Monday, March 30, 2015

"ከዝንጀሮም እንገኝ ከአዳምና ሄዋን ወንድምና እህት ነን» የክብር ዶ/ር ዙምራ ኑሩ"

በቴዎድሮስ ተ/አረጋይ
አንጋፋው የአውራምባ ማህበረሰብ መስራች የክብር ዶክተር ዙምራ ኑሩ እሱ «ምንም እንዳልሰራሁ ሁኖ ይሰማኛል» ቢልም ሀሳቡ መሬት ወርዶ ፣ ዘር አፍርቶ ከዜሮ ቀና ወደ ማለት ሲጓዝ አይቷል ። እርሱ በቁሙ እያለ ማህበረሰቡ በንቀትና በጥላቻ ከመታየት ወጥቶ እንደ አንድ የባህል ቅርስ ሊጎበኝ በቅቷል ። በራሱ የህይወት ፍልስፍና ማህበረሰቡን ያነፀው ይህ ሰው ለእኛ ባይደንቀንም ነጮቹ ግን ህይወትና ፍልስፍናው አስደምሟቸው የክብር ጥሪ ያደርጉለታል ። ከወራት በፊት ከጥሪዎቹ አንዱን ተቀብሎ ፈረንሳይ ውስጥ የክብር ጉብኝት አድርጎ በ10 ቀናት ቆይታው በሔደበት የተናገረው ከቁም ነገር ተቆጥሮለት በፈረንሳይኛና በእንግሊዘኛ ቋንቋዎች ዶክመንታሪ ተሰርቶለት ተመልሷል ። በተመሳሳይም ከተለያዩ ሀገራት የጉብኝት ጥያቄ ይቀርብላታል ።
ዙምራ ሰሞኑን አዲስ አበባ በመጣ ጊዜ አግኝቶኝ የመጣበትን ጉዳይ ከተወያየን በኋላ ለኢትዮ ዴይሊ ፖስት ዌብ ሳይት አንባብያን የሚከተለውን አውግተናል ፡፡
zumera






















 ኢትዮ ዴይሊ ፖስት ፡- ዙምራ አዲስ አበባ እንዴት መጣህ ?
 ዙምራ፡- በመኪና ተሳፍሬ ነዋ ።
 ኢትዮ ዴይሊ ፖስት፡ በመኪናማ ነው ። ለምን አላማ መጣህ ማለቴ ነው እንጂ ።
 ዙምራ፡- አላማዬ ብዙ ነው ። እናንተ ጋዜጠኞችንም ልወቅሳችሁ ነው የመጣሁ ።
 ኢትዮ ዴይሊ ፖስት፦ ምን አደረግን ?
  ዙምራ፡- ጥሩነትና መጥፎነትን አበጥራችሁ ሕዝቡ ልብ ውስጥ አላደረሳችሁም ። ሰው በጥሩው ብቻ አይማርም ።    ከክፋትም ይማራል ። የእናንተ ድርሻ ፣ የምሁራኑም ድርሻ ክፉ ከደግ እንዲለይና እንዲታይ ማድረግ ነው ፡፡     እናንተ ናችሁ ሀገርን የምትለውጡት ። እናንተ ናችሁ ሀሳብን በጥሩ መሬት ላይ እንዲዘራ የምታደርጉ ። ይህን ነው የምጠይቃችሁ ። እናንተ መልካም ዘር ናችሁ ብላችሁ አምናችሁ መች ወደሰው አደረሳችሁን መች ሀሳባችን ሰውጋ ደረሰ 
 ኢትዮ ዴይሊ ፖስት፡- ደርሷል እንጂ ዙምራ እኔ ራሴ ካንተ ጋር ሁለት ሶስቴ አውርቼ ጽፌዋለሁ ። ተጽፎም  ተነቧል ። ሌሎችም ይህን አድርገዋል ። ዛሬ ብዙ የከተማ ሰው ስለ እናንተ በርቀትም ቢሆን ያውቃል ።
 ዙምራ፡-   ማወቅ ምንድ ነው ?  እስቲ እንተኑ ልጠይቅህ ።
 ኢትዮ ዴይሊ ፖስት፡-     ከባድ ጥያቄ ነው ። ጥልቅ ሀሳብ ነው ። ግን እንዲያው ባጭሩ በዚያ በምታውቀው ጉዳይ በቂ መረጃ መያዝ ፣ ጉዳዩን መረዳት ተብሎ ሊታሰብ ይችላል?
ዙምራ፡- እኛ ደግሞ ታወቀ የምንለው መሬት ወርዶ ስናየው ነው ። የእኛን ሀሳብ ሕዝቡ ተረድቶት ተሆነ መች ሰላም መጣ  መች ሰው ከጠብ ራቀ  እኛ አንድ እንደሆንን መች ሕዝብ በሞላ አንድ ሆነ  ሀሳባችንማ ከሀገር አልፎ በአፍሪካና በአውሮባ ተዳርሶ ነው ያለ ። ግን አንድነት ፣ ፍቅር ፣ ሰላም መች መጣ  ጠብና እርግማኑ አይደለም የተስፋፋው  ይህ ሳይሆን ደግሞ ሰው ጋር ደርስን ልንል አንችልም ። እኛ ማዳረስ አይደለም የያዝን ፤ መድረስ ነው ።
ኢትዮ ዴይሊ ፖስት ፡- ማዳረስና መድረስ ምኑ ላይ ነው ልዩነታቸው ?
ዙምራ፡- እንደው ለጥያቄ እንዲያጫውትህ ነው እንጂ እውነት ሳታውቀው ቀርተህ ነው የጠየከኝ  እኔ ግን እመልሳለሁ ። ማዳረስ የምንለው ይህን በከተማ የሚገኘውንና ሰው የሰማውን ነው ። ይሄ በሬዲዮና በቴሌቪዥን የሚነገረው ሁሉ ማዳረስ አይደለም የሚባል  መድረስ ሲባል ግን ተልብ ዘንድ መቅረብ ነው ። ተልብ የደረሰ ተመሬትም ደርሶ ነው የሚገኝ ። ተልብ ታልደረሰ ግን እዚያው በዚያው ነው ነጥሮ የሚመለስ ።
ኢትዮ ዴይሊ ፖስት ፡-አሁን ያለንበት ወቅት በሀገር አቀፍ ደረጃ ምርጫ የሚደረግበት ወቅት ነው ። በአውራምባ ማህበረሰብ ውስጥ የምርጫ ስርዓት በምን መልኩ ይከናወናል ?
ዙምራ፡- በሌላ አካባቢ ያለውን ምርጫ በወጉ ስለ ማላውቀው የምናገረው የለኝም ።
ኢትዮ ዴይሊ ፖስት ፡-     በአውራምባውን ብቻ ንረገረኝ ።
ዙምራ፡- ማህበረሰቡ ይሆነኛል የሚለውን ሰው በየሶስት ዓመቱ ይመርጣል ። ጥሩ ሰርቷል ታለ ድጋሚ ይመርጠዋል ። ካልሰራ ደግሞ ሦሶቱን ዓመት ሳይሞላ ያስቀረዋል ። ስድስት ዓመት ከሰራ በኋላ ግን በቃህ ይባላል ። እኛ ዘንድ ና ውጣ ና ውረድ ለማለት ይሉኝታ የለብንም። ደሞስ የሚመረጠው ማህበረሰቡን ለማገልገል እንጂ በማህበረሰቡ ለመገልገል አይደለም ። ሕዝቡ በወጉ አልሰራህልኝምና ውረድ ካለው ምን ይሻ እዚያው ወንበሩ ላይ ይቀመጣል  ሕዝቡ አልፈልግህም ብሎት እሱ ግን አልወርድም ታለ ቀድሞም የደበቀው አንድ ነገር አለ ማለት ነው ።
ኢትዮ ዴይሊ ፖስት፡- አንድ ሰው እንዲያገለግል ተመርጦ አልፈልግም ሊል ይችላል?
ዙምራ፡- ይችላል መብቱ ነው ። እስካሁን ግን ያፈነገጠብን የለም ።
ኢትዮ ዴይሊ ፖስት፡- ሃላፊነቱን በአግባቡ ባለመወጣቱ ሦስት ዓመቱ ሳይደርስ እንዲወርድ የተደረገስ የለም?
ዙምራ፡-   የለም ። እንደውም ጨምር ነው የሚባለው ።
ኢትዮ ዴይሊ ፖስት፡-እዚህ በሀገራችንም ሆነ በሌሎች ሀገሮች ሰዎች ሲመረጡ ሙስና ውስጥ መግባት ወይም ስልጣናቸውን አለአግባብ መጠቀም አለ ። አንዲህ በሚሆን ጊዜ አለጊዜው ከስልጣኑ ታወርድታላችሁ ?
ዙምራ፡-   እንደ እቅድ አለ ። ገጥሞን ና ውረድ ያልነው ግን የለም ። አንድ ሳንቲም የሰው ገንዘብ መውሰድ ሀጢአትም ወንጀልም ነው ። እንኳን የሰው ገንዘብ የወደቀንም አንስቶ ኪሱ የሚከት የለም ። ካሁን ቀደም አልደረሰብንም ። ተመርጦ ማስተዳደር በማህበረሰባችን ቀላል ነገር አይደለም ። እሱ ሃላፊ ሆኖ ራሱን ሊያንቆራጥጥ ሳይሆን ህዝቡን ጓዝ አድርጎ የሚሸከም መሆን አለበት ። ይህ ሃላፊነት ነው አየተሰጠው ወይም እየተሰጣት ያለው ። ስለዚህ እንደውም ሃላፊ መሆኑን ማንም አይፈልገውም ። ግን ለእኛ ሌላ ማንም አይመጣልንም ። ለዚሁ ነው ሕዝቡ አገልግለኝ ሲባል እምቢ የማይባለው ።
ኢትዮ ዴይሊ ፖስት፡- በተመራጭና በሌላው የማህበረሰብ አባል መሀል ያለው የኑሮ ልዩነት ምን ይመስላል ? እዚህ ከተማ ምረጡኝ !» ማለት ከሕዝብ ይልቅ ለራስ ነው ።
ዙምራ፡- ለራሱማ ምን ያገኛል እኛ ዘንድ ? እንዲያውም የተመራጩ ቤት በብዙ መልኩ ወደኋላ ነው የሚቀር ። በአመት መጨረሻ ትርፍ ሲከፋፈል ተመራጩ ሌላው ካገኘ በኋላ ነው የሚሰጠው ። የተለየ ጥቅም ምንም አያገኝም ። ለስብሰባ ከተማ ሲሄድ አበል ይሰጣል መቼም ። የእኛ ሰው የተሰጠውን አበል እጄ ገባ ብሎ አያባክነውም ። ከተማም ቢሆን ፣ ገንዘቡም በእጁ ቢሆን ቆሻሻ በሽታ ላይ የሚጥለው አይሁን እንጂ ዝቅ ያለውን መኝታ ነው የሚይዘው ። ወደ አውራምባ ሲመለስ የያዘው ሂሳብ ይወራረዳል ። የውሎ አበሉ ተጠቅሞበት የተረፈው ለማህበሩ ነው ገቢ የሚሆነው ። በሳምንት አንዱን ቀን ለግላችን የምናውለው ነው ። ምናልባት በዚያን ቀን በሰብሰባ ተሳትፎ ተሆነ ያን ለግሉ ማድረግ መብቱ ሊሆን ይችለል ።
ኢትዮ ዴይሊ ፖስት፡- ይህ የምትነግረኝ ታሪክ በእርግጥ መሬት ላይ ወርዶ ተግባራዊ የምታደርጉት ነው ?
ዙምራ፡- አሀ ነው እንጂ ። እያወራን ያለነው በቁም ነገርም አይደለ አንተን ለማሳሳት ባወራ ጉዳዩን የሚያውቀው ሰው ይታዘበኝም የል? መዋሸት የት ጥግ ያደርሳል  እስተዛሬ የተናገርኩት ሁሉ መሬት ወርዶ ባይገኝ እንዴት ለውጥ እናመጣ ነበር  ደግሞስ አንተ አውራምባ ድረስ መጥተህ አይተህን የለ
ኢትዮ ዴይሊ ፖስት፡- አሁን አንተና ባለቤትህ የመጣችሁት ለማህበረሰቡ ስራ ነው አዲስ አበባ ወር ገደማ ቆይተናል ብላችኋልና የውሎ አበል ማህበሩ ላይ የሚሰጣችሁ ?
ዙምራ፡- በመንገድ ስላለን ለምን ይዘው አልጋና በምንመገበው ምግብ እንጂ እዚህማ የአውራምባ ሰዎች ቤት ነው ያረፉነው ለምግብና ለአልጋ አናወጣም ስለዚህ የውሎ አበል አያስፈልገንም ለታክሲ የሚሆን ወጪ ብቻ ነው ያለን ። አበሉ ቢሰጠንም አጠራቅመን መመለሳችን አይቀርም ። ምክንያቱም እዚህ የመጣነው ማህበረሰቡን ብቻ ለማገልገል እንጂ እኛ ለመገልገል አይደለም ።
ኢትዮ ዴይሊ ፖስት፡- ጋዜጠኞችን ከማናገር ባለፈ በአሁኑ ጉዞህ የመጣህበት ዋናው ጉዳይ ምንድነው ?
ዙምራ፡- አስፈላጊ የሆነው ጉዳይ ሁሉ ዋና ነው ። የማያስፈልግ ጉዳይ ብቻ ነው ዋና የማይሆን ። ባሁኑ የመጣ ነው ብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ካሁን በፊት ጠርተናቸው መጥተው ጎብኝተውን ነበረ ። የስራ መሳሪያዎቻችን በሰው ጉልበት መሆኑ ቀርቶ በኤሌክትሪክ እንዲሰራ መላ እንዲፈልጉልን ልናዋያቸው ነው የመጣን ።
awramba socity
ኢትዮ ዴይሊ ፖስት፡- የመጣችሁበት ጉዳይ ተሳካ ታዲያ ?
ዙምራ፡- እንግዲህ ምንም አይልም ። ይሳካል ብለን ነው የምናምን ።
ኢትዮ ዴይሊ ፖስት፡- አውራምባን ከጎበኘሁበት ከዛሬ 4 አመት ገደማ ወዲህ ምን ለውጥ አለ በማህበረሰቡ ውስጥ ?
ዙምራ፡- ለውጥ የለም ። የእኛ ማህበር እዚያው ባለበት ይረግጣል እንጂ እልፍ ብለን መስራት አልቻልንም ሀሳቡ ሳይጎድለን ስራው አያለን ምርታችንን ለሕዝብ የምናቀርብበት ቦታ አየቸገረን ነው ። ባህርዳርም ብንሄድ እዚህ አዲስ አበባ ብንመጣም ቦታ በሊዝ ግዙ ነው የሚሉን ። እኛ ያለን ብር ሳይሆን ሀሳብና የስራ ፍቅር ነው ። ሀሳብ ደግሞ ብቻውን ሊዝ አይገዛም ። ሒደታችን እያደገ መራመድ አልቻልንም ። ካለንበት ማደግና መለወጥ ካልቻልን ደግሞ አባላቶቻችንን ይፈረካከስብናል ብለን እንሰጋለን ። አውራምባ ለራሱ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም እየሆነ ነው ያለው ። ከዜሮ ተነስቶ ማደግ ይቻላል ብሎ ያምናል ። እምነቱንም በተግባር አውሎ አሳይቷል ።
ኢትዮ ዴይሊ ፖስት፦ከዜሮ ተነስታችሁ የት አደጋችሁ ? እስቲ ንገረን ።
ዙምራ – ማደግ መቼም ጥግ የለውም ። ካለህብት መሻሻል ማደግ ነው ። ከቦንጋ ስደት መልስ በ1985 ስንመጣ የቆሎ ተማሪ ጎጆ የመሰለ ነው እዚህ የነበረው ። የምንመገበው አጥተን ከገበያ ጥጥ ገዘተንና ፈትለን የጥጥ ፍሬውን እየጨመቅን ለልጆቻችን በፍንጃል እያከፋፈልን ነው የኖርነው ። በዚህ 8 እና 9 አመት ነው በወጉ በልተን ማደር የጀመርነው ። አሁን ግን ቤታችን በወጉ ተሰርቶ የገቢ ምንጭ አያስፋፋን ነው ። ሕዝቡ እየኖረ ነው ። አኔ ግን የምሰጋው ጉዳይ አለኝ ።
ኢትዮ ዴይሊ ፖስት፡-  ምንድነው ስጋትህ ?
ዙምራ፡- እርምጃችን ተገድቦ ስራችን ካላሰፋንና ሕዝቡ ስራ አጥ ተሆነ ያልተማሩ ዱርዮዎች ሲያስቸግሩን የተማረ ዱርዬ መፍጠር ነው የሚሆነው ። የነገ ሕይወታችን ምንድነው ? የነገ የኢትዮጵያ እድል ያሳስበኛል ፡፡
ኢትዮ ዴይሊ ፖስት፡- ስው ነህና አንድ ቀን ትሞታህ ። በዚያን ጊዜ ሳልሰራው ቀረሁ የምትለው ምን አለ?
ዙምራ – የሞት ነገር የሚያሳስበኝ አሁን በቁሜ እያለሁ ነው ።ከሄድኩ በኋላ ሄጃለሁ ። እስካለሁ ያለው ነው የሚያሳስበኝ ። እኔ ሕይወቴ አስካለ ልስራ ። የእኔ ችግር ሕይወቴ እያለ አልሰራሁም ። ወደ ወጣቱ ገብቼ ማድረግ ያለብኝን አላደረኩም ። የሚያደራጅልኝ አላገኘሁም ። አልሰራሁም ። ምን ሰርቼ? ገና በሀሳብ እንጥልጥል ላይ ነው ያለሁት ።
ኢትዮ ዴይሊ ፖስት፡- የአውራምባ ማህበረሰቡን መፍጠር በራሱ አንደትልቅ ስራ ተደርጎ ሊቆጠር አይችልም ?
ዙምራ፡- አንተ ትልቅ መስሎህ ይሆናል ። እኔ ግን ያሰብኩትን ያህል አልሆነልኝም ። እኔ የማስበው በአውራምባ ያለችን አንድ ጎጥ አይደለም ። ሙሉ ሰላም ማምጣት ነው ያለብን ። አውራምባ ቀርቶ ኢትዮጵያም ሰላም መሆኗን ለብቻው ሰላምን አያመጣም ። ሙሉ ሀገሮች ሰላም መሆን አለባቸው ። ሁሉም ሀገሮች የሰውን ልክ ማወቅ አለባቸው ። እኛ ከዝንጀሮም አንገኝ ከአዳምና ሄዋን ወንድምና እህት ነን ። የአንድ ዘር ግንድ ነን ። ይህ ሀሳቤ በአየር ላይ ሄዷል ። ከሀገር ሀገር ተዳርሷል ። ሆኖም ሃሳቡ ሰላምን እስካላመጣ ድረስ ግን ምን ሰራሁ ያስብላል አየር ላይ ነው ያለ ። መሬት አላረፈም ።
ኢትዮ ዴይሊ ፖስት፡- የአለማችን ሁኔታ ስናይ የሰው ልጆች ከህብረት ወደ ግለኝነት ፣ ከአንድነት ወደ መነጣጠል እየሄዱ ነው ። የአንድ ሀይማኖት ፣ የአንድ ብሔር ፣ የአንድ ሀገር ሰዎች እንኴ አንድ ገበታ ላይ አብረው መቅረብ እያቃታቸው ይመስላል ። ይህ የምን ጉድለት ይመስልሃል ?
ዙምራ፡- የእኔን ሀሳብ ነው የምነግርህ እንጂ የእነሱን አላውቅም ። እኔ ግን ይህ ሆኖ ማየት ነው የምፈልገው ።
ኢትዮ ዴይሊ ፖስት፡-እያንዳንዱ ህዝብና ሀገር ላይ ያለውን እውነታ ባታውቀውም ግን የሰው ልጆች የቱን ነገር ስለሳቱ ይመስልሃል ይህ የመጣባቸው ?
ዙምራ፡- እንግዲህ ለኔ እንደምለው ከሆነ የሰው ልጆ አንድ አካል መሆንን አጥተናል የሩቁን ትተህ የአክስትና አጎት ልጅ ካልክ በኋላ ሌላውን አያገባኝም ነው የምትል አለምን ዛሬ ብሄድ ማንንም የሰው ልጅ ሳገኝ እቅፍ አድርጌ ተሳስሜ ተጨዋውተን መለያየት አስካልቻልን ድረስ ሀሳቤ ሰው ጋር ደረስ ማለት አልችልም
ኢትዮ ዴይሊ ፖስት፡- እኔ ባልኖር ማህበረሰቡ ወደ ኋላ ይመለሳል ብለህ ትሰጋለህ ?
ዙምራ፡- አልሰጋም  በእርግጥ ማህበረሰቡ ከችግሩ ከምኑ አኳያ ሊተወው ይችላል  መነሳት ሲያቅታቸው ሊተውት ይችላሉ ።ግን በአለም ላይ ሀሳቡ መቀጠሉ አይቀርም ብዬ አስባለሁ 

No comments:

Post a Comment