Monday, August 17, 2015

ታሪክን ስናስታውሰው !

ምስሉ ከኤድዋርዶ ገጽ የተወሰደ ነው





ይህ ቪዲ  ለዛሬው ትውልድ የሚያሳየን እውነት አለ ፡፡ ዛሬ ስለኢትዮጵያውንት ለማውራት ሰቀቀን የሆነበት ዘመን ላይ
ብንደርስም የዚህ ታዳጊ  ጥልቅ መልክት ግን ስለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውነት መንፈስ መለስ ብላን እንድናስብ እና
ያ  የአንድንት መንፈስና ስለሀገር የማሰብ ወኔ ወዴት ጥሎን ሸሸ እንድንል ያደርጋል፡፡ በዚያውስ እምዬ ምኒልክ ዛሬ ነሀሴ 12 ቀን
ነው የተወለዱት ሲል ታሪክ ዘክሮልናል ፡፡ ታዲያ የዚህ ታዳጊ መልክት ለሳቸው ማታሰቢያ ቢሆንስ….
ማንም በአስተሳሰቡ የማይፈረጅባት ፤ በማንነቱ የማይጉላላባት፤ የሰላምና የፍቅር ሀገር ትሆን ዘንድ እመኛለሁ ኢትዮጵያ ፡፡


ደራስያንን እንደሰው ያለመመልከት አባዜ

    አለማየሁ ገላጋይ




















ፊት ለፊት ስራው፣ ከበስተጀርባ ደግሞ ህይወቱ ይገኛል፡፡ ሥራው የህይወቱ ማጣቀሻ ነው የሚሉ አሉ፡፡ በዚህም ሥራውን እንደ አነፍናፊ ውሻ አስቀድመው ህይወቱን ያንጎዳጉዳሉ፡፡ “እንዲህ ሲል የፃፈው በህይወቱ እንዲያ ስለሆነ ነው፡፡” በማለት ሥራና ህይወቱን ያጋባሉ፣ ያፋታሉ፡፡ ስለዚህ የደራሲ ቤት በሩ ቢዘጋም ከመግባትና ከመውጣት አይከላከልም፡፡ የደራሲ ደጃፍ ውሻ ቢታሰርበትም አያስፈራም፡፡ ቢታጠርም ከዘላዮች አያመልጥም፡፡ 
እኛ ዘንድ እንዲያ ለማድረግና ለመሆን የሚያስችል ሁኔታ የለም፡፡ ደራሲ የጓዳ ህይወቱ ቀርቶ አደባባይ የዋለው ሥራው እንኳን “በሙሉ አይን” አይታይም። ሀዲስ አለማየሁ፣ በዓሉ ግርማ፣ መንግሥቱ ለማ፣ ከበደ ሚካኤል፣ ፀጋዬ ገብረመድህን… የኖሩት ቀርቶ የፃፉትም የሚታየው በእሽኩርምሚት ነው። ከሥራዎቹ ፊት “ተልመጥማጮች” ያጠሩት የሙዚየም “ክር” አለ፤ አይታለፍም፡፡ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያም አለ፤ “በእጅ መንካት ክልክል ነው” የሚል፡፡ እኔ የሚገርመኝ “የተልመጥማጮቹ” በክር ማጠርና መንገር አይደለም፡፡ የእኛ አክብሮ ሥነ - ፅሁፍን በሙዚየም ህግ መጎብኘት እንጂ …፡፡ 
“የሀዲስ ዓለማየሁ ፍቅር እስከ መቃብር ተረታማ ነው” ከተባለ “ቱግ” የሚሉ “አንቀራባጮች” አሉ። “በዓሉ ግርማ ልቦለድ ያድፋፋል፤ አጨራረሱ መሰላቸት የሚታይበት የተካለበ ነው” ከተባለ የሥራው “ተሸላሚዎች” ፣ “ሐይማኖት የግል ነው፣ ለምን ይነካብናል?” በማለት ህገ መንግሥት መጥቀስ ይዳዳቸዋል፡፡ “የመንግሥቱ ለማ ግጥሞች ጥብቀትና ፍላት የሌላቸው በተሃ ናቸው” ከተባለስ? ጉዳዩን የቤተሰብ ፖለቲካ አድርገው “አብዬን?” የሚሉና የዛገ ጦር ከራስጌ የሚመዙ ሞልተዋል፡፡ “ከበደ ሚካኤል መከሩ፣ ዘከሩ እንጂ አልተቀኙም” የሚል ካለ፣ “ባባቶቻችን ደም” ይዘፈንበታል፡፡ “ፀጋዬ ገብረመድህን ግጥም እንጂ ዝሩው ያዳግተዋል” ብሎ በህይወት መኖር ያዳግታል … 
የእኛ ሥነ - ፅሁፍ መብላላት ሲገባው የሚደነብሸው ለዚህ ሳይሆን ይቀራል? ገንዘብ ያወጣሁበትን መፅሐፍ ለመግዛት፣ ጊዜ ያፈሰስኩበትን ልቦለድ (ለማንበብ)፤ ቦታ የሰጠሁትን ሥራ ለማስቀመጥ … እንዴት በሌሎች እይታ እንድገመግመው እገደዳለሁ? እንዳቅሜ ከቻልኩ “ብበላው”፣ ካልቻልኩ “ብደፋው” ከውይይት ያለፈ ከሳሽና ወቃሽ ሊመደብብኝ ይገባል?... 

“ላምባ” ፊልም መሰረቁ ከሰብዓዊ ዓላማው አስተጓጎለው ተባለ (አለማየሁ አንበሴ)

 ሌብነት እንኳ አይነት አለው !
 
 በእውነት በ”ላንባ” ፊልም ላይ የተፈጸመው ዝሪፊያ ህሊናችን ከውዴት ነው ያሰኛል፡፡
በአንድቤት ውስጥ አንድና ከዚያ በላይ በኩላሊት ህመም እየተሰቃዩ ባሉ ህማን ላይ እንደመቀለድ ነው፡፡  ….እንኳንስ ድሀው
ምንም የሌለው ገንዘብ ያለውን እያደኸየ ያለ ፤ ድንገት ማንንም የሚጥል ህመም ፤ እድሜና ጾታን የማይለይ ህመምን
ለመዋጋት የሚደረግን ጥረት የሚያኮላሽ ተግባር ….. በአውነት ያማል ፡፡ ሌብነት እንኳ አይነት አለው ፡፡
ይህን አንብባቹ ፍረዱ !!!!!!!!!!!
“ላምባ” ፊልም መሰረቁ ከሰብዓዊ ዓላማው አስተጓጎለው ተባለ

“25 ተመልካቾች ራሳቸውን ስተው ወድቀዋል”
               ፊልሙ የተመልካች አድናቆትን አትርፏል 
                                
      በመጋቢት ወር መጨረሻ ላይ ተመርቆ ለዕይታ የበቃው “ላምባ” ፊልም ተሰርቆ በኢንተርኔት በመለቀቁ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከሲኒማ ቤት የወረደ  ሲሆን ከተነሳለት ሰብዓዊ ዓላማም እንዳስተጓጎለው ተገለፀ፡፡ በእውነተኛ ታሪክ ላይ ተመስርቶ የተሰራው ፊልሙ፤ በአንድ ኩላሊት ህመምተኛ ላይ የሚያጠነጥን ሲሆን ለእይታ በቀረበባቸው ጊዜያት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተመልካች እንደነበረው ታውቋል፡፡ 
ፊልሙ በዘውዲቱ ሆስፒታል ውስጥ ለሚገነባው የኩላሊት ህክምና ማዕከል በሚሊዮን ብር የሚገመት ገቢ ለማሰባሰብ ታቅዶበት የነበረ ቢሆንም ማንነታቸው ባልታወቀ ሰዎች ተሰርቆ በኢንተርኔት በመለቀቁ ዓላማው እንደከሸፈ የፊልሙ ፕሮዱዩሰሮች ይገልፃሉ፡፡ 
ፊልሙ ከሲኒማ ቤት በምን ሁኔታ ተሰርቆ እንደወጣ ያልታወቀ ሲሆን ፕሮዱዩሰሮቹ፣ “በበርካቶች እጅ መግባቱን በማረጋገጣችን ወደ ክስ ለመሄድ እምብዛም ጥረት አላደረግንም” ብለዋል፡፡ ፊልሙ ከአብዛኞቹ ሲኒማ ቤቶች የወረደ ቢሆንም በአሁኑ ሰዓት በላፍቶ ሞልና በአምባሳደር ሲኒማ እየታየ እንደሆነ ታውቋል፡፡ 
የተመልካቹ ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ እንደነበር የጠቆሙት የፊልሙ ደራሲና ዳይሬክተር አቶ አንተነህ ኃይሌ፤ በኩላሊት ህመምተኛ ላይ የሚያጠነጥነው ፊልም እጅግ አሳዛኝ በመሆኑ የተነሳ በተለያዩ ሲኒማ ቤቶች 25 ተመልካቾች ራሳቸውን ስተው እስከመውደቅ መድረሳቸውን ተናግረዋል፡፡ 
800ሺ ብር ገደማ እንደፈጀ የተነገረለት “ላምባ”፤ በሸገር 102.1 ሬዲዮ የ“ለዛ” ፕሮግራም “የዓመቱ ምርጥ ፊልም” ሽልማትን በሶስት ዘርፎች በመመረጥ እየመራ እንደሚገኝ አዘጋጁ ጋዜጠኛ ብርሃኑ ድጋፌ ለአዲስ አድማስ ገልጿል፡፡ 
“ፊልሙን የሰራነው ለምናከናውነው የበጎ አድራጎት ስራ ማነቃቂያ እንዲሆን ነበር” ያለው የፊልሙ ፀሐፊና ፕሮዱዩሰር አንተነህ ኃይሌ፤ በ4 ወራት የሲኒማ ቤት ቆይታው ለኩላሊት ህክምና ማዕከል ማሰሪያ ድጋፍ (በአጭር የስልክ መልዕክት) ወደ 300ሺ ብር የሚጠጋ ገቢ ማሰባሰብ እንደተቻለ ጠቁሟል፡፡ 
በአሁን ሰዓት በዘውዲቱ ሆስፒታል  የኩላሊት ህክምና ማዕከል ህንፃ ግንባታ ተጠናቆ የህክምና መሳሪያዎችን ለመግዛት የሚያስችለውን ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለማግኘት ፊልሙን ማሳየት ጨምሮ የተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሞች ታቅደው  እንደነበር አቶ አንተነህ ለአዲስ አድማስ አስረድቷል፡፡ 
ፊልሙ ባይሰረቅ ኖሮ ዩኒቨርሲቲዎችን ጨምሮ በተለያዩ የ2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች በማሳየት እስከ ግማሽ ሚሊዮን ብር ገቢ ለማሰባሰብ ታስቦ እንደነበር ፕሮዱዩሰሮቹ ገልፀዋል፡፡ በተለይ በመጪው መስከረምና ጥቅምት ወራት የመንግስት ባለስልጣናትን ጨምሮ ለተለያዩ ባለሀብቶችና በውጭ አገር ለሚገኙ ኢትዮጵያውያንም በማሳየት ላቅ ያለ ገቢ ለማስገኘት ታስቦ ነበር፡፡
ከፊልሙ ይገኛል የተባለው ገቢ ከዚህ በኋላ የሚሳካ ባይሆንም የኩላሊት ማዕከሉን ግንባታ ለማስፈፀምና ቁሳቁሶችን ለማሟላት ህብረተሰቡ በስፋት የሚሳተፍበት የቴክስት መላኪያ ቁጥር ከቀጣይ ሳምንት ጀምሮ ይፋ እንደሚደረግ ታውቋል። 
ከጀርመን ሃገር በተገኘ ብድር የተገዙ 20 ያህል የኩላሊት ህክምና ማሽኖች በቅርቡ ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው ይተከላሉ ያሉት አቶ አንተነህ፤ ሌሎች ማሽኖችን ለማስገባት ለሚያስፈልገው 60 ሚሊዮን ብር ደግሞ የተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሞች እንደታቀዱ ገልፀዋል፡፡
በተመልካቾች ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነትን ያተረፈው “ላምባ” ፊልም መሰረቁ በአገሪቱ የፊልም ኢንዱስትሪ ዕድገት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር የፊልም ባለሙያዎች ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡ በ“ላምባ” ፊልም ላይ በመሪ ተዋናይነት የሚሰራውን ዕውቁን አርቲስት ግሩም ኤርሚያስ ጨምሮ ሌሎች በርካታ አርቲስቶች ተውነውበታል፡፡
http://www.addisadmassnews.com/

Thursday, July 9, 2015

ሸሌ ነኝ

  ከህይወት እምሻው ገጽ የተውሰደ

‹‹ነይ እዚህ ጋር ልብስሽን አውልቀሽ ውስጥ ሳትገቢብርድልብሱ ላይ ተኚ›› ሲለኝ፤ ልማድ ሆኖብኝ መግደርደር ዳድቶኝ ነበር፡፡
ድሮ፤ ልጃገረድ እንዳለሁ ጊዜ መሽኮርመም፡፡
ሰው እንጂ ሴት ያልሆንኩ መስሎኝ፡፡
ስጋ ሸጬ እንጀራ ልገዛ ያልመጣሁ መስሎኝ፡፡
ገንዘብ ተቀብዬ ደስታን ልሰጥ ያልመጣሁ መስሎኝ፡፡
አንገቴን እንደሰበርኩ ወደ አልጋው ሄድኩ፡፡ ሲያገኘኝ እሄድ እንደነበረው አይደለም አካሄዴ፡፡ ሰበር ሰካ የለውም፡፡ እዩኝ እዩኝ የለውም፡፡ ተገዝቶ ወደ ሚታረድበት ቦታ እንደሚሄድ በግ ነው አካሄዴ፡፡
ገዢዬ፣ የማያውቀኝ ሰው ፊት ልብሴን ሳወልቅ የመጀመሪያዬ እንደሆነ አያውቅም፡፡
ገዢዬ፣ በገንዘብ ተገዝቼ ከወንድ ለመተኛት ስመጣ የመጀመሪያዬ እንደሆነ አያውቅም፡፡
ገዢዬ፣ ለዚህ ስራ ድንግል እንደሆንኩ አያውቅም፡፡
ልብሴን ማውለቅ ሳልጀምር እየፈራሁ፤ ‹‹ይቅርታመብራቱን ታጠፋው?›› አልኩት፡፡፡
ዞር ብሎ አየኝና ‹‹ሃሃ! ታሾፊያለሽ እንዴ…! ለምንድነው የማጠፋው…!›› አለኝ፡፡ ይስቃል፡፡
ፈራሁ ብለው አያምንም፡፡ በሰቀቀን ዝም ብዬ ማውለቅ ጀመርኩ፡፡ የአልጋው ጫፍ ላይ ኩምትር እንዳልኩ ድንገት እስካሁን መኖሩን ያላወቅኩት ብርድ አንዘፈዘኝ፡፡ ሳል ጀመረኝ፡፡ ይሄን ጊዜ ሰውየው ዞር ብሎ አየኝና፤ ‹‹ምነውብርድቲቢ ምናምን አለብሽ እንዴ?›› አለኝ፡፡
‹‹አይበርዶኝ ነው...አያመኝምአሁን በርዶኝ ነው….›› ብዬ ብርድ ልብስ ውስጥ ገባሁ፡፡
‹‹ኖኖ! ከላይ ሁኚአትግቢ …››አለኝ ቶሎ ብሎ፡፡ ቀጭን ትእዛዝ ነበር፡፡
እምቢ ብዬ መሄድ እንደማልችል ማወቁ አስከፋኝ፡፡
እሺ ብዬ ስለመጣሁ እምቢ ብዬ እንደማልሄድ እርግጠኛ መሆኑን ሳውቅ ከፋኝ፡፡
ከነሳሌ ከብርድልብሱ ወጣሁ፡፡
መጥቶ አጠገቤ ተኛ፡፡ሰውነቴ በፍርሃት ተንዘፈዘፈ፡፡ የውስጥ ሱሪ ብቻ ሲቀረው እርቃኑን ነው፡፡
እግዜር በሚያውቀው፤
ከማላውቀው ሰው ቤት ለማደር መምጣት አልፈለግኩም ነበር፡፡
የማላውቀው ሰው እጆቹን ጭኖቼ መሃል አስገብቶ እንዲፈነጭ አልፈለግኩም ነበር፡፡
የማላውቀው ሰው ጆሮዬን ተጠግቶ እንዲያቃትትብኝ አልፈለግኩም ነበር፡፡
ግን ሰውየው አስገድዶ አላመጣኝም፡፡
አልደፈረኝም፡፡
ያስገደደኝ ኑሮ ነው፡፡
የደፈረኝ ድህነት ነው፡፡
ሲነጋ እና ከኔ ጋር ያለውን ጣጣውን ሲጨርስ የሰጠኝን አምስት መቶ አዳዲስ ብሮች እንደያዝኩ በትእዛዝ ያወለቅኩትን ልብሴን በከፍተኛ ፍጥነት ለበስኩ፡፡ ያወለቅኩት ክብሬ ግን አልጋው ላይ ቀርቷል፡፡
‹‹ቅዳሜ እመጣለሁ..ማን ብዬ ላስጠራሽ ?›› አለኝ በተኛበት፡፡
እንድሄድ ፈልጓል፡፡ አገልግሎቴ አብቅቷል፡፡
አሁን እንደተፋቀ የሞባይል ካርድ ነኝ፡፡
አሁን እንደተጫረ የክብሪት እንጨት ነኝ፡፡
በድጋሚ በጉጉት የሚያየኝ በሚቀጥለው ቅዳሜ መጥቼ እፎይ ማለት ሲያምረው ነው፡፡
ስሜን ነግሬው ዞር አልኩና ቦርሳዬን አንጠልጥዬ ለመሄድ ስዞር፤
‹‹ማነሽበሩን በደንብ ዝጊው›› አለኝ አልጋው ላይ ተገላብጦ ጀርባውን እየሰጠኝ፡፡
ፊት እንኳን የማይገባኝ ሰው መሆኔን ሲነግረኝ ነው በጀርባው የሚያናግረኝ፡፡
የሚታወስ ስም እንደሌለኝ ሲነግረኝ ነው ማነሽ ያለኝ፡፡
ይሄን ሳስብ ተዛባሁ፡፡
ተዛነፍኩ፡፡
ካለ አጥንት እንደተፈጠረ ሰው ሰውነቴ ለመቆምም ለመሄድም እምቢ እያለ ወደ ታክሲ ተራው ሄድኩ፡፡
ተኝቶ የነጋለት ሰው ይተራመሳል፡፡
ታክሲው ውስጥ ገብቼ መስኮቱን ደገፍ አልኩና ያለ እቅድ ስቅቅቅ ብዬ ማልቀስ ጀመርኩ፡፡ ከአይኔ ግድብ የሚፈሰው እምባ ጉንጬቼ ላይ የሚደርቅ ሳይሆን አዋሽ ወንዝ ለመግባት ያልም ይመስል ይንዠቀዠቃል፡፡ ከክብሬ ጋር አውልቄው የነበረው የአንገት ልብሴ ላይ ያርፋል፡፡ከክብሬ ጋር አውልቄው የነበረው ጃኬቴ ላይ ያርፋል፡፡ ከክብሬ ጋር አውልቄው የነበረው ሱሬዬ ላይ ያርፋል፡፡
በለቅሶዬ መሃል፤ ‹‹አይዞሽ….ሁሉም ያልፋል›› የሚል ድምፅ ሰማሁና ዞርኩ፡፡
ከእኔ በእድሜ የምታንስ ልጅ ናት፡፡
‹‹ሁሉም ያልፋል›› የሚል የታክሲ ጥቅስ አንብባ የምትደለለው ለዚያ ነው፡፡ ትንሽ ልጅ ስለሆነች፡፡ በቂ ስላልኖረች፡፡ አንዳንድ ነገሮች እንደኔ ላለው ሰው እንደማያልፉ የሚያስተምራት የሕይወት ልምድ ስለሌላት፡፡ ቀልደኛ!
ዝም ብዬ አየኋትና በእሺታ ጭንቅላቴን ነቅንቄ ተመልሼ ወደ መስኮቱ ዞርኩ፡፡
ሁሉም ቢያልፍ ኖሮ ዛሬ እዚህ ታክሲ ውስጥ እያለቀስኩ ባልተቀመጥኩ፡፡
ሁሉም ቢያልፍ ኖሮ ለአምስት መቶ ብር አምስት መቶ ቦታ ባልተሰባበርኩ፡፡
ሁሉም ቢያልፍ ኖሮ እኔ ትርሲት የአቶ ከለላው እና ወይዘሮ ስምረት ሴት ልጅ፣ የብሌን ታላቅ እህት፣ የዳዊት ታናሽ እህት፣ የዳግም ፍቅረኛ ሆኜ በቀረሁ፡፡
አሁን ግን ትርስቲት ሸሌዋ ነኝ፡፡
ሸሌ ነኝ፡፡
ሸሌ ብቻ፡፡
ይህንን ሰውየው አይን ውስጥ አይቼዋለሁ፡፡
ይሄንን ሰውየው ትእዛዝ ውስጥ ሰምቼዋለሁ፡፡
ይሄንን ሰውየው ‹‹በሩን በደንብ ዝጊው›› ንግግር ወስጥ አድምጨዋለሁ፡፡
ሸሌ ነኝ፡፡
ለማንበብ ደቂቃ የሚፈጅ ስም በመስጠት የኔን ስራ ቅዱስ ማድረግ አይቻልምና ‹‹ የለም፤ አንቺ እኮበወሲብ ንግድ የተሰማራች ሴትነሽ!›› ብላችሁ አታፅናኑኝ፡፡
ከዛሬ ጀምሮ ሸሌ ነኝ፡፡
በረሃብ እያዛጋሁ ቤቴ ገባሁና ከሰል አቀጣጠልኩ፡፡ ሳልበላ ውሃ ላፈላ፡፡ ሳልበላ በፈላ ውሃ ልታጠብ፡፡ ሳልበላ በፈላ ውሃ ገላዬን ልታጠብ፡፡ ሸሌነቴን በፈላ ውሃ ሙልጭ አድርጌ ልታጠብ፡፡
ውሃው እስኪፈላ ልብሶቼን አውልቄ ከሌሎቹ ልብሶቼ ጋር እንዳይቀላቀሉ በቤቴ አንዷ ማእዘን ላይ ሰብስቤ ጣልኳቸው፡፡ ብዙ ልብስ የለኝም ግን እነዚህን ልብሶች መልሼ እለብሳቸው አይመስለኝም፡፡
ራቁቴን የሰመጠች አልጋዬ ላይ ቁጭ ብዬ ውሃው እስኪፈላ እየጠበቅኩ ቤቴን አየሁት፡፡ ለሰው የሚነገር ነገር ስለሌለኝ እንትኑ እዚያ ጋር፣ እንትኑ ደግሞ እዚያ ጋር አለ ብዬ ላወራችሁ አልፈልግም፡፡
በዋጋ ከተሰላ፤ አሁን ያለኝ ዋጋ የከፈልኩበት አምስት መቶ ብር ብቻ ነው፡፡ አልጋዬ ላይ የተቀመጠው አምስት መቶ ብር፡፡
ምናልባት ካልገመታችሁ፤ እንዲህ ያለውን ዋጋ ያልከፈልኩበት ብር ለማግኘት ሞክሬ ነበር፡፡ ማለቴ ዘልዬ ሸሌ አልሆንኩም፡፡
አሳጥሬ ልንገራችሁ እና ምንም ስራ ሰርቻለሁ፡፡ ግን እኔን እና እኔን የሚጠብቁ ቤተሰቦቼን ሆድ ፀጥ የሚያደርግ፣ አንገት ቀና የሚያደርግ፣ ደረት አስነፍቶ የሚያስሄድ ስራ አላገኘሁም፡፡
እውነቴን ነው የምላችሁ፤ እንጀራ ፍለጋ ሴት የሆንኩት ሰው ሆኜ ስላልተሳካልኝ ነው፡፡
ልድገመው፡፡
እንጀራ ፍለጋ ሴት የሆንኩት ሰው ሆኜ ስላልተሳካልኝ ነው፡፡
የስጋ ለስጋ ኑሮን የመረጥኩት ሌላ ነገር ሆኜ መኖር ስላልቻልኩ ነው፡፡
ለምሳሌ የሆነ ሰሞን የሆነ ኤን ሸሌ የመሆን አዝማሚያ ያሳየነውንም፣ ገብተው የተንቧቹበትንም ሴቶች ሰበሰበና፤ ‹‹ከዚህ አስነዋሪና ቆሻሻ ስራ ነፃ እናውጣችሁ፤ ያልገባችሁበትንም እናድናችሁ›› አለን፡፡
‹‹አልጋ አንጣፊ ስለሆነች ከአልጋ ለመውደቅ ቅርብ ናት›› ብለው ነው መሰለኝ ፕሮጀክቱ ውስጥ አስገቡኝ፡፡ ደስ ብሎኝ ገባሁ፡፡ ኤን ኦው ‹‹አማራጭ የገቢ ማግኛ ዘዴዎች›› በሚል ለግማሻችን ጥልፍ፣ ለግማሻችን ዳንቴል ስራ አስተምሮ ‹‹በሉ እንግዲህ ሂዱና ንፁህ ስራችሁን እየሰራችሁ በብልፅግና ኑሩ>> ብሎ አንድ ኮንቴነር ቤት ተከራይቶልን ሄደ፡፡
እኔ ከጥልፎቹ መሃል ነበርኩ፡፡
እንደተማርኩት እየጠለፍኩ አዲሱንና ንፁሁን ስራዬን ነፃ መውጫዬ፣ መልካም እጣ ፈንታዬ፣ የእግዜር ካሳዬ አድርጌ ተቀብዬው ስራ ጀምሬ ነበር፡፡
ብዙዎቻችሁ ‹‹አንዴ ሸሌ የሆነች ወይ ለመሆን ያኮበኮበች ሴት ሁሌም ሸሌ ናት›› ብላችሁ እንደምታስቡ አውቃለሁ፡፡
በሚኒ ስከርት መንገድ መቆም የለመደች ሴት ‹‹እስከ ጉልበት›› የስራ ቀሚስ ቢሮ መቀመጥ አትችልም ብላችሁ እንደምታምኑ አውቃለሁ፡፡
የራሳችሁ ጉዳይ!
እኔ ግን በዛ ሰሞን እፎይታ ተሰምቶኝ ነበር፡፡
ሳልጠፋ ስለተገኘሁ ደስ ብሎኝ ነበር፡፡
ሳልሰበር ስለተጠገንኩ እፎይ ብዬ ነበር፡፡
ሸሌ መሆን የሚያጓጓኝ ሰሞን፣ የከጃጀለኝ ሰሞን፤ አልጋ አንጣፊ ሆኜ የምሰራበት ቡና ቤት ውስጥ ያሉ የሚቀርቡኝ ሸሌዎችን ገድል እና እሮሮ በታላቅ ትኩረት፣ በቀን በቀን እሰማ ነበር፡፡ አይ ነበር፡፡
በመሸ ቁጥር ‹‹ኮንዶም አድርግ አታድርግ›› ጭቅጭቅ በጭንቅላቱ ሳይሆን በእንትኑ ከሚያስብ ወንድ ጋር እየተጣሉ በፖሊስ መዳኘት አለ በሚሉት የማስፈራሪያ ወሬዎች ተሰላችቼ ነበር፡፡
‹‹በጥፊ ካልመታሁሽ ደስ አይለኝም›› እያለ ከላይም ከታችም ከሚደበድበኝ ወንድ ጋር አድሬ የከፈለኝን ገንዘብ በድብደባ ያበጠ ፊቴን ለመታከም ማዋሉ መረረኝ በሚሉ ሴቶች ዋይታ ተማርሬ ነበር፡፡
እሺዝርዝሩ ይቅርባችሁና እንዲያው በደፈናው በጨለመ ቁጥር ባለተራ ወንድ እላዬ ላይ ስለማይንደፋደፍብኝ የእውነት ደስ ብሎኝ ነበር፡፡
ከዚህ እጣ ፈንታ ለጥቂት ስላመለጥኩ፤ ደስ ብሎኝ ነበር፡፡
እናም፤ ቀን ቀን እየጋለ አቅልጦ እንደ ውሃ ሊያፈሰኝ በሚዳዳው ሙቀት ሲመሽ ሲመሽ ጥፍር አውጥቶ ሰውነቴን በሚቧጭቀኝ ብርድ ሳልማረር፣ እዛች ኮንቴነር ውስጥ ቁጭ ብዬ ጥልፌን እጠልፍ ነበር፡፡
በየወሩ ‹‹አሁንስ በቃኝእንኳን ትርፍ ሊያመጣ ለሚያከስር ስራ ደግሞ!› እያሉ ከጥልፉም ከዳንቴሉም ጎራ ወጥተው ሸሌነትን የመረጡ፣ ወይም ወደ ሸሌነት የተመለሱ ጓደኞቼን እያየሁ እንኳን በንፅህና ጎዳና ለመቀጠል ብዙ ለፋሁ፡፡
ብዙ ታተርኩ፡፡ ብዙ ወጣሁ፡፡ ብዙ ወረድኩ፡፡
ንፁሁ ስራዬ ግን ከሰው በታች አደረገኝ እንጂ ከፍ አላደረገኝም፡፡
ሱቄን የሚጎበኙ ወንዶች ሁሉ፤ ጥልፍ ጠለፍኩበትን አልጋ ልብስ ከመግዛት ይልቅ እኔን ጠልፈው አልጋ ውስጥ ማስገባት ነበር የሚታትሩት፡፡
በአምስተኛው ወር የከሸፈውን ፕሮጀክት ተከትሎ የከሸፈውን ህልሜን ኮንቴነሩ ውስጥ ጥዬ ወደ ‹‹ሰጥቶ የመቀበል›› አለም መጣሁ፡፡
የዛሬው ሰውዬ የመጀመሪያዬ ነበር፡፡ ‹‹›. ዬ፣ አንደኛ ክፍሌ፡፡
ሳልዋረድ መብላት ብፈልግም፣ ሳልገላመጥ መኖርን ብሻም የሞከርኩት ሁሉ አልሳካ ብሎኝ ሸሌ ሆንኩ፡፡
ባላያችሁትና ባልኖራችሁት ሕይወቴ ፈርዳችሁብኝ ብትሰድቡና ብትረግሙኝም፤
አለም ስትፈጠር ገና ያኔ ------ከገበሬነት በፊት፣ ከአናጢነት በፊት፣ ከአስተማሪነት በፊትከምንም አይነት ስራ በፊት ‹‹ሲወርድና ሲዋረድ›› እዚህ የደረሰውን ስራዬ ግን በእርግማንና በስድብ ወጀብ ከምድረ ገፅ እንደማይጠፋ ታውቁታላችሁ፡፡
ምክንያቱም፤
በጨለማ በጨለማ ዝቅ ብዬ ያገኘሁት ገንዘብ እጄን የሚጠብቁ ቤተሰቦቼን ከፍ እንደሚያደርግልኝ አውቃለሁ፡፡
ቀን የተጠየፉኝ ሰዎች ማታ እንደሚያመልኩኝ አውቃለሁ፡፡
ቆሻሻው ስራዬ ንፁህ እንጀራ እንደሚገዛ አውቃለሁ፡፡
ስለዚህ፤ ወንድ ሊሆን የሚመጣን ወንድ ሴት ሆኜ እያስተናገድኩ እንደ ሰው እኖራለሁ፡፡
ሸሌ ነኝ፡፡

ከዛሬ ጀምሮ ሸሌ ነኝ፡፡