ሙዚቃ

Released by Six Degrees Records on the Meklit album We Are Alive, March 2014 http://meklitmusic.bandcamp.com/album... Directed by Pete Lee, Choreography: Shawnrey Notto, Dancers: Shawnrey Notto & Zeik McCarter Director of Photography: Drew Daniels
>

ከቅዱስ ያሬድ እስከ ኢህአዴግ

  አለማየሁ አንበሴ


ከቅዱስ ያሬድ እስከ ኢህአዴግ
“የኢትዮጵያ ሙዚቃ፤ ኢንዱስትሪ መሆን አልቻለም ተባለ”
የአሁን አዝማሪዎች አስመሳይነት ይንፀባረቅባቸዋል”

  “የሙዚቃችን እድገት ለሃገር ልማት” በሚል መሪ ቃል የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማህበር ጋር በመተባበር ባለፈው ረቡዕ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቤተ መፃህፍትና ቤተ መዛግብት ኤጀንሲ በተዘጋጀ ፕሮግራሞች ላይ ሁለት ሙዚቃ - ተኮር ጥናታዊ ፅሑፎች ቀርበዋል፡፡
የመጀመሪያውን ጥናት “የኢትዮጵያ ሙዚቃ ከየት ወደ የት” በሚል ርዕስ ለታዳሚው ያቀረበው የሙዚቃ ባለሙያው ሰርፀ ፍሬስብሃት ሲሆን የኢትዮጵያን ቀደምት የመካከለኛ ዘመንና የቅርብ ጊዜውን የሙዚቃ ታሪክ አስዳስሷል፡፡
የኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ መነሻው ቅዱስ ያሬድ መሆኑን የጠቆመው ሰርፀ፤ የሙዚቃ ድምፅን በምልክት የገለጠ የዓለም የመጀመሪያ ሰው መሆኑን የሚያረጋግጡ በርካታ ጥናታዊ መሰረቶች እንዳሉ ገልጿል፡፡
ስለኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ በአብዛኛው ጀምስ ብሩስን በመሳሰሉ ሀገር አሳሾችና የነገስታት ባለሟል የውጭ ሃገር ዜጎች መፃፉን አመልክቶ፤ ቅዱስ ያሬስ ለሙዚቃ ያበረከተው አስተዋፅኦም በነዚሁ ታሪክ ነጋሪዎች ፍላጎት ልክ የቀረበ በመሆኑ ከምዕራባውያን የሙዚቃ ልሂቃን ያነሰ ስፍራ ይሰጠዋል፡፡ ነገር ግን ቅዱስ ያሬድ ሙዚቃን የቀመረው በ6ኛው ክፍለ ዘመን ሲሆን ምዕራባውያን ለመጀመሪያ ጊዜ ሙዚቃን በምልክት ማስቀመጥ የጀመሩት በ9ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው ብሏል፡፡ ስለ ቅዱስ ያሬድ የሚገባውን ያህል መረጃ ከኢትዮጵውያን የታሪክ ተመራማሪዎች ባለመቅረቡም የዓለም የድንቃድንቅ መዝገብ ላይ መስፈር እየቻለ አለመስፈሩን እንዲሁም ከአለማቀፍ ታላላቅ የሙዚቃ አባቶች ዝርዝር ውስጥ አለመካተቱን ጥናት አቅራቢው አስመልክቶ፤ እውነታውን ለዓለም ገልጦ በማሳየት ረገድ ከኢትዮጵያውያን የታሪክ ተመራማሪዎች ብዙ ይጠበቃል ሲል የቤት ሥራ ሰጥቷቸዋል፡፡
እስከ 17ኛው ክፍለ ዘመን የዘለቀው የቅዱስ ያሬድ እንዲሁም የተማሪዎቹና የተከታዮቹ ቤተ ክህነትን አስታኮ የተጓዘውን የሙዚቃ እድገት ዘመን የተካው እስከ 20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የቆየው የጎንደር የአዝማሪ ሙዚቃ ዘመን መሆኑን ያወሳው ጥናት አቅራቢው፤ የአዝማሪነት ባህል በጎንደር፣ ወሎ እና አማርኛ ተናጋሪ በሆኑ ማህበረሰቦች፤ በትግራይ፣ በአገው እንዲሁም በደቡብ ኢትዮጵያ የከፍቾ ብሔረሰብ ዘንድ በዘመኑ ይታወቅ እንደነበር ገልጿል፡፡
በጎንደር የስልጣኔ ዘመን መንፈሳዊውም አለማዊም ሙዚቃ በእኩል ተዋህደው ይደመጡና በነገስታቱ ዘንድ ቅቡልነት እንደነበራቸው የጠቆመው ሰርፀ፤ በዚህ የተነሳ በዘመኑ “አንድ ካህን ለነፍስህ መማፀኛ፤ አንድ አዝማሪ ለመንፈስህ መዝናኛ” የሚል አባባል ይዘወተር እንደነበር ጠቅሷል፡፡
አሁን ድረስ የባህላዊ ሙዚቃ መለያ የሆኑ የሙዚቃ መሳሪያዎችም በወቅቱ በየማህበረሰብ ክፍሉ ጎራ ተሰጥቷቸው እንደነበር ገልፆ፤ክራር- የሽፍታዎችና ጦረኞች፣ ማሲንቆ - የአዝማሪዎች፣ በገና - የቤተ ክህነት፣ ዋሽንት - የእረኞች… የሙዚቃ መሳሪያ ሆነው ዘመን ከዘመን አገናኝተዋል ብሏል፡፡
በወቅቱ የነበሩ አዝማሪዎች አዝማሪነትን ለሃቅ መግለጫ ይጠቀሙበት እንደነበርና በዚህም መስዋዕት እስከመሆን መድረሳቸውን ያወሳው አጥኚው፤ በአሁን ዘመን ያሉ አዝማሪዎች አስመሳይነት ይንፀባረቅባቸዋል ሲል ተችቷቸዋል፡፡ ዘመናዊ ሙዚቃ ተብሎ የሚታመነውን የፈረንጆቹን የሙዚቃ መሳሪያዎች ለሙዚቃ ማዋል የተጀመረው በቤንሻንጉል ክልል የሚገኙ የባህል ሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋቾችን በማሰልጠን እንደሆነ ያስታወሰው ባለሙያው፤ በነዚህ ሰዎች አማካኝነት ወደ መሃል ሃገር ቀስ በቀስ ገብቶ፣ በንጉሰ ነገስት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግስት ዘመናዊ ሙዚቃ (በዘመናዊ መሳሪያዎች የተቀነባበረ) እግሩን እንደተከለ ገልጿል።
ለኢትዮጵያ የዘመናዊ ሙዚቃ እድገት በቅርፅም በአደረጃጀትም የንጉሡ ዘመን የተሻለ እንደነበር ሰርፀ በጥናቱ አመልክቷል፡፡ ለዚህም በማስረጃነት ያቀረበው በሚገባ የተደራጁ ኦርኬስትራዎችና የሙዚቃ ቡድኖች መመስረታቸውን እንዲሁም ሙዚቃዎች በስፋት በሸክላ መታተም መጀመራቸውን ነው፡፡ ከዚህም አንፃር የንጉሡ ዘመን ለዘመናዊ ሙዚቃ ማበብ ጉልህ ስፍራ ነበረው ብሏል፡፡
የደርግ ሶሻሊዝም አብዮትን ተከትሎ የሙዚቃ ስራ አዲስ መልክ መያዝ የጀመረ ሲሆን በአንድ ማዕከል ስር የነበረው የሙዚቃ ስራ በየቀበሌው በተደራጁ የኪነት ቡድኖች አማካኝነት በየህብረተሰቡ ደጃፍ እንዲዳረስ መደረጉ ሙዚቃን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ያሸጋገረ ክስተት እንደነበር ባለሙያው አስታውሷል፡፡ በደርግ ዘመን በተለይ እስከዛሬም በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ ጉልህ ሰፍራ በያዘው የ“ህዝብ ለህዝብ” ቡድን አማካይነት ሙዚቃችን ለመጀመሪያ ጊዜ ለዓለም ህብረተሰብ ሊተዋወቅ በቅቷል ያለው ሰርፀ፤ “ዋሽንግተን ፖስት”ን የመሳሰሉ ታላላቅ አለማቀፉ መገናኛ ብዙሃን ስለ ኢትዮጵያ ሙዚቃ በአድናቆት እንዲፅፉ የተገደዱበት ወቅት ነበር ብሏል፡፡
“ህዝብ ለህዝብ” እስከዛሬም መደገም ባልቻለ መልኩ ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ከፍታ መጨመሩን የገለፀው ጥናት አቅራቢው፤ በደርግ ዘመን ዋነኛ ችግር የነበረው የውጭ ምንዛሬ እጥረት ሙዚቀኞች ስራዎቻቸውን በሸክላ ማሳተም እንዳይችሉ እንቅፋት እንደሆነባቸው ያስረዳል፡፡ ሌላው ደርግ ከነበረበት የምዕራባውያን ጥላቻ የተነሳ የውጭ ሀገር ሙዚቃዎች እምብዛም ተቀባይነት ስላልነበራቸው የሃገረሰብ ሙዚቃዎች ያደጉበት ወቅት ነበር ይላል - ሰርፀ፡፡
የደርግ ስርአት ለሚያራምደው ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ይጠቅማሉ የተባሉ ወደ 10ሺ የሚጠጉ መዝሙሮች መዘመራቸውም በጥናቱ ተመልክቷል፡፡
አጥኚው የኢህአዴግ ዘመን ላይ ሲደርስ፤ መንግስትና ሙዚቃ ግንኙነታቸው የላላበት ወቅት ነው ብሏል፡፡ ሆኖም ግን የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ግንቦት 29 ቀን 2003 ዓ.ም ባደረጉት ንግግር፤ የኪነ ጥበብ መስፋፋት ለማህበረሰባዊ ግንባታ ያለውን ድርሻ ጠቁመው ኪነጥበብ የመጨረሻውን ልማት እንደሚያረጋግጥም መግለፃቸውን አስታውሷል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰመግለፅ መንግስታት የነበረው የመንግስት ጣልቃ ገብነት ኢ-ዲሞክራሲያዊ መሆኑን በመጥቀስ በዚህ ስርዓት ውስጥ ኪነ-ጥበቡ ነፃነቱ የተጠበቀ መሆኑን እንደተናገሩ አጥኚው አውስቷል፡፡
ይሁን እንጂ በዚህ ዘመን ያሉ ሙዚቀኞች፤ ይህን ነፃነት በሚገባው መጠን መጠቀም አልቻሉም ሲል የተቸው ጥናት አቅራቢው፤ በሙዚቃው የተካኑና ጥናት ያጠኑ ግለሰቦች ቢፈጠሩም የሙዚቃው እድገት ግን የታሰበውን ያህል አልሆነም ብሏል። የሃገሪቱ ሙዚቃ ወደ ኢንዱስትሪ መሸጋገር ሲገባውም ገና በተበታተነ ደረጃ ላይ መሆኑን ጠቁሟል፡፡
ሙዚቀኞች ነፃነቱን መጠቀም አለመቻላቸው እንደተጠበቀ ሆኖ መንግሥት ሙሉ ለሙሉ ከኢንዱትሪው አካባቢ ራሱን ማግለሉ፣ ሙዚቃ ለማህበረሰብና ለሃገር ያላትን አስተዋፅኦና ሚና በአግባቡ እንዳትወጣ አድርጎታል ብሏል - የሙዚቃ ሃያሲና ተመራማሪው ሰርፀ ፍሬስብሃት፡፡ 

Ethiopian New Music

No comments:

Post a Comment