Wednesday, July 10, 2013

‹‹ታወር ኢን ዘ ስካይ›› እንደ ጮራ ፈንጥቆ የጠፋው ትውልድ ታሪክ

 መላኩ ደምሴ 
‹‹መጽሐፍ የማነብ ሳይሆን ፊልም የምመለከት ነው የመሰለኝ፤››፣ ‹‹ለመሆኑ እንዲህ ዓይነት መጽሐፍ አገራችን ውስጥ ተጽፎ ያውቃል ወይ?››፣ ‹‹ይህንን መጽሐፍ ለመጻፍ የሚያስፈልገው ወኔ ከየት ይሆን የሚገኘው?››፣ ‹‹ከበቀል፣ ከጥላቻና ከወገንተኝነት ነፃ ሆኖ ለመጻፍ ማን የደፈረ አለ?››፣ ወዘተ የወቅቱን አነጋጋሪና አስገራሚ መጽሐፍ ‹‹ታወር ኢን ዘ ስካይ›› ካነበቡ ሰዎች በብዛት የተደመጡ ናቸው፡፡

ባለፈው ሰኞ ከቀትር በኋላ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ፋካልቲ እሸቱ ጮሌ አዳራሽን ከአፍ እስከ ገደፉ ሞልተው ከነበሩ በርካታ ሰዎችም የተደመጠው ከዚህ ይበልጥ እንጂ አያንስም፡፡ በቅርቡ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ተጽፎ ለንባብ የበቃው የ‹‹ታወር ኢን ዘ ስካይ›› መጽሐፍ ደራሲ ሕይወት ተፈራ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን አጠናቃ የዛሬ 40 ዓመት በ18 ዓመቷ ዩኒቨርሲቲ ስትገባ፣ በጻፈችው መጽሐፍ ላይ እንደተገለጸው፣ ከዚህ በፊት አይታው ከማታውቀው ወጣት ጓደኛዋና ሕይወቷን ከለወጡ ተከታታይ ኹነቶች ጋር እንደምታገናኝ አስባው አታውቅም፡፡

ግን ‹‹ያ ትውልድ›› እያልን የምንጠራው ታላቁን የየካቲት 66 አብዮት ያዋለደ ትውልድ አባል ሆና ከምጡ እስከ ልደቱ፣ ከወበቁ እስከ ሰቆቃው በውስጡ አልፋለች፡፡ በፍቅር፣ በተስፋና በጀግንነት ተጀምሮ፣ በግራ መጋባት፣ በሽብርና በመጨረሻም በእልቂት የተጠናቀቀው አብዮት ውጣ ውረዶች በጸሐፊዋ ነፍስ ዘርቶ ቀርቧል፡፡ ይህ ለሕዝቡ ነፃነት፣ ፍትሕና ብልፅግና መስዋዕትነት የከፈለ ትውልድ አምጦ የወለደው አብዮት በጉልበተኞች ተቀምቶ በአሳዛኝ ሁኔታ ያ ሁሉ እስርና ፍጅት ሲካሄድ የዚህ መጽሐፍ ደራሲ በተዓምር ተርፋ ለዚህ ዘመን የሚሆን ታሪክ ይዛ ቀርባለች፡፡ ሕይወት ተፈራ በመጽሐፍዋ ውስጥ እንደተረከችው ለበርካታ ጊዜያት ተዓምር በሚያስብሉ በርካታ አጋጣሚዎች ሕይወቷ ከአደጋዎች ተርፎ ለዚህ መብቃቷ ራሱን የቻለ ታሪክ ይወጣዋል፡፡

ይህ የዚያን ትውልድ ማዕከል አድርጎ የቀረበ ታሪክ በብዙዎች ዘንድ አድናቆትን ያገኘው በደፋር አዕምሮና በሰከነ ዕድሜ ታሪኩ ሳይዛባ በመጻፉ ብቻ አይደለም፡፡ ከሁሉም በላይ ይዞት በመጣው ምክንያታዊ አስተሳሰብ ጭምር ነው፡፡ ጸሐፊዋ ይህንን መጽሐፍ የጻፈችው በሕይወቷ ላይ ትልቅ አሻራ ያሳረፈባት የኢሕአፓ አመራር የነበረው ጌታቸው ማሩ የተባለ ዝነኛ ወጣት አደራ ተሸክማ ነው፡፡ ‹‹መጽሐፉን የፃፍኩት ያለምክንያት ከመጠፋፋትና አላስፈላጊ መስዋእትነት ከመክፈል በመውጣት እንነጋገር እንወያይ የሚለው የጌታቸው ማሩ ሐሳብ በውስጤ ስላለ ነው፤›› ብላለች፡፡

የፊውዳሉ ሥርዓት ኢሰብዓዊ ጭቆና ያንገፈገፈው ትውልድ ለሥርዓት ለውጥ ሲነሳ ዓላማውና ግቡ ነፃነት፣ ማኅበራዊ ፍትሕና ብልፅግና ለማምጣት የነበረ ቢሆንም፣ ብዙዎች ከዚህ ቀደም እያድበሰበሱ እንደተረኩት ሳይሆን በስልትና በስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ላይ በመለያየቱና ወደ ደም መፋሰስ በመግባቱ የደረሰው መከራ አገሪቱን ከል አልብሷታል፡፡ ሕይወት በዚህ መጽሐፍ አማካይነት የራሷንና የጌታቸውን ታሪክ መነሻ በማድረግ የተጓዘችበት መንገድ ግን እሷ እንዳለችው መጽሐፉ እንደ ጮራ ፈንጥቆ የጠፋው ትውልድ ታሪክ የተቃኘበት ነው፡፡ መጽሐፉን ያነበቡ በርካታ ሰዎችንም አክብሮት እንዲቸሯት ያደረገው አስገራሚው አቀራረቧ ብቻ ሳይሆን ሕሊናዋን በነፃነት መጠቀሟ ነው፡፡ በእርግጥ ኢሕአፓ፣ መኢሶን፣ ደርግ፣ ወዘተ የሚባሉ የወቅቱ የአብዮቱ ኃይሎች በፈጠሩት ልዩነት ምክንያት ከስክነት ይልቅ ወደ ግንፍልተኝነት የተቀየሩ የዘመኑ ወጣት አብዮተኞች ስህተት ዛሬ ላይ ተሁኖ በዛሬው ሚዛን እንደማይለካ የብዙዎች እምነት ቢሆንም፣ ሌላው ቀርቶ በአንድ ድርጅት ውስጥ ሆነው መደማመጥና በሐሳቦች ላይ መከራከር ያለመፈለግ የፈጠረው አስከፊ ውጤት በመጽሐፉ ውስጥ ጎልቶ ይታያል፡፡ ባለፈው ሰኞ ውይይት ወቅትም ሕይወት ያነሳችው ይህንኑ ነው፡፡ በኢሕአፓ ውስጥ በተፈጠረ የመስመር ልዩነት ምክንያት ዝነኛው ታጋይ ብርሃነ መስቀል ረዳ ሸሽቶ ወደ ገጠር ሲገባ፣ በጓዶቹ ላይ ከመጠን በላይ እምነት የነበረውን የጌታቸው ማሩን አሳዛኝ ግድያ ትተርክልናለች፡፡

‹‹ለጌታቸው ማሩ ራሴ ለራሴ የሰጠሁትን ኃላፊነት አለመወጣቴ እረፍት ይነሳኝ ነበር፡፡ አሁን ግን በዚህ መጽሐፍ ምክንያት እፎይታ ተሰምቶኛል፡፡ የጌታቸው ማሩ አሟሟት ሳይነገርና ሳይጠየቅ በመቅረቱ ጥብቅና ልቆምለት፣ ጉዳቱን ለኢትዮጵያና ለዓለም ሕዝብ ልነግርለት በማለት ይህንን መጽሐፍ ጽፌያለሁ፡፡ በዚህ መጽሐፍ ጌታቸውን ሰገነት ላይ ላስቀምጥ ሳይሆን ተገቢውን ቦታ ለማሰጠት ነው፡፡ የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው የሚለው ፍልስፍና የሚያስከፍለውን ዋጋ አይተናል፡፡ የእኔ ብቻ ይደመጥ የሚለው አስተሳሰብ የሚያስከትለውን አደጋ እናውቃለን፡፡ ታሪኩ የእኔ ወይም የጌታቸው ብቻ አይደለም፡፡ እንደ ጮራ ፈንጥቆ የጠፋው ትውልድ ታሪክ ነው፤›› ነበር ያለችው፡፡ ሕይወት ይህንን መጽሐፍ የጻፈችው ጭቆናን ለማስወገድ ተነስቶ የወደቀውን ትውልድ ለማሞገስና ለማወደስ ቢሆንም ያለፈው ታሪክ እንዳይደገም፣ በፊት የታየውን ያለመደማመጥና ያለመቻቻል ችግር ለዚህ ትውልድ በማሳየት ውይይት ለማድረግ ይረዳል በማለት እንዳዘጋጀቸው ገልጻለች፡፡ ዓላማውን ስታስረዳም ጣት ለመጠነቋቆልና ለመወነጃጀል ሳይሆን አዲሱ ትውልድ ምን መውረስ አለበት በሚል መሆኗን አስረድታ፣ ታሪክ የትናንት ብቻ ሳይሆን ዛሬንና ነገን ለማየት ጭምር በመሆኑ ካለፈው በመማር፣ በመከባበር፣ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ በመፍታትና አንድ በመሆን አገሪቷን ለሕዝቦቿ የተሻለች እንድትሆን ለማድረግ መሆኑን ስትናገር በከፍተኛ ጭብጨባ ታጅባለች፡፡

በውይይቱ ላይ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ፣ ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ፣ ዶ/ር ጌታቸው ሳህለ ማርያም፣ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ፣ አምባሳደር ታደለች ኃይለ ሚካኤልና አቶ ወልደልዑል ካሳ ለመወያያ የሚሆኑ መነሻ ሐሳቦችን አቅርበዋል፡፡ ያለፈው ትውልድ አባላት የሆኑት እነዚህ ምሁራን በተመደበላቸው አሥር ደቂቃ ውስጥ ባነሷቸው ሐሳቦች መነሻ የተለያዩ ጉዳዮች ተነስተዋል፡፡ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ የተማሪዎች ንቅናቄን፣ ፕሮፌሰር ገብሩ አብዮትንና የሚቀሰቅሱትን ጉዳዮች፣ ዶ/ር ጌታቸው የትውስታና የግለ ታሪክ አጻጻፍንና ተያያዥ ጉዳዮች፣ ዶ/ር ዳኛቸው መጽሐፉን በፍልስፍና አተያይ የቃኙበት፣ አምባሳደር ታደለች የመጽሐፉን አዘገጃጀትና ታሪካዊ ዳራ ከጸሐፊዋ ጋር ከነበራቸው ቅርበት ያዩበትና አቶ ወልደልዑል ካሳ የዚያን ዘመን ሰው ሆነው ገለጻ አድርገዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት አስተያየታቸውን ለታዳሚዎች ያጋሩ የተለያዩ ተናጋሪዎች መጽሐፉን ከስሜት የነፃ፣ ወገናዊ ያልሆነ፣ ለአገሪቱና ለሕዝቡ ነፃነት ታግሎ የወደቀው ትውልድ ማስታወሻ ብለውታል፡፡ ፖለቲካ ኮረንቲና እሳት በሆነበት አገር ውስጥ ፖለቲካ ፍቅር እንዲሆን ያደረገች ጸሐፊ በማለት ሙገሳ ያቀረቡ አስተያየት ሰጪም ነበሩ፡፡ የዚያን ዘመን ወጣት መሆናቸውን ያስታወሱ አንድ አስተያየት ሰጪ፣ ‹‹መጽሐፉ ውስጥ ጌታቸውን የእኔ ጀግና ብለሻል፡፡ አንቺ ደግሞ የእኛ ጀግና ነሽ፤›› በማለት አወድሰዋል፡፡ አንዲት አስተያየት ሰጪ፣ ‹‹ያለፈውን ሕይወታችንና ያለፍንበትን ውጣ ውረድ ያሳየሽበት መጽሐፍ በመሆኑ፣ አንቺ ለጌታቸው የገለጽሽውን ፍቅር ያህል እኔም ለመጽሐፍሽ ያለኝን ከልብ የመነጨ ፍቅሬን እገልጻለሁ፤›› ነበር ያሉት፡፡ ‹‹ለካ ነበር እንዲህ ቅርብ ነበር አሉ የተባለው እቴጌ ጣይቱ?›› በማለት ያለፈው ትውልድ የነበረው ፍቅር፣ መተሳሰብና ከራስ ወዳድነት የራቀ መንፈስ የታለ ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ አሁንም ‹‹እኔ ብቻ ልክ ነኝ›› የሚለው አባባል መቼ ይሆን የሚያበቃው ሲሉም ጠይቀዋል፡፡

በሌላ በኩል በዚህ ዘመን የሚታየው የመፈራረጅ፣ የመጠላላትና የማክረር ፖለቲካ መነሻው ከዚያ ትውልድ የተወረሰ በመሆኑ መፍትሔ ማፈላለግ እንደሚያስፈልግ ያነሱም አሉ፡፡ መደማመጥ፣ ጤናማ ውይይትና ክርክር ማካሄድ፣ ከእኔ በላይ ላሳርና አገር ወዳድ ማን አለ የሚለው ፉከራ የሚቆምበት፣ የመሳሰሉ ሐሳቦችም ተነስተዋል፡፡ የዚያን ትውልድ አብዮታዊ ትግል የሚያኮስሱ የሚመስሉ በጅምላ የመነዳትና ያነበበውን እንደወረደ ተግባራዊ የማድረግ የመሳሰሉ ሐሳቦች ደግሞ አልፎ አልፎ ቁጣ ሲፈጥሩም ታይተዋል፡፡ ያ ትውልድ ትልቁ ችግሩ ለራስ ባዕድ መሆኑና ለጥቅስ ቅርቡ መሆኑ፣ ያነበበውን ከተጨባጭ ሁኔታ ጋር ማገናዘብ አለመቻሉ የመሳሰሉ ትችቶች የቀድሞዎቹን የኢሕአፓ አባላት ፀጉር ያቆሙ አስተያየቶች ነበሩ፡፡

ብዙዎችን ያግባባው ወይም ሐሳቡ ሲነሳ የብዙዎችን ጭብጨባ ያስተናገደው ወይም የብዙዎች ጭንቀት የሚመስለው የመፈራረጅና የመጠላላት ፖለቲካ ነበር፡፡ በመግባባትና በመደማመጥ መነጋገር ሲቻል ጥላቻ መፍጠር ዋጋ እንደሌለው ማሳያ የነበረው የፕሮፌሰር ባህሩ ምሳሌ ነው፡፡ እሳቸው እንዳሉት በቀይ ሽብር ሰማዕታት ሙዚየም መሠራት ምክንያት ውይይት ተጀምሮ እንደነበር፣ ከዚያ በኋላ የዚያ ትውልድ አባላት ለአራት ቀናት ዘግተው የተወያዩበት ጅምር ሳይቀጥል ቀርቷል፡፡ የመቻቻል ፖለቲካ ለአዲስ ሥርዓት ምሥረታ ወሳኝ መሆኑን አንስተው፣ ያ ሁሉ የመከራ ዘመን አልፎ መነጋገር ሲጀመር የሚፈጥረው ስሜት ልብ የሚነካ እንደነበር አስረድተዋል፡፡ ግን መቀጠል አልቻለም፡፡

ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ ዓላማን ለማሳካት ሲባል ማንም ሰው ወንድሙን ወይም እህቱን አይገድልም ብለው፣ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ እዚህ የደረሰችው በእዚያ ትውልድ መስዋዕትነት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በአንድ አስተያየት ሰጪ ‹‹ትውልዱ ከራሱ ጋር ተጣልቶ ነበር›› ለተባለው አስተያት፣ ‹‹ትውልዱ ከራሱ ጋር ተጣልቶ አያውቅም፡፡ በታክቲክና በስትራቴጂ በመለያየት ብዙ ስህተት ሠርተናል፡፡ ራሳችንን ወቅሰናል አሁንም እንወቅሳለን፡፡ የሕይወት መጽሐፍ ሰላም ይፈጥራል፡፡ የተነሳነው ለሕዝባችን ነፃነት ነው፡፡ ይህ ታሪክ የእኛ ቅርስ ነው፡፡ ማንም እየተነሳ እንደ ከብት እየተነዱ እንዲለን አንፈልግም፡፡ ታሪካችንን የሚያንቋሽሸውን እንታገላለን፡፡ እንደዚያ ዓይነት አንባቢ ትውልድ አልተፈጠረም፡፡ ከአድዋ ድል ወዲህ የመጀመሪያው ጀግና ትውልድ ነው፡፡ ይህ ትውልድ የደሃ ገበሬ ልጅ ነበር፡፡ እኔ የቄስ ገበሬ ልጅ ነኝ፡፡ አታውቁም አትበሉን፡፡ እናውቃለን፡፡ ከእኛ በፊትም ተራማጅ አሳቢዎች ነበሩ፡፡ የውድ ወዳጄን ባህሩ ዘውዴን ዘ ፓዮኒርስ አንብቡ፤›› ብለዋል፡፡ ዶ/ር ዳኛቸው ከፍልስፍናው ወጣ ባለው አስተያየታቸው እነዚያ ወጣቶች ክቡር መስዋትነት ከፍለው የወደቁ ናቸው ካሉ በኋላ፣ በሃያዎቹ ውስጥ የነበሩት ወጣቶች በ40 ዓመታቸው ምን ይፈጥሩ እንደነበር እናስብ ብለዋል፡፡

ፕሮፌሰር ገብሩን በስሜት ያናገራቸው አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ስለዚያ ትውልድ ሲያነሱ የገለጹዋቸው ምሳሌዎችና ትንተናዎች ቢሆኑም፣ በአሁኑ ጊዜ በሕይወት ባሉ የትውልዱ አባሎች መካከል የሚታዩ ሽኩቻዎችና ግጭቶች ዛሬም በርደው ወይም ሰክነው አለመታየታቸው እንቆቅልሽ መሆኑ በስፋት ይታወቃል፡፡ በአንድ ወቅት ዶ/ር ደረጀ ዓለማየሁ የሚባሉ የመኢሶን የቀድሞ አመራር አባል በጋዜጣ እንዳስነበቡት፣ የኢሕአፓና የመኢሶን አመራሮች ደርግ እጅ ላይ ወድቀው አሰቃቂው ምርመራ ክፍል ውስጥ ሲገናኙ የሁለቱም ወገኖች አስተያየት ያ ሁሉ ጥላቻና መጋደል ለዚህ ነበር የሚል ይመስል ነበር፡፡ በዝምታቸው ውስጥ ሁለቱም ወገኖች የተጋሩዋቸውን ሲጋራዎቻቸውን እየማጉ ሲተያዩ መልዕክቱ ቁጭ ብለው የሚተያዩትን ያህል ሰከን ቢሉ ኖሮ ልዩነቶች ወደ መሣርያ መማዘዝ አያደርሱም ይመስል ነበር ያሉት፡፡

ጸሐፊዋ ሕይወት ጌታቸው ማሩን በመጽሐፉ ውስጥ ስትተርክ ሁሌም ለመወያየት፣ ለመደራደርና ለመከራከር ዝግጁ መሆኑን ነው፡፡ ነገር ግን ‹‹የበላይ አካል›› ተብለው የሚጠሩት ሰዎች ይህንን ባለመምረጣቸው ጌታቸው ከጓዶቹ ጋር በመሠረተው ድርጅት አማካይነት ተገድሎ አካሉ ተቆራርጦ በጆንያ መጣሉን ትተርካለች፡፡ በውይይቱ ላይ ስታስረዳ፣ ‹‹ዓላማዬ የጌታቸውን ታሪክ በመተረክ የትውልዱን ታሪክ ነው ያወሳሁት፡፡ ጌታቸው የዘመኑ ውጤት በመሆኑ የጥንካሬውን ያህል የራሱ ድክመት ይኖረዋል፡፡ የነበሩብኝን ክፍተቶች ለመድፈን ስል ነው ጓደኞቹን በማናገር ከልጅነቱ ጀምሮ ሰብዓዊ ባህሪውን ለማሳየት የሞከርኩት፤›› ብላለች፡፡ በመጽሐፉ ውስጥ ደግሞ ከእሱና ከፓርቲው ለመምረጥ እስክትቸገር የገባችበትን አስጨናቂ ፈተና እያሳየችን በመጨረሻ በሕይወቷ ለውጥ ማየት ስትጀምር የደረሰችበትን ድምዳሜ ትነግረናለች፡፡ ጌታቸው ተገድሎ ሐዘኗን በውስጧ አምቃ የተሰጣትን የፓርቲውን ተልዕኮ በአስገራሚ ዲሲፕሊንና ትጋት ስትወጣ ጌታቸው ከፓርቲው አይበልጥም በማለት ደምድማ ነበር፡፡ ለዚህም ነው ዳኛ ፊት ባልቀረበችበት ነገር ግን ያለፍርድ ከተገደሉ የትግል ጓዶቿ በተሻለ ሁኔታ 15 ዓመት እስራት ተፈርዶባት ከርቸሌ ከገባች በኋላ አዲሷ ሕይወት ብቅ የምትለው፡፡ በመጽሐፍዋ የመጨረሻ ገጽ ላይ በመጨረሻ ነፃነቷን እንዳገኘች፣ ሰብዓዊ ፍጡር ማለት ምን እንደሆነ እንደተማረች፣ የግለሰብ ኃላፊነትና ሞራል ትስስር ተምኔትን ከመገንባት የበለጠ መሆኑን እንደተረዳች ገልጻለች፡፡ እንዲያም ሆኖ ጌታቸው ማሩ ከተባለው ፍቅረኛዋና የዘመኑ የተማሪዎች ንቅናቄ መሪ የተማረችው እንዳላት ያስረዳችው፣ እሱ የሕይወቷ ጀግና በመሆኑ ከእሱ የወረሰችው ለሰው ልጆች ሕይወት ክብር፣ ለመቻቻልና ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት መትጋትን ነው፡፡ ብዙዎችንም ያስማማው ይኼው ነው፡፡

በእርግጥም መጽሐፉ እንደተባለለት የፍቅር፣ የአብዮት፣ የተስፋ፣ የህልሞች፣ የብጥብጥ፣ የሽብር፣ የእምነት፣ የክህደት፣ የሰቆቃ፣ የግራ መጋባት፣ ራስን የመለወጥና የሰው ልጅ መንፈስ የአሸናፊነት ኃይል ይታይበታል፡፡ ግን ይህ መጽሐፍ ብዙዎች እንዳሉት ዛሬ ላይ ተሁኖ ትናንትንና ነገን አሸጋግረው የሚያዩበት ነው፡፡ ትናንት በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ወጣቶች በዓላማ ፅናት ለግል ጥቅማቸውና ክብራቸው ሳይጨነቁ ለሰፊው ሕዝብ ልዕልና ራሳቸውን አሳልፈው የሰጡበትን ጀግንነት በስፋት ይዳስሳል፡፡ እነዚህ ወጣቶች ለእኩልነት፣ ለነፃነት፣ ለማኅበራዊ ፍትሕና ለሰብዓዊ ክብር ሲሉ ላመኑበት ዓላማ ወደር የሌለው መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡ በትግሉ ሒደት የተፈጠሩ ስህተቶች ዘግናኝ ዋጋ ቢያስከፍሉም በተለያዩ ጎራዎች ውስጥ ሆነው ላመኑበት ዓላማ የወደቁ ሰማዕታት ግን መቼም ቢሆን ሊዘከሩ እንደሚገባ በውይይቱ ላይ ተንፀባርቋል፡፡ ይህ መጽሐፍ ለአዲሱ ትውልድ እንደ ገጸ በረከት የቀረበ ያህል ለጸሐፊዋ ሙገሳ የቀረበላት ያለምክንያት አይመስልም፡፡

በውይይቱ መጨረሻ ላይ የውይይቱ ታዳሚዎች የገዙትን መጽሐፍ በደራሲዋ ፊርማ ለመታሰቢያነት ለመውሰድ ያደረጉት ርብርብ ይህንኑ የሚገልጽ ነበር፡፡ ግማሽ ሰዓት ያህል የወሰደው የማስፈረም ሥነ ሥርዓት ሲካሄድ ኦማር ካያም፣ ‹‹ዛሬን የመሰለ አስደሳች ቀን እያለልህ የሞተው ትናንትናና ያልተወለደው ነገ ለምን ያስጨንቁሃል?›› ያለው አባባል በዚህ መጽሐፍ አማካይነት የተሻረ ይመስል ነበር፡፡ ‹‹ለምን?›› የሚል መጠይቅ ሲቀርብም፣ ‹‹ትናንትን የመሰለ ውብ ግን በደም የጨቀየ አብዮት በሰከነ አዕምሮ ካልተዘከረ፣ ስለአሳሳቢው ነገ እንዴት ልንጨነቅ እንችላለን?›› የሚል ምላሽ አዕምሮ ውስጥ ያቃጭላል፡፡ ሕይወት በዚህ ልብ ሰቃይ መጽሐፍዋ የትናንቱን መከራና ስቃይ ስታስቃኝ የሺዎችን ሞት፣ እስራት፣ ግርፋትና መከራ ዘክራለች፡፡ ብዙዎችንም ያስማማው እሷ ከስምንት ዓመት በላይ ታስራ ወጥታ ከዓመታት በኋላ የጻፈችው መጽሐፍ የሰው ልጅ ከበቀል በፀዳ አዕምሮ ሳይጨመርና ሳይቀነስ ታሪክን መጻፍ እንደሚችል ነው፡፡ የእስር ቤት ጓደኛዋ አምባሳደር ታደለች፣ ‹‹እስር ቤት ከምንም ነገር በላይ ሰውን በሰውነቱ ማየት ጀመርን፡፡ ኢሕአፓና መኢሶን ተብለው የተለያዩና ይጣሉ የነበሩ ሰዎች በሒደት መነጋገር ጀመሩ፡፡ መነጋገር ሲጀመር ብዙ ነገሮች ረገቡ፡፡ አሁን ደግሞ የህሊና ቁስል አለ፡፡ አሁን በሕይወት ያለን ሰዎች ራስን ከመከላከል ወጥተን በመጠቋቆም ሳይሆን በመቻቻል መንፈስ መነጋገር ይቻላል፡፡ ስንወድም በጅምላ ስንጠላም በጅምላ መሆን የለበትም፡፡ ከዚህ ስንፀዳና ትክክለኛውን ነገር ማየት ስንጀምር ከህሊና ቁስል እንወጣለን፤›› ብለዋል፡፡ የሕይወት መጽሐፍም ሳይጨመርና ሳይቀነስ የተጻፈ መጽሐፍ ነው ሲሉ እማኝነታቸውን ሰጥተዋል፡፡

‹‹ታወር ኢን ዘ ስካይ›› መጽሐፍ በትውስታ ወይም በግለ ታሪክ የቀረበ ልብ አንጠልጣይ መጽሐፍ ሲሆን፣ ከመጀመርያው ገጽ እስከ መጨረሻው ድረስ ነፍስን ሰቅዞ የሚይዝ እንደሆነ ብዙዎችን ያግባባ ነው፡፡ ይህ መጽሐፍ በከፍተኛ ጥንቃቄና በታዋቂ ምሁራን እገዛ ከፍተኛ አርትኦት ተደርጎበት ለአንባቢያን የቀረበ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ አሳታሚነት በ428 ገጾች ተሰናድቶ የቀረበው ይህ መጽሐፍ በቅጂው ብዛት አናሳነትና በአማርኛ ቋንቋ ለምን አልተተረጎመም በማለት በርካቶች ጥያቄ ያቀረቡበት ነው፡፡ የታሪኩ ባለቤት የሆነው ሕዝብ በገዛ ቋንቋው ያን የታሪክ ጠባሳ ካላነበስስ ፋይዳው ምንድነው? ተብሎም ተጠይቋል፡፡ በሰኞው ውይይት ላይ ጸሐፊዋ እዚያው የተረከበችውን የአማርኛ የመጀመሪያ ረቂቅ በማሳየትና የረቂቁን አዘጋጅ በማመስገን በቅርቡ ለአንባቢያን እንደሚደርስ ቃል ገብታለች፡፡

‹‹ታወር ኢን ዘ ስካይ›› ሌላው አስገራሚ ገጽታው በውይይቱ ተሳታፊዎችም ሆነ በአንባቢያን ዘንድ የጎደለው ነገር አለ ተብሎ ጥያቄ አለመነሳቱ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት አወዛጋቢና አከራካሪ ጉዳይ ላይ ቀርቶ በዕለት ተዕለት የሥራ ክንውን ውስጥ በርካታ ህፀፆችና ጉድለቶች እየተነቀሱ ሲወጡ ከውስን ማብራሪያ ፍለጋዎች ውጪ ጉድለት አለመነሳቱም አስገራሚ ነበር፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ለዚህ ጸሐፊ አስተያየታቸውን የሰጡ አንድ የቀድሞ የዩኒቨርሲቲ መምህር፣ ‹‹ራሱን አርነት ያወጣ መንፈስ ከወገንተኝነትና ከአልባሌ ነገር ጋር ምንም እንደማያገናኘው ሁሉ፣ ሕይወት ከአስመሳይነትና ከአድርባይነት ራሷን ነፃ ካወጣች ቆይታለች፡፡ ሕይወቷን አሳልፋ የሰጠችለት ትግል በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ጓዶቿን አሳጥቷት ለማን ብላ ትዋሻለች? እኛ ተሸናፊዎቹ እያስመሰልን እንኑር እንጂ እሷማ አሸናፊ ከሆነች ቆይታለች፤›› በማለት ወደር የሌለውን አድናቆት ገልጸውላታል፡፡ ‹‹ይህ ገጸ በረከት የቀረበለት ትውልድ በአርዓያነት ይዘክራት፤›› ሲሉም አደራ ብለዋል፡፡
http://www.ethiopianreporter.com

No comments:

Post a Comment