል ይችላል፡፡ መፅሔት ተፈራ የምትባል ልጅ ያመጣችው “ሀገር” የሚል የፊልም ፅሁፍም አለ፡፡ የሷን ቆንጆ ድርሰት እንደገና እያዋቀርኩት ነው፡፡ እሱን የመስራት እቅድ አለኝ፡፡ ዳግማዊ ፈይሳ የፃፈው “የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልጅ” የሚል ፅሁፍም በፕሮጀክት እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ ከዚያ “ግድብ” የሚል ሃሳብ አለኝ፡፡ ያስፈልጋል አያስፈልግም የሚለውን ግን እወስናለሁ፡፡
ለኢትዮጵያ ምን አደረግህላት፣ ኢትዮጵያስ ምን አደረገችልህ?
ኢትዮጵያ ወለደችኝ፤ አሳደገችኝ፡፡ እኔ ምን እንዳደረኩላት አላውቅም፡፡ ምክንያቱም የማደርገው ነገር በሙሉ ለመኖር፣ ለራሴ ደስታ ለማግኘት፣ ህይወት ጣፋጭ እንድትሆንና ልጆቼን ለማሳደግ በማደርገው ሩጫ ውስጥ የሚካተት ስለሆነ፣ ለኢትዮጵያ ይህን አደረግሁላት ልል አልችልም፡፡

Monday, July 29, 2013

በቴሌ የ1.6 ቢሊዮን ዶላር ማስፋፊያ ላይ ዓመት የፈጀው የቻይና ኩባንያዎች ፍጥጫ

 ዮሐንስ አንበርብር

  -  ሁዋዌና ዜድቲኢ ፕሮጀክቱን ተካፈሉት
  -    የውጭ ቴሌኮም ኩባንያዎች እየገቡ ነው

ኢትዮ ቴሌኮም በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ መሠረት የተጣለበትን ግብ ለማሳካት የቀረፀውን የ1.6 ቢሊዮን ዶላር የማስፋፊያ ፕሮጀክት እንዲያከናውኑለት ከዓመት በፊት ሁለቱን የቻይና ኩባንያዎች ከመረጠ በኋላ፣ ሁለቱ ኩባንያዎች በፕሮጀክቱ ላይ የበላይነትን ለማግኘት በፈጠሩት ፉክክር ምክንያት አንድ ዓመት የፈጀ ውጥረትና ሥጋት የተሞላበት ድርድር በማካሄድ በዚህ ሳምንት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

ውሳኔውንም ተከትሎ ኢትዮ ቴሌኮም ሁዋዌ ቴክኖሎጂ ከተባለው የቻይና ኩባንያ ጋር የ800 ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ውል ስምምነት ባለፈው ሐሙስ ምሽት በሸራተን አዲስ ተፈራርሟል፡፡ በዚህ የስምምነት ሥነ ሥርዓት ላይ በኢትዮ ቴሌኮም የተበተነው ጋዜጣዊ መግለጫ የውል ስምምነቱ የሚፈጸመው ከሁለቱ የቻይና ኩባንያዎች ከሁዋዌና ከዜድቲኢ ጋር መሆኑን ቢገልጽም፣ ስምምነቱን የፈረመው ግን ሁዋዌ ብቻ ነው፡፡ ዜድቲኢ ከተባለው የቀድሞውን የማስፋፊያ ፕሮጀክት ካከናወነው የቻይና ኩባንያ ጋር የሚቀር ድርድር ስላለ ቀሪው የ800 ሚሊዮን ዶላር ስምምነት ለጊዜው አልተፈረመም፡፡

ዜድቲኢ በዚህ የኮንትራት ስምምነት ላይ ያልተገኘው በኢትዮ ቴሌኮም ውሳኔ ቅር በመሰኘት መሆኑን የኢትዮ ቴሌኮም ምንጮች ለሪፖርተር የገለጹ ቢሆንም፣ በኮንትራት ስምምነቱ ላይ የተገኙት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የኢኮኖሚ ዘርፍ አስተባባሪና የኢንፎርሜሽንና ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ደብረ ፅዮን ገብረ ሚካኤል ከሞላ ጐደል ከሁለቱም ኩባንያዎች ጋር በመርህ ደረጃ ስምምነት ላይ ተደርሷል በማለት፣ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ነገር ግን ዜድቲኢ ቅሬታ ከሌለበት ኮንትራቱን ለምን እንዳልፈረመ እንዲያብራሩ ሲጠየቁ፣ ስምምነቱ በመርህ ደረጃ በመሆኑ ቀሪ መጠናቀቅ የሚገባቸው ጉዳዮች መኖራቸውንና እነሱን ለማጠናቀቅ ተጨማሪ ውይይት እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡

ሙስና በኢትዮ ቴሌኮም

የውጭ ጋዜጠኞች የኅዳሴ ግድብ ጉብኝት - የማርታ ትውስታ

የኢትዮጵያ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽንስ ጉዳዮች ፅ/ቤት ተቀማጭነታቸው አዲስ አበባ የሆነ የውጭ መገናኛ ብዙኃን ወኪሎችን ወደ ኅዳሴ ግድብ ግንባታ ሥፍራ ወስዶ አስጎብኝቷል፡፡

ከጋዜጠኞቹ መካከል የአሜሪካ ድምፅ ዘጋቢዋ ማርቴ ፋን ደር ቮልፍ ተገኝታለች፡፡
ማርቴ ስለጉብኝቷ፣ ስላየችው፣ በኅዳሴ ግድብ ዙሪያ ስለሚሰማውና እርሷም ስለሚሰማት ከሰሎሞን አባተ ጋር ተጨዋውታ ነበር፡፡

 ሙሉውን የማርታ ትውስታ በተያያዘው የድምፅ ፋይል ውስጥ ያገኙታል፤ ያዳምጡት፡፡

http://amharic.voanews.com

የዘመኑ መንፈስ




በእውቀቱ ስዩም

ባገራችን ባሁኑ ጊዜ ብዙ ተከታይ ያለው ሃይማኖት ብሄርተኝነት ይባላል፡፡የብሄርተኝነት ምእመን ከሆንክ የነፍስ አባት ይኖርሀል፣በጭፍን የምትቀበለው ቀኖና ይኖርሀል፣ነገ የምትገባባት የተስፋ ምድር ይኖርሀል፣ከሁሉ በላይ ደግሞ ብርቱ ችግርህን የምትደፈድፍበት የመስዋእት በግ ይኖርሀል፡፡
ሃይማኖቶች ምእመናንን ብቻ ሳይሆን መናፍቃንንም ያፈራሉ፡፡ብሄርተኞች በስሜት የሚነድደውን ምእመን ብቻ ሳይሆን የኔ ቢጤውን መነፍቅም እንደሚያፈሩ አንርሳ፡፡በነገራችን ላይ ሃይማኖትን መካድ ማለት ሃይማኖት የሚያነሳቸውን አብይ ጥያቄዎች መካድ ማለት አይደለም፡፡እንዲሁም፣ ብሄርተኝነትን መካድ ማለት የኢትዮጵያን ብሄር ብሄረሰቦች ህልውና መካድ ማለት አይደለም፡፡በዚህ ጉዳይ ፣መናፍቅ መሆን ማለት፣ የብሄርተኛ ነቢያት ሰለ ጭቆና ስለ ነጻነት  ብሎም ስለ ኢትዮጵያዊነት የሚያቀርቡትን አጉል እምነት መጠራጠር ማለት ነው፡፡
ከኢትዮጵያዊነት እንጀምር፡፡
ከዘመናችን የብሔርተኝነት ነቢያት አንዱ ጃዋር መሐመድ በቅርቡ ከእንቁ መጽሔት ጋር ባደረገው ቃለመጠይቅ  ላይ ስለኢትዮጵያዊነት የሚከተለውን ይላል፡፡
‹‹…ኢትዮጵያን የመሠረታት የሶሰትዮሽ ጦርነት ግብግብ ነው፡፡በአማራው፣በኦሮሞው፣በትግሬው ግብግብ ውስጥ ወደ መጨረሻ ላይ በአመራር ስር የበላይነቱን የያዘው አማራው ነበር፡፡በዚህ የተነሳ አሁን የምናያት ኢትዮጵያ ማንነቷ በአማራ ባህላዊ ሥርጭት እና በአማራ ፖለቲካ የተገነባች ነች፡፡የኢትዮጵያ አገራዊ ማንነት የምንለው የአማራ ባህላዊ ማንነት ነው››
ጃዋር የኢትዮጵያን መሠረት የሦስት ብሄረሰቦች የስልጣን ግብግብ አድርጎ ወስኖታል፡፡ በመጀመርያ፣ ሌሎች  ብሄረሰቦች በግብግቡ ተሳትፎ እንዳልነበራቸው አድርጎ ማቅረቡ አንድ ጉድለት ነው፡፡ ግን ዋናው ቁምነገር ይሄ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ የግጭት ውጤት ብቻ እንደሆነች አድርጎ ማቅረቡ ነው ትልቁ ስሕተት፡፡ ሲጀምር፣ የግብግብ ታሪክ መሠረት ይንዳል እንጂ መሠረት አይገነባም፡፡ እንደኔ ግምት፣የኢትዮጵያ መሠረት የሆነው ብሄረሰቦች ለጋራ ሕልውና ሲሉ የሚያደርጉት የመደጋገፍ ታሪክ ነው፡፡
ዛሬ ዛሬ፣ ታሪክ ከላሾች፣የብሄሮችን ‹‹ግብግብ››ታሪክ ሞቅ አድርገው፣አኳሽተው ሲጽፉ፣የብሄሮች መደጋገፍ ታሪክን ግን ቸል ይሉታል፡፡ አለያም እጅግ በቀዘቀዘ ስሜት፣ በጥቂት መስመሮች ብቻ ጨረፍ አድርገው ያልፉታል፡፡ለነገሩ፣ከፋፋይነትን ብቸኛ ያስተዳደር ፈሊጥ አድርጎ የሚቆጥር ሰው በታሪክ ገጾች ውስጥ መመልከት የሚፈልገው ክፍፍልን ብቻ ነው፡፡ታሪክ ግን ብዙ በጎ የትብብር ገጠመኞችን መዝግቧል፡፡ለምሳሌ ጀግናው አጼ ዮሐንስ አራተኛ በበዛሬይቱ ኤርትራ  የግብጽን ወራሪ ጦር ድል የነሡት የትግራይ ጀግኖችን ብቻ አሠልፈው አልነበረም፡፡ በዚህ ጦርነት ከግብጽ ጎን ሆኖ፣የተዋጋው አሜሪካዊው ጋዜጠኛ ዊልያም ዴይ እንደመሠከረው ወልቃይቶች፣ጥልጣል የተባሉ የአፋር ንኡስ ክፍሎች፣የወረኢሉ ኦሮሞዎች ለንጉሰነገስቱ ድጋፍ ለማድረግ ተሸቀዳድመዋል፡፡በራስ ወሌ የሚመሩ የአማራ ወታደሮች ተሳትፈዋል፡፡የጎንደር ቀሳውስት ለጦርነቱ ድጋፍ ለማድረግ አድዋ ገብተዋል፡፡ የጎጃሙ ራስ አዳል የደርሼልሀለሁ አለኝታቸውን አሳይተዋል፡፡ የሸዋው ንጉስ ምኒልክ ሳይቀር በመቶ የሚቆጠሩ በቅሎዎችንና ማበረታቻ ልከዋል፡፡ ዝርዝሩን ማንበብ ለሚፈልግ Muslim Egypt Christian Abyssinia የተባለውን የዚህ ደራሲ ማስታወሻ  ገጽ 291-292 ያንብብ፡፡ መጽሐፉን በኢንተርኔት ቤተ-መጻህፍት ውስጥ በብላሽ ማግኘት ይቻላል፡፡

ከተለያየ መአዘን የመጡ እኒህ ኢትዮጵያውን ከዘመቻው የሚያገኙት ድልን ብቻ አልነበረም፡፡ በዘመቻ ወቅት ባህል ይዋዋሳሉ፣ቃላት ይወራረሳሉ፣ ስንቅ ያዋጣሉ፣ ልምድ ይለዋወጣሉ፡፡ በሂደት ተቃራኒ ከሚመስሉ ልማዶች የነጠረ ኢትዮጵያዊ ባህል  እንደ አረቄ ይወጣል፡፡ ይህን በመዋጮ የተገኘ ባህል ‹‹የአማራ ባህል ››ብሎ ማጥበብ የጸና ድጋፍ ያለው አይመስለኝም፡፡
ጃዋር‹‹አሁን የምናያት ኢትዮጵያ ማንነቷ በአማራ ባህላዊ ሥርጭትና በአማራ ፖለቲካ የተገነባች ነች›› በማለት ሳይወሰን ‹‹የኢትዮጵያ አገራዊ መለያ ማንነት የምንለው አማራ ብሄራዊ ማንነት ነው›› ሲል ይጨምራል፡፡ ጎበዝ ኧረ በህግ አምላክ!!! የኢትዮጵያ ባህልኮ ካንድ አለት የተጠረበ ሕንጻ አይደለም፡፡ ከብዙ የመዋጮ ጡቦች የተገነባ  ነው፡፡ ጃዋር እያንዳንዱን ጡብ ቀርቦ ቢመረምረው እዚህ የደረሰበት እርግጠኝነት ውስጥ የሚደርስ አይመስለኝም፡፡
እስቲ ከደቃቅ ምሳሌ እንጀምር፡፡ ኢትዮጵያን የማስተዋወቅ ስራ ሲሠራ አስቀድሞ የሚመጣው የቡና ስነ-ስራታችን ነው፡፡ አንዲት ጠይም ፣ባለሹርባ ሴት፣ያበሻ ቀሚስ ለብሳ  ቡና ስትቀዳ የሚያሳይ ምስል በየቦታው ማየት የተለመደ ነው፡፡ይህ ችክ ያለ ምስል በስነ-ስእል ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ ቢዮንሴና  ጆን ኬሪ አገራችንን በጎበኙበት ሰአት የቡና ስነስርአት ተሳታፊ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡ ይህ ማለት የውጭ እንግዳ የቡና  ስርአታችንን እንደ ኢትዮጵየዊ መለዮ እንዲመዘግብልን ፈልገናል ማለት ነው፡፡ ለዋለልኝ መኮንን እና ለጃዋር መሀመድ ይህ የአማራ ባህል መሆን አለበት፡፡ በመጀመሪያ እይታ ይመስላል፡፡ ጉዱ ዝርዝሩ ላይ ነው፡፡ የሴትዮዋ ሹርባ ከሐማሴን ወይም ከተንቤን ሴቶች ልማድ ጋር ስምም ነው፡፡ ያበሻ ቀሚሱን የሽሮሜዳ ጋሞ የሸመነው ሊሆን ይችላል፡፡ ጀበናው የጂማ ሙስሊም ኦሮሞዎች ያስተዋወቁት ነው፡፡ አቦል ቶና በረካ አረብኛ ወይም የተወላገደ አረብኛ የተገኙ ቃላት ናቸው፡፡ ዛሬ በክርስቶስ ትንሳኤ በአል በሉባንጃ የሚታጀብ ቡና የማያፈላ ክርስትያን ኢትዮጵያዊ ማግኘት ይከብዳል፡፡ ከጥቂት መቶ አመታት በፊት ግን ቡና የእስላም ልማድ  ተደርጎ ይቆጠር ነበር፡፡ የቡና ትርኢት የሙስሊም አበው በኢትዮጵያ ባህል ላይ የጨመሩት በጎ መዋጮ እድርገን ልንቆጥረው እንችላለን፡፡ ኢትዮጵያ  ጊዜ በተባለው አናጢ  ከብዙ ጡቦች የተገነባች ናት የምንለው ለዚህ ነው፡፡

ጃዋር አማራው የራሱን ባህል በኦሮሞው ላይ እንደጫነ ሲያምን ተገላቢጦሹ ያለው አይታየውም፡፡ ኦሮሞ በረጅም ዘመን፣በሠፊ ምድር፣ ሰፍሮ የመኖሩን ያክል በጎረቤቶቹና በወደረኞቹ ላይ የባህል ተጽእኖ አላሳደረም ማለት ብርቱ ባህል የለውም ከማለት አይለይም፡፡ ባገራችን ዋና ዋናዎቹ የባህል ቀራጺዎች ጦርነትና ሐይማኖት ናቸው፡፡ ለምሳሌ ፣ጀግኖችን እና ነገስታትን አባ በዝብዝ አባ ታጠቅ፣ አባ ዳኘው አባ ነጋ ወዘተ እያሉ መሰየም ገናና ኢትዮጵያዊ ባህል መሆኑን ብዙዎቻችን እናውቃለን፡፡ ብዙዎቻችን የማናውቀው ይህንን ባህል ያስተዋወቁት ለግማሽ ምእተአመት ያክል ኢትዮጵያን ያስተዳደሩት የየጁ ኦሮሞዎች መሆናቸውን ነው፡፡ ብላቴን ጌታ ማህተመ ሥላሴ ወልደ መስቀል በለው በተሰኘው መጽሐፋቸው ይህንን እንዲህ በማለት ያረጋግጣሉ-
‹‹ነገስታቱ ‹‹አባ›› ወይም የእገሌ ባለቤት በሚል ቅጽል ስም መጥራት የጀመሩት የኦሮሞዎችን ወይም የወረሸሆችን ልምድ በመከተል ነው 1838 ዓም ወዲህ እንደሆነ ታሪክ ይነግረናል፡፡ ወትሮ ግን በተለይም 1474-1713 ዓም ባለው ጊዜ ውስጥ ቅብዓ መንግሥቱ በሚደረግላቸው ሰአት ይወጣላችው የነበረው የግርማ ስም ወይም ስመ መንግስት ‹‹ሰገድ›› የሚል ኃይለቃል በመጨመር እንደነበር ቀጥሎ ያለው ያረጋግጣል፡፡ ወናገድ ሰገድ፣ አጽናፍ  ሰገድ፣ አድማስ ሰገድ፣ መለክ ሰገድ፣አድያም ሰገድ ሉል ሰገድ››በማለት ይዘረዝራሉ፡፡
ከጥቅሱ ሦስት ፍሬ ነገሮችን መረዳት ይቻላል፡፡
1- ይህ ባህል ባንድ የዘመን ምዕራፍ ላይ ከኦሮሞ ብሄረሰብ የመነጨ የኢትዮጵያ ባህል ነው፡፡
2- ባህሉ ብርቱ ተጽእኖ ከመፍጠሩ የተነሳ አማራና ትግራይ ነገስታት ለረጅም ዘመን ይጠቀሙበት የነበረውን የስያሜ ዘይቤ ሽሯል፡፡
3- አማራው ታሪክ ጸሀፊ ለባህሉ አስተዋዋቂዎች የባለቤትነት እውቅና ሰጥተዋል፡፡


በሃይማኖት ረገድም ተመሳሳይ ነገር ነው የሚገጥመን፡፡ ለምሳሌ አቴቴ የሚለውን ቃል ደስታ ተክለወልድ ሲተረጉሙ ‹‹ዛር፣በሴት ስም የምትጠራ፣ ውቃቤ አማሮች ከኦሮሞዎች የወረሷት ጨሌ የሚያጠልቁላት አቴቴ ጊንቢ ሐራ አቴቴ ዱላ እያሉ እንቀት የሚቀቅሉላት አምልኮ ባእድ፣ትርጓሜ ጠባቂ ማለት ነው››ይላሉ፡፡
‹‹አምልኮ ባእድ ››የሚለውን አሉታዊ ሐረግ፣የክርስትያን አድልኦ ያለበት ፍርድ አድርገን እንለፈው፡፡ ዋናው ፍሬ ነገር፣ የአሮሞው ባህል  በአማራው  ባህል ላይ ተጽእኖ ማሳደሩን ማወቃችን ነው፡፡ ይህም አንዱ ብሄረሰብ ሁልጊዜ ጫኝ ሌላው ብሄረሰብ  ሁልጊዜ ተሸካሚ እንደነበረ አድርገው ሊነግሩን የሚፈልጉትን ሰዎች ያስተባብላል፡፡ በሁለቱ ግዙፍ ብሄረሰቦች መካከል የነበረው ግኑኝነት የእኩዮች ልውውጥ ነው፡፡ የባህሎች ውርርስ ነው ማለት እንችላለን፡፡ ነገርን ነገር ያነሳዋልና፣ የማንኩሳ ዘመዶቼ የሚያስደነግጥ ነገር ሲገጥማቸው ‹‹አቲቲን ወሰድከው›› ይላሉ፡፡ ቀልቤን ገፈፍከው ለማለት ነው፡፡ የኦሮሞ ባህላዊ ተጽእኖ በወለጋ ድንበር ላይ ቆሟል ያለው ማነው?

ስለጉዲፈቻ ባህል ብዙ ሰዉ የሚያውቅ ይመስለኛል፡፡ በጦርነት ወቅት ምርኮኞችን ባርያ ማድረግ ወይም መግደል በብዙ ማህበረሰቦች የተለመደ ነው፡፡ በኦሮሞ አበዋዊ ባህል ውስጥ ግን ምርኮኞች በልጅነት ይታቀፋሉ፡፡ ከሌላ ብሄረሰብ ቢመጡም የኦሮሞ ብሄረሰብ የሚያገኘውን መብት ሳይነፈጋቸው ያድጋሉ፡፡ ይህንን ልማድ በአማራው ማህበረሰብ ውስጥም እናገኘዋለን፡፡ ለምሳሌ በጎጃሙ ንጎስ ተክለይማኖትና በወለጋ መሳፍንት መሀል በተደረገው ጦርነት የተማረከው ብላቴና ነገሮ ዋቅጅራን እንደልጅ አሳድገውታል፡፡ ክርስትና አስነስተው ተክለኢየሱስ አሰኝተውታል፡፡ ራሱ በጻፈው ማስታወሻ ‹‹በጠጅና በስጋ አደግሁ›› በማለት የመሳፍንት ልጆች ያገኙት የነበረውን ምቾት ሳይነፈገው ማደጉን ይመሰክራል፡፡ ነገሮ ከማእረግ ወደ ማእረግ እየወጣ የንጉሱ ጸሐፌ ትዝዛዝ እስከመሆን ደርሷል፡፡ ተመሳሳይ መልኩ  በሸዋ ምርኮኛው ቆሴ ዲነግዴ በቤተመንግስት እየተቀማጠለ አድጎ ሐብተጊዎርጊስ በሚል ስመ ክርስትና የኢትዮጵያ የጦር ምኒስትር እስከመሆን ደርሷል፡፡ ሰዎችን በልዩ ቋንቋቸው ምክንያት ባይተዋር ማድረግ ኢትዮጵያዊ ባህል አልነበረም፡፡

እኩዋን ባህላችን አማርኛችን እንኳ የጉራማይሌነታችን ምስክር ነው፡፡ አሁን ኦሮምኛ ያልተነካካ አማርኛ ማግኘት  ይቻላል?፡፡ እሰቲ ለናሙና ያክል ‹‹ተወርዋሪ ኮከብ›› ከተባለው የዮሐንስ አድማሱ ምርጥ የአማርኛ ግጥም ውስጥ ጥቂት መስመሮች ልቆንጥር፡፡
1 ተወርዋሪ ኮከብ በራሱ ነበልባል በራሱ ነዲድ ተቃጥሎ የጠፋ
ተወርዋሪ ኮከብ በምናውቀው ሰማይ ነበረ በይፋ
2ሜዳና ተራራ በመሐል ሸለቆ
ጨፌውና መስኩ በኒህ ተደብቆ
3 ሐቀኛ ጠፍቶበት በዋለበት መልቲ
ጌጥ ነው ድንቁርና የገዳዮች ሎቲ
4 ብልጭ ብሎ ጠፋ
ተወርዋሪ ኮከብ የሐሳብ አንጋፋ
በመረጥኳቸው መስመሮች ውስጥ የሚገኙት ‹‹ይፋ፣ ጨፌ፣ መልቲ፣ ሎቲ፣ አንጋፋ፣›› የተባሉት ቃላት ኦሮሚኛ ናቸው፡፡ ካንድ የአማርኛ ግጥም ይህን ያህል ኦሮሚኛ ከተገኘ በሙሉ መዝገበ ቃላት ውስጥ ምን ያህል ሊገኝ እንደሚችል አስቡት፡፡ ይህን ያክል ነው የተዋሀድነው፡፡
የኢትዮጵያ ባህል የተውጣጣ ባህል እንጂ ጃዋር እንደሚለው የአማራ ባህል ብቻ አለመሆኑን በመጠኑም ቢሆን ያሳየሁ ይመስለኛል፡፡ ጃዋርን እዚህ ላይ ላሰናብትና ለማጠናቀቂያ የምትሆን አንዲት አንቀጽ ልጨምር፡፡
ባህልን ማክበር ጥሩ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በስሜት ሚነድደው የብሄርብሄረሰብ ፖለቲካችን፣ ዜጎች ለባህል ያላቸውን ፍቅር ወደ ጭፍን አምልኮአዊ ፍቅር እያዘቀጠው ነው፡፡
ባባቶቻችንና በእኛ መካከል የባህል ፋይዳ ልዩነት ያለ ይመስለኛል፡፡ አባቶች ባህላቸውን ያገኙት በኑሮ ጣጣ አስገዳጅነት ነው፡፡ ለምሳሌ የኔ አያት ቁምጣ ሱሪ የሚታጠቀው ከሌሎች ብሄረሰቦች ለየት ብሎ ለመታየት አይመሰለኝም፡፡ በቂ አቡጀዲ ስላላገኘ ነው፡፡ ወይም ለስራ እንዲያመቸው ባጭር መታጠቁ ይሆናል፡፡ እኔ ግን የብሄረሰቦች ቀን ሲከበር ቁምጣ ለብሼ ራሴን በማስጎብኘት እንድኮራ ይጠበቅብኛል፡፡ ጉድ እኮ ነው!!! ጋቢ በጥንት ጊዜ የሙቀት ምንጭ ነበር፡፡ ዘንድሮ የኩራት ምንጭ ሊሆን ይቃጣዋል፡፡
የዛሬዎቹ ባህል አምላኪዎች ባህል ሲያስቡ ለውጥን ይረሳሉ፡፡ ባንድ ወቅት የሚያኮራው ያንድ ብሄረሰብ ባህል በሌላው ወቅት ይናቃል፡፡ ባንድ ወቅት የሚያስሸልመው በሌላ ጊዜ ያስቀጣል፡፡ ከጥቂት መቶ አመት በፊት ዝሆን መግደል በማህበረሰቡ ዘንድ ትልቅ ከበሬታ የሚያጎናጽፍ ተግባር ነበር፡፡ ዝሆን የገደለ ልዩ አምባር ክንዱ ላይ ያጠልቃል፡፡ እስኪ ዛሬ ያባቶቼን ባህል ለማክበር ነው ብለህ  ፓርክ ውስጥ አርፎ የተኛውን ዝሆን ግደል፡፡ በአምባር ምትክ ካቴና ይጠልቅልሀል፡፡
የብሄር ብሄረሰቦች አልባሳት የተባለውን የተደጋገመ ግን ያልታሰበበት ቃል ከዚህ አንጻር ቃኙት፡፡ ሲጀምር ፣ዛፍ እንኳ ቅርፊቱን በሚቀያይርበት ዓለም፣ብሄር ብሄረሰቦች በየጊዜው አልባሳታቸውን አይቀያይሩም ወይ?፡፡ የብሄረሰቡ አልባስ ሲባል በየትኛው ዘመን የሚለበሰው ነው? የእንዳለጌታ ከበደ እናት ሲነግሩን፣ ዛሬ በጉራጌ ዘፈን ላይ በቲቪ የምናየው የሴቶች ሻማ ቀሚስ በደርግ ዘመን የተጀመረ ነው፡፡ ከዚያ በፊት የነበረው ሸማ ነው፡፡ ከሸማው በፊት ደግሞ የቆዳ ቀሚስ ይለበስ ነበር፡፡
ሌላው፣  አንድ ማህበረሰብ አልባሳት በየማእረጉ ልዩ ልዩ ልብሶች ይኖሩታል፡፡ ወታደሩ ያባ ገዳውን ልብስ የሚለብስ አይመስለኝም፡፡ ባሮች ከጌቶች ልብስ ጋር የሚመሳሰል ልብስ እንዲለብሱ አይፈቀድላቸውም ነበር፡፡ በፊውዳል ማህበረሰብ ከላይ አስከታች መልበስ መከናነብ የጨዋነት ምልክት ነው፡፡ ይህንን በሸዋና በትግራይ ብቻ ሳይሆን በቅድመ ምኒልክ ከፋ ውስጥ እናገኘዋለን፡፡ ባንጻሩ፣ባሮች  በከፊል ተራቁተው መታየት አለባቸው፡፡ ባጠቃላይ በኢትዮጵያ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ አለባበስ በበሄረሰብ ላይ ሳይሆን በመደብ ላይ የተመሰረተ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ስለዚህ የብሄር አልባሳት የሚባለው እንደ ማንኛውም ሾላ በድፍን ሐሳብ በጥርጣሬ መታየት አለበት፡፡
ትውልዱ የባህል ፈጣሪ መሆን ሲገባው፣የባህል ሙዚየም ሆኖ ተተክሏል፡፡አፈወርቅ ገብረኢየሱስ ባንድ ወቅት እንዳለው ‹‹ካባቶቹ የማይበልጥ ትውልድ፣ እንዳልተፈጠረ ይቆጠራል››
ማሳረጊያ

ኢትዮጵያን አንድ አድርጎ ያቆያት የነገስታቱ ጉልበት ብቻ ነው ብለው የሚያስቡ ሰዎች ኢትዮጵያ የተሸመነችበትን ውስብስብ ክር ማየት ያልታደሉ ናቸው፡፡ዛሬ ኢትዮጵያን በታትነን ክልላችንን እናድናለን ብለው ባደባባይ ሳያፍሩ የሚናገሩ ሰዎችን የምናይበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡በርግጥ ኢትዮጵያ ማእበል ከበረታባት እንደ ታይታኒክ ትሰጥም ይሆናል፡፡ግን መርከቢቱ ስትሰጥም የመርከቢቱ ሳሎን ብቻውን አይንሳፈፍም፡፡የመርከቢቱ ጓዳ ብቻውን አይተርፍም፡፡ኢትዮጵያ ስትከስም ብሄሮች ተነጥለው ይለመልማሉ ማለት ተፈጥሮ አመሏን እንደ ግትቻ የትም ጥላለች ማለት ነው፡

http://borumeda.blogspot.com/