Tuesday, August 18, 2015

ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ከተናገሯቸው ታሪካዊ ንግግሮች በጥቂቱ !

ዛሬ በማህበራዊ ድረገጽ  ከተቀባበልናቸው ነገሮች ታሪካዊ ቀንነቱን በመንተረራስ ዳግማዊ አጤ ምኒልክና (እምዩ ምኒልክ)
እቴጌ ጣይቱ (ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ) የተወለዱብት ቀን ዝክርን  ነው ፡፡

እኔም ካየሁት ላካፍላችሁ



- ሰው ሁሉ እኩል ስለሆነ ማንም ሰው ሰውን ባሪያ አይበል ።
- ሁሉም ሰው በየኃይማኖቱ ይደር ።

-
ድኻ እወደደበት ቦታ ይቀመጥ በዘር በወገን ልዩነት አይከልከል

-
የመሬት ጥያቄ ላቀረቡ የውጭ አገር ሰዎች ንጉሡ የሰጡት መልስ፡- ‹‹ የኛ አገር ፍትሐ ነገሥት ልዑሎች መሬት ይሽጡ አይልም ያገሬ መሬት ባለቤቱ ሌላ ነው ከአባቶቻቸው እየተቀበሉ ያቆዩት መሬት ነው ... መሬቱ የሁሉም ስለሆነ አይሸጥም ማንም ሰው መሬቱን ሊሸጥ አይችልም መሬትን መሸጥ፣ መስጠትም የሚችለው የመሬቱ ጌታ ነው ››

-
ለመንግሥት ተሿሚዎች የሰጡት መመሪያ፡- ‹‹… እንቅልፍ ሳትወዱ መጠጥ ሳታበዙ፣ ገንዘብን ጠልታችሁ ተግታችሁ ሥራችሁን ፈጽሙ እኔ እናንተን ስለአመንኩ እናንተም የምታምኑትን ገንዘብ የማይወደውን፣ ድኻ የማይበድለውንና የሚረዳችሁን ሰው እያመለከታችሁኝ ከሥራው በመግባት መንግሥታችንን እርዱ ››

-
በጣም ወደኋላ የቀረን ሕዝቦች ነን ገና የሚሠራ ብዙ ሥራ ስላለ ወጣቶቻችን መማር አለባቸው

-
አባት ያለህ የአባትህን እሰጥሀለሁ፤ አባትህን መርቅ አባት የሌለህ አባትህ እኔ ነኝና ደጅ ጥናኝ

-
እኔ ቤት እንጀራ የለም እንጀራ ያለው ትምህርት ቤት ስለሆነ እሠራሁት ትምህርት ቤት ልጆቻችሁም እያስገባችሁ አስተምሩ

-
የኔ ርስት ኢትዮጵያ ናት የግል ርስት አልፈልግም ደግሞስ የተሾምነው እርስት ከተካፈልን ለሕዝቡ ማን ያካፍለዋል?

-
ሐገራችን አንድትለማ የሚቀርቡንን ሁሉ በታላቅ ደስታና በአክብሮት እንቀበላቸዋለን በሌላ ለሚመጡብን ግን ሁላችን ሳናልቅ ሀገራችንን ለባዕድ አሳልፈን እንሰጥም

-
የሚጠሉህን ሰዎች ከማጥፋት የሚጠላብህን ማጥፋት እንዲሉ የሸፈቱባቸውን የወጉአቸውንና ያሤሩባቸውን ሰዎች በጋብቻ በዝምድና ወይም ወዳጅ አድርገው ያቀርባሉ እንጂ ክፉን በክፉ መመለስና መበቀልን አይሹም
- አንድ የፈረንሳይ ዜጋ የቦታ ግዥ ፈቃድ ሲጠይቃቸው ምኒልክ በሰጡት መልስ - ‹‹ ያገሬ መሬት የሁሉም ኢትዮጵያዊ ስለሆነ መሬት መሸጥ መለወጥ የሚችለው ሕዝቡ ነው ደግሞስ የውጭ ዜጎች መሬት እንዲገዙ ከፈቀድኩና ባለመሬት ከሆኑ ለኔ ምን ቀርቶ እገዛለሁ ? ›› አሉ
እቴጌ ጣይቱ ብጡል ለወራሪውና ለፋሺስቱ ጣልያን ከተናገሩት ታሪካዊ ንግግር በከፊል : -
" እኔ ሴት ነኝ ፡፡ ጦርነት አልወድም ፤ ነገር ግን ሀገሬን እንደዚህ ያለ ክብር የሚነካ ዘለፋ ከምትሸከም ጦርነትን እመርጣለሁ ፡፡ ሂድ መንገዱን ጨርቅ ያድርግልህ ! እግሩን ለጠጠር ደረቱን ለጦር አስጥቶ ደሙን ለሀገሩ ፍቅር አፍስሶ ለአፈሩ ክብር ለብሶ እሱ ወድቆ ሀገሩን የማያቆም እዚህ ያለ እንዳይመስልህ ! ሂድ! የኢትዮጲያን ሰው ባታውቀው ነው፡፡ ለሀገሩ መሞት ማለት ለሀበሻ ጌጡ ነው ፡፡ ሂድ ባሻህ ግዜ ተመለስ ተሰናድተን እንጠብቅሃለን ፡፡ ያንተን ወንድነትና የጣይቱን ሴትነትም ያን ግዜ እናየዋለን ሂድ መንገዱን ጨርቅ ያድርግልህ ፡፡ "
ስለሰውነት ክብር ፣ ስለሀገር ነፃነት ለሚቆረቆሩት ለእምዬ ምኒልክ 171 ኛ እና ለእቴጌ ጣይቱ ብጡል 175 ኛ መልካም የልደታቸው መታሰቢያ ዕለት ይሁን !!!
" ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር "