Written by አለማየሁ አንበሴ
በየሁለት ሣምንቱ እሁድ መርካቶ አንዋር መስጊድ አካባቢ 4 ሰአት ግድም የደረሰ ማንም ሰው አንድ የተለየ ክስተት መመልከቱ አይቀርም፡፡ ነገሩ አዲስ የሚሆንበት ለእንደኔ ዓይነቱ እንግዳ እንጂ የአካባቢው ነዋሪዎችማ ለምደውታል፡፡ ላለፉት ሦስት ዓመታት ሲካሄድ የቆየ አስደማሚም አስገራሚም ሰብዓዊ ተግባር ነው፡፡ ከልጅነቱ ጀምሮ በአካባቢው የሚታወቀው ብላቴናው አስመሮም ተፈራ፤ በመርካቶ ዙሪያ በየጎዳናው የወደቁ የአዕምሮ ህሙማንን እያነሳ ገላቸውን ያጥባቸዋል፡፡ ፀጉራቸውን ይላጫቸዋል፡፡ አዲስ ልብስ ያለብሳቸዋል፡፡ ምግብም ያበላቸዋል፡፡
የአዕምሮ ህሙማኑን የሚያጥብበት ሰወር ያለ ስፍራ ባለመኖሩ አውራጐዳና ላይ እርቃናቸውን ሲያጥባቸው ማየት የተለመደ ትዕይንት ነው፡፡
አስመሮምን ከልጅነቱ ጀምሮ እንደሚያውቁት የሚናገሩት የ70 ዓመቱ የአካባቢው አዛውንት አቶ መሃመድ ጀማል፤ “ሰፈር ውስጥ ሲላላክልንና ሲያገለግለን ያደገ ልጅ ነው፤ አሁንም ሰዎች የሚፀየፏቸውን የአዕምሮ ህሙማን ለመንከባከብ የሚያደርገው ጥረት የታዛዥነቱና የቀናነቱ ነጸብራቅ ነው” ይላሉ፡፡ በልጅነቱ ከቤተሰቦቹ ተለይቶ በችግር ማደጉን እናውቃለን ያሉት አዛውንቱ፤ ያለፈበትን ህይወት አስታውሶ እነዚህን ምስኪኖች በሽታ አለባቸው፣ ተባያቸው ይተላለፍብኛል ሳይል ላለፉት ሦስት ዓመታት በቋሚነት ሲያጥባቸው፣ ሲያለብሳቸውና ሲመግባቸው ተመልክቻለሁ” ሲሉ እማኝነታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ብላቴናው አስመሮም (ባሪያው) የተወለደው ከረዩ ሰፈር ቢሆንም ከቤተሰቦቹ ጋር በተፈጠረው አለመግባባት ገና የ8 ዓመት ህፃን ሳለ ነበር ወደ ጎዳና የወጣው፡፡ የአሜሪካን ግቢ ነዋሪዎች ባደረጉለት ድጋፍም በልጅነቱ በተለያዩ ስራዎች ላይ ለመሰማራት እንደቻለ ይናገራል። አስመሮም በየሁለት ሳምንቱ እሁድ ገላቸውን የሚያጥባቸው፣ ፀጉራቸውን የሚላጫቸውና ልብሳቸውን የሚቀይርላቸው እንዲሁም ምግብ የሚያበላቸው የአዕምሮ ህሙማን ቁጥር 25 ደርሰዋል፡፡ በዚህም የተነሳ እየተሳቀቅሁ በአደባባይ ርቃናቸውን ሳጥባቸው ተገድጄአለሁ ይላል፡፡ ይሄን ሰብዓዊ ተግባር ለመፈፀም ወጪው ከፍተኛ እንደሚሆን መገመት አያዳግትም፡፡ እሱ ደግሞ መኪና አጥቦ አዳሪ ነው፡፡
አስመሮም እንደሚለው፤ የታክሲ ሹፌሮች ባይኖሩ ኖሮ ይሄን በጐ ተግባር ለማከናወን አይችልም ነበር፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ባለፈው እሁድ በስፍራው ተገኝቶ ለህሙማኑ የሚደረገውን እንክብካቤ ከተመለከተ በኋላ ከወጣት አስመሮም ተፈራ ጋር በሰብዓዊ ተግባሩ ዙሪያ ተከታዩን አስገራሚና አስደማሚ ቃለምልልስ አድርጓል፡፡
“መልካም ሥራ ማለት የወንድምህን ስቃይ አይቶ አለማለፍ ነው”
መርካቶ አካባቢ ጐዳና ላይ የወደቁ የአዕምሮ ህሙማንን መንከባከብ የጀመርከው መቼ ነው?
የጀመርኩት በልጅነቴ ነው፡፡ ከ3 አመት ወዲህ ግን ቁጥራቸው እየበዛ በመምጣቱ እንደምታየው በጐዳና ላይ ነው የማጥባቸው፡፡
ወደዚህ ሰብዓዊ ተግባር ለመግባት ያነሳሳህ ምንድነው?
በልጅነቴ እዚህ መርካቶ ጃሊያን ግቢ ስመጣ አፍራ የምትባል ልጅ ቁሽሽ ብዬ ታየኛለች፡፡ እቤታቸው ወስዳ ሰውነቴን አጥባኝ፣ ልብስ አለበሰችኝ፡፡ አንዳንዴ ቤተሰቦቿ “ከቤት አስወጪው” እያሉ ይቆጧት ነበር። እሷ ግን በድብቅ ሁሉ እያጠበች ምግብ ትሰጠኝ ነበር።
ያኔ እሷ ለእኔ ያደረገችልኝ በጐ ነገር፣ ያሳየችኝ ሰብዓዊነትና ርህራሄ ውስጤ ሰርፆ የገባ ይመስለኛል፡፡ ቆሻሻዬን ሳትጠየፍ ነበር ከቤተሰቦቿ ተደብቃ የምታጥበኝ፡፡ ያኔ እኔ ገና 10 ዓመት እንኳ አልሞላምኝም ነበር፡፡ ዛሬ በተራዬ እኔም እነዚህን ሰዎች ስንከባከብ ደስታዬ ወደር የለውም፡፡ በጣም ነው የምደሰተው፡፡ የሚከፋኝ ይህን ማድረግ ካልቻልኩ ነው፡፡ አንድ ሰው የሚለብሰው ልብስ ካለው፣ እቤት የሚያስቀምጠውን ትርፍ ልብስ ለምን ለታረዘው ወንድሙ አያለብሰውም? አንዳንድ ሰው እኮ ከአምስት አመት በላይ ሳይለብሰው አይን አይኑን እያየ የሚያስቀምጠው ልብስ ቤቱ ይኖረዋል። እስቲ አስበው… የሰብአዊ ፍጡርን ዋጋ እንዴት ሰው ሠራሽ ከሆነው ጨርቅ እናሣንሰዋለን?! ተቀዶ አልቆ የሚጠፋውን ጨርቅ ለነፍሳችን መልካም ሰርተንበት፣ የታረዘውን አካል ብናለብስበት ምን አለ?!
እኔ አሁንም በዚህ አስተሳሰብ ስለተቃኘሁ ይሄን ከማድረግ ወደ ኋላ አልልም፡፡ ፈጣሪ ወገኖችህን በዚህ መልኩ አገልግል ብሎ ስላዘዘኝ፣ ጉድጓዴ እስኪማስ ድረስ ይሄን ከማድረግ ወደ ኋላ አልልም፡፡ እነዚህ ወገኖቻችን እኮ አዕምሯቸው ታመመ እንጂ እንደኛው ስጋ ለባሽ ናቸው፡፡ ይበርዳቸዋል፣ ይጠማቸዋል፣ ይታረዛሉ፡፡ እኛ ለአንድ ቀን ገላችንን ካልታጠብን አሳከከኝ እንል የለ እንዴ! እነሱ እኮ ስንት አመት ሙሉ ልብሳቸው በገላቸው ላይ ተጣብቆ ነው ያለው። እናም አፍንጫችንን ይዘን ከምንሸሻቸው ለምን አናፀዳቸውም? ይሄን ብናደርግ ምን ይጐድልብናል? መልካም ስራ ማለት እኮ የስጋ ለባሽ ወንድምህን ስቃይ አይቶ አለማለፍ ነው፡፡
አየህ የአዕምሮ ህሙማን እራበኝ ብለው መናገር አይችሉም፡፡ ወይ ፈዘው አይን አይንህን ያዩሃል እንጂ እርቦኛል አይሉህም፡፡ እንዲህ ዓይነት ሰዎች በየጐዳናው እያሉ፣ የተራረፈንን እንጀራ ገንዳ ውስጥ የምንደፋ ከሆነ፣ የኛ ሰብአዊነት ምኑ ጋ ነው። በዚህ አጋጣሚ እንጀራ ገንዳ ውስጥ የሚደፉ ሰዎች፣ ለአንዱ የተራበ ወገናቸው ቢሠጡት፣ እነሱ በመስጠታቸው ደስታን ሲያገኙ፣ ያ ሰው ደግሞ በልቶ በማደሩ ህይወቱን ያተርፋል፡፡
ገላ ማጠቡን እንዴትና በምን አጋጣሚ ጀመርከው?
አንድ ጊዜ አንዲት ልጅ እዚሁ (አሜሪካን ግቢ) አካባቢ የወር አበባዋ ፈሶ መሬት ላይ ወድቃ ነበር። የሚያያት ሰው ሁሉ ከንፈሩን እየመጠጠ፣ አንድና ሁለት ብር እየሰጣት ሲያልፍ አያለሁ፡፡ ምን ማለት ነው ብር መስጠት ብዬ ተገረምኩ፡፡ እቺን ልጅ አንስቼ ባጥባት እጄ አይቆረጥ አልኩና አንስቼ አጠብኳት፤ የእነ ካሊድ እናት (የአካባቢው ነዋሪ ናቸው) የውስጥ ሱሪዎችንና አልባሳትን ሰጠችኝ፡፡ በቃ በዚያች ልጅ ሰበብ ውስጤ የፈቀደውን ተግባር ማከናወን ማድረግ ጀመርኩ፡፡
ከታጠቡ በኋላ ምግብም ታበላቸዋለህ፡፡ ምግቡን ከየት ነው የምታገኘው?
ምግቡን ቀድሜ ነው የማዘው፡፡ አንድ ምግብ 15 ብር ነው፡፡ ገላቸውን ስናጥባቸው የሚያዩን ሰዎች በሚሰጡን እርዳታ ነው ምግቡን የምገዛው። ሌሊት ተነስተው ውሃ ለሚቀዱልኝና ለሚያግዙኝ ሰዎችም እከፍላቸዋለሁ፡፡ ገላቸውን ከታጠቡ በኋላ ልብሳቸውም በአዲስ ስለሚቀየርላቸው ወጪ አለው። ለ25 ህሙማን በአንድ እሁድ… ለምግብ፣ ለውሃ፣ ለልብስ፣ ለሣሙና፣ ለፂምና ፀጉር መላጫ እስከ 3500 ብር የፈጃል፡፡ ይሄ ወጪ በአብዛኛው የሚሸነፈው በመንገድ ላይ ሲያልፉ የምንሰራው አስደስቷቸው ገንዘብ በሚለግሱን ሰዎች ነው፡፡
አብዛኛውን ድጋፍ የምታገኘው ከማን ነው?
እውነቱን ልንገርህ… የሁልጊዜም ተባባሪዎቻችን የታክሲ ሹፌሮች ናቸው፤ እነሱ ካለቻቸው ላይ ሣይሰጡን አያልፉም፡፡ ተሳፋሪያቸውንም ያስተባብራሉ፡፡ እኔ በአብዛኛው ልብስ ከነጋዴዎች ስገዛም ሆነ ምግብ ሣዝ እጄ ላይ ምንም ሣይኖረኝ፣ ከህብረተሰቡ የሚሰበሰበውን ተማምኜ ነው፡፡ አንዳንዴም ካልተሟላ ራሴ እንደምንም ብዬ እዳዬን እከፍላለሁ፡፡ የታክሲ ሹፌሮች ባይኖሩ እነዚህን ሠዎች በዚህ መልኩ ማልበስም ሆነ መመገብ አልችልም ነበር፡፡ የእነሱ ድጋፍ ወደር የለሽ ነው፡፡
በአካባቢው ላይ ያሉ ሰዎችም ከፍተኛ ድጋፍ ያደርጉልኛል፡፡ የእነ ካሊድ እናት ነኢማ፣ አደሬ፣ እነ አብዲ ባሪያው… ምን ልበልህ… በቃ የጃሊያ ሠፈር ህዝብ በጣም ተባባሪዬና ደጋፊዬ ነው፡፡ እኔ ውልደቴ ከረዩ ሠፈር ቢሆንም ያሳደገኝ የጃሊያ ህዝብ፣ ድጋፉ ባስፈለገኝ ጊዜ ሁሉ ፊቱን አዙሮብኝ አያውቅም፡፡
የአዕምሮ ህሙማን እንደመሆናቸው መጠን ለማጠብ ስትይዟቸው አያስቸግሩም?
እሱማ ያስቸግራሉ፡፡ ያው ታግለን ለሦስት ለአራት ሆነን ተሸክመን እናመጣቸዋለን፡፡ አንዴ ምን ሆነ መሠለህ? አሻሮ ይባላል፣ የአዕምሮ ህመምተኛ ነው፡፡ በጣም ጉልበተኛ ነው፡፡ እኔ እግሩ ስር ገብቼ ሁለት እግሩን ግጥም አድርጌ ይዤው ለአራት ተሸክመነው መጣን፡፡ አምጥተን ልክ ሁለት ባልዲ ውሃ ስናፈስበት፤ “ኡፍ…” አለና ፀጥ ብሎ ተቀመጠ፡፡ ብታምንም ባታምንም ውሃ ሰውን ያረጋጋል፤ የተለየ መንፈስ ያመጣል፡፡ ከዚያ በኋላ ራሱ ሣሙና እየመታ መታጠብ ጀመረ፡፡ ፀጉሩን ተላጨ፡፡ በመጨረሻ በተረጋጋ ስሜት፤ “እግዚአብሔር ይስጥልኝ” ብሎ ሄደ። በተደጋጋሚም ቀኑን ቆጥሮ ራሱ መጥቶ ይታጠብ ነበር፡፡ አሁን ግን ወዴት እንደሄደ አላውቅም፤ ጠፍቷል፡፡
ህመማቸው የተሻላቸውና ስራ የጀመሩት በአብዛኛው ራሣቸው መጥተው ይታጠባሉ፡፡ ያልተሻላቸውን በየሁለት ሳምንቱ እሁድ ጠዋት እየዞርን ተሸክመንም ቢሆን አምጥተን፣ አጥበናቸው ልብስ ቀይረንላቸው፣ ምግብ አብልተናቸው እንሸኛቸዋለን፡፡ ታዲያ እንዲያ ሲወራጩ የነበሩት ከታጠቡ በኋላ የተረጋጉ ሰው ሆነው ይሄዳሉ፡፡
አንተ በምን ሥራ ነው የምትተዳደረው?
በአነስተኛ ደላላነት እና መኪና በማጠብ (ላቢያጆ) ስራ ነው፡፡ ሌላ ነገር የለኝም፤ የምኖረውም በዚህች የቆርቆሮ ዳስ ውስጥ ነው (2x1 የሆነች የመንገድ ላይ የቆርቆሮ የጥበቃ ቤት ናት፡፡) እነሱም እዚሁ መጥተው አብረውኝ እየተጫወቱ ነው የሚያድሩት፡፡ ምን አለፋህ… ህይወቴ በሙሉ ከነሱ ጋር የተሳሰረ ነው፤ ልለያቸው ብልም አልችልም፡፡
ከመንግሥትም ሆነ ከሌሎች ድርጅቶች የተደረገልህ ድጋፍ አለ?
እስካሁን ምንም የተደረገልኝ ድጋፍ የለም፡፡ እኔ ዛሬ እነዚህን ሰዎች የማጥበው ህዝብ እያየ ጎዳና ላይ ነው፡፡ ቦታ ቢኖረኝ ግን ክብራቸውን በጠበቀ መልኩ እንዲታጠቡ ማድረግ እችል ነበር፡፡ ብዙ ጊዜ ሴቶች፤ “ኧረ እባክህ እኛንም እጠበን” ይሉኛል፡፡ እንዴት አድርጌ ነው የማጥባቸው? ሴት ልጅን አደባባይ ላይ ማጠብ ነውር ነው፡፡ እዚህ አካባቢ አንዲት ከመሬት መነሳት የማይችሉ አሮጊት ሴትዮ አሉ፤ ባየኋቸው ቁጥር አዝናለሁ፡፡ እሳቸውም፤ “ኧረ እባክህ ልብሱ በላዬ ላይ እየተጣበቀ ነው” ይሉኛል (በላብ ማለት ነው) ግን ምን ማድረግ እችላለሁ? አስቸጋሪ ነው፡፡ በጣም የቸገረኝ ሴቶቹን የማጠቢያ ቦታ ነው፡፡ ወንዶቹንም ቢሆን ቦታ በማጣት መንገድ ላይ ማጠቤ ያሳቅቀኛል፡፡ ቦታ ቢኖረኝ ግን አብረውኝ ሁሉ እየኖሩ ብንከባከባቸው ደስ ይለኝ ነበር፡፡ በተሻለ መንገድ የበለጠ ብንከባከባቸው ነፍሴ ትረካለች፡፡
ሌሎች የምትንከባከባቸው አቅመ ደካሞች እንዳሉም ሰምተናል…
አንተ መንገድ ላይ ያሉትን ትላለህ… ፀሃይና ጨለማን ለይተው የማያውቁ በየቤቱ አሉ፡፡ ጎረቤት ዞር ብሎ የማያያቸው፣ ሰው የራባቸው ስንቶች አሉ። እሁድ ከሰዓት ሁሌ የምጎበኛቸው ሰዎች አሉ፤ ስሄድ እንዴት ደስ እንደሚላቸው! 10 ልጆቻቸው ሞተውባቸው በድንጋጤ ታመው አልጋ ላይ የዋሉ እናት አሉ፡፡ ቤታቸው ሰው አይገባም፡፡ እሳቸውም ከቤታቸው መውጣት አይችሉም፡፡ አንድ ቀን እህቴ ስለሴትየዋ ነግራኝ ቤታቸውን አሳየችኝ፡፡ ስገባ ቤቱ በጣም ይሸታል፡፡ ከጓደኞቼ ጋር ሆነን ቤቱን አፀዳን፣ እሳቸውንም አጠብናቸውና፤ “ማዘር ምን እንዲደረግልዎት ይፈልጋሉ?” አልኳቸው፡፡ “እኔ ምግብም ገንዘብም አልፈልግም፤ የራበኝ ሰው ነው፤ የምፈልገው ሰው ብቻ ነው” አሉኝ፡፡ አሁን በየጊዜው እየሄድን እንጠይቃቸዋለን፡፡ በዚህ አጋጣሚ አንዳንዴ ጎረቤቶቻችንን መጐብኘት መልካም ነው እላለሁ፡፡
እግዚአብሔር ይመስገን… እኔ የተሻላቸውንና የመስራት አቅሙ ያላቸውን በደላላነቴ የተዋወቅኋቸውን ሰዎች እያስቸገርኩ ስራ እንዲያገኙም አደርጋለሁ፡፡ አሁን ጤነኛ ሆነው በሞራል ስራ መስራት የጀመሩ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ሰው ሰርቶ አምስት ብር ሲያገኝና ለምኖ ሲያገኝ አንድ አይደለም፡፡ ሰርቶ ያገኘው ያስደስተዋል፣ ይቆጥበዋል፤ በልመና ያገኘው አያስደስተውም፤ ምናልባት የእለት ጉርሱን ሊሸፍንለት ይችላል፤ ነገር ግን ዘላቂ አለመሆኑን ሲያውቀው ደስታ ይርቀዋል፡፡
ከወደቁበት ጐዳና ተነስተው የተሻለ ህይወት የሚመሩ ሰዎች አሉ?
አዎ! አንድ የጎንደር ልጅ ነበር፡፡ ስሙን መጥቀስ አልፈልግም፡፡ ከብዙ ዓመታት በፊት አባቱ ከመርካቶ እቃ አስጭነህ ና ብለው ገንዘብ አሲዘው ይልኩታል። እዚህ ሲመጣ ብሩን ይዘረፋል፡፡ የዛሬ 4 ዓመት ገደማ ተክለሃይማኖት አካባቢ ጸጉሩ እላዩ ላይ ተድበልብሎ፣ ጎዳና ላይ ወድቆ እናየዋለን፡፡ “ለምን ይሄን ልጅ አናጥበውም” እንልና በግድ ይዘን እየጮኸ እናጥበዋለን።
ሲታጠብ የእግዚአብሔርን ስም እየጠራ ያመሰግን ነበር፤ ፀጉሩን ላጨነው፤ አዲስ ልብስ አለበስነው፤ ጥሩ ምግብ አበላነው፡፡ ወዲያው “እባካችሁ የጎንደር መሳፈሪያ ስጡኝ፤ ሃገሬ ልግባ” አለን፡፡ እኛም ከህዝቡ (ህዝቡ ስልህ እዚያው የነበሩ ምስኪኖች ጭምር አዋጥተውለታል) አሰባስበን ላክነው፡፡ ጎንደር ሲሄድ እናትና አባቱ ሞተው፣ አንድ እህቱ ብቻ ቀርታለች። ያ ልጅ ከ3 ዓመት በኋላ ባለፈው መጣና “እዚህ አካባቢ አንድ ጥቁር ልጅ ፈልጌ ነው” ይላል፤ እኔን መሆኑ ነው፡፡ “አስመሮም ሰላም ነህ?” አለኝና አለቀሰ፤ እህቱም አብራው ነበረች፤ አለቀሰች፡፡ ሻይ እየጠጣን “አላወከኝም?” አለኝ፤ “አላወኩህምም” አልኩት፡፡ ጭንቅላቱ ላይ የነበረውን ኮፊያ አውልቆ፣ ሳጥበው የማውቀውን ጠባሳ ሲሳየኝ በጣም ነበር የደነቀኝ፡፡ ከዚያ በኋላ የተለያዩ ድጋፎችን አድርጎልኝ፤ እሱም በተራው ስናጥብ አግዞን ሄደ፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ከእህቱም ከእሱም ጋር በስልክ እንገናኛለን፡፡
ሌላ የምታስታውሰው ተመሳሳይ ገጠመኝ አለህ?
አዎ! ልጁ የደህና ቤተሰብ ልጅ ነው፡፡ እዚሁ ከወደቀበት አንስተን ልብሱን ስንቀይርለት፤ “ለገሃር አካባቢ ወንድሜ አለ፤ ሱቅ ከፍቶ ይሰራል አገናኙኝ” አለ፡፡ ይዤው ሄጄ የተባለው ሱቅ ቀድሜ ገባሁና፤ “እገሌ የሚባል ወንድም አለህ?” አልኩት ባለሱቁን፡፡ “አዎ፤ ከጠፋ ብዙ ጊዜ ሆኖታል” አለኝ፡፡ “ይኸው” ብዬ ሳገናኘው፤ እምባውን መቆጣጠር አልቻለም፡፡ እንዲህ አይነት ብዙ ገጠመኞች አሉ፡፡ ሰው ከወደቀበት ተነስቶ ንፁህ ሲሆን ተስፋው ይለመልማል፣ ስነልቦናው ይታደሳል፡፡ ህክምና የሚያስፈልጋቸው ካሉም፣ 6 ኪሎ አካባቢ አንዲት ፈረንጅ ሃኪም አለች፤ እሷ ጋ እወስዳቸውና በነፃ ታክምልኛለች፡፡
http://www.addisadmassnews.com/

No comments:
Post a Comment