Tuesday, July 23, 2013

መንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ

የመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሕንፃ የመሠረት ድንጋይ ታኅሣሥ ፲፭ ቀን ፲፱፻፳፬ / ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሲያስቀምጡ የእስክንድርያ ኮፕት ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ ዮሐንስ እና የሀገር ጳጳሳትም በተገኙበት ልዩ ጸሎት እና ቡራኬ ተሠጥቶ ተመረቀ። ቤተ ክርስቲያኑ ሲታነጽ ቀዳሚ ዓላማው ለአገራቸው ነፃነት ሲታገሉ ለተሰው አርበኞች መካነ መቃብር እንዲሆን ታቅዶ ነው። የደብሩም ስም የሚያመላክተው ይኼንኑ እንደሆነ ነው። ታላቁ ምሁር ዓለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መንበር የሚለውን ቃል በቁሙ ወንበር፣ ግርንቡድ፣ መኖሪያ፣ ማረፊያ፣ መቀመጫ፣ ዙፋን፣ አትሮንስ፣ ድንክ፣ እረፍት፣ መደብ፣ ለመቀመጫ የተለየ ከፍ ያለ ቦታ እንደሆነ ሲገልጹ፤ ጸባኦት ደግሞ ሰራዊት፣ ጭፍራ፤ የጦር ሕዝብ፤ ብዙ ወታደር፤ ያርበኛ ጉባኤ፤ የዠግና ማኅበር እንደሆነ ያብራራሉ

በጥንታዊት ኢትዮጵያ ክርስቲያናዊ ባህል መሠረት አብዛኛዎቹ ንጉሠ ነገሥቶቿ ካሠሯቸው አብያተ ክርስቲያናት በመጀመሪያ ያሠሯቸው፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታዮች ፈጣሪ አምላክንበአካል ሦስት፣ በባሕሪ አንድምልክት የቅድስት ሥላሴን ቤተ ክርስቲያን ነው።
ለምሳሌ፦
  • ፩ኛ/ በፍጹም ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያንነታቸውቆስጠንጢኖስየተባሉት እና አምልኮተ ጣዖትን አጥፍተው የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓት የወሰኑት ዓፄ ዘርአ ያዕቆብ ከአሳነጿቸው አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ በጣም ትልቅና ታሪካዊ የሆነውን ሸዋ ውስጥ ያለውን ደብረ ብርሃን ሥላሴን ቤተ ክርስቲያን አሠርተዋል።
  • ፪ኛ/ ጎንደር መንግሥት የዜማንና የስብሐተ እግዚአብሔር ውሳኔን የሰጡት ዓፄ ኢያሱ አድያም ሰገድ ካሠሯቸው አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ከፍተኛ ደረጃ ያለውን ቤተ ክርስቲያን አሳንፀው በቅድስት ሥላሴ ስም ሰይመውታል።
  • ፫ኛ/ ዓፄ ዮሐንስ ንጉሠ ነገሥት እንደተባሉ ወዲያውኑ አድዋ ከተማ የሚገኘውን የደብረ ብርሃን ቤተ ክርስቲያን አሳንፀው በቅድስት ሥላሴ ስም ሰይመውታል።
ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እንዲሁ ንጉሠ ነገሥት በተባሉ በመጀመሪያው ዓመት የሕንፃውን ሥራ አስጀምረው ሲፈጸም በቅድስት ሥላሴ ስም እንዲጠራ አደረጉ።
ዲያቆን ዳንኤል ክብረት 'ኢትዮጵያ፡- ነጠላ እና ጋቢ' በሚል ጽሑፉ ላይ የቅድስት ሥላሴ ታቦት የመጣው በግራኝ ጊዜ ከፈረሰው ከወሎው መካነ ሥላሴ እንደሆነና ከዚያ ተወስዶ ወግዳ መኖሩን፣ ከወግዳ ራስ ጎበና አምጥተው ሸዋ አዲስ ዓለም ፍየታ እንዳኖሩት ከዚያም ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ ደግሞ አዲስ አበባ አራት ኪሎ እንዳመጡት ይዘግባል፡፡

የሕንፃው ግንባታ

የሕንፃው ግንባታ ልዩ መልክ ባለው እቅድ ተገንብቶ በሮችን መገጣጠምና ጌጣ ጌጥ ነገሮችን ማስገባት ሲቀር ፲፱፻፳፰ / ፋሺስት ኢጣልያ አገራችንን በግፍ ለመውረር ስለተነሳ ሥራው መቆም ግድ ሆነበት። የፋሺስት ኢጣልያ ጠቅላላ ኃሣብ ኢትዮጵያ ሙሉ ክብር ፈጽሞ ለመግፈፍ እና የእራሱን አሻራ ለማላከክ ስለነበር፣ የዚህን ካቴድራል የአሠራር ጥራት እና የቦታውንም አቀማመጥ ምቹነት በመገንዘብ ካቶሊክ ካቴድራል ለማድረግ ወሰነ። ሆኖም በግድ እና በግፍ ወሰደው ላልመባል ግምቱን ሰጥቶ መውሰድን መርጦ የጊዜውን የቤተ ክርስቲያን ኃላፊዎች በማስፈራራት ግምት ከፍዬ ልውሰደው ሲል ጠየቃቸው። ያገኘው መልስ ግን <<ዛሬ መብቱ ያንተ ነው። በግድ ለመውሰድ ትችላለህ፤ ግን በፈቃዳችን አናደርገውም>> የሚል ቆራጥ መልስ በመሆኑ፣ እጠላት እጅ ሳይገባ ቀረ።

የምርቃቱ ሥነ ሥርዓት

፲፱፻፴፫ / በተገኘው ድል ንጉሠ ነገሥቱ ሲመለሱ፣ የሕንፃው ሥራ እንደገና ተጀምሮ በቅልጥፍና ተሠርቶ ካለቀ በኋላመንበረ ጸባኦትተብሎ በቅድስት ሥላሴ ስም ተሰይሞ ጥር ቀን ፲፱፻፴፮ /ም፤ መሳፍንት፣ መኳንንት፣ ሊቃውንት፣ የሴት ወይዛዝር፣ የጦር ሠራዊት በተገኙበት ተመረቀ። ካቴድራሉ መታሰቢያነቱም በ፭ቱ የጠላት ወረራ ዓመታት ለተዋጉት አርበኞች ሆነ። ቅዳሴ ቤቱ ከተባረከ በኋላ በባህር የተጣሉትን፤ በገደል የወደቁትን እና በማይታወቅ ቦት የረገፉትን አርበኞች ዐጽም ተሰብስቦ በዚሁ ዕለት በልዩ የጸሎት ሥነ ሥርዓትና በታላቅ የሰልፍ አጀብ ተቀበረ።





የቅድስት ስላሴ ቤተክርስቲያን የመጀመሪያ ቅርጽ


በካቴድራሉ የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ንጉሠ ነገሥቱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የሚከተለውን ዐዋጅ አስነገሩ።
እጅግ ከፍ ያለው የዓለም ሁሉ ገዥ እግዚአብሔር ኢትዮጵያ ለሕዝባችን ለእናና ለአርበኞቻችን በየጊዜው ካደረገልን ወደፊትም ከሚያደርግልን ከታላላቅ ችሮታ ከሚቆጠሩት ሥራዎች አንደኛውን ዛሬ ስለፈጸመልን ልናመሰግነው ይገባናል። ለንጉሠ ነገሥት ቤተ ዘመዳችን ደንበና የዕረፍት ሥፍራ እንዲሆን በመሠረትነው የክብር ቦታ በሥራቸውና በመሥዋዕትነታቸው ውለታቸውን ልንመልስላቸው የተገባቸው አገልጋዮች ደንበኛ የርስት ተካፋይ እንዲሆኑ ፈቀድን። የሚገባቸውን ፈጽመው ማረፋቸውን ስንመሰክርላቸው በዐጽማቸው ፊት የክብር ሰላምታ እንሰጣለን።

በዚሁም ሥነ ሥርዓት ላይ ለልዩ ልዩ የጦር ሠራዊት መለዮ የሚሆነው ሰንደቅ ዓላማ በዚህ ካቴድራል እንዲውለበለብ ፈቀዱ። ይህም በጦር ሜዳ ለወደቁት አርበኞች፣ ለሕያዋኑ ጦር ሠራዊት መታሰቢያ እና የጦሩ መለያ የሚሆን ነው።
የቅድስት ስላሴ /ክርስቲያን ፎቶግራፍ በድሮ ዘመን

ስለዚህም ንጉሠ ነገሥቱ በሚከተለው ምስክር ወረቀት የተረጋገጠውን ሽልማትም አደርጉ።
ኢትዮጵያ ከጠላት ለመከላከል በጦር ሜዳ ላይ ለወደቁት ጦረኞቻችን መታሰቢያ እንዲሆንና በጦር ሠራዊታችን ውስጥ ሆነው ኢትዮጵያ ለተከላከሉና ለረዱ፤ ወደፊትም ለሚከላከሉና ለሚረዱ ለታማኝ ዜጎቻችን ሁሉ በመልካም ፈቃዳችን ውለታቸውን በልዩ ለመግለጥ ምኞታችን ስለሆነ፤ በሕገ መንግሥታችን ፲፭ኛው ክፍል የተመለከተውን ዓይተን ይህንን ለመፈጸም፦
ታላቁን የሥላሴን ኒሻን ኮርዶን ሸልመናቸዋል። አዲስ አበባ ጥር 21 ቀን ፲፱፻፴፯ / ጸሐፌ ትእዛዝ ወልደ ጊዮርጊስ የጽሕፈት ሚኒስትር

፪ኛው የቅጽል ሥራ


መንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ከተስፋፋ በኋላ አሁን የያዘውን ቅርጽ እንደያዘ

፲፱፻፴፮ / የተመረቀው የቤተ ክርስቲያን ሕንፃ አዲስ አበባ ሕዝብ ብዛይ እየጨመረ ሲሄድ በመጥበቡ ፲፱፻፴፱ / አዲስ ቅጽል ሥራ ተጀምሮ አሁን ያለውን መልክና ሥፋት ሊያገኝ ችሏል። የአሁኑ ሕንፃ ወለል ስፋት ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ ፴፯ ሜትር ሲሆን ከሰሜን ወደደቡብ ፳፯ ሜትር ነው። ቁመቱም መካከሉ ላይ ፴፭ ሜትር ነው። በውስጡ ካሉት ዓምዶችና ከቅድስቱ ጀምሮ ያለው ሕንፃ በመጀመሪያው ጊዜ የተሠራው ያልተነካ ነው። በሰሜንና በደቡብ ያሉት ግንቦች ግን ፲፱፻፴፱ / የተቀጠሉት ግንቦች ናቸው።

የካቴድራሉ አሠራር

በመቅደሱ ውስጥ ሦስት መንበሮች ይገኛሉ። የተሠራበትም ዋጋው ፸፭ ብር ሲሆን፣ መካከለኛው በአጋእዝተ ዓለም ቅድስት ሥላሴ የተሰየመ ነው። መንበሩ ከወርቅ፣ ከብር፣ ክዝሆን ጥርስ፣ ከወይራ እንጨት ነው። ልዩ ልዩ የሥዕል ጌጣ ጌጦች በምሥራቅ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሞኖግራምና ዘውድ፣ በቀኝ እና በግራው መላእክትም አሉበት። ከፍ ብሎ ከአጎበሩ ላይ ደግሞ ክብር የተሠራ ምሴተ ሐሙስን የሚያስታውስ ማዕድ ይገኛል። በደቡብ ደግሞ በከርሠ ሐመሩ ላይ የንግሥት ሳባ ኒሻን፣ በአጎበሩ ግን የጰራቅሊጦስ ሥዕል ይገኛል። በአጎበሩ ተሸካሚ ዓምዶች ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ የሕይወት ታሪክና የስንዴ ቅርጽ ይገኝበታል።
በየ፬ቱ ማዕዘን ላይ የኪሩቤልና የሱራፌል ቅርጽ ወይም በአራቱ ወንጌላውያን የሚመሰሉት የሰው፣ የአንበሳ፣ የላም እና የንስር ቅርጽ ከብዙ ዓይንና ከየስድስቱ ክንፍ ጋር ይገኛል።ይሄ ሥራ በኢትዮጵያውያን አርቲስቶች የተሠራ ሲሆን በቤተ መንግሥቱ ልዩ ግምጃ ቤት ሹም በብላታ አድማሱ ረታ ተጠባባቂነት ነው።
ከዋናው መቅደስ በስተቀኝ በቅድስት ማርያም የተሰየመው መቅደስ ይገኛል። ከዋናው መቅደስ በስተግራ ደግሞ በመጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ የተሰየምው መቅደስ ይገኛል።የመቅደኡ ግንብ በሞላ በሞሴይክ የተሠራ ነው። ከቅድስቱ ውስጥ በቀኝ እና በግራ ከእንጨትና ከዝሆን ጥርስ የተሠሩ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እና እቴጌ መነን ወንበሮች (ዙፋናት) ይገኛሉ። እንዲሁም በዚሁ በቅድስት ውስጥ በቀኝ ለሴት ወይዛዝር፣ በግራ ለወንድ መኳንንት የተለየ የክብር መቀመጫ ይገኝበታል።


የቤተ ክርስቲያን ጌጣ ጌጥ

በሰሜንና በደቡብ በየመስኮቱና በየግንቡ የቅዱሳንና የመላእክት፤ የቅድስት ማርያም ሥዕል ይገኛል። በተለይ ግን በቅድስቱ ውስጥ ከግንቡ ላይ ከምሥራቅ ከፍ ብሎ ሥዕለ ሥቅለት፣ ዝቅ ብሎ ከበሩ ራስ ላይ ምስለ ፍቁር ወልዳ ይገኛሉ በዚህም ሥዕል ቀኝና ግራ ግርማዊ ጃንሆይና ግርማዊት እቴጌ እንደተማፀኑ ያመለክታል። ቀኝና ግራ ባሉት መቅደሶችላይ ያሉት ሥዕሎች ደግሞ ፩ኛው ጥምቀት ፪ኛው ኪዳነ ምሕረትን ያመለክታሉ።
በደቡብ በኩል ደግሞ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ኢትዮጵያ ጉዳት ዓለም መንግሥታት ማኅበር ያመለከቱበትን ጀኔቭ ጉባኤ የሚያመለክት ሥዕል ይገኛል።
በሰሜን በኩል ደግሞ የንጉሠ ነገሥቱን ወደ ኢትዮጵያ መመለስና ኦሜድላ ላይ ሰንደቅ ዓላማውን ሲተክሉ ያሳያል። በምዕራብ በኩል ኢትዮጵያ ሰማዕታት ዐጽም ከልዩ ልዩ ቦታዎች ተሰብስቦ በክብር ወደዚህ ቅዱስ ቦታ መግባቱን የሚያመለክት ሥዕል ይገኛል።

ሌሎች ሥዕሎች

በአቶ አገኘሁ እንግዳ በአቶ እምአላፍ ኅሩይ አቶ አለፈለገ ሰላም እና አቶ መዝሙር ዘዳዊት የተሣሉ፦
  • ፩ኛ/ ኢየሱስ ክርስቶስ ዕርገት የሚያመለክት ከፍ ብሎ ከኮፖላው ላይ
  • ፪ኛ/ ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግመኛ ምጽዐት የሚያስታውስ ሥዕል
  • ፫ኛ/ የሀገርና የውጭ አገር ቅዱሳን ሥዕሎች ይገኛሉ።

ማጣቀሻዎች

  1. ^ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፤ "መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሓዲስ" (፲፱፻፵፰ /))

ዋቢ ምንጭ

  • የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሐዋርያዊ ድርጅት፣ትንሣኤ፡ የሃያ አምስት ዓመታት መንፈሳዊ እርምጃ” (፲፱፻፶፱ /) ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት።
  • http://www.danielkibret.com/2011/10/blog-post_28.html
http://am.wikipedia.org/

No comments:

Post a Comment