Monday, December 21, 2015

“በወሮበሎች ስውር ደባ” ተሰቃይቻለሁ (ከአዲስ አድማስ)

- በየሄድኩበት ሁሉ ጥቁር ካልሲ ይጥሉብኝ ነበር
- “መድሃኒት እየሰረቀ ይሸጣል” ብለው አስወርተውብኛል

አዲስ አበባ ነው ተወልደው ያደጉት፡፡ የዕድሜያቸውን ግማሽ ያሳለፉት በውጭ አገራት ነው፡፡ በማህበረሰብ ጤና የማስተርስ ዲግሪ
ይዘው ለንደን በሚገኝ አንድ ትልቅ ሆስፒታል ውስጥ በሲኒየር ነርስነት እያገለገሉ እንደሚገኙ ይናገራሉ፡፡ አቶ ሄኖክ አያሌው ላለፉት
አራት ዓመታት “በወሮበሎች ስውር ደባ” (Gang stocking) ሲሰቃዩ እንደቆዩና በተለያዩ የራሳቸው ጥረቶች ከችግሩ ነፃ መውጣታቸውን
ይገልፃሉ፡፡ የወሮበሎች ደባ፤ አንድ ግለሰብ በወሮበሎቹ ስሙ ከጠቆረና “ብላክ ሊስት” ውስጥ ከገባ በኋላ ወደ ውድመት እንዲያመራ
የሚያደርግ ስርዓት ነው ይላሉ አቶ ሄኖክ፡፡













በወሮበሎቹ ወጥመድ ውስጥ የገባሁት በእንግሊዝ አገር ሳለሁ በተዋወቅኋት ዮዲት ጉዲት የተባለች ሴት ሰበብ ነው የሚሉት የታሪኩ
ባለቤት፤ ከእሷ ጋር ባለመግባባት ከተለያዩ በኋላ በወሮበሎቹ ጥቃት መከራቸውን ማየታቸውን ያስረዳሉ፡፡ “የወንበዴዎቹ ዓላማ
ያጠመዱትን ሰው ስም በማጥፋትና በማጠልሸት በብቸኝነት፣ በጭንቀትና በፍርሃት ማሸበር ነው ይላሉ አቶ ሄኖክ፡፡ በተከበርኩበት
ትልቅ ሆስፒታል ውስጥ “መድኃኒት እየሰረቀ ይሸጣል” ብለው አስወርተውብኛል ያሉት የታሪኩ ባለቤት፤ በየሄድኩበት ሁሉ ጥቁር ካልሲ
ይጥሉብኝ ነበር… በማለት የደረሰባቸውን ያስረዳሉ፡፡ ባለፈው አራት ዓመት የደረሰባቸውን ስቃይም፣ “የዲያስፖራው ስውር ደባ” በተሰኘ
መፅሃፋቸው ተርከውታል፡፡ መፅሀፉ “The Jaws of Evil” በሚልም ወደ እንግሊዝኛ ተተርጉሞ ባለፈው ሳምንት ከአማርኛው ጋር
ተመርቋል፡፡ የ49 ዓመቱ ጐልማሳ አቶ ሄኖክ አያሌው “የወሮበሎች ስውር ደባ” በሚሉት ጉዳይ ዙሪያ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት
ዮሴፍ ጋር ተከታዩን ሰፊ ቃለ-ምልልስ አድርገዋል፡፡


ከአገር የወጡት መቼና እንዴት ነው?
እኔ ከአገር የወጣሁት በደርግ ስርዓት ማብቂያ አካባቢ ነው፤ በፈረንጆቹ 1990 መጀመሪያ ላይ ማለት ነው፡፡ ወደ 25 ዓመት ገደማ አልፎኛል፡፡ የወጣሁበት ዋናው ምክንያትም በወቅቱ በነበረው ብሔራዊ ውትድርና ለመሄድ ባለመፈለጌ ነው፡፡ መጀመሪያ ከኢትዮጵያ በቀጥታ ወደ ፖላንድ ሄድኩኝ፣ እዛ አንድ ሳምንት ከቆየሁ በኋላ ወደ ስዊድን አመራሁ፡፡ ለ11 ዓመታት በስዊድን ከቆየሁ በኋላ ሌላ አንድ አመት በተለያዩ አገራት ማለትም ጀርመን አሜሪካና ሌሎች አገራት ተዘዋውሬ ካየሁ በኋላ እንግሊዝ ገባሁ፡፡ ይኸው አሁን በለንደን መኖር ከጀመርኩኝ 14ኛ ዓመቴን እያገባደድኩኝ ነው፡፡ 
በለንደን ምን እየሰሩ ይኖራሉ? ምንድን ነው ያጠኑት?
ስዊድን የቆየሁት በትምህርትም በስራም ነው፡፡ እንግሊዝም እንደዛው፡፡ በማህበረሰብ ጤና የማስተርስ ዲግሪ አለኝ፡፡ ለንደን ውስጥ በሚገኝ አንድ ሆስፒታል የ“Intensive care unit” (የፅኑ ህሙማን ክፍል እንደማለት) ሲኒየር ስፔሻሊስት ነርስ ሆኜ እያገለገልኩ እገኛለሁ፡፡
እስቲ የወሮበሎች ስውር ደባ (Gung stocking) ምን ማለት እንደሆነ ያብራሩልኝ?
ጋንግ ስቶኪንግ (የወሮበሎች ደባ) ማለት በጉዳዩ ዙሪያ በታተሙ የተለያዩ መጽሐፍት ላይ እንደተገለፀውና እኔም በህይወቴ ደርሶ እንደተረዳሁት፣ አንድ ግለሰብ በወሮበሎቹ ስሙ ከጠቆረና “ብላክ ሊስት” ውስጥ ከገባ በኋላ ወደ ውድመት እንዲያመራ የሚያደርግ ስርዓት ነው፡፡ 
“የዲያስፖራው ስውር ደባ” በተሰኘው መፅሀፍዎ ላይ እንዳነበብኩት፤ ወሮበሎች የተባሉት አካላት ያጠመዱት ሰው ባለበት ሁሉ ይገኛሉ፡፡ ግለሰቡ አገር ቢቀይርም ይከተሉታል፡፡ ይህን የሚያደርጉት እንዴት ነው? የወሮበሎቹ ሥራ ሳይንሳዊ ነው ወይስ ምትሃታዊ?
ጋንግ ስቶኪንግ ከሌሎቹ ደባዎች ወይም የማጥቂያ ስልቶች ለየት የሚለይበት የራሱ ባህሪ አለው፡፡ አንደኛ ህጋዊ ያልሆኑ ዘዴዎችን ይጠቀማሉ፡፡ በሌላ በኩል እነሱ ብቻ አጥቅተው አይተውሽም፡፡ የራስሽ ወዳጅ ዘመዶች፣ የስራ ባልደረቦችሽ፣ ቤተሰብሽ… ብቻ ሁሉም ያንቺ የሆነ ሁሉ በአንቺ ላይ እምነት እንዳይኖራቸው ያደርጉሻል። ይህን የሚያደርጉት በአንቺ ላይ ያልሆነ ወሬ ፈጥረው በማስወራት ነው፡፡ ከዚያ ሁሉም አንቺን ይጠረጥርሻል። በአይነቁራኛ ይመለከትሻል፡፡ ብቻ የሆነ ፍርሃት፣ ብቸኝነት፣ ጭንቀት… ዙሪያሽን እንዲከብሽ ያደርጉሻል። ይህን ሲያደርጉ ምንም አይነት ማስረጃ ላለማስቀረት ይጥራሉ፡፡ ከዚያ ካለፈ በጣም ትንሽ ማስረጃ ብቻ ይተዋሉ፡፡ ይህን ሴራቸውን ፖሊስ ጣቢያ ሄደሽ ክስ ብትመሰርቺ፣ መጽሐፍ ልፃፍና ሌላውን ላስተምር ብትይ በመረጃና በማስረጃ ማስደገፍ ስለማትችይ ዝም ብለሽ ከመሰቃየት ውጭ የምታመጭው ነገር የለም፡፡
ሳይንሳዊ ነው ወይስ ምትሀታዊ ላልሺው፤ ወሮበሎቹ ለደባቸው የሚጠቀሙት የስነ - ልቦና መጽሐፍትን ነው። ምንም ምትሀት የላቸውም፤ በአማርኛው መጽሐፌ ላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት፤ እነሱ ሰው ምን ቢደረግ ጭንቀትና ፍርሀት ሊገጥመው እንደሚችል ትልልቅ የስነ ልቦናና የህክምና ተመራማሪዎች የፃፏቸውን መጽሐፍት በማንበብ ነው ሽብራቸውን የሚፈጥሩት፡፡ የዚህ ችግር ሰለባ የሆኑ በተለይ ኢትዮጵያዊያን የሚያዳምጣቸው ስለሌለ የባሰ ችግር ውስጥ እየገቡ ነው፡፡ 
ጉዳዩ ቅድም እንዳልሽው ልክፍት፣ ምትሀት ወይም ድግምት ስለሚመስል በዚህ ችግር ውስጥ ያሉ ሰዎች ይህንን ችግር ሲናገሩ ተለክፏል፣ ተደግሞበታል፣ ቡዳ በልቶታል… እየተባሉ ፀበል ይወሰዳሉ፤ ከዚያ ሲያልፍም ጠንቋይ ቤት ይወስዷቸዋል፡፡ “ኧረ አላበድንም ጤነኛ ነን” ሲሉ “ይኼው ያስለፈልፈዋል” እየተባሉ ብዙ ችግር ይደርስባቸዋል፡፡ ይሄ በችግር ላይ ችግር፣ በስቃይ ላይ ስቃይ ነው የሚሆንባቸው፡፡ በአገራችን አንድን ነገር ደጋግሞ ሰው ደጃፍ ላይ መጣል ለምሳሌ ዶሮ እያረዱ በተደጋጋሚ ሰው በር ላይ መጣል፣ ወፍ እያረዱ ሰው ሳሎን ውስጥ በተደጋጋሚ መጣል ድግምት ነው እየተባለ እንደሚያብዱት አይነት ነው፤ ግን ይሄ ከዚያ ይለያል፡፡ 
ልዩነቱ ምንድን ነው?
እኔ በህይወቴ ደርሶ እንዳየሁት፤ ያ ታርዶ በተደጋጋሚ የሚጣለው ዶሮ ወይም ወፍ አይደለም ሰዎቹን የሚያሳብዳቸው፤ ድግግሞሹ ብቻ ነው፡፡ ዶሮው ወይም ወፉማ በቃ የሞተ ነው፡፡ የሚጣሉት ነገሮች ባይደጋገሙና አንዳንድ ጊዜ ብቻ ቢሆን ኖሮ አያሳብዱም ነበር፡፡ ወሮበሎቹም አንድ ሰው ራሱን እንዲያጠፋ፣ እንዲያብድ፣ እንዲወድም ከሚጠቀሙባቸው መንገዶች አንዱ ባጠመዱት ሰው ላይ ፍርሃትና ሽብር ለመልቀቅ አንድን ነገር በተደጋጋሚ ማድረጋቸው ነው፡፡ 
በመጽሐፉ ላይ እንደጠቆሙት፤ እርስዎን የሚያሸብሩት በጥቁር ካልሲ ነበር?
አዎ ነገሩ እስኪገባኝና እስክነቃባቸው ድረስ በመኝታ ቤቴ፣ በመታጠቢያ ክፍሌ፣ በቢሮዬ መሳቢያና በምቀይረው ጫማ ውስጥ እንዲሁም መኪናዬ ላይ ጥቁር ካልሲ ይጥሉ ነበር፡፡ ይሄ በጣም ያስፈራል ይዘገንናል። የምትይዢ የምትጨብጪው ይጠፋሻል፡፡ ልትዝናኚ ሌላ ቦታ ብትሄጂም እዛ ቦታ ቀድሞ ጥቁር ካልሲ ይጠብቅሻል። 
በሌላ በኩል ለረጅም ጊዜ ፓስወርዴ ጠፍቶኝ ስባዝን ነበር፤ በኋላ ስልኬ በእነርሱ እንደተጠለፈ አወቅሁኝ፡፡ ኢንተርኔት የምትጠቀሚ ከሆነ ፓስወርድሽን ሰብረው በመግባት ከአንቺ ጓደኞች ጋር እንደ አንቺ ሆነው ኢ ሜይል ይደራረጋሉ፤ ምስጢርሽን ይወስዳሉ፤ ፌስ ቡክ ላይ ገብተው ካንቺ ጓደኞች ጋር ያወራሉ፡፡ ብቻ የሚሳናቸው ነገር የለም፡፡ እኔ እስኪ አገር ልቀይር ብዬ ጀርመን ስሄድ የማርፍበት ቦታ ቀድሞ ጥቁር ካልሲ ተጥሎ ነበር፡፡ ስዊድንም ስሄድ የማርፍበት የጓደኛዬ ቤት በር ላይ ይሄው ካልሲ ተጥሎ ጠበቀን። ይሄ ላልነቃበት ሰው ከድግምትስ በላይ አይሆንም እንዴ?
ወሮበሎቹ የሚያጠምዱት ማንን ነው? ምክንያታቸውስ ምንድን ነው?
በማንኛውም ሁኔታ፣ በየትኛውም ጊዜ፣ የትኛውም ሰው ወጥመድ ውስጥ ሊገባ ይችላል፡፡ ነገር ግን መጀመሪያ ምክንያት ያስፈልጋል፡፡ ከምክንያቶቹ አንዱና ዋናው ከወሮበሎቹ ከራሳቸው ወይም ከዘመዶቻቸው ጋር የተጣላ ካለ ይጠመዳል፡፡ በፆታዊ ግንኙነት ሴቷ በቃኝ ብላ ወንዱ መቀጠል ከፈለገም ያስጠቁራታል፡፡ 
ለእርስዎ ወጥመድ ውስጥ መግባት ምክንያት የሆነችውና በመጽሐፉ ውስጥ ዮዲት ጉዲት በሚል ከተገለፀችው ሴት ጋር እንዴት ተገናኙ? እንዴትስ ለወጥመዱ ምክንያት ሆነች?  
እኔና ዮዲት ጉዲት በሶስተኛ ሰው ነው የተገናኘነው። እኔም እሷም በማናውቃት ሴት አማካኝነት ተገናኘን። እኔ በወቅቱ ትዳር ለመመስረትና ቤተሰብ ለማበጀት እፈልግ ስለነበር ዮዲትም ባል ትፈልጋለች ተብሎ ነው የመጣችው፡፡ ነገር ግን እሷ ትዳር ሳይሆን የመኖሪያ ፈቃድ ነበር የምትፈልገው፡፡ እሷ መኖሪያ ፈቃድ ሳይኖራት በህገ ወጥ መንገድ ለንደን ውስጥ የምትኖር ሴት ነበረች፡፡ ከተቀራረብን በኋላ ብዙ ነገሮች ምቾት አልሰጡኝም። በአጠቃላይ እኔ የምፈልገው አይነት ስብዕና ያላት ሴት ባለመሆኗ ግንኙነቱን ለማቋረጥ ተገደድኩኝ፡፡ እሷ አለመፈለጓ ስላሳመማት ልትበቀለኝ ፈለገችና አስጠቆረችኝ፡፡ 
ለካስ የወሮበሉቹ አባል ነበረች፡፡ ይህን እርምጃ ከመውሰዷ በፊት “አንተ ካልወደድከኝና ልታገባኝ ካልፈለግህ ቢያንስ መኖሪያ ፈቃድ እንዳገኝ ፈርምልኝ” የሚል ጥያቄ ሁሉ አቅርባልኝ ነበር፡፡ እኔ እንዲህ አይነት ህገ -ወጥ ስራ ባለመፈለጌ እዚህ ችግር ውስጥ ገባሁ። ከዚያ በኋላ ያየሁትን መከራና ስቃይ መጽሐፉ ላይ አንብበሽዋል፡፡ በጣም ተከብሬ በምሰራበት ሆስፒታል ውስጥ “ሄኖክ መድሀኒት እየሰረቀ ይሸጣል”  ብለው አውርተውብኝ ስሸማቀቅ ኖሬአለሁ፡፡ ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ፤ ንፅህናሽን ለማስረዳት ብትሞክሪ ሰሚ የለሽም፡፡ በዚህ የተነሳ ብዙ ስቃይ ደርሶብኛል፡፡ 
ለዮዲት ጉዲት ብፈርምላት ወይም ባገባት ኖሮ ከዚህ ወጥመድ ነፃ እሆን ነበር ብለው ያስባሉ?
በፍፁም! የባሰ አዘቅት ውስጥ፣ የባሰ ችግር ውስጥ እገባ ነበር፣ በህይወት መቆየቴንም እጠራጠራለሁ። በጣም አደገኛ ሰው ስለመሆኗ በተዋወቅንባቸውና ስለሷ ለማወቅ በሞከርኩባቸው ጥቂት ጊዜያት ለመረዳት ችያለሁ፡፡ 
በመስሪያ ቤት መድሃኒት ይሰርቃል በሚል ከተወነጀሉ በኋላ ነፃነትዎን ለማወጅ “Lie detective” በተባለ መሳሪያ 17 ሺህ ብር ከፍለው በመመርመር፣ እውነቱ ተረጋግጦ በሚሰሩበት ሆስፒታል ተቀባይነትን እንዳገኙ በመፅሀፉ ገልፀዋል፡፡ ሌሎች የችግሩ ሰለባዎች ታዲያ ለምን ይህን ዘዴ አይጠቀሙም?
ትክክል ነው፤ ቴክኖሎጂው መጥፎም በጐም ጐኖች አሉት፡፡ ለመጥፎ ከተጠቀምሽው መጥፎ ይሆናል፤ ለመልካም ከተጠቀምሽው እንደዚሁ። እኔም አለመታመኑ ሲበዛብኝ፣ የሚሰማኝም ሳጣ ነው ወደ መሳሪያ ምርመራው የሄድኩት፡፡ በዛ ነው ነፃ የወጣሁት። እኔ ነርስ እንደመሆኔ የስራና የውጭ ካልሲዬ የተለያየ ነው፡፡ ሆስፒታል ስገባ ከውጭ አድርጌ የገባሁትን ጫማና ካልሲ አውጥቼ፣ የሆስፒታሉን ሳደርግ ያወለቅሁት ውስጥ ጥቁር ካልሲ ይጨምራሉ። ይሄንን ሳመለክት አይሰሙኝም፡፡ ተከብሬ በኖርኩበት ሆስፒታል ውስጥ የመድሃኒት ሌባ ተብዬ ሁሉም ሲጠቋቆሙብኝ፣ በቃ ወደ ዲቴክቲቭ ምርመራ ሄድኩኝ። ውጤቱ “ነፃ ነው” አለ። ይህንን ለሆስፒታሉ የበላይ አካል አቀረብኩ። በጣም ጉድ  ተባለ፡፡ 
ከዚያ በኋላ ሆስፒታሉ ለእኔ ጥበቃና ክትትል ማድረግ ጀመረ፡፡ ከዚያም አልፎ በስራ ቦታዬ፣ በምቀመጥበት ወንበር አካባቢ “ሲሲ ቲቢ” የተባለ ሳያቋርጥ በተከታታይ የሚቀርፅ ቪዲዮ ካሜራ ተገጠመ። በዚህ ካሜራ በተገኘ ውጤት አራት የሆስፒታሉ ሰራተኞች ደባ ሲሰሩ ተገኝተው ከስራ ሲባረሩ፣ በከባድ ማስጠንቀቂያም የታለፉ አሉ፡፡ እጃቸው ረጅም ነው ወሮበሎቹ፡፡ 
ሌሎቹ ለምን ይህን መሳሪያ አይጠቀሙም ለተባለው አንደኛውና ዋናው ምክንያት የችግሩን መንስኤ አለማወቃቸው ነው፡፡ እንዳልኩሽ ችግሩ ሲደጋገምባቸው እየተሸበሩ እየፈሩ ብቸኛ እየሆኑ ስለሚሄዱ ከሰው ጋር ለመመካከርና መፍትሔ ለማግኘት እድል አያገኙም፡፡ 
ቀደም ሲል  ወሮበሎቹ ደባውን ሲሰሩ ከቻሉ ምንም አይነት መረጃ ላለማስቀረት ካልሆነም ትንሽ መረጃ ብቻ ይተዋሉ፤ ይህ ደግሞ ተበዳዮች ፍትህ እንዳያገኙ ያደርጋል ብለውኛል፡፡ እርስዎ መጽሐፍ ለመፃፍ የሚያስችል መረጃ እንዴት ማሰባሰብ ቻሉ?
እኔ ነገሮች ሲደረጉ ቪዲዮ እንድቀርፅ፣ የሰው ማስረጃ እንዳሰባስብ፣ ፎቶ እንዳነሳና ሌሎች መረጃዎችን እንዳሰባስብ፣ መጽሐፍ ጽፌም ሌሎች እንዲማሩበት ለማድረግ የቻልኩት ችግሩ ምን እንደሆነ ቀድሜ በማወቄ ነው፡፡ በወሮበሎች ወጥመድ ውስጥ መውደቄን ስላወቅሁኝ ነው፡፡ ሌሎቹማ ስለማያውቁት ፖሊስ ጣቢያ ሄደው “እንዲህ እያደረጉኝ ነው፤ እንዲህ እየሆንኩኝ ነው” ብለው ሲያመለክቱ “መረጃ አምጡ” ይባላሉ። ይህን ማድረግ አይችሉም፤ እንደውም እንደ አዕምሮ በሽተኛ ነው የሚታዩት፡፡ የወሮበሎቹም ዓላማ ይሄው ነው፤ ተዓሚነትን ማሳጣት፡፡ የመጽሐፉ ዋና አላማም የችግሩ ተጠቂዎች መንስኤውን አውቀው ከችግሩ እንዲወጡ፤ ችግሩ ያልደረሰባቸውም አጠቃላይ የችግሩን ምንነት አውቀው፣ ችግሩ ሲመጣ እንዲከላከሉ ክትባት እንዲሆናቸው ነው፡፡ 
በመኖሪያ ቤትዎ፣ በሚሄዱባቸው ሆቴሎች፣ በመስሪያ ቤትዎና በሌሎችም ቦታዎች በርካታ ጥቁር ካልሲዎች ተጥለውበታል፡፡ በመጨረሻ ካልሲዎቹን አጥበው መጠቀም እንደጀመሩ ነው በመጽሐፉ የገለፁት። እንዴት ደፈሩ?
እንዳልኩሽ መጀመሪያ ጥቁር ካልሲ ሲጥሉብኝ እበረግግ ነበር፡፡ በመጨረሻ ግን ለመድኩት፤ ስለዚህ በጣም በሙቅ ውሃና በኬሚካል አጥቤ መጠቀም ጀመርኩኝ፤ እንደውም አድርጌው ቢያዩኝ እላለሁ። ካልሲው ምንም የለውም፤ በቃ ካልሲ ነው፤ ስለዚህ እኔም ላበሳጫቸው ብዬ ነው የማደርገው፡፡ በቃ ምንም አልሆንኩም፡፡ 
“የዲያስፖራው ስውር ደባ” የተሰኘው መጽሐፍዎና “The Jaws of Evil” በሚል ወደ እንግሊዝኛ የተመለሰው መፅሃፍ ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ ሆቴል ተመርቀዋል። የመፃህፍቱ መተርጎምና መመረቅ ፋይዳው ምንድን ነው?
“የዲያስፖራው ስውር ደባ” የተፃፈው ከአንድ ዓመት በፊት ነው፡፡ ዓላማውንም ቀደም ብዬ ነግሬሻለሁ። አሁንም ብዙ ኢትዮጵያኖች በችግሩ እየተሰቃዩ ነው። መጽሐፉን ያስመረቅኩት ይበልጥ ችግሩ ትኩረት እንዲያገኝ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የችግሩ ተጠቂዎች ቀን አለ፡፡ ባለፈው ጥቅምት ወር በርሊን ጀርመን ውስጥ ተከብሯል፡፡ እኛ አገር እንኳን ቀኑ ሊከበር ችግሩ በቅጡ የታወቀ አይመስለኝም። በእኔ መጽሐፍ ላይ እንዳየሽው ጥቂቶች በተወሰነ ደረጃ ችግሩን አውቀውት የደረሰባቸውን ምስክርነት አንብበሻል፡፡ በመጽሐፍ ምረቃው ላይም የደረሰባቸውን  ስቃይ ሲናገሩ ሰምተሻል። እኔም እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሁለት ዓመት በፊት ለበጐ አድራጐት ስራ መጥቼ አላስቆም አላስቀምጥ ሲሉኝ፣ ፖሊስ ጣቢያ ብሄድ እንደ እብድ ነው ያዩኝ እንጂ የሰማኝ የለም፡፡ ስለዚህ በመጽሐፉ ምረቃ እለት የተገኙ ሚዲያዎች የችግሩን ስፋት ለሰው እንዲያስገነዝቡ፤ ሰዎችም መጽሐፉን አግኝተው እንዲያነቡ ለማድረግ ነው፡፡ ወሮበሎች መጽሐፉ እንዳይመረቅ ሁለት ጊዜ አዳራሽ ተከራይቼ አስከልክለውኛል፡፡ ስለዚህ ህዝብም መንግስትም ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጠው ለማድረግ ሞክሬያለሁ፡፡ 
መጽሐፉን የሚችል ገዝቶ፣ የማይችል በማንኛውም መልኩ እኔን ቢያገኘኝ በነፃ ለመስጠት ዝግጁ ነኝ፡፡ እስካሁን ወደ 600 መጽሐፍት በነፃ ሰጥቻለሁ፡፡ በችግሩ ውስጥ ያለ ሰው ካለም ቀርቦ ቢያማክረኝ ከተሞክሮዬና ከልምዴ በማካፈል፣ ከችግሩ እንዲወጣ ለማገዝ ፈቃደኛ ነኝ፡፡ 
በመጽሐፉ ላይ ስሞት ኩላሊቴ፣ ልቤ፣ ሌላውም የሰውነት ክፍሌ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ይሰጥልኝ፤ የቀረው አካሌ ለምርምር ይዋል ብለው ቃል ገብተዋል። በህይወት እያሉም በየጊዜው ደም እንደሚለግሱ ገልፀዋል። ደግነትዎ በጣም አልበዛም?
 (በጣም እየሳቁ) ደግነት በጣም በዛ አይባልም፡፡ ደግ ከሆኑ በጣም ደግ መሆን ያስፈልጋል፡፡ ለነገሩ ይሄን ሁሉ የገለፅኩት እንዲህ “ህጋዊና ሰላማዊ ሰው ሆኜ ነው ይሄ ሁሉ የደረሰብኝ” ለማለት እንጂ ይህን አደረግሁ ብዬ ጉራ ለመንዛት አይደለም፡፡ 
ሌላው በወሮበሎች የሚጠመደው ግለሰብ እንደኔው ዓይነት ሰላማዊ ሰው ነው፤ የሚለውን ለማስረዳት ፈልጌ ነው፡፡ በመጽሐፌ ካሰባሰብኳቸው መረጃዎች በፊት የወሮበሎቹ አባል ሆነው ሲያጠምዱ የነበሩ አሁን ራሳቸው የተጠመዱ አጋጥመውኛል፡፡ ስለ ልብና ኩላሊቴ ቃል የገባሁት ስዊድን በስደት እንደገባሁና መንጃ ፈቃድ ላወጣ ስል ነው፡፡ እዚያ አገር መንጃ ፈቃድ ለማውጣት ስትሄጂ፤ ስትሞቺ ኩላሊት፣ ልብ፣ አይን መስጠት ትፈልጊ እንደሆነ ፎርም ይቀርብልሻል፤ እኔም ያኔ ነው ቃል የገባሁት፡፡ ወደ ለንደን ስመጣም በዚያው አቋሜ ነው የፀናሁት፡፡ ደምም በቁሜ ሆኜ ለመለገስና የሰዎችን ህይወት ለማትረፍ ቃል በገባሁት መሰረት እየለገስኩ እገኛለሁ፡፡ 
በመጨረሻ የሚናገሩት ካለ … 
ከሁሉ በፊት ፈተናዬን ተጋፍጦ ጦርነቴን ያሸነፈልኝን የሄኖክን አምላክ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፡፡ በስራዬ ከጐኔ የነበሩትን ሁሉንም አመሰግናለሁ፡፡ በመጨረሻም ወሮበሎች የያዙት ሥራ፤ አርጅተው ሲደክሙ ስንቅ የማይሆናቸው ነገር ነው፡፡ ስለዚህ ከህሊናችሁ ታረቁ እላለሁ፡፡ የተጠቂ ቤተሰቦችም ልጆቻችሁ፣ እህትና ወንድሞቻችሁ የሚሏችሁን ስሟቸው፡፡ አዳምጧቸው፤ አዋቂ ቤት፤ ጠንቋይና ባለዛር ቤት እየወሰዳችሁ ችግር አትደርቡባቸው፡፡ የኢትዮጵያ መንግስትም ለችግሩ ትኩረት ይስጥ እላለሁ፡፡ አመሰግናለሁ፡፡  
http://www.addisadmassnews.com/    

No comments:

Post a Comment