ተጻፈ በ ምሕረተሥላሴ መኰንን
![]() |
የፀሐይ ዮሐንስ |
‹‹ማንበብና መጻፍ ዋናው ቁም ነገር፤ ከሕይወቴ ጐሎ እሸበር ጀመር›› የሚለው ስንኝ የብዙዎች ትዝታ ነው፡፡
በጊዜው በመሠረተ ትምህርት ዘመቻ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደነበረውም ይታመናል፡፡ ‹‹ሳብ ሳም››፣ ‹‹ተባለ እንዴ›› እና ‹‹ያላንቺማ›› የፀሐዬ (ብዙዎች እንደሚጠሩት) ስም ከሚነሳባቸው ዘፈኖች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ በተመሳሳይ ስለ ሀገር ያዜማቸውም የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ፀሐዬ ‹‹የኔታ›› የተሰኘ አልበም በቅርቡ ለቋል፡፡ አልበሙንና አጠቃላይ የሙዚቃ ሕይወቱን በሚመለከትምሕረተሥላሴ መኰንን ከፀሐዬ ዮሐንስ ጋር ቆይታ አድርጋለች፡፡
ሪፖርተር፡- ከመታወቅህ አስቀድሞ የሙዚቃ ሕይወትህ ምን ይመስል ነበር?
ፀሐይ፡- ጃንሜዳ አካባቢ መኖሬ ወደ ሙዚቃ ለመግባቴ ትልቁ ምክንያት ይመስለኛል፡፡ የልጅነቴን ተሰጥኦ እዛ ነው ያዳበርኩት፡፡ በምንነጋገርበት በዚህ የጥምቀት ሰሞን ብዙ ትዝታ አለኝ፡፡ ጥምቀት ለሙዚቃ ፍቅሬ መንገድ የከፈተ ነው፡፡ ያደግኩበትም ግቢ ጃንሜዳ አጠገብ ባለው ሙዚቀኛ ግቢ ነው፡፡ ጥላሁን፣ መሐሙድና ብዙነሽ የነበሩበት ክብር ዘበኛ ኦርኬስትራ ትልቁን ሚና ተጫውቷል፡፡ ጠዋት ደብተር ይዤ ሄጄ እዛ እውላለሁ፡፡ ክብር ዘበኛ ባልሠራም የክብር ዘበኛ ልጅ ስለሆንኩኝ ልጅነቴ በሙዚቃ ተጣጥሞ አልፏል፡፡
ሪፖርተር፡- ድምፃዊነትን ሙያዬ ብለህ ‹‹በርታ ዘመዴ››ን ከተጫወትክ በኋላስ?
ፀሐይ፡- ያኔ ዜማ ማውጣት ጀመርኩ፡፡ ‹‹ማንበብና መጻፍ›› የኔ ዜማ ነው፡፡ አቶ ተስፋዬ ለማ አምባሳደር ቴአትርን ባቋቋሙበት ጊዜ በ1970 ዓ.ም. ከጓደኞቼ ጋር የመጀመሪያ ቅጥሬን አምባሳደር አደረግኩ፡፡ ከዛ በፊት ከክብር ዘበኛ ጋር ለዕድገት በኅብረት ዘመቻ ‹‹በርታ ዘመዴ ዘማቹ ጓዴ››ን ከሒሩት በቀለ ልጅ ጋር ሆነን ሠርተናል፡፡ ከዛ በኋላ አሻራዬ ያረፈባቸው 14 አልበሞች አሉኝ፡፡
ሪፖርተር፡- የመጀመሪያ አልበምህ እንዴት ነበር?
ፀሐይ፡- ሙዚቃ ቤቶች ፕሮዲውስ ያደርጉ ስለነበር ልምድ ያለው ሰው ይፈልጋሉ፡፡ በዛ ወቅት ገና ልጅ ነኝ፡፡ ስሜት እንጂ ልምድ የለኝም፤ ስሜቴን ወደ ተግባር ለመቀየር ገንዘብ ስለሚያስወጣ ፕሮዲውሰሩ ይቸገራል፡፡ እንደ ምንም የመጀመሪያው ካሴት በሱፐር ሶኒክ ሙዚቃ ቤት አሳታሚነት ተሠራ፡፡ ጥሩ እየተሸጠ እያለ በአጋጣሚ እነ መሐሙድ አህመድና ውብሸት ፍስሐ ወደ ኤሜሪካ ከዋልያስ ባንድ ጋር ሄደው በኤሌክትሮኒክስ መሣሪያ ታጅበው ‹‹ማለዳ ማለዳ›› ያለበትን ካሴት አወጡ፡፡ ካሴቱ የእኔን ሸፈነውና ብዙ ሳይደመጥ አለፈ፡፡ በዓመቱ በንዴት ‹‹ፍንጭቷ››ን ሠራሁ፡፡ ‹‹ፍንጭቷ››ን ይዤ ስወጣ ፀሐዬ ዮሐንስ የሚለው ስምም ተገኘ፡፡
ሪፖርተር፡- ትንሹና ከፍተኛውስ ክፍያ ስንት ነው?
ፀሐይ፡- ያልተለመደ ዘዬና ድምፅ ይዤ ስለመጣሁ በሽያጭ ‹‹ፍንጭቷ›› በጣም ኃይለኛ ነበር፡፡ ‹‹ሳብ ሳም››፣ ‹‹ተባለ እንዴ›› እና ‹‹ያላንቺማ›› በጣም ጥሩ ሥራዎች ነበሩ፡፡ የመጀመሪያ ክፍያዬ 3,000 ብር ነበር፡፡ እንደ ጀማሪና በወቅቱ ገንዘቡ ከነበረው ዋጋ አንፃር ትልቅ ነበር፡፡ የ300,000 ሺሕ ብር ያህል አቅም ነበረው፡፡ የመጀመሪያ ካሴት ስም ማግኛ ስለሆነ ከክፍያ ይልቅ ስም ማግኘቱ ላይ አተኩሬ ነበር፡፡
ጥበብን በገንዘብ መለካት አስቸጋሪ ነው፡፡ በተለይ በእኛ ሀገር በሥራውና በተሸጠው መጠን አይከፈልም፡፡ መልካም ሥራ በመሥራት መልካም ስም ነው የሚተርፈው፡፡ በ‹‹ተባለ እንዴ›› ጊዜ ክፍያው 100,000 ሺሕ ብርም ደርሶ ነበር፡፡ ከ‹‹ተባለ እንዴ›› በኋላ የካሴት ሥራ የተበላሸበት ዘመን ነው፡፡ ሰው ሸጦ የሚያተርፍበት ጊዜ አልነበረም፡፡ ኮምፒዩተር መጣና በደቂቃ ሁሉም ሰው የሚቀዳበት ደረጃ ደረሰ፡፡ ሲዲ ከመምጣቱ በፊት ሽያጭ ጥሩ ነበር፤ ከፍተኛ የገቢ ምንጭም ነበር፡፡ ኦሪጅናል ካሴት 13 ብር ይሸጥ ነበር፡፡ ለማባዛት ባዶ ካሴት አምስት ብር ማስቀጃ ሦስት ብር ነበር፡፡ አምስት ብር ጨምሮ ኦሪጅናል መግዛት ስለሚመረጥ ገበያ ነበር፡፡ ዛሬ በአንድ ፍላሽ እስከ 500 ዘፈን ስለሚያዝ ኦሪጅናል የሚገዛ የለም፡፡ አቁሞ የሚያስኬደን ከኮንሰርት የሚገኝ ገንዘብ ነው እንጂ ዛሬ የሚሠራው ለነገ አያበረታታም፡፡ ጥበቡ እየሞተ ይመስለኛል፡፡ ባወጣሁት ልክ ካላገኘሁ የመሥራት አቅሜ ይዳከማል፡፡ ዛሬ እኔ ነገ ደግሞ ሌላው ከዘርፉ ይወጣል፡፡ በ‹‹የኔታ›› አልበም ብዙ ነው ያወጣሁት፡፡ የሚመጣውና የሚገኘው ተመጣጣኝ ካልሆነ ነገ ለጥበብ ብዬ ለፍቼ ልሠራ አልችልም፡፡ አልበሙ በሙሉ ባንድ ነው የተሠራው