ባህል



የሀገር ባህል ቤቶቻችን

 

 by Noah Negashi 

ካዛንችስ መናኸሪያ አካባቢ በምትገኘው ፈንድቃ የባህል ቤት ድንገት በሁለት ሳምንት ዓርብ ቀን ለሚመጣ እንግዳ አካባቢው ላይ ያለው ግርግር ትንሽ ግራ ሊያጋባ ይችላል፡፡ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት አካባቢ ሲሆን ብዙዎች በር ላይ ቆመው፣ ተሰልፈው ፈንድቃ በምትገኝበት ጠባቧ ግቢ ውስጥ ሲገቡ ማየት የተለመደ ነው፡፡

ይቺ ትንሽ ቤት በኢትዮጵያ የሀገር ባህል ልብስ የተጊያጊያጠች ስትሆን፣ ሰፌድ፣ በርጩማ፣ መደብ የሚመስል መቀመጫ የቦታው መለያ ነው፡፡ ቤቱ የተለያዩ ፎቶዎችንም የያዘ ነው፡፡ የዚህ ቤት ሙዚቃው ብቻ ሳይሆንበት አብሮነት፣ ፍቅር፣ የሀገር ስሜት በሙዚቃ የሚሰማበት ቤት ነው፡፡ ቤቱ በሰው ይጨናነቃል ማለት ለዚህ ቤት ማጋነን አይደለም ከተለያዩ ቦታዎች፣ ከተለያዩ ሀገሮች የመጡ ሰዎች በሙዚቃ አንድ የሚሆኑበት ቦታ ነው፡፡ ወንበር (በርጩማ) ላይ መቀመጥ ለሚፈልግ ሰው ሳይመሽ (ቀድሞ) መምጣት ግዴታ ሲሆን ካለበለዚያ ግን ወለል ላይ መቀመጥ ወይም መቆም ይባስ ብሎም ቦታ ሳያገኙ መመለስ የለመደ ነው፡፡ መመለስ ያልፈለጉ ሰዎች በሩ ላይ ቆመው ማዳመጥን የሚመርጡም አይታጡም፡፡




ምሽቱ የሚጀመረው የዱሮ ሙዚቃዎችን ከሸክላው ማጫወቻ በሚደመጥ ሙዚቃ ሲሆን አንዳንድ ጊዜም ሌሎች ቤቶች ሊሰሙ የማይችሉ ወይም ተሰምተው የማያውቁ የዱሮ ሰርግ ዘፈኖች እዚህ ቦታ ይሰማሉ፡፡ 

እነዚህ ሙዚቃዎች ዘመናት ወደኋላ አሻግረው አድማጭን የሚወስዱ ሲሆን ሙዚቃ ምን ዓይነት እንደነበረም የሚዘክሩ ናቸው፡፡ ብዙ ሰዎች ወለል ላይ መቀመጣቸው ቅር የማይላቸው ሲሆን ፍቅር በተሞላበት ሁኔታም ተጠጋግተው ቁጭ ብለው ጠጃቸውን ይጠጣሉ፡፡

በሸክላ ከሚደመጡት ሙዚቃ በመቀጠል ኢትዮ ከለር ባንድ ቦታውን ሲረከብ የሰውን ስሜት መግለጽ በሚከብድ ሁኔታ የቦታው ድባብ ይቀየራል፣ ጭብጨባው፣ ጩኸቱም ደመቅ ባለ ሁኔታ ይቀጥላል፡፡

ስመ ጥርና የዕድሜ ባለፀጋ የሆኑት ዮሐንስ አፈወርቅ በተለይም ፍቅር እስከመቃብርን የሬዲዮ ትረካ ላይ በሚታወቀው ዋሽንት ልብን በሚመስጥ መልኩ የባንዱ አንድ አካል ናቸው፡፡

ምሳሌ ለገሠ በከበሮው እናም ፋሲካ በክራሩን የተመልካቹን ቀልብ ይቆጣጠራሉ፡፡ ሰው ቢያረጅም መቼም ሙዚቃ አያረጅም በሚመስል ሁኔታ ሀዋ ሶማሊኛ ሙዚቃዋን ስትጫወት ሙዚቃው ፈንቅሏቸው ተነስተው የሚደንሱ እንዲሁም በጭብጨባና በጩኸት ደስተቸው የሚገልጹ ብዙዎች ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የወላይትኛው ሙዚቃ ተጫዋች ኃይል በተሞላበት ሁኔታ ሲጫወት ሌላ የሚማርክ ትዕይንት ነው፡፡ 
በሚንቆረቆር ድምጿ ሠላማዊት የዚነት ሙሀባን ዘፈን እንዲሁም የተለያዩ ዘፋኞች ጐንደርኛ፣ ኩናምኛ፣ ኦሮምኛ፣ ወላይትኛ፣ ሶማሊኛ ሲጫወቱ ቤቷን ትንሿ ኢትዮጵያ ያስብላታል፡፡ ሙዚቀኞቹ ብቻ ሳይሆን መላኩ ስብርብር እያለ ሲጨፍር አጥንት ያለው አይመስልም፡፡

ባንዱ በሌለበት ሌሎች ቀኖች ደግሞ ከተለያየ አሽሙራቸው ጋር አዝማሪዎች አሉ፡፡ ከዚህ በተለየ መልኩ የብዙ ምሽቶች ፈርጥ የሆነችውና ‹‹ስሜት ቀስቃሽ›› በሆነው አዘፋፈኗና በቅፅል ስሟ የምትታወቀው ቢዮንሴም የፈንዲቃ ሌላ ክስተት ነች፡፡ 
የአዝማሪዎቹ ድፍረት ለየት ያለ ነው፡፡ ብዙ ጊዜም ቦታው ላይ ግጥም በመፍጠርም የታወቁ ናቸው፡፡ እንደ ዱሮው ግጥሞቻቸው በቅኔ የተሞሉ ሳይሆኑ ብዙ ነገሮች በቀጥታ የሚባሉ ሲሆኑ አንዳንዶችንም ሊያስቀይሙ የሚችሉ ናቸው፡፡ ቦታው ያለ ሳንሱር ምንም ነገር  የሚነገርበት ነው፡፡ በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ባለ ማኅበረሰብ ላይ የማይባሉና አስነዋሪ ተብለው የሚታሰቡ ነገሮችም ለዚህ ቦታ እንደ ማንኛውም ቀላል ነገር ናቸው፡፡ አዝማሪዎች ምንም ቢናገሩ ብዙ ታዳሚዎች ቅር የማይሰኙ ሳይሆን ማሞገስም ማወደስም ማንቋሸሽም በዚህ ቦታ የተለመደ ነው፡፡ አዝማሪዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተቀየሩ የከተሜነት ቅርፅ እየያዙ እዚህ ደርሰዋል፡፡ በሌላ መንገድ የአዝማሪ ቤቶችን የማኅበረሰቡ ሞራል የሚገሰስበት ሁሉም ነገር በነፃነት የሚገለጽበት ቦታ አድርጐታል፡፡

ኢትዮጵያ ለዘመናት የገጣሚዎች አገር ናት ተብላለች፡፡ ይሔን ካስባሉት ምክንያቶች ውስጥ ብዙዎች ዕውቀትን ፍለጋ (ቅኔን ለመማር) የሚንከራተቱባት፤ የብዙ ገጣሚዎች ሀገር፣ እያንዳንዷ የሕይወት አካል በግጥምና በዘፈን የሚገለጽባት ሀገር ስለሆነች ነው፡፡ 

እንደ ስሜነህ በትረ ዮሐንስ ‹‹ሚዩዚክ ኤንድ ፖለቲክስስ ኢን ትዌንቲዝ ሴንቸሪ ኢትዮጵያ ኢምፓየር ሞደርናይዜሽን ኤንድ ሪቮሉሽን›› የሁለተኛ ዲግሪ መመረቂያ ጽሑፍ አዝማሪዎች በድፍረታቸው ምክንያት የከፈሉትንም ዋጋ ይገልጻል፡፡ 1763 .. አካባቢ ራስ ሚካኤል ስሁል ‹‹በብልግናቸው›› ምክንያት የቀጧቸውም አንዱ ክስተት ነው፡፡

በዓመታትም ውስጥ ተፅዕኖ የፈጠሩ ብዙ አዝማሪዎች የነበሩ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ ፃድቄ አንዷ ናት፡፡ በአፄ ምኒልክ ቤተ መንግሥት ዝነኛ የነበረችው ይቺ አዝማሪ በዓድዋ ጦርነትንም ሰዎችን በማነቃቃት ተፅዕኖ የፈጠረች ሰው ነች፡፡ 
እነዚህ አዝማሪዎች በሰምና ወርቅ ሀብታም በሆነውን ግጥማቸው፣ ውብ በሆነው አገጣጠማቸው የኢትዮጵያን ሙዚቃ አንድ ምዕራፍ ያሻገሩና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንም ቅኔ በዘፈን በተወሰነ መልኩ ማስተላለፍ የቻሉ ናቸው፡፡ 
በኢትዮጵያ ታሪክ አዝማሪዎች በተለይም የቤተ መንግሥት አዝማሪዎች ትልቅ ሚና የተጫወቱ ሲሆን ነገሥታትን በማወደስ እንዲሁም በመተቸትና ጥላሸት በማልበስ የማይደፈሩትን መንካት የቻሉ ናቸው፡፡ 

የዚያን ጊዜ የነበሩት ራሶችና ደጃዝማች አዝማሪዎች ምን አሉ እያሉ ይጠይቁ እንደነበር ታሪክ ይዘክራል፡፡ በጣልያን አምስት ዓመት ወረራ ወቅትም አዝማሪዎች እንደ ነፃነት ታጋዮች ጣልያኖች ያዩዋቸው የነበረ ሲሆን የጣልያን ወረራን በመቋቋም ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡

ስሜነህ እንደሚገልጸውም ጣልያኖች ብዙ አዝማሪዎችን የገደሉ ሲሆን፣ ይሔም ሕዝቡን አነሳስተው ያሸፍቱብናል በማለት ነው፡፡ ጣልያኖችም በቴሌግራም ምን ያህል አዝማሪዎች እንደገደሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ በብልጠታቸው፣ በጥበባቸውና በቅኔ አዋቂነታቸውም ከሞት ያመለጡ አዝማሪዎች ነበሩ፡፡ ከእነዚህም አንደኛው ‹‹ኃይለ ሥላሴ ይሙት›› ብሎ ሲምል የተገኘ አዝማሪ በተጠየቀበት ወቅት ኃይለ ሥላሴ እንዲሞት እየተመኘ እንደሆነም ገልጿል፡፡

እንደ በሻህ ተክለ ማርያም ያሉ ሙዚቀኞችም ማሲንቆ ትተው ቫዮሊን እንዲጫወተ የተገደዱበት ሁኔታም ነበር፡፡ ይህ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣው የአዝማሪ ባህል በከተማውም እየቀጠለ መጥቶ በተለይም በአንድ ወቅትም ካዛንችስን የአዝማሪዎች ሰፈር አድርጓት ነበር፡፡ 

ከአሥር ዓመት በፊትም በቅርብ ርቀት የአዝማሪ ቤቶችም አንበሽብሸውት ነበር፡፡ በአሁኑ ሰዓት እነዚህ አዝማሪ ቤቶች ጠፍተው በአሁኑ ሰዓት ፈንድቃና እልም መጣ የሚለው ‹‹ይወዳል›› የተባለው አዝማሪ ቤቶች ብቻ ቀርተዋል፡፡ የፈንድቃ ባለቤት የሆነው መላኩ በላይ ለእነዚህ አዝማሪ ቤቶች መቀነስ ብሎ የሚያቀርበው አንዱ ምክንያት አዲሱ ከካሽ ሬጅስትራር አሠራር ጋር ተያይዞ የሚካሄደው አሠራር እንደሆነ ይገልጻል፡፡ 

መላኩ እንደሚገልጸውም ከሀያ ዓመታት በፊትም አዝማሪ ቤቶች ታዋቂ የነበሩ ሲሆን በተለይም በዕድሜ ገፋ ያሉ ሰዎች እየመጡ የግጥም ዕውቀታቸውን የሚጠበቡበት ስፍራ ነው፡፡

መላኩ ለአዝማሪዎች አዲስ የሆነ አሠራርም ፈጥሯል፡፡ አዝማሪዎች ከደንበኞች በሚያገኙት ሽልማት የገቢ ምንጫቸውን ያገኙ የነበሩ ሲሆን ወርሃዊ ደመወዝ እንዲያገኙም አድርጓል፡፡

ሕልሙ የተለያዩ የኢትዮጵያ ብሔሮችን መወከል የሚችሉ ክለቦችን ማየት በመሆኑ ከምሳሌ ለገሠና ከእንድሪስ ጋር በመሆን ሁሉንም የሚያጠቃልል ኢትዮ ከለር የሚባል ባንድ ለማቋቋም በቅቷል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ለጃዝ፣ ስፓ፣ ሂፕ ሆፕ፣ ሮክ እንዲሁም ለሌሎች አማራጭ ሙዚቃዎችምና የግጥም ምሽቶችም መድረክ መፍጠርም ችሏል፡፡ 

ይሔ ቦታ የተለያዩ ሙዚቃዎችን በማገናኘት መድረክ መፍጠር እንደቻለ የሚገልጸው መላኩ ፈንድቃም በተለያዩ ፀሐፊዎችም ተደንቋል፡፡ መላኩ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ኮንሠርቶችም የሚጋበዝ ሲሆን ሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ የተለያዩ ቦታዎች ላይ ስለ እስክስታ ወርክሾፕ ሰጥቷል፡፡ ኢትዮ ከለር ባንድም አኬሽያ ጃዝ ፌስቲቫል ላይ ምርጥ ባንድ በሚል ከሦስት ዓመት በፊት ተሸልሟል፡፡ 

እሱ እንደሚናገረው ቦታው በተለያዩ ደንበኞች ከሳምንት እስከ ሳምንት የሚጨናነቅ ሲሆን የአዝማሪዎቹን ነገር ጥምዘዛ እንደሚወዱት ይናገራል፡፡ 
መላኩ ጨምሮ እንደሚያስረዳውም ብዙ አዝማሪዎች ግጥሞቹን የተለማመዷቸው ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ በመደጋገምም ይታወቃሉ፡፡ 

የአዲስ አበባ ነዋሪዎችም ይሔን ቦታ የሚያዘወትሩ ሲሆን በተለይም በበዓላት ጊዜ ሞቅ ደመቅ ይላል፡፡ እንዲህም ቢሆንም የማኅበረሰቡ ለአዝማሪዎች ያለውን ዝቅ ያለ አመለካከት ያበሳጨዋል፡፡ ብዙ ሰዎች 20 ብር የመግቢያ ክፍያ ለመክፈል የሚያማርሩ ሲሆን ለሌሎች ክለቦች 80 ብር ለመክፈል እንደማያቅማሙም ይናገራል፡፡ 

ምንም እንኳን የተመሠቃቀለ ስሜት አዝማሪዎች ላይ ቢኖርም ሞቅ ደመቅ ያደረጓትና የብዙ ቱሪስቶችም መገኛ የነበሩት አዝማሪ ቤቶች በአዲሶቹ ባህል ቤቶች ወይም በመጠጥ ቤቶች ተተክተዋል፡፡

አዲስ አበባ ውስጥ የቱሪስቶች መናኸሪያ የሆኑ የተለያዩ የባህል ቤቶች የሚገኙ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ ሀበሻ 2000 ዮድ አቢሲኒያ፣ ቶቶት፣ እልፍኝ ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህ ተመሳሳይነት የሚታይባቸው ቤቶች ብዙ ደንበኞቻቸውም ቱሪስቶች ናቸው፡፡ አንዳንዶቹም የባህል ቤቶች ቱሪስቶችን ለማስተናገድ ቆርጠው የተነሱ በሚመስል ሁኔታ ምን ዓይነት ሙዚቃ መድረክ ላይ እንደሚጫወቱም በእንግሊዝኛም የሚያስተዋውቁበትም አጋጣሚ አለ፡፡

ብዙዎቹ ባህል ቤቶች ክራር፣ ማሲንቆ፣ እንዲሁም ከበሮ የሚጫወቱ ሙዚቀኞች ያሉባቸው ሲሆን ዳንሰኞቹም የተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎችን ሊወክሉ የሚችሉ አልባሳትም ይለብሳሉ፡፡ ቦታዎቹ ኢትዮጵያዊ እንዲመስሉ የተጌጡ ሲሆኑ የሚያቀርቡትም የምግብ ዓይነቶች ክትፎ፣ ጥብስ፣ እንዲሁም ታዋቂው መጠጥ ጠጅ የቤቶቹ መለያ ናቸው፡፡ 

እነዚህ ቤቶች በጾም ወቅት ቀዝቀዝ ቢሉም በበዓላትም ሞቅ ደመቅ ይላሉ፡፡ ከእነዚህ ቤቶች ውስጥ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ፊት ለፊት የሚገኘው ወይን የባህል ምግብ አዳራሽ አንዱ ነው፡፡ 

የሚያስገርመው የዚህ ቤት ዲዛይን የቤቱ ባለቤት የወይዘሮ ፍቅርተ ከተማ ውጤት ነው፡፡ መድረኩ አካባቢ በጉራጌ ጐጆዎች የደመቀ ሲሆን አካባቢውንም የሚያሳይ ሥዕልም ከጀርባው አለው የቤቱ መብራት በኢትዮጵያ የአሣሣል ስልት በሆነው (አይኮኖግራፊ) የተጠለፈና ከሸምበቆ የተሠራ ነው፡፡ 

ፍቅርተ እንደምትገልጸው ቤቱ 1950ዎቹ በፈረንሳይ አርክቴክት ዲዛይን የተደረገ ሲሆን ከአዲስ አበባ ሒልተን ሆቴልም ጋር አብሮ እንዲሔድ የታሰበ ነው፡፡ በጥንት ጊዜ ቤቱ በተለያዩ ባለቤቶች ተይዞ የነበረ ሲሆን ለተለያዩ መሥሪያ ቤቶች በቢሮነት አገልግሏል፡፡ 

ፍቅርተና ባለቤቷ ቦታውን ከተረከቡ በኋላ እንደገና ለማስተካከል ስድስት ወራት ያህል የፈጀባቸው ሲሆን ሁለት ሚሊዮን ብር ያህልም ፈጅቷል፡፡ ምንም እንኳን ብዙ ቢለፋበትም ገበያው አመርቂ ሊሆን አልቻለም፡፡ 

ደንበኞች መጡ አልመጡም ሙዚቀኞቹ በደስታ ከሳምንት እስከ ሳምንት ይዘፍናሉ፣ ይጨፍራሉ፡፡ ዘፋኞቹ ከዘፈን ወደዘፈን እየሔዱ የተለያዩ የኢትዮጵያን ድምፅ ያሰማሉ፡፡ በፍጥነትም ከመድረክ ወርደው ልብሳቸውንም ቀይረው በመምጣት ዘፈናቸውንም ይቀጥላሉ፡፡ 

አብዛኛውንም ጊዜ ዳንሰኞቹ በተመልካቹ መሀል በመዘዋወር ለዳንስ ተመልካቹን ይጋብዛሉ፡፡ አንዳንዴም ወደ መድረኩ በመጋበዝ የሚያስደንሱ ሲሆን በተለይም የውጭ ሀገር ቱሪስቶች እስክስታውን ለማስመሰል ሲሞክሩ የሚያዝናና ትዕይንት ነው፡፡ ቦታው ከሙዚቃው በተጨማሪ የተለያዩ አርቲስቶች ሥራ የሆኑ ሥዕሎችም ይዟል፡፡

በሮቹ፣ መስኮቶቹ፣ ወንበሮቹ፣ የቤቱ ቁሳቁሶች በአጠቃላይ ኢትዮጵያዊ በሆነ መልኩ የተሠሩ ናቸው፡፡ 

ፍቅርተ እንደምትናገረው የደንበኞቹ ዓይነት ከጊዜ ወደ ጊዜ ይለያያል፡፡ አንዳንዴ በውጭ ቱሪስቶች ሲሞላ፣  አንዳንዴም ኢትዮጵያውያን ይበዙበታል፡፡ 
አዲስ አበባ ብዙ የሀገር ባህል ቤቶች እንደሌሉ የምትገልጸው ፍቅርተ የዚህ ምክንያትም ብዙ ሰዎች በዲጄዎች የሚያጫውቱትን ሙዚቃ መምረጣቸው ነው፡፡ ‹‹ብዙ ሰዎች ወደእነዚህ ቦታዎች ለመምጣት የተለያዩ በዓላትን ይመርጣሉ፡፡ እነዚህ ቤቶች የየቀኑ የሕይወታቸው አካል አይደሉም›› ትላለች ፍቅርተ፡፡

የተለያዩ ደንበኞችን ለመጨመር የግጥም ምሽቶችን እንዲሁም ጃዝ ሙዚቃን በባህል ቤታቸዉ የማስተዋወቅ ዕቅድ አላቸው፡፡ የተለያዩ አርቲስቶችም መጥተው እንዲጫወቱም ይጋበዛሉ፡፡ 

ፍቅር ዓለሙ በዳንሰኝነት እዚህ ቤት የሚሠራ ሲሆን ይሔንን ሙያ የጀመረውም ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የሚተላለፉ ቪዲዮ ክሊፖችን በማየትና በመለማመድ ነው፡፡ ለሁለት ዓመታት ያህል በነፃ ብሔራዊ ቴአትርም አገልግሏል፡፡ ከዚያም በተለያዩ ባህል ቤቶች እንደነ ትንሽዋ ቤት፣ መቀሌ በሚገኘው ሀበሻ 2000 ኢትዮ ሚሌኒየም ሠርቷል፡፡

አብዛኛውን ጊዜ አመሻሽ ላይ እየመጣ በሳምንትም ለስድስት ቀናት ይሠራል፡፡ ፍቅር እንደሚገልጸው ጉራጊኛና ወላይትኛ ዳንሶች ብዙ የውጭ ሀገር ቱሪስቶች የሚመርጧቸው እንቅስቃሴዎች ሲሆኑ በዚህ ቦታም የኢትዮጵያ ባህልን ማስተዋወቁ ልባዊ ደስታ ይሰጠዋል፡፡ 

አሳዬ ዓለማየሁ ወይን የባህል ምግብ አዳራሽ የሚሠራ ትግርኛ የሚዘፍን ሲሆን መዝፈን የጀመረውም ከአሥር ዓመት በፊት ነው፡፡ 

http://shaybuna.com 


No comments:

Post a Comment