Monday, July 1, 2013

የአርበኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ከአገር እንዳይወጡ ታገዱ

ሊቀ ትጉሃን አስታጥቄ አባተ
    ፍርድ ቤት ቀርበው በ25 ሺሕ ብር ዋስ ተለቀቁ

የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ሊቀ ትጉሃን አስታጥቄ አባተ፣ ተጠርጥረው በተከሰሱበት ከፍተኛ የማታለል ወንጀል ምክንያት ከአገር እንዳይወጡ ሰኔ 21 ቀን 2005 ዓ.ም. የእግድ ትዕዛዝ ተላለፈባቸው፡፡

ቀደም ባለው ቀጠሮ ሳይቀርቡ በመቅረታቸው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አምስተኛ ወንጀል ችሎት ለሰኔ 21 ቀን 2005 ዓ.ም. ታስረው እንዲቀርቡ ባዘዘው መሠረት ሰኔ 21 ቀን 2005 ዓ.ም. የቀረቡ ሲሆን፣ በመጀመርያ ቀጠሮ ያልቀረቡበት ምክንያታቸውን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡

በሕመም ምክንያት ሊቀርቡ አለመቻላቸውንና በዕለቱም በሕመም ላይ መሆናቸውን ለችሎቱ አስረድተዋል፡፡ ሰኔ 11 ቀን 2005 ዓ.ም. ተጠርጣሪዎቹ የተመሠረተባቸው ክስ ተሰምቶ የእምነት ክህደት ቃላቸውን መስጠት ቢገባቸውም፣ ዓቃቤ ሕግ ከክሱ ጋር የሚያያይዘው ቀሪ ማስረጃ እንዳለው ገልጾ፣ ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጠው በመጠየቁ ክሱ ሳይሰማ ቀርቷል፡፡

ሌላው ዓቃቤ ሕግ ለችሎቱ ያመለከተው ጉዳይ ተጠርጣሪዎቹ በአርበኞች ማኅበር ሠራተኞች ላይ ዛቻና ማስፈራራት እያደረሱ መሆኑን፣ ፕሬዚዳንቱ ቢሮ ባይገቡም ቤታቸው ውስጥ ሆነው እየሠሩ መሆናቸውን፣ በዚህ ሁኔታ ከቀጠሉ የማኅበሩ ንብረቶች አደጋ ላይ መሆናቸውን በማስረዳት፣ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥለት ጠይቋል፡፡

የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆችም ዓቃቤ ሕግ ያቀረበው ማመልከቻ በማስረጃ የተደገፈ መሆኑን ለችሎቱ በመግለጽ፣ የዓቃቤ ሕግ አቤቱታ ተዓማኒነት እንደሚጐድለው በማስረዳት አቤቱታው ውድቅ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል፡፡ ሊቀ ትጉሃን አስታጥቄም በቤታቸው መሥራታቸው ለመታመማቸው ማስረጃ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ድብደባ፣ ማስፈራሪያና ዛቻ እየደረሰባቸው ስላሉት የማኅበሩ ሠራተኞችና የዓቃቤ ሕግ ምስክሮችን በሚመለከት ዓቃቤ ሕግ በማስረጃ የተደገፈ አቤቱታ በጽሕፈት ቤት በኩል እንዲያቀርብ በማሳሰብ፣ ፕሬዚዳንቱ በ25 ሺሕ ብር ዋስ እንዲለቀቁ አዟል፡፡ ክስ ለመስማትና የእምነት ክህደት ቃል ለመቀበል ለሐምሌ 4 ቀን 2005 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
http://www.ethiopianreporter.com 

No comments:

Post a Comment