Tuesday, July 2, 2013

ገብረክርስቶስ ደስታከዐፅም ጋር ጨዋታ! (አይቀርብህም ወይ፣ ከሞት ጋር ትንቅንቅ) ሰለሞን ተሰማ ጂ


ገብሬ፣ ምን ዓይነት ሰው እንደነበረ የማያውቁ ጥቂቶቹ አይደሉም፡፡ ግን-ግን ማን ነበረ-ገብሬ? ከዐፅም፣ ከልደት፣ ከስደት እና ከሞት ጋር ምን ምስጢር ነበረው? “ከዐፅም” ጋር በስንኞቹ ለመነጋር፣ “ከዐፅም” ጋር በስዕሎቹ ለመመሳጠር ምን አሰኘው? ከሰው የተለየ ምን ተዓምር ነበረው? ከጠፈር፣ ከባዕድ አገር፣ ከእናት አገር፣ ከከበሮ፣ ከክራር፣ ከከተሜና ከባላገር ጋር የሚያዋየው ምን ጉድ ነበረው? በዚህ ጽሑፋችን፣ እነዚህንና ሌሎቹንም የገብሬን ሰብዕና ገላጭ የሆኑ ርዕሰ-ጉዳዮች በአንክሮት እንመረምራለን፡፡. 

መግቢያ፤
ሁላችንም ነገ ሟቾች መሆናችንን አሳምረን እናውቃለን፡፡ ስንሞትም በባሕላችን መሠረት፣ ከክርስቲያን ወይም ከሙስሊም መቃብር (ወይም “ጓሮ”) መቀበራችንንም እናምናለን፡፡ ግና፣ ያላረጋገጥነው ነገር ቢኖር፣ ከሞት አድማስ ባሻገር መኖር ወይም አለመኖራችንን ነው፡፡ ገብረክርስቶስ ደስታ ገና በጠዋቱ፣ ገና በልጅነቱ ሞትን አሸንፎ እንዴት ኅያው መሆን እንደሚችል ማሰላሰል ያዘ፡፡ ገና በልጅነቱ፣ ሥራው ሁሉ ስለሞት ማውጠንጠንና መመራመር ሆነ፡፡ 
በምድረ ኢትዮጵያ፣ ሞት ብዙዎቹን አሰቃይቶና ገድሎ፣ ዐጽማቸውን መዘባበቻ፣ አስክሬናቸውን መላቀሻ ሲያደርገው ለዘመናት ኖሯል፡፡ ገብረክርስቶስም ይሄንን ግፍ፣ የሞትን በኢትዮጵያውያን ላይ እንደልቡ መንፈላሰስ በዐይኑ አይቷል፡፡ በልቡም ቂም ይዟል፡፡ ሞት፣ ገብሬ እንደሚጠላው ያውቀው በጣም ዘግይቶ ነው፡፡ ቆይቶ፣ በጣም ቆይቶ—ገብሬ ሊያዋርደው የተፈጠረ “አበሻ” እንደሆነ ገባው፡፡
ገብሬ ማነው?
በጥቅምት 5 ቀን 1924 ዓ.ም ከአባቱ ከአለቃ ደስታ ነገዎና ከእናቱ ከወ/ሮ ዐፀደማርያም ወንድማገኘሁ በሐረር ከተማ (በተለምዶ “ሚካኤል ጓሮ”) እየተባለ በሚጠራው ቦታ ተወለደ፡፡ ከቤታቸውም ፊት-ለፊት፣ ከሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ጀርባ ያለ ነው፣ ሰፊ የክርስቲያኖች መቃብር ሥፍራ አለ፡፡ ግንብ የሌለው፡፡ አጥርም የለውም፡፡ ገብሬም በሕፃን እግሩ ድክ-ድክ ብሎ፣ በልጅነት ዐይኑ ተገርሞ፣ እነዚህን ቀብሮችና ቀባሪዎች፣ የመቃብር ሐውልት ቀራፂዎችና ከልብ አዝነው የሚንሰቀሰቁትን ሐዘንተኞች እያየ አደገ፡፡ ሞትን መጋፈጥ እንዳለበትም ወሰነ፡፡ 
ግና፣ ሞትን እንዴት በድል አድራጊነት መጋፈጥ እንዳለበት አላወቀምና ተጨነቀ፡፡ ተሳቀቀ፡፡ ያ! ሞት የሚባለው መርገምትም፣ ይባስ ብሎ እናቱን ገና የሦስት ዓመት ከ6 ወር ህፃን እያለ እንደነጠቀው አውቋል፡፡ ሞትም የተፈጠረውን ሁሉ እንደመከር ሰብል ማጨድ ያዘ፡፡ ገብሬን ተስፋ ለማስቆረጥ አስቦ ነበር፡፡ ምኞቱን ለማጫጫት፣ ሕልሙን ለመስረቅ፣ ወኔውን ለመስለብ ብሎ ሞት ጨከነ፡፡ 
በ1927 አጋማሽ ላይ የወልወል ግጭትን ምክንያት አድርጎ፣ የጣልያን ወራሪ ጦር ገሚስ ሐረርጌን ያዘ፡፡ ሞትም፣ በጣልያኝ ጠብመንዣ ወይም ሽጉጥ፣ ወይም ከመርዝ ጋር ገብሬንና ዘመዶቹን ሊረፈርፋቸው ወሰነ፡፡ ብልሁ የገብሬም አባት፣ ገብሬንና ሌሎች ልጆቻቸውን አስከትለው ወደ አዲስ አበባ ሸሹ፡፡ ሞት እየተናደደም፣ እየተማረረም፣ ከዐይኑ የተሰወረውን ገብሬን ለሁለት ዓመታት ያህል ሲያድነው ቆየ፡፡ በየካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም ላይም በአዲስ አበባ ከተማ፣ በሩዶልፎ ግራዚያን ጭፍጨፋ ወቅት ሊያስገድለው ቀነ-ቀጠሮ ቆረጠ፡፡ ሞትንና ጠረኑን የሚያውቀውም የአምስት ዓመት፣ ከአራት ወር ከሰባት ቀኑ ገብሬም፣ አልጋ ሥር ገብቶ፣ ያንን ተናዶ የነበረውንና ጨካኑን መልዓከ-ሞት አመለጠው፡፡ ሦስት ቀን ሙሉ ገብሬን የሚያገኝ መስሎት፣ ከአስከሬን ላይ ዐይኑን ጎልጉሎ፣ ከአሁን-አሁን አገኘሁት ሲል ሰነበተ፡፡ ገብሬንም ሳያገኘው ስለቀረ፣ “በቃ ሞቷል! አረፍኩ!” ሲል ተፅናና፡፡ 
ገብሬ ግን፣ በፋሺስት ታስረው የተጋዙት አባቱ በ1933 ዓ.ም እስኪፈቱ ድረስ፣ ጣሊያኖቹ ለዓላማቸው ማሰራጫ በከፈቱት (ቢላላ) በሚሰኘው የጣሊያኖች ትምህርት ቤት ውስጥ ገብቶ የጣሊያን ትምህርት እየተማረና (ጥቁሯ እመቤት) የተባለውን መዝሙራቸውን እንዲዘምር ስለተገደደ፣ እየዘመረ ነበር፡፡ ነፃነት ተመልሶ፣ ንጉሠ ነገሥቱ በሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም አዲስ አበባ እንደገቡ ሰሞን፣ ገብሬና አባቱ ወደ ሐረር ተመለሱ፡፡ ለጥቂት ዓመታትም እዚያው ቆዩ፡፡ አባቱም የቀድሞ ሥራቸውን ቀጠሉ፡፡ መጽሐፍ መደጎስ፣ ቤተ ክርስቲያን ማገልገል፣ ሥርዓተ-ቀብር ማሳረግ፣ ሌላም-ሌላም፡፡ ህይወት፣ እንደቀድሞዋ መፍሰሷን ቀጠለች፡፡  
አንድ ቀን ለቀስተኞች ሲያዝኑ ቄሱም—አባ ደስታ ነገዎ ሲያሳርጉ ሳለ፣ በድል አድራጊነት ዐይኖቹን በልጥጦ በሰው ልጅ ላይ ሲሳለቅ የነበረውን ሞት፣ ገብረክርስቶስ የአባቱን ካባና ድጉስ መጽሐፍት ሊቀበላቸው ሲመጣ አይቶት ክው-ብሎ ደነገጠ፡፡ “አንተ ሞገደኛ! አንተ ቱማታ! አለህ ለካ!” ሲልም ንዴት በተቀላቀለበት አስደንጋጭ ድምፁ ለራሱ ወላፈተ፡፡ ሞትም፣ “ቆይ ባልሰራልህ”  ሲልም ሰይጣናዊ ፈገግታውን ፈገገ፡፡ 
ገብሬ ግን፣ ሞት፣ ለቅሶ፣ ቀብር፣ ማሳረግ፣ ዝክር፡፡ አሁንም ሞት፣ አሁንም ለቅሶ፣ አሁንም ቀብር፡፡ የቀሳውስቱ ማሳረጊያ፣ የሰባት፣ አስራ ሁለት፣ የአርባ ቀን፣ የሰማኒያ ቀን፣ የሙት  ዓመት፣ የሰባት ዓመት፣… ዝክር-ዝክር-ዝክር፡፡ እንዴት ሞትን የልብ-ልብ እንደሰጠው መርምሮ ተረዳ፡፡ ከዚያም ሞትን እንዴት ሊያሸንፈው እንደሚችልና ድል እንደሚያደርገው ሲያወጣና ሲያወርድ ከረመ፡፡ 
በፈረንጆቹ አገር፣ ብዙዎች ሞትን እንዴት አሰቃይተው እንደገደሉት ማጥናት ጀመረ፡፡ ሆሜር ሄድስ፣ ኤዞብ፣ ሶፎክለስ፣ ዩሪፒደስ፣ ሴኔካ፣ ቾሰር፣ ቦካሺዬ፣ ፔትራርች፣ ሼክስፒር፣ ሚካኤል አንጀሎ፣ ሊኦናርዶ ዳቬንቺ፣ ኢማኑኤልና ፒካሶ (ከገጣሚዎቹና ከሰዓሊዎቹ መካከል) ሞትን እንዴት አድርገው በቁሙ እንደገደሉት አነበበ፡፡ በተለይም ከ1933 ዓ.ም እስከ 1938 ዓ.ም ድረስ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በራስ መኮንን ት/ቤት ሲከታተልና፣ ከ1940 ዓ.ም እስከ 1943 ዓ.ም ድረስ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በጀኔራል ዊንጌት አዳሪ ት/ቤት እየተከታተለ ሳለ፣ ከቀለም ትምህርቱ ጎን-ለጎን ስለ ጥንታዊውና ዘመናዊው የአውሮፓ ሥነ-ጽሑፍና ሥነ-ጥበብ ታሪክ በሰፊው ለማንበብና ለማጥናት ቻለ፡፡ የገብሬ ወርቃማ የልጅነትና የወጣትነት ወቅትም በቀለም ትምህርት፣ በግል ንባብ ጥረት፣ በስፖርታዊ ልምምድ-ትጋት ጣፋጭ ሆኖ አለፈ፡፡ 
ከዊንጌት ቆይታው በኋላ (ከ1944-1948 ዓ.ም) ድረስ ባሉት አምስት ዓመታት ውስጥ ገብሬ የአሳርና የመከራ ተከታታይ ዓመታትን ፉት አለ፡፡ በተለይም፣ በገብሬ ህይወት ውስጥ ጉልህ ተጽእኖ ያላቸው ወላጅ አባቱ፣ አለቃ ደስታ ነገዎ፣ በመስከረም 21 ቀን 1947 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡ ገብሬም ሞትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አምርሮ ጠላው፡፡ በሞትም ላይ ደረቱን ገልብጦ፣ ትከሻውን ሰብቆ፣ ብዕሩን አንቆ፣ ሃዘኑን ሳይሆን ቁጣውን፣ ሙሾውን ሳይሆን ፌዙን እንዲህ ሲል ይደረድረው ጀመረ፤
   …...ግማሽ ቀልድ አላውቅም
ሞት እንደሆን ልሙት፣ በሴኮንድ መቶኛ
እንቅልፍ እንደሬሳ፣ ዘላለም ልተኛ፡፡
መንገድ ስጡኝ ሰፊ፣
ከሲኦል ሚሊዮን፣ ቢሊዮን ብቃጠል
ከገሀነብ እሳት ሚሊዮን ነበልባል፡፡
መንገድ ስጡን ሰፊ፣
ስሄድ እኖራለሁ፤
ሰማየ-ሰማያት እመዘብራለሁ፡፡
የተዘጋውን በር፣ እበረግዳለሁ፡፡
የሌለ እስቲፈጠር፣ የሞተ እስቲነቃ፣
በትልቅ እርምጃ፣ ከመሬት ጨረቃ
ስጓዝ እኖራለሁ!
(ገብረክርስቶስ ደስታ፣ “የጠፈር ባይተዋር”)
በገብሬ ውብ ቋንቋ፣ በገብሬ ድፍረት ሞት ተከነ፡፡ ተናደደ፡፡ ብዙዎች የሚፈሩትን ሞት፣ ገብሬ “ግማሽ ቀልድ ነህ” ሲል ዘበተበት፡፡ ብዙዎች የሚፈሩትንም ሲኦል፣ ገብሬ “በሴኮንድ-መቶኛ” “በሚሊዮንኛ”፣ ሲያስፈልግም “በቢሊዮን እጥፍ ና” እኔ ምን ተዳዬ-ሲል አናናቀው፡፡ ሞትም የመልስ ምት ሊሰጠው አስቦ፣ ታላቅ እህቱንና ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ በልቡ ውስጥ ነግሳ የነበረችውን ፍቅረኛውን ነጠቀው፡፡ ሞት፣ እልህ ይዞትም፣ የአራት ታላቅ ወንድሙ የሆነውን በ1950ዎቹ ውስጥ ነጠቀው፡፡ ገብሬም የሞትን ሕልውነት ፈፅሞ ማስተባበሉን ገፍቶበት ኖሮ፣ “ለአባቴ” ባለው ግጥሙ ውስጥ እንዲህ ሲል ተቀኘ፡፡
ታውቃለህ ብዙ ነው፣ መንገዱ ብዙ ነው፡፡
ሞት እንደንቆቅልሽ
ጅምሩ-ማለቂያው፣ መካከሉ ዳር ነው፡፡
ዐይን የማይጨበጠው፣
ሕይወትን ሲያነቡት፣ ወደ ግራ ሞት ነው፡፡
(ብለህ ነግረኸኛል፡፡)…..
ሳቅ፣ አሁንም በሞት፣
(እዚህ የሌለ ሳቅ)
በጸጥታው ቦታ፣ ሙዚቃ ሁንበት!
(ዝም ያለ ሙዚቃ!!!)
ለሟች አባቱ ቅኔ እየደረደረ የተጋፈጠውን ሰው፣ የሞት-ደመኛውን ገብሬን፣ ሞት አዘናግቶ ሊገለው/ሊቀጨው አደባ፡፡ የሬሳ ሳጥንም ገዝቶ ይጠብቀው ጀመር፡፡ ገብሬም ሞትን በባዮሎጂ ትምህርቱ አማካኝነት ሊጋጠመውና ሊያሸንፈው ከጅሎ የባዮሎጂ ተማሪ ሆነ፡፡ ከሦስት ሴሚስተር በኋላ ግን፣ ስሜት አልሰጥህም ቢለው ጊዜ ጥሎት ወጣ፡፡ ሞት፣ በገብሬ ውሳኔ ግራ ተጋባ፡፡ “ምን አስቦብኝ ይሆን?” ሲል ተጨቀ፡፡ ገብሬም እንደምድራዊ መለኮት የሚያያቸው አባቱ፣ በልጅነቱ ያስተማሩትን የቀለም ቅብ፣ የመጽሐፍት ድጎሳና ቅርፃ-ቅርጽ ሙያ ሊቀጥለው ፈለገ፡፡ የአባቱን ፈለግ ተከትሎም ሊገፋበት ወስኖ፣ በ1943 ዓ.ም ከዊንጌት ቆይታው በኋላ ትቶት ወደ ነበረው የነፍስ-ጥሪው ተመለሰ፡፡ በአጭር ጊዜም፣ ዝናንና ክብርን ተጎናፀፈበት፡፡
በ1953 ዓ.ም በወርኃ የካቲት ወደ ጀርመን ሀገር የቦን ከተማ ከተለያዩ የጀርመን፣ የፈረንሳይ፣ የሩሲያና የሌሎች ሀገሮች ሰዓሊያን ጋር በቡድን የሥዕል ትርኢቱን አቀረበ፡፡ ለዚህም ልዩ ተሰጥኦው፣ የጀርመን መንግሥት የአንድ ዓመት የነፃ መኖሪያና የስቱዲዮ ፈቃድ ሰጠው፡፡ (ሞት፣ በሳጥኑ ጠርዝ ላይ ተቀምጦ-አጓራ፡፡ የደም-ግፊቱ እስኪነሳበት ድረስ አንዘፍዛፊ ብስጭት ያዘው፡፡) ገብረክርስቶስ ደግሞ በግጥሞቹ ኪነታዊ ቃላት ሲተገትገው የነበረውን ሞት በብሩሹ፣ በቀለሙ፣ በሸራውም ላይ አሰቃይቶ መቀጣጫ አድርጎት ሊያሳየው ፈለገ፡፡ ስለዚህም ዘመናዊውን የአውሮፓ የጥበብ መንፈስና የአሠራር ስልት ያጠና ጀመር፡፡
የኤክስፕሬሽኒዝምን የአሳሳል ስልትንም ከሚከተሉ ሌሎች ሰዓሊያን ጋር ተባብሮ በመስራት ሞትን ያሰቃየው ጀመር፡፡ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ዘጠና ውብ ስዕሎችና አይረሴ ግጥሞችንም ከሀገረ ጀርመን ሆኖ ያምጥ ጀመር፡፡ እንዲህ እያለ በረጅሙ ዘመረ፤
ለምለም ነው አገሬ፡፡
ውበት ነው አገሬ፣ ገነት ነው አገሬ፡፡
እዚያ ዘመድ አለ፡፡
ሁሉም የእናት ልጅ ነው፣
ሁሉም የአባት ልጅ ነው፣
ጠላትም አንዳንዴ፣ ይመጣል መቃብር
ባለጋራም ቸር ነው፣ ያገር ልጅ ሲቸገር፡፡
ብሞት እሄዳለሁ፤ ከመሬት ብገባ፤
እዚያ ነው አፈሩ፣ የማማ ያባባ፡፡
ስሳብ ሄዳለሁ፣ ቢሰበርም እግሬ
አለብኝ ቀጠሮ፣ ከትውልድ ሃገሬ
አለብኝ ቀጠሮ፤
ከትውልድ አገሬ፣ ካሳደገኝ ጓሮ፡፡” እያለ ተቀኘ፡፡
(ገብረክርስቶስ ደስታ “ሀገሬ”)
በስንኞቹ እንዳለውም፣ በመጋቢት ወር 1954 ዓ.ም ወደ ሀገሩ ተመለሰ፡፡ የመልኩንም ማማር፣ የወኔውን መጋል የተመለከተው አጅሬ ሞትም፣ የተቀመጠበትን የሬሳ ሳጥን ከፍቶ አየውና አኩርፎ ተኛ፡፡ ሸለብም አደረገው፡፡ ገብሬም በ1955 ዓ.ም በተከፈተው የሥነ-ጥበብ ትምህርት ቤት ገብቶ ወጣቶችን ማስተማር ጀመረ፡፡ በግንቦት 3 ቀን 1956 ዓ.ም የ27 ሥዕሎችን ኤግዚቢሽን በኤክስፕሬሽኒዝም የአሳሳል አቅጣጫ (ፈለግ) ተከትሎ አቀረበ፡፡ ሞት በእንቅልፍ ልቡ ሳለ “ለምጽ” የሚባል በሽታ ልኮ በአኳራጃዊ አሲዱ ፊቱን ሸለመው፡፡ ሞት ፈገግ አለ—በእንቅልፍ ልቡ እንዳለ፡፡
በዓመቱ በ1958 ዓ.ም ገብረክርስቶስ የቀ.ኃ.ሥ የሥነ-ጥበብን ሽልማት ሲሸለም፣ ሞት ከእንቅልፉ ባኖ ነቃና የገብሬን ንግግር በጥሞና አዳመጠ፡፡ ገብሬም፣ ጉሮሮውን ጠራርጎ መላ ኢትዮጵያውያን ከእንቅልፍና ከሞት ድብርት የሚቀሰቅስ አደገኛ ጥሪ አስተላለፈ፡፡ እንዲህ ሲልም ገብሬ፣“ክተት ሰራዊት!” አለ፡፡ ነጋሪቱንም ጎሰመ፡፡ “ሥልጣኔ ራሱ ታሪክ እንደመሆኑ መጠን፣ ውጤቱንና መጨረሻውን ለማየት የአንድ ወይም የሁለት ሰው ዕድሜ በቂ ላይሆን ይችላል፡፡ ግን አዳዲስ የሥልጣኔ በር መክፈት፣ የዛሬውን ትውልድ ለማነቃቃት ተገቢ ሲሆን፣ የመጪውን ትውልድ እርምጃም በቅድሚያ ማሰናዳትም ማለት ነው፡፡ አዳዲስ የሥልጣኔ መንገድ በሚከፈትበት ጊዜም ሁሉ፣ ምናልባት ብዙ ሰዎች ሊገባቸው የማይችል ሐሳብ ስለሚፈጠር አንዳንድ ተቃራኒ ድምፅ መሰማቱ አይቀርም፡፡” አለ፡፡ ሞት ግን፣ ራሱን ከሰማየ-ሰማያት ሊከሰክስ ደረሰ፡፡ መታገስ አቃተው፡፡….
ከ1969-1971 ዓ.ም ድረስ እንደ የመጀመሪያው “የብሔራዊ የሥዕል ጋላሪ” ሊቆጠር በሚችለው የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት የባህል አዳራሽ (ስቱዲዮ) ውስጥ፣ ገብሬ ተማሪዎቹንና ተከታዮቹን አስተባብሮ የስዕል አብዮት መራ፡፡ 1960ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ እየፋመና እየጋመ የመጣውን ሕዝባዊ አመፅ፣ መንፈሱን አትግቶለት ኖሮ፣ በአጽም ቅቦቹ አጀባቸው፡፡ (የፀጋዬን ገ/መድህን አጽም-በየገፁም በዚህ ወቅት ላይ ነበር የተመደረከው፡፡ ገብሬም፣ እነሊስትሮን፣ መልስ ወዳገርቤትን፣ የካቲት 12ን፣ ያለፈው መልካሙ ጊዜን፣ ሐረር ገበያን (መጋላ ጉዶ)ን፣ እኔ ነኝ ገብሬን፣ እኔ በገዛ እጄን፣ ጎልጎታን፣ ጃብሲዋን ልጃገረድ፣ ቀይ ብርሃንን፣ የድሆች ቤተሰብን፣ በራሪ ወፍን፣ በቁኔትን፣ ጠላቂ ጀንበርን፣ ፀደይና ሌሎችንንም ሥዕሎቹን ያካተተ (የ72 ስዕሎቹን ኤግዚብሽን) “አጠቃላይ የሥዕል ትርኢት” በሚል የመሰነባበቻ ርእስ፣ በ1969 ዓ.ም ማገባደጃ ላይ አቀረበ፡፡ ሞትም፣ በሬሳ ሳጥኑ ውስጥ ተኝቶ በአጉሊ መነፅሩ የአፅም ስብስብ የሆኑትን ረቂቅ ሥዕሎች እያየ አይኑን በልጥጦ ቀረ፡፡ “እንደ አንተ ያፌዘብኝ የለም! ቆይ ባልሰራልህ!” ሲልም ድምጹን አሰምቶ ዛተ፡፡
የመልዓከ-ሞትም ዛቻ የምር ሆኖ በ1970ዎቹ የተንቦገቦገውን የቀይ ሽብርንና የነጭ ሽብርን እልቂቶችን ይዞ ከተፍ አለ፡፡  በሸራው ላይ በሚስላቸው የአጽም ስዕሎቹ አማካይነት ደፍሮ ሲያላግጥበት የነበረውን ገብሬንም አምርሮ ጠላው፡፡ በዚህ የተቆጣውም ሞት፣ በመንግሥቱ ኃ/ማርያም፣ በሻለቃ ጌታቸው ሺበሺ፣ በሻምበል መላኩ ተፈራና “በአረመኔው” የአራት ኪሎው ከበደ-ተመስሎ በየጎዳናው ልጅ-አዋቂ፣ ወንድ-ሴት፣ የተማረ-ያልተማረ ሳይል፣ ኢትዮጵያን ከዳር እስከዳር በደም አበላ አጥለቀለቃት፡፡ ሞት ቀልድ አለማወቁን፣ ዲሞክራሲያዊ መብት አለማክበሩን፣ ለፍትህና ለሥርዓት አለመገዛቱን፣ ህዝባዊ መንግሥት እንዲቋቋም አለመፈለጉን በአረመኔዎቹ-የደርግ ሰው በላዎች መንፈስ ውስጥ ሰርጎ ኖሮ፣ መራራ ታሪካዊ ቁስልና ጠባሳ ጥሎ ሄደ፡፡
በሁኔታው ግራ የተጋባው ገብረክርስቶስም፣ በመስከረም 1971 ዓ.ም ግፍና እልቂት አላይም፣ ሞት ሲነግስ አልታዘብም ብሎ ወደ ጀርመን ተሰደደ፡፡ በልጅነቱ ያየውን የፋሽስቱን ግራዚያኒን ጭፍጨፋ፣ ሀገር-በቀል ቆዳና ተክለ-ሰውነት ተክኖ ሲንደላቀቅ ዳግመኛ አላይም፣ ብሎ ስደትን መረጠ፡፡ ሞትን ከማየት፣ የሚጠላውን የባዕድ አገር ኑሮ ያለውድ በግድ መረጠ፡፡ ምሬቱንም እንዲህ ሲል አዜመው፡፡

ያለቦታው ሔዶ ሰው የሚጋፋበት፣
ጥርስ ያልነቀለበት፣
እትብቱ ዘመዱ-ያልተቀበረበት፣
ባዕድ መሬት ባዕድ
ዐይኑ ውሃ ሆኖ ቦታው ጭጋግ ለብሶ፣
አገሩ እየዋኘ፣ ሔዶ ተመልሶ
አገሩ ናፈቀው
(ገብረክርስቶስ ደስታ“የባዕድ አገር”)
ብዙም ሳይቆይ ከጀርመን ወደ አሜሪካን ሄደ፡፡ እንደአጋጣሚ ይሁን ወይም ገብሬ ፈልጎት ባልታወቀ አኳኋን፣ በጊዜው አንድም ኢትዮጵያዊ ባልነበረበት የኦክላሆማ ከተማ መኖር ጀመረ፡፡ በልቡ፣ “የሞትን ዓለም ሞት ይገባት ይሆን?” ሲልም ጠየቀ፡፡ ሞትንም ያልናቀውን ያህል፣ ይህቺ የሞትና የእልቂት ዓለምም ሞት ይገባታል ሲል አብሰለሰለ፡፡ ሞትም ይበልጥ ተናደደ፡፡ ገብሬንም አምርሮ ጠላው፡፡ ይባስም ብሎ፣ “ይህችን ውብ ዓለም የሞት ዓለም ናት! ይላል እንዴ?” ሲል ለደርጎቹ አሳበቀ፡፡ ደርጎቹም በሀገር ክህደት ጠርጥረው እንደወገባቸው ቅማል ጠመዱት፡፡ ገብሬ ግን እንዲህ እያለ ይቆዝም ነበር—በብቸኝነት፡፡
ሰው-ሰው መሆኑን፣ የሚያሳውቅ ከሆነ፣
በጭካኔ ሞት፡፡
ኦ! ሞት ስጠኝ እስከ ዘላለም፤ የሬሳ ክምር መዓት!
የሰው ልጅ ጥፋት-መቃብር፤
የሰው ልጅ መኖር ወይም አለመኖር
የሠው ክፋት ትል-የማይሞት፤
የሰው ተንኮል መርዝ-የማይበገር
ጥቁር ቀይ፣ ቀይ ጥቁር!......
በገብሬ ብዕርና የብሩሹም ቀለም እጅግ የቆሰለው ሞት፣ በመጋቢት 21 ቀን 1973 ዓ.ም ጮቤ ረገጠ፡፡ ያን የተዳፈረውን፣ ያን ያፌዘበት፣ ያን ያላገጠበት- ገጣሚውና ሰዓሊው ገብረክስቶስ ደስታ ስለመሞቱ ዜና ሰማ፡፡ ጆሮውንም ኮርኩቶ አዳመጠ፡፡ ከንፈሩ- ደርቆ፣ ዐይኑን ተበልጥጦ የገብሬን አስክሬን ሳጥን ውስጥ ሲገባ እስከሚያየው ድረስ አላመነም ነበር፡፡ ሲገባም አየውና፤
“አንተም…. ገብሬ!” የጀመረውን ዐረፍተ ነገር መጨረስ አቅቶት፣ ተናነቀው፡፡ ገብሬም፣…..
ዐይን የማያየውን፣ ሐሳብ ያያል ሔዶ፤
እጅ የማይነካውን፣ ልብ ያንቃል አሳዶ፣
ተመለሽ አልልም
ጉዞ አይቋረጥም፡፡
ዓለም እያረጀ፣ ዓለም ይፈጠራል፣
አበባ በፍሬው፣ ሕይወቱን ያድሳል፡፡
የጽጌረዳ እሾህ፣ ያበባው ጠባቂ
ሣቂ ባክሽን ዓለም፣ እባክሽን ሳቂ!
ሲል፣ የገብሬ ግጥማዊ ድምጽ እንደነጎድጓድ አንባረቀበት፡፡ የተፈጠረውን ሁሉ ገና በአበባው፣ በማፍሪያው ወቅት የሚያጭደውም ሞት፣ በገብሬ ግጥም በሸቀ፡፡ “ሌላ ብላ! አንተ ገና በሦስት ዓመት ከመንፈቅህ፣ የሞትን ማሰቃያ መላ አሳደህ አግኝተህ የሸወድከኝ አንሶህ፤ ሌሎችንም ትቀሰቅስብኛለህ እንዴ ደግሞ!? አንተ የሸወድከኝ ይበቃኛል!” አለ-በምሬት፡፡ የድምፁ ቃና ከልብ ማዘኑን ያሳብቅበት ነበር፡፡ ይህንን ተናግሮ ሲያበቃም ሞት የመቀበሪያ ሳጥኑን በአክብሮት እየለቀቀ ሳይታወቀው በመንሽ ጥፍሩ ፊቱን ሞዠቀው፡፡ የተንጨፋረረ ፀጉሩንም ነጨው፡፡ በጣም ጥቂት የሆኑትን የገብረክርስቶስን ቀባሪዎች ተከትሎም ጉዞ ጀመረ፡፡ ወደ ባዕድ አገር የመቃብር ሥፍራ፡፡ አጅሬ ሞት—እንደዚያን ዕለት እጅግ አዝኖ፣ ተከፍቶና ቆዝሞ አይታወቅም ነበር፡፡
መዝጊያ
የገጣሚውና የሰዓሊው የገብረክርስቶስ “አፅም” በክብር ለሀገሩ ጥርኝ አፈር እንዲበቃ፣ ከተቻለም-ለገብሬ ልዩ ትርጉም ባለው “የሐረሩ የሚካኤል ጓሮ” ቢቀበር፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተከፈተለትን “የገብረክርስቶስ ደስታን የሥነ-ጥበብ ማዕከል” ምሉዕ ያደርገዋል፡፡ በሀገርም ውስጥ በውጪም ያለነው የከያኒው አድናቂዎች ተባብረን ገብሬን “አፅም” ከባዕድ አገር እናምጣው፡፡
http://semnaworeq.blogspot.com/

No comments:

Post a Comment