Monday, August 26, 2013

መጽሃፍና ስጋ፡፡ ሀብታሙ ስዩም


የዛሬ ወር ግድም ከኔ መጽሃፍ መደብር ጎን ስጋ ቤት ተከፈተ፡፡የስጋቤቱ ባለቤት ሰዎች አለማየሁ በሬዎች አራጅ አየሁ እያሉ የሚጠሩት ጎልማሳ ነበር፡፡
አለማየሁ ሻኛ ቤቱን በከፈተ ሰሞን በኔ መጽሃፍ ቤት ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ እንደሌለ በማሰብ ምንም አልተሰማኝ ነበር፡፡ከጥቂት ቀናት በኃላ ግን ለአምሮት የተከፈተ ስጋ ቤት ለአዕምሮ የተከፈተን መጽሃፍ ቤት ሊያዘጋ እንደሚችል ተረዳሁ፡፡
አለማየሁ መጽሃፍ ለመግዛት የመጡ ደንበኞችን መደብ ስጋ ማስገዛት የሚያስችል መተት ሳያስቀብር አልቀረም፡፡ስጋ ቤቱ በተከፈተ በመጀመሪያው ቀን ወትሮ በሳምንት አራት ውድ መጽሃፍትን የሚገዙኝ ሰዎች ከሱ ሁለት መደብ ሽኮና ገዙና ከኔ ሁለት የተረት መጽሃፍትን ብቻ ገዝተው ሄዱ፡፡ በሁለተኛው ቀን እኒሁ ደንበኞቼ ከሱ ሶስት ኪሎ የጭን ስጋ ከአስመተሩ በኃላ ከኔ የጭን ቁስል የሚለውን መጽሃፍ ብቻ ገዝተውኝ ሄዱ፡፡በሶስተኛው ቀን እኒሁ ደንበኞቼ በሱ እልፍኝ ተሰገሰጉ እኔን ግን የእግዜር ሰላምታ ነፈጉ፡፡
አለማየሁ በዚህ የሚረካ ሰው አልነበረም ለጥየቃ የሚመጡ አንባቢዎችን ሳይቀር ወደ ስጋ ቤቱ ለማስኮብለል ጥረቱን ቀጠለ፡፡
አንድ ቀን አንድ አዲስ መጽሃፍ ወዳጅ ወደ ሱቄ መጣና
‹‹ስለ ሃረር ከተማ የተጻፈ መጽሃፍ አለህ?››ብሎ ከመጠየቁ አለማየሁ ከስጋ ቤቱ መስኮት በኩል አንገቱን አስግጎ፤‹‹እዚህ ከሃረር ሰንጋ ላይ የተመተር ናሽፍ ስጋ አለ፡፡››አለ በጮማ የተጋረደውን የወይፈኑን በድን እያሳየው፡፡ሰውየው ሶስቴ አይኑን አርገብግቦ አራቴ ምራቁን ዋጠ፡፡
‹‹ሰው በምግብ ብቻ አይኖርም!››ስል አንባረቅኩ የገዥውን ቀልብ ወደኔ ለመመለስ፡፡
‹‹ትክክል ነው ! ሰው በምግብ ብቻ አይኖርም ካልተበላ ግን ያነበቡት አይዘልቅም፡፡አይደለም እንዴ?››አለ አለማየሁ ከወይፈኑ ሻኛ ላይ የቆረጠውን ሙዳ ስጋ ተንጠራርቶ ለሰውየው እያጎረሰው፡፡ሰውየው ባፉ ያለው ስጋ ስስነት የአለማየሁን ስድነት ሲጋርደው ታወቀኝ፡፡ቀልቡን ለመመለስ ጥረቴን ቀጠልኩ፡፡አለማየሁ ንግግሬን እየተከታተለ ያናጥበኛል፡፡
‹‹ይሄ መጽሃፍ እጅግ አሪፍ መጽሃፍ ነው፡፡ሌላ ቦታ ብትጠይቅ ከ200ብር በታች አታገኘውም፡፡››
‹‹እግዜር ያሳይህ 200ብር እኮ የአንድ መደብ ስጋ ዋጋ ነው¡››
‹‹መጽሃፉ እጅግ ጠቀሜታ ያለው መጽሃፍ ነው!››
‹‹ሽህ ጠቀሜታ ቢኖረው መቸም እንደ ቋንጣ ተዘልዝሎ አይቀመጥ¡››
‹‹ደንበኛየ ስለምትሆን ይሄን መጽሃፍ ከገዛህ ስለ ስንፈተ ወሲብ የሚያወራ መጽሃፍ እመርቅልሃለሁ፡፡››
‹‹ምራቂውንስ ለኛ ተወው፡፡አንድ ኪሎ የሾርባ አጥንት ለገዛ ግማሽ ኪሎ ሽንፍላ የሚመርቅ ከኛ ሌላ በዚች አለም ላይ የት አለ፡፡››
አለማየሁ አሸነፈ፡፡
በቀጣይ ሳምንታትም ሽንፈቴ ቀጠለ፡፡
ከኔ ሱቅ የሚነሳው የአሮጌ መጽሃፍ መዐዛ ያሰባሰባቸው አንባቢዎች፡፡ከስጋቤቱ የሚነሳው የትኩስ ጥብስ መኣዛ አሸፈታቸው፡፡ምን እናንብ እያሉ ያማክሩኝ የነበሩ ወጣቶች ምን አንብላ ሊሉት አለማየሁን ወዳጅ አደረጉት፡፡የቤተክርስቲያን ልጆች ሳይቀሩ ዳዊት ሊገዙ መጥተው ዳቢት ሲያስመዝኑ ታዩ፡፡
ከእለታት በአንዱ ደግሞ ያልታሰበ መርዶ ደረሰኝ፡፡አለማየሁ ጠቀም ያለ ገንዘብ ለአከራያችን ከፍሎ የኔን መጽሃፍ ቤት ሊጠቀልለው መሆኑ ሰማሁ፡፡ስጋቤቱ ሲሰፋ መጽሃፍ ቤቱ እንደሚጠፉ ግልጽ ሆነ|፡፡
ነገሩን በሰማሁ ቀን እንደ እብድ አደረገኝ፡፡war and peace የተሰኘውን ሰው ላይ ቢወድቅ ሲጥ የሚያደርግ መጽሃፍ እንደላውንቸር ተሸክሜ በስጋ ቤቱ ተከሰትኩ፡፡

አራጅ አየሁ የአንድ ምስኪን ወይፈን ሽንጥ በአንድ ጨካኝ ፋስ እየከተከተ ነበር፡፡
‹‹ደህና አደርክ አለማየሁ!››አልኩት አሰነዛዘሩ ንዴቴን አለዝቦብኝ፡፡
‹‹ይመስገነው ፡፡››አለኝ ቀና ሳይል፡፡ይመስገነው አባባሉ ለአምላክ ይሁን ካለተቃውሞ ለሚከተከትለት ወይፈን ግልጽ አይደለም፡፡
‹‹ለመሆኑ መጽሃፍት ያላቸውን ጠቀሜታ ታውቃለህ?››አልኩት ለማስረዳት ቋምጨ፡፡
‹‹አዎ አውቃለሁ የኤርትራ ጉዳይን የመሰሉ ግዙፍ መጻህፍት ገጻቸው ስጋ ለመጠቅለል ግሩም ነው፡፡››
የአለማየሁ መልስ ከአለማየሁ ቴወድሮስን አጽም አለመመለስ በላይ ያበሳጫል፡፡ግን ስለመጻህፍት ጠቀሜታ በማስረዳት ከጀመረው ጸረ-ንባብ አካሄድ እንዲታቀብ ለማስረዳት ጥረቴን ቀጠልኩ፡፡
‹‹መጽሃፍ አንብበህ ታውቃለህ?››አልኩት የሚሰነዝረው ፋስ አካላቴ ላይ ያረፈ ይመስል እየተሰቃጠጥኩ፡፡
‹‹አዎ !ሁሉንም የበአሉ ግርማ መጽሃፍት አንብቢያለሁ፡፡››
‹‹እንግዲያውማ ደራሲው የሚለው መጽሃፍ ላይ መላጣው ሰውየ ሲራክን ‹‹ከመጽሃፍ ሌላ ወዳጅ የለህም እንዴ ?››ብሎ ሲጠይቀው ‹‹ ጥሩ መጽሃፍ ከወዳጅ ይበልጣል፡፡›› ያለውን ታስታውሳለህ? ማለት ነው ፡፡››
አልኩት አዎ ቢለኝ እንዴት ከዚህ ጥቅስ ተነስቼ ሀሳቡን እንደማስቀይረው እያቀድኩ፡፡
‹‹አይ እኔ እንኳ የማስታውሰው ሃዲስ በተባለው መጽሃፉ ላይ ፊታውራሪ ተካ ስጋ አቆራረጥ እና አያያዝ አበላል የማያውቅ ሰው ሲገጥማቸው በንዴት ቶሎሳን እየጠሩ ‹ምንድነው ይሄ ስጋ እንደሽንኩርት የሚከትፈው ቢለዋውን ቀማውና አቆራረጥና አበላል አሳይልኝ …እንዲህ ነው፡፡›የሚሉትን ነው፡፡
ለአለማየሁ ስለመጽሃፍ ጠቀሜታ የሚያስረዳ ጥቅስ ከመመዘዝ ክብረነገስትን በቃል መያዝ እንደሚቀል አሰብኩ ፡፡ደንቆሮነቱን ልነግረው በማሰብም፡፡
‹‹ሰምና ወርቁ ተሰማ እሸቴ በተሰኘው መጽሃፍ ላይ፤
ምንኛ ነቀፍኩት ደንቆሮነትን
እኔስ የምመኘው ታስሮ መማርን፡፡
የሚለውን ቅኔ ብታነብ ኖሮ እንግባባ ነበር ››አልኩት፡፡እሱ መች ሚሸነፍ ሆነና
‹‹ማንበቡንስ አንብቤዋለሁ
ጎድን ከዳቢት ሰብራዳ
ይገባ ነበር ለእንግዳ
አያችሁ ወይ ይሄን ቀን
ታላቅ ታናሽ ሲሆን፡፡
ከሚለው ቅኔ ስለማይበልጥብኝ እንጂ፡፡›› ሲል መለሰልኝ፡፡
የያዝኩትን መጽሃፍ ጭንቅላቱ ላይ ባሳርፍበት ተመኘሁ፡፡ግን መጽሃፌ ጭንቅላቱ ላይ ከማረፉ በፊት ፋሱ ጭንቅላቴ ላይ ቢያርፍ የሚሆነው ታውሶኝ ተውኩት፡፡

ያላሰብኩት የበቀል ስሜት በውስጤ ተጸነሰ
ማርከስ አውርለስ
The best revenge is to be unlike him who performed the injury.እንዳላለ ሁሉ፡፡
ፍሬድሪክ ኒቼ
it is impossible to suffer without making some one pay for it. Every compliant already contains revenge .
እንዳለው ሁሉ ፡፡
ማርቲን ሉተር ኪንግ
Man must evolve for all human conflict and method which reject revenge aggression and retaliation.
እንዳላለ ሁሉ፡፡
ከቀናት በኃላ አከራየን የተወሰኑ ቀናት ከለመንኳቸው በኃላ የተሰደዱ ደንበኞቼን ቢቻል ወደኔ ሱቅ ለማምጣት ባይቻል ከአለማየሁ ስጋ ቤት ለማስወጣት መላ ፈጠርኩ፡፡
የመደርደሪያየን ሩብ ክፍል ከመጽሃፍት ነጻ አደረኩት በምትኩ ሽንጥና ታላቅ ሰቀልኩበት፡፡
ከውጭ በደማቁ ምርጥ ምርጥ መጽሃፍት አሉ፡፡ስጋም አለ፡፡ ብየ ለጠፍኩ፡፡
ፍላጎቴ ለስጋው የሚመጡ ሰዎችን ንባብ አሰለምዳለሁ የሚል ነበር፡፡
እንዳሰብኩት በዛ ያሉ ሰዎች ወደ ሱቄ መምጣት ጀመሩ፡፡ለስጋ የተውኩት የመደርደሪያው ክፍል እየሰፋ መጣ፡፡ ለመጽሃፍት የተውኩት ክፍል ሲጠብ ታየኝ፡፡
በአመቱ መጨረሻ ላይ የአለማየሁ ስጋ ቤት እንደሚዘጋ ርግጠኛ ነኝ፡፡ርግጠኛ ያልሆንኩበት እንድሮው ለመጻህፍት ጠበቃ መቆሜን ነው፡፡ምክንያቱም ከመደርደሪያየ ላይ የስጋ ዘር የመጽሃፍ ዘርን ከገረሰሰ ወራት አልፈዋል፡፡ከአይምሮየ ላይ የስጋ ብር የመጽሃፍን ክብር ካሰረሳኝ ብዙ ቀናት ሄደዋል፡፡

1 comment: