Monday, June 22, 2015

ዳሪዮስ ሞዲ እና ትዝታዎቹ


ጥንቅር፡ አፈንዲ ሙተቂ
-----

ዳሪዮስ ሞዲ በዛሬው ዕለት ይህቺን ዓለም በሞት ተሰናብቷል፡፡ ያ ጣፋጭ ድምጹ ዳግመኛ ላይሰማ በዚያው ጠፍቷል፡፡ ሆኖም በህይወት በነበረበት ዘመን በትዝታዎቹና በግል ህይወቱ ዙሪያ ከተለያዩ መጽሔቶች ጋር ቃለ-ምልልስ አድርጓል፡፡ እኔም ትዝታዎቹን እንደሚከተለው አጠናቅሬአለሁ፡፡

=== ትውውቅ==
በቅድሚያ እድሜአቸው ከሃያ ዓመት በታች ለሆነ ወዳጆቻችን አጭር ማስተዋወቂያ እነሆ ብለናል፡፡
“ዳሪዮስ ሞዲ” በኢትዮጵያ ታሪክ ከታዩ ባለግርማ ሞገስ የሬድዮ ጋዜጠኞች አንዱ ነው፡፡ ይህ ጋዜጠኛ በተለይ የሚታወሰው
ሀ/. ግንቦት 13/1983 ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለ-ማሪያም ሀገር ጥለው መሄዳቸውን በገለጸበት ዜና
ለ/. ግንቦት 20/1983 ኢህአዴግ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ በኋላ ድምጹን ያሰማ የመጀመሪያው ጋዜጠኛ በመሆኑ እና በሌሎችም የሬድዮ ጣቢያው ታሪካዊ ኩነቶች ነው፡፡ በተጨማሪም በዘመነ ደርግ እና በኢህአዴግ ዘመን የመጀመሪያው ዓመት ከመንግሥት የሚተላለፉ መግለጫዎችንና አዋጆችን የሚያሰማው በአብዛኛው እርሱ ነበር፡፡
===== ዳሪዮስና የ“ቡሽቲ” ወሬ===
ዳሪዮስ አራት ኪሎ አንድ ካፍቴሪያ ውስጥ የገጠመውን እንዲህ ያጫውተናል፡፡
“ቡና ቤቱ ውስጥ ቡና እየጠጣሁ ነው፡፡ ሁለት ሰዎች ከኔ ፈንጠር ብለው ተቀምጠዋል፡፡ ከአንደኛው ጋር በዓይን እንተዋወቃለን፡፡ አንደኛውን ግን አላውቀውም፡፡ ከኔ ጋር የማይተዋወቀው ሰዉዬ “የሬድዮውን ድምጽ ከፍ አድርጉት” አለ፡፡ ተደረገለት፡፡ በአጣጋሚ እኔ የሰራሁት ፕሮግራም እየተላለፈ ነበር፡፡ እርሱም በአውስትራሊያ የተካሄደውን ውስጥ የጽንስ ማሳደግ ፕሮግራም የሚመለከት ነበር፡፡ ይኸውም አንድን ወንድ ሆዱን ቀደው ጽንስ ይከቱበታል፡፡ ከዚያም ሆዱን ይሰፉታል፡፡ ጽንሱ እያደገ ሄደ፡፡ የሰውየውም ባህሪይ ጽንሱ ባደገ ቁጥር የሴት ባህሪይ እየመሰለ ይሄዳል፡፡ ይህንን ነበር ያቀረብኩት፡፡
ሰውየው ይህንን ሲሰማ በመደነቅ “ከየት እንደሚያመጣው አይታወቅም፡፡ ትሰማዋለህ? ይሄ ቡሽቲ መሆን አለበት” አለ፡፡ ከርሱ ጋር የነበረው ሰውዬ (ከኔ ጋር በዐይን የሚተዋወቀው) ወሬውን እንዲያቆም ቢጠቅሰው አልሆነለትም፡፡ ጭራሽ ሰውዬው ወደኔ ዞሮ “አይመስልህም ወንድም?” አለኝ፡፡ እኔም “አዎ ልክ ነህ” አልኩት፡፡ “እንዴት ወንድ ልጅ ያረግዛል ብሎ ያወራል፡፡ አወቅሽ አወቅሽ ቢሏት መጽሐፍ አጠበች እንደሚባለው ነው፡፡ ሁለተኛ ይህንን ሰው አልሰማውም” አለና እንደገና ወደኔ ዞሮ “ይሄ ቡሽቲ አይደለም?” አለኝ፡፡ “ነው” አልኩት፡፡ በወቅቱ ከመቀበል በስተቀር ምንም መልስ የለኝ፡፡
(አቢሲኒያ መጽሔት፡ ቅጽ 1፤ ቁጥር 2፤ የካቲት 1985)
=====ዳሪዮስ እና ግንቦት 13===
ግንቦት 13/1983፡፡ ከቀኑ 6፡00 ሰዓት፡፡ የኢትዮጵያ ድምጽ ብሔራዊ አገልግሎት (የአሁኑ የኢትዮጵያ ሬድዮ) ማንም ያልጠበቀው ዜና አስተላለፈ፤ እንዲህ የሚል፡፡
“ለረጅም ዓመታት በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ሲካሄድ የነበረው የርስ በርስ ጦርነት ያስከተለውን የኢትዮጵያዊያን ህይወት መጥፋትና ከኑሮ መፈናቀል ለማስቀረት በልዩ ልዩ መልክ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል፡፡ ሆኖም ችግሩ አልተቃለለም፡፡ ይልቁንም ወደ ባሰ ደረጃ እየተሸጋገረ በመሄድ ላይ ይገኛል፡፡ ስለዚህ ደም መፋሰስ እንዲቆምና ሰላምም እንዲሰፍን በልዩ ልዩ ወገኖች የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ከስልጣን መውረዳቸው እንደሚበጅ የታመነበት ስለሆነ ይህንኑ በማመዛዘን ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለማሪያም ከስልጣናቸው ወርደው ከኢትዮጵያ ውጪ ሄደዋል”
ዜናውን ያነበበው ድምጸ መረዋው ዳሪዮስ ሞዲ ነበር፡፡ ዳሪዮስ ከኢትኦጵ መጽሔት ጋር ባደረገው ቃለ-ምልልስ በጊዜው የነበረውን ሁኔታ እንደሚከተለው ገልጾታል፡፡
ኢትኦጵ፡- ዳሪዮስ ያንን ዜና ስታነበው ፍርሃት አልተሰማህም?
ዳሪዮስ፡ ለምን ትንሽ ሰፋ አድርጌ አልገልጽልህም? በወቅቱ የማስታወቂያ ሚኒስትር የነበሩት አቶ አብዱልሓፊዝ ዩሱፍ ጋዜጠኛ ጌታቸው ኃይለማሪያምን ወደ ቢሮአቸው ያስጠሩታል (ጌታቸው ያኔ የቅርብ አለቃዬ ነበረ)፡፡ ጌታቸው ከሚኒስትሩ ቢሮ ተመልሶ እንደመጣ “ቆይ ከዚህ እንዳትሄድ” አለኝ፡፡ “ለምን” ስለው “የሚነበብ ዜና አለ” አለኝ፡፡ “እኔ እኮ ተረኛ አይደለሁም” አልኩት፡፡ “አይ! አንተ ነህ የምታነበው አለኝ”፡፡ እና በዚያው አነበብከኩት፡፡
ኢትኦጵ፡ ዜናው ምን እንደሆነ አስቀድሞ አልተነገረህም?
ዳሪዮስ፡ በፍጹም! እንኳንስ እኔ ጌታቸው ራሱ ያወቀ አልመሰለኝም፡፡ ብቻ በቃ “የሚነበብ ዜና አለ” ነው የተባልኩት፡፡ ስድስት ሰዓት ሲደርስ ስቱዲዮ ገባሁ፡፡ ያኔ ወረቀቱን ሰጡኝ፡፡ “ለሀገርና ለህዝብ ደህንነት ሲባል ከሀገር እንዲወጣ ተደርጓል” ይላል፡፡
ኢትኦጵ፡-አልደነገጥክም?
ዳሪዮስ፡ በጭራሽ! እንዲያውም እውነት ለመናገር ትልቅ ደስታ ነው የተሰማኝ፡፡ ልክ አንብቤ እንደጨረስኩ “አሁን ወደምትፈልግበት መሄድ ትችላለህ ተባልኩ”፡፡
(ኢትኦጵ መጽሔት፡ ቅጽ 3- ቁጥር 36፤ ግንቦት 1994)
====የዳሪዮስ ልጆች====