ትዝብት

 
ኤፍ.ኤም እና እንግዶቹ
B.G

እንግዳ - ሃሎ! ኤፍ.ኤም!
ኤፍ.ኤም - ሄሎ! ስም ማን ልበል!?
እንግዳ  - የማን የኔ!?
ኤፍ.ኤም - አዎ!
እንግዳ - ገርማሜ
ኤፍ.ኤም - ከየት ነው?
እንግዳ - ያለሁበት ነው?
ኤፍ.ኤም - አዎ!
እንግዳ - ከሰፈረ ሰላም
ኤፍ.ኤም - ያባት ስም ማን ልበል?
እንግዳ - የማን የኔ!?
ኤፍ.ኤም - አዎ!
እንግዳ - በለጠ!
ኤፍ.ኤም - ምን ፈልገህ ነው?
እንግዳ - ማን እኔ?
ኤፍ.ኤም - አዎ!
እንግዳ - ሙዚቃ ነዋ!
ኤፍ.ኤም - የማንን ካሴት ነው?
እንግዳ - ካሴቱ ነው?
ኤፍ.ኤም - አዎ!
እንግዳ - ከናንተው ነዋ!
ኤፍ.ኤም - አይ ማን የዘፈነውን ነው የምትፈልጉት ማለቴ ነው፡፡
እንግዳ - ማን እኔን ነው?
ኤፍ.ኤም - አዎ!
እንግዳ - «ጭር ሲል አል ልወድም» የሚለው ይሁንልኝ
ኤፍ.ኤም - ጭር ሲል አይወዱም!?
እንግዳ - ማን እኔ?
ኤፍ.ኤም - አዎ!
እንግዳ - ምን?
ኤፍ.ኤም - ጭር ሲል አይወዱም ወይ!?...ይፈራሉ?
እንግዳ - ማን?
ኤፍ.ኤም - እርስዎ!
እንግዳ - እንዴት ወንድ አይደለሁ እንዴ፡ ለምን ቸእፈራለሁ!?
ኤፍ.ኤም - ታዲያ ለምን መረጡ?
እንግዳ - ማን?
ኤፍ.ኤም - እርስዎ!
እንግዳ - ምኑን!?
ኤፍ.ኤም - ሙዚቃውን
እንግዳ - ስለምወደው ነዋ!
ኤፍ.ኤም - ለማን ነው የመረጡት?
እንግዳ - ምኑን?
ኤፍ.ኤም - ሙዚቃውን?
እንግዳ - ! ለባለቤቴ ለድንቡልቃ
ኤፍ.ኤም - ለማን አሉ?
እንግዳ - ነገርኩህ እኮ!ባዶቤት ጥላኝ ለጠፋችው ለባለቤቴ ለድንቡልቃ ብያለሁ፡፡
ኤፍ.ኤም - እሺ! ተቀብለናል
እንግዳ - ምኑን!?
ኤፍ.ኤም - ምርጫዎን!
እንግዳ - ሆሆ! ለናንተ ማን አለና? ለባለቤቴ ድንቡልቃ  እኮ ነው ያሉኩት!
 ስልኩ ተቋረጠ፡
Ashagre Hailu
  ከአቶ ገብረዋህድ ጓዳ የቤት ካርታና የገንዘብ ዓይነት፤ ከአቶ መርክነህ ጓሮ ደግሞ ብር ሲወጣ ጉድ ብለን ተመለከትን፤ ከሃገራችን ከርሰ ምድር ውስጥ ወርቅ፡ ነዳጅ፡ ፖታሽ፡ . . . ወዘተ ካልሆነ ደግሞ ቢጠፋ ቢጠፋ ሲቆፈር ውሃ አይጠፋም ብለን እንጠብቅ ነበረ፡፡ የሰሞኑ የሙስና ተጠርጣሪዎች ጓዳቸውና ጓሮአቸው ሲበረበር የሚወጣው ብርና ዶላር መሆኑ እያስገረመኝ ነው፡፡ ቦታ አጥተው ነው ወይስ ያልተደረሰበት ቦታን አጣበው ከጨረሱ በኋላ ይሆን ወደ ጓዳና ወደ ጓሮአቸው የዞሩት ? በዚህ ዘመን ለቤት መስሪያ እንዲያውም ለቀብር እንኳን መሬት በጠፋበት ጊዜ እነሱ መሬቱንም ብሩንም በማግበስበስ ምን ያህል ገብጋቦች መሆናቸውን አይተናል፡፡ ግራ የሚያጋባው ግን ይህ ሁሉ ሲሆን ምን እየተጠበቀ እንደነበረ ነው፡፡ የተያዙት ዝርክርኮቹ ሌቦች ሲሆኑ ጠንቃቆቹ የመንግስት ሌቦች ደግሞ ምን አይነት ዘዴ ሊጠቀሙ እነደሚችሉ ማሰብ አስቸጋሪ ነው፡፡ ግን ግን ህዝቡን ያስመረሩትና በግልጽ ሌብነት ውስጥ የተዘፈቁት የጉምሩክ ሰዎች ብቻ ናቸው ? ወይስ ሌሎቹ ከተፈቀደላቸው መጠን አላለፉም ? እነደዚያ ከሆነ መጠኑ ይነገረንና በጉጉት እንጠብቅ፡፡
 
Anteneh Yigzaw
 
የስኳር ጉዳይ የማይመለከተው “ህዝብ”
የሃያኛው “ግንቦት ሃያ” ዋዜማ…
ሰፊው የአዲስ አበባ ህዝብ መፈክሩን እያሰማ፣ ባንዲራውን እያውለበለበ፣ የወረቀት ቆብ አድርጐ “እልል” እያለ መስቀል አደባባይን ከማጥለቅለቁ በፊት፡፡ አርብ ተሟጥጣ አልቃ ቅዳሜ ከመምጣቷ በፊት፣ ምድረ አዲስ አበቤ ሰልፍ ከመውጣቷ በፊት ... በህዝቦች የጋራ ትግል ዕውን የሆነች የህዝቦች የጋራ ድል ለሃያኛ ጊዜ ከመከበሯ ቀድሞ፡፡ የመድፍ ተኩሱ መላውን ህዝብ ከመቀስቀሱ በፊት፡፡ ከአርብ ምሽት እስከ ንጋት የዘለቀውን ... መንግስት ያላወቀውን(?) ሌላኛውን በእየዕለቱ የሚካሄድ ሰልፍ በየጓዳዋ ስታስተናግድ ነበር ያመሸችው - አዲስ አበባ!
ከመላው ህዝብ በፊት ሌላው ህዝብ “ጌዳውን”፣ “ሼክ ኢት ቤቢ”፣ “ፑር ዩር ሃንስ አፕ ኢን ዘ ኤር” ሲባባል አምሽቶ አደረ፡፡ ሌላው ህዝብ! ... “መላው” ሳይሆን “ሌላው” የአዲስ አበባ ህዝብ! ከሌላው የአዲስ አበባ ህዝብ ጋር ነበርኩ፡፡ ከእኩለ ሌሊት እስከ ውድቅት፣ አልፎም እስከ ንጋት ከሌላው ህዝብ መሀል ነበርኩ፡፡ ... ከስካር እንጂ ከስኳር ጉዳይ ከሌለው ከሌላው ህዝብ ጋር አመሸሁ፡፡ የዘይት ጉዳይ ከማያስጨንቀው ከሌላው ህዝብ ጋር አደርኩ፡፡ ሌላው ህዝብ በ “አስሊ”፣ ሌላው ህዝብ በ “በአካል-ፀ”፣ ሌላው ህዝብ በ “ሰሌክት”፣ ሌላው ህዝብ በ “አሊዜ”፣ ሌላው ህዝብ በ “ቴምፕቴሽንስ”፣ ሌላው ህዝብ በየአዲስ አበባ ጓዳዎች ... እኔ እዚህ ካለው ሌላው ህዝብ ጋር ነኝ ... እዚህ ...”ኢሊዩዝን”!!
“ኢሊዩዝን” ሌላው ህዝብ ነገር አለሙን ረስቶ አለሙን የሚቀእበት ምሽግ ነው፡፡
ቀን ቀን በወረፋ ፊልም ከሚታይበት አምባሳደር ሲኒማ ቤት አዳራሽ ስር ሲመሻሽ የሚከፈት በር አለ፡፡ ይህን በር አልፎ ለመግባት ለአንድ ሰው ሰላሳ ብር ይከፈላል፡፡ ይህ በር ወደ ሌላኛው የፊልም አዳራሽ የሚያስገባ ነው፡፡ “ኢሊዩዝን” ከአምባሳደር ስር የሚገኝ ሌላ የሌላው ህዝብ የውድቅት ፊልም መስሪያ እና መመልከቻ ጓዳ ነው፡፡ እስኪነጋ የተለያዩ ትዕይንቶች የሚታዩበት “ስክሪን” ነው፡፡
ልዩነቱ የማታው ፊልም ስም የለውም፡፡ ኮሜዲ፣ ትራጀዲ፣ ሰስፔንስ፣ አድቬንቸር፣ አክሽን ብለው አይፈርጁትም፡፡ ዳይሬክተሩ አይታወቅም፡፡ ተዋናዩን ከተመልካቹ መለየት አይቻልም፡፡
ፊልሙን ለመስራትም ሆነ ለመመልከት ብቸኛው መስፈርት 30 ብር ከፍሎ ወደ አዳራሹ መዝለቅ ነው፡፡ ከዚያ 
በኋላ የፊልሙ አካል መሆን ይቻላል፡፡ “ኢሊዩቅን” - ስምን እንትን ያወጣዋል!! ...ቅዠት! ... ውቅንብር! ... ድብልቅልቅ! ... እሱ የሚገኘው ከአገር መከለከያ ሚኒስቴር አፍንጫ ስር ነው! ዙሪያ ድንበሩን ከወራሪ ሃይል ነቅቶ የሚጠብቀው “መከላከያ” እዚህ መሀል ከተማ እንቅልፍ ጥሎት ሲያንኮራፋ፣ ከአውሮፓና ከሩቅ ምስራቅ የመጣ ነእ ወራሪ ደጃፉ ላይ ሴቶችን በዶላርና በዩሮ እያማለለ ይማርካል፡፡
ሴቱ፣ ወንዱ፣ አገሬው፣ መጤው፣ ህፃኑ፣ አዛውንቱ ... ሁሉም በኢሊዩቅን ሜዳ ላይ ቅልጥ ያለ ጦርነቱን ያደራዋል፡፡
“ቀን ለሰራዊት ... “ ብሎ ተረት ኢሊዩቅን ውስጥ ቦታ የለውም፡፡ ይሄኛው ሰራዊት ... ከመላው ህዝብ መሐል ተነጥሎ እስከ ንጋት ቆሞ የሚያድረው፡፡ ይሄ ሌላው ህዝብ ተረትም ... ዘይትም ጉዳዩ አይደለም፡፡
እዚህ ዘይት አይደለም የወጥ ማጣፈጫው፡፡ ... ተኪላ እንጂ! ስቶልቺሊያ ... ጐርደን ... ብላክ ሌብል ... ሳምቡካ ... ቮድካ ... ካማካዚ ... እነዚህ እነዚህ ናቸው የሌላው ህዝብ የጣዕም ምንጮች፡፡ ከሌላው ህዝብ መሀል ነኝ፡፡
የመላውን ህዝብ ድል ማብሰሪያ መድፍም፣ የመላውን ህዝብ እንቀት መግለጫ እሮሮም ... ሁለቱንም የማይሰማው ሌላው ህዝብ ውስጥ ነኝ፡፡
ሌላው ህዝብ እንቀት አይወድም፡፡ ይሄ ...ውድነት፤ እጥረት፣ ገበያ ...ብሎ ነገር አይመለከተውም፡፡ የአገር እንቀት፣ የአገር ለቅሶ አይሰማውም፡፡ የአገር ለቅሶ ይቅርና የአገር ዘፈንም ምቾት አይሰጠውም፡፡
ሬጌ ነው የሚደላው፡፡ ራፕ ነው የሚመቸው፡፡ በራጋ ነው መውረግረጉ፡፡ በብሉዝ ነው መደንከሩ፡፡ ለሌላው ህዝብ ስካር እንጂ ስኳር አይደለም እንቀቱ፡፡ እኩልነት የሰፈነበት የኢሊዩዝን ሪፐብሊክ ... ነዋሪዎቿ ይቅርና እንግዶቿም እኩል ሆነው የሚኖሩባት ናት፡፡ እዚህ ሴት እና ወንዱ እኩል ነው፡፡ እኩል ይጠጣል ... እኩል ይሰከራል፡፡ እኩል ይጨሳል ... እኩል ይደነሳል፡፡
ለሌላው ህዝብ አዲስ አበባ ሁሉም ሞልቶ የተረፈባት የድሎት ከተማ ናት፡፡ ሌላው ህዝብ የአቅርቦትም የፍላጐትም ችግር የለበትም፡፡ ገበያውም ኪሱም ሙሉ ነው፡፡ እንዳሻው ይመዝዛል፣ እንዳሻው ይገዛል፡፡
ከቦሌ መድሃኒያለም እስከ አትላስ፣ ከሀያ ሁለት እስከ ቦሌ፣ ከኦሎምፒያ እስከ መስቀል ፍላወር ገበያው እስከ ንጋት ይደራል፡፡ ሌላው ህዝብም ድፍን ሌሊት ከወዲያ ወዲህ እየጋለበ ያሻውን ይሸምታል፡፡
ከሌላው ህዝብ ጋር ነኝ፡፡ “ጌራፕ ስታንዳፕ ስታንዳፕ ፎር ዩር ራይት ...” ተብሎ በሬጌ ቀረርቶ ይቅርና ሌላው ህዝብ ወትሮም ለመብቱና ለክብሩ እንደተዋደቀ ነው፡፡ ይሄው “ጃሎ” እያለ ይፎክራል አንዱ፡፡ ጠርሙሱን መዝዞ ይውረገረጋል፡፡ “ያዙኝ ልቀቁኝ” ይላል፤ ወደ ሌላው የሌላው ህዝብ ወጣት እየተንደረደረ፡፡ ምክንያቱን መገመት ባልችልም በሆነ ጉዳይ መጋጨታቸው ገብቶኛል፡፡
ጠርሙሱን ወርውሮ የሌላኛውን አናት ከመፈንከቱ በፊት ግን የሌላውን ህዝብ ሰላም የማስከበር አገራዊ ግዴታ የተጣለባቸው ቀይ ለባሽ ወጠምሾች ጣልቃ ገቡ፡፡
የተጋጩት ወጣቶች በቁጥጥር ስር ዋሉ፡፡ ሌላው ህዝብ ያለ አንዳች ችግር በሰላማዊ ሁኔታ መስከሩን ቀጠለ፡፡
“ቺኩን ነካክቶበት ይሆናል” አለ አንዱ የፀቡን ሰበብ በመገመት፡፡ እርግጥ ግምቱ እውን ከሆነ ይህንን ድርጊት የፈፀመው ከመላው ህዝብ መካከል የመጣ ስግብግብ ሰው መሆን አለበት፡፡ ታዲያ! ሌላው ህዝብ ውስጥ የሴት እጥረት የለም፡፡ ሌላው ህዝብ ሲያሻው ገዝቶ፣ ሲፈልግ ጐትቶ የፈለጋትን ሴት ከጐኑ ሻጥ አድርጐ ነው የሚዝናናው፡፡ ሴቱ ሞልቶ ተርፏል፡፡
አሁን ለምሳሌ እነዚህ ጥጉን ይዘው ከብበው የሚጠጡት ሦስት ቆነጃጅት አሉ፡፡ ከእነሱ ጋር ቀርቦ ተግባብቶ አንዷን “ማብሰል” ሲችል ምን ነካው እና ነው የሰው ቺክ ነካክቶ ፀብ የሚፈጥረው?! እርግጠኛ ነኝ ... ይህ ሰው የሌላው ህዝብ ቋሚ አባል አይደለም! የሩቅ አገር ሰው ሳይቀር በሰላማዊ ሁኔታ ቆነጃጅትን “አስምጦ” እኑ ላይ አስቀምጦ ያሻውን እያደረገ አይደል እንዴ?
ይሄው ፈረንጁ ... ጩጬዋን እኑ ላይ ጥዶ ያበስላል፡፡ ሌላው ህዝብ ተግቶ ያጨሳል ... ተግቶ ይጨሳል፡፡ “ቀበሌ”፣ “ወረፋ”፣ “ምዝገባ”፣ “የሸማቾች ማህበር” ...ይህ ሁሉ የሌላው ህዝብ ጉዳይ አይደለም፡፡
“ጋዝ” “ዘይት” ምናምን ብለህ ሌላውን ህዝብ አትጨቅእቀው፡፡ “ጋዝ ላይት” ነው እሱ የሚያውቀው፡፡
“የሚረጋው”፣ “የማይረጋው” ብሎ ዘይትን መከፋፈል ሌላው ህዝብ ጉዳዩም አይደል!፡፡ “ጀሪካኑ ጠፋ”፣ “ባለ አንድ ሊትሩ አለቀ” እንዲህና እንዲያ ያለ ሮሮ ሌላውን ህዝብ አያውቀውም፡፡
ነጋዴው ዘይት ማስመጣት አቁሞ፣ መንግስት “እኔ ላምጣ” ይበል ...ሌላው ህዝብ ጉዳዩም አይደል፡፡ ዘይት በጅንአድ ይከፋፈል አልያም በኢትፍሩት ሱቆች ሌላው ህዝብ አያገባውም፡፡
እንኳን የህዝብ ሮሮ አገር ምድሩን የሚያምሰው፣ ለህዝብ ድል ክብር ተብሎ ንጋት ላይ የተተኮሰው፣ የመድፍም ድም ሃይል አግኝቶ የእሱን ጆሮ መች ደረሰው?!
ይሄው እስከ ንጋት ሲጋት፣ ... ሙሉ ሌሊት ሲጠጣ ... አርብ አልፎ ቅዳሜ መጣ!!
“ጋምቤ” ብሎ ይፎክራል፣ “ቺርስ” ብሎ ያነጣጥራል፣ ምንስ ቢሆን የዘር አይደል ... የአልኮል ጥይት “ዋን ሻት” ብሎ በራሱ ጉሮሮ ይቆጥራል፡፡ “ጋምቤ” እዚህም እዚያም ይፎከራል፡፡ “ዋን ሻት” ብሎ ያነጣጥራል ... ራሱን ለመግደል በራሱ ላይ ተኪላ ያንቆረቁራል፡፡ ራሱን ግዳይ ጥሎ ለራሱ ይፎክራል፡፡ ሌላው ህዝብ ጀግናው!! ኑሮ መች ፈትኖት ... ኑሮ መቼ ጥሎት! “ኢንፍሌሽን” ብሎ ጣጣ “ኢሊዩቅን” መች ሊመጣ! “መርካቶ” ና “ሾላ ገበያ” አትበሉት ሌላውን ህዝብ፡፡ ጉልትም፣ ገበያም፣ አትክልት ተራም የእሱ አይደሉም፡፡
ገበያው ሱፐር ማርኬት ነው፡፡ ግዢው ከበርገር ቤት ነው፡፡ ሽንኩርት፣ ዘይት፣ ጨው፣ በርበሬ፣ ስንዴ ዱቄት ... ሌላም ሌላም ቅራቅንቦ ከየገበያው ተገዝቶ ... ከየጉልቱ ተሸምቶ ... በየኪችኑ ገብቶ ... በየሼፉ እጅ ተሰርቶ ... ጣጣውን ጨርሶ ... “ፒዛ” ከሆነ በኋላ ነው ሌላው ህዝብ ዘንድ የሚደርሰው፡፡
ስለዚህ ሌላው ህዝብ ከ”ፒዛ” “ፒዛ” እያማረጠ ይበላል እንጂ ዘና ብሎ፣ የተጠየቀውን ከፍሎ፣ የጨው መጥፋት መቼ ጨንቆት?! ...መች አሳስቦት ስንዴ ዱቄት?! ከሌላው ህዝብ ጋር ነኝ!!
የምን እንቀት ... የምን ድብርት ... የምን ኑሮ ... የምን ጣጣ ... ዘና ብሎ ከሚደንስ ... ፈታ ብሎ ከሚጠጣ ... ከሌላው ህዝብ ጋር ነኝ፡፡
ቢፈልግ ለምን አይነጋም! ... ሌላው ህዝብ ምን አጣደፈው! ታክሲ አያጣ ... ባስ አያልፈው! ቢያደክመው እንኳን መጠጡ ... ቢያዝለው እንኳን ዳንሱ፣ ያርፍበት “ገስት ሃውስ” አያጣ ... ይእነቀው እንጂ ኪሱ! ከመላው ህዝብ ይሁን እንጂ ... ቤት ክራይ የራስ ምታቱ፣ ሌላው ህዝብማ “ፔንሲዮን” ... “ገስት ሃውስ” ናት ጐጆው ቤቱ! ይብላኝ እንጂ ለመላው ህዝብ በታክሲ እጦት ለሚጉላላ ... ሌላው ህዝብማ መሄድ ሲያስብ፣ መርቼዲሱ ናት የእሱ መላ! ባሻው መስመር የምትወስደው፣ ሳትገደብ በ “ታፔላ”! “ደብል” “ደብል” ያስጨምራል ... ቢያሻው “ሜዞ” ቢያሻው “ሙሉ” “ሬድ” “ብላክ” ያስወርዳል ... ያስደግማል እየጠጣ፣ “ይሄን ታህል በቃህ” የሚል እንደዘይት ኮታ አልወጣ!!
መላው ህዝብ ታክስ ያማርራል፡፡
“ተጨማሪ እሴት” እያለ አናቱን ባሳብ ያዞራል፡፡
በ”ቫት” ይክሰረሰራል፡፡
ሌላው ህዝብ ዳንስ ያሳምራል፡፡
“ተጨማሪ ሴት” ፈልጐ ይዞራል፡፡
በ”ባት” ይንሰረሰራል፡፡
መላው ህዝቧ ኑሮ መሮት፣ ሲያልጐመጉም አንገት ደፍቶ
ሌላው ህዝቧ ይደንሳል ፣ ሙሉ ሌሊት እንቅልፍ አጥቶ
ሌላው ህዝቧ ለ“በርበሬ”፣ “ሞላልኝ?” ሲል ለቲማቲም
ሌላው ህዝቧ ያማርጣል፣ አሪፍ “ማሳጅ” አሪፍ “ስቲም”!
መላው ህዝቧ ሊትር ዘይት፣
አገኝ ብሎ ተሰልፎ .
መምረጥ ትቶ የዘይት ዘር፣ “የሚረጋ” “የማይረጋ”
ሌላው ህዝቧ ይላል ውስኪ፣ “የተወጋ” “ያልተወጋ”!
አቤት ይቺ ሀገር
መላው ለ”ሳሙና”፣ ሌላው ለ”ሳውና” ...
ህዝብ እዚህም እዚያም እንደተሰለፈ ...
መላው ለ”ስኳሩ”፣ ሌላው ለ”ስካሩ” ...
ቀበሌ እና ቦሌ ህዝብ እየጐረፈ ...
ወዲህና ወዲያ ሆኗል የእኛ ነገር
ለካ እንዲህም አለ ... ሁለት ህዝብ፣ አንድ አገር
https://www.facebook.com/anteneh.yigzaw/posts/10151632285854549 

No comments:

Post a Comment