Thursday, May 2, 2013

‹‹ያምራል ብለው ከተናገሩት…››ከኑሮ እና ፖለቲካ /ቁጥር - 2 የተወሰደ/ በኃይሉ ገ/እግዚአብሔር


ሰውየው አርቲስት ነው፡፡ ወዳጄ እንዳጫወተኝ፡፡ ማታ ማታ ሰክሮ ወደ ቤቱ ይገባል አሉ፡፡ ትህትና ይዞን ‹‹ማታ›› እንበልለት እንጂ እርሱስ የሚገባው ለጠዋት በቀረበ ሰዓት ነው አሉ፡፡ ይህ አርቲስት እቤቱ እንደገባ የመጀመሪያው ተግባሩ ልጆቹን መቁጠር ነው፡፡
አሳዛኙ ነገር ልጆቹ ለመቆጠር ብለው ከሚያምር እንቅልፍ ላይ ሁሌ እንዲነሱ መገደዳቸው ነው፡፡ ሲዘገንን! ለመሆኑ ልጆቹ ስንት ናቸው? አራት፡፡ ‹‹አንድ፣ ሁለት፣ ሦስት፣… ቆይ ! ቆይ ! ቆይ ! ተሳሳትኩ እንዴ ! እናንተ ሁላችሁም ቀጥ ብላችሁ ቁሙ፤ አንድ፣ ሁለት፣ እ… አንተ ትንሹ ና ከፊት ሁን፤ አዎ ! አንድ፣ ሁለት፣ ሦ.. አይ! አይ! ከሴት መጀመር አለበት፤ ነይ አንቺ ከፊት፤ አንድ፣ ሁለት፣ ሦስት..›› እያለ ሲቆጥር ይነጋል አሉ ሌሊቱ፡፡ /የዚህ ሰውዬ ቤተሰብ አባል ከመሆን ያዳነን እግዚሃር ምስጋና ይግባው አቦ !/
‹‹ሚስቴን እወዳታለሁ፤ ባለቤቴን እወደዋለሁ፤ በፍቅር የማምን ሰው ነኝ፤ ባለቤቴ ሕይወቴ፤ ሚስቴ ማለት እናቴ፤ ፍቅር ሰጥቶ ፍቅር የሚቀበል ጓደኛ አለኝ፡፡ ልጆቼ፣ ጌጦቼ…›› ዓይነት የታዋቂ ሰዎችን ዲስኩር በመጽሔትና በጋዜጣ ማንበብ፤ እንዲሁም በቴሌቪዥን እና በሬዲዮ ማየት እና ማድመጥ የለመድነው ጉዳይ ነው፡፡
እንደ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ አባት ሁሉ፣ ‹‹ሚስቱ ማለት አገልጋዩ፣ እጮኛው ማለት የስጋ ፈቃድን ከማሟያ ውጪ ትርጉም የሌላት፣ ልጆቹ ማለት በሞቅታ ከደካከመ በኋላ ማታ መጥቶ ኮርኩሞ የሚያስተኛቸው ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ገመና ነውና በሚዲያው በኩል ወደ አደባባይ ሲወጣ የቅድስናን ካባ ለራሱና ለጎጆው ያለከልካይ ይሸልማል፡፡ /‹‹ለምን ይዋሻል?›› አለ ኮሜዲያን ተስፋዬ ካሣ!/
አስታውሳለሁ አንድ ጊዜ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እንግዳ ሆኖ የቀረበ አንድ አርቲስት፣ /‹‹አርቲስት የብዙ ጥበበኞች መጠሪያ በመሆኑ የባለታሪኩን ማንነት ለመሸሸግ ጠቅሞኛል/ ስለ ትዳሩ ሲናገር፣ ‹‹ባለቤቴ ለእኔ ሙሉ ሰው መሆን የተጫወተችው ሚና ቀላል አይደለም፡፡ እሷ ማለት ለእኔ ከምንም በላይ ናት፤ እሷ ከእግዚአብሔር የተሰጠቺኝ ድንቅ ስጦታ ናት፡፡ የእኔ የዛሬው ማንነቴ ካለእርሷ የማይታሰብ ነው!›› ይላል፡፡
ይህን ውዳሴውን ባዘነበ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አንድ መጽሔት ላይ ስለአርቲስቱ እንዲህ የሚል ዜና ወጣ፤ ‹‹የአርቲስቱ የረዥም ዓመታት ትዳር ፈረሰ !›› የሚል፡፡ አስገራሚው ነገር ዜናው አይደለም፤ ለምን ትዳሩን እንደፈታ የተጠየቀው አርቲስት ሲናገር፣ ትዳሩ ለዓመታት በውዝግብ የተሞላ እንደነበር በቃለ መጠይቁ ላይ መግለፁ እንጂ፡፡
‹‹ያምራል ብለው ከተናገሩት ይከፋል ብለው የተዉት ይሻላል !›› እንዲሉ አባቶች አንዳንድ ጊዜ ለመልካም ገፅታ ግንባታ ተብሎ የሚነገር ነገር ውሎ አድሮ የሚያመጣው መዘዝ ብዙ ነውና እንደው ታዋቂ ሰዎች ስትናገሩ ጠንቀቅ ብትሉ መልካም ነው፡፡ /የዚህ ጽሑፍ ጸሐፊ ምክር ነው/
‹‹መጠንቀቅ ማለት ግን በዝምታ ራስን መሸበብ ወይም እውነታውን ለመግለፅ አለመፍቀድ ማለት እንዳልሆነ ደግሞ ብንረዳ ሸጋ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም እሠራበት ለነበረ አንድ መጽሔት አንድ ታዋቂ አርቲስት ቃለ መጠይቅ ሳደርግለት በመጀመሪያ ያሳሰበኝ ነገር ቢኖር የትዳሩን ሁኔታ እንዳልጠይቀው ነበር፡፡ ሰውየውን በቅርበት አውቀው ነበርና፣ ‹‹ለምን?›› አልኩ ተገርሜ፡፡ ‹‹አይ ጥሩ አይደለም !›› በሚል ኮስተር ያለ አጭር መልስ ነገሩን ዘጋው፡፡ ሰውየው ባለትዳር እና ሁለት ልጆች ያሉት ነበር፡፡
እግዚኦ! የአንዳንዱ ሰው ሥጋ ደካማነት ደግሞ ያለቅጥ የበዛ ነው፡፡ ይህ አርቲስት የትዳር ሁኔታውን እንዳይጠየቅ የፈለገበትን ምክንያት እኔ ስጠረጥር፣ ስለትዳሩ እውነተኛ መረጃ ካቀበለ በሥጋ ፈቃድ ዐይን የሚያያቸውን ቆነጃጅት ያጣል፡፡ እነእርሱን ከሚያጣ ደግሞ እንጀራ የሚበላበትን ሙያ ቢያጣ ይመርጣል፡፡ ስለምን? ቆነጃጅቱ ራሳቸው የእንጀራው አካል ናቸውና፡፡ /ለምንድነው ግን አብዛኛው የጥበብ ሰው የትዳር ሁኔታውን እና ገቢውን ሲጠየቅ የሚበሳጨው?/
በጥቅሉ በታዋቂ ሰዎች እንዲህ ዓይነቱ ገመና በቅርብ ሆነው እንዲዝናኑ የተፈቀደላቸው ብቸኛ ሰዎች ቤተሰብ፣ ቤተ ዘመድ እና ጎረቤት ብቻ ናቸው፡፡ አዎና ! ጥቂት የማይባሉ ህፃናት በቴሌቭዥን ብቻ እያዩት እንደሱ ለመሆን የሚመኙት ‹‹ታዋቂው›› ሰው ባለቤቱን እንደ ኳስ እየለጋ እየኖረ ሚዲያ ላይ ሲቀርብ ግን፣ ‹‹ሚስቴ ማለት እናቴ !›› ሲል እንደማየት ምን የሚያዝናና ነገር ይኖራል!? …ምንም!
የሚሠሩት ፊልም ‹‹ሮማንስ›› እና ‹‹ኮሜዲ›› ሆኖ በእውኑ ዓለም ደግሞ ለቤተሰባቸው ‹‹ሆረር›› የሆኑ ተዋንያን እንዳሉ ለመታዘብ የሚታደሉት እነዚህ ሰዎች ብቻ ናቸው፡፡ /እውነትም ታድለው! ጥሩ መዝናኛ ሳይኖራቸው አይቀርም/
ወደ ተዋንያን ከመጣን አይቀር በዚሁ ጨዋታችንን እንቀጥል፡፡ በመጽሔት ወይም በጋዜጣ ላይ የሚደረግላቸውን ቃለ ምልልስ ሳነብ ከሚያዝናኑኝ ግለሰቦች ዋነኞቹ ተዋንያን ናቸው፡፡ /አንዳንድ ተዋንያን ለማለት ነው/ በተለይ፣ ‹‹የምትሠራውን የፊልም ተውኔት ትመርጣለህ? ወይስ…?›› ለሚለው ጥያቄ የሚሰጡት መልስ፡፡
‹‹ይገርምሃል፤ እኔ እንደ ሌሎች ተዋንያን አይደለሁም፡፡ የምሠራው በቅድሚያ ‹ስክሪፕት› አይቼ ነው፡፡ ‹ስክሪፕቱ› ጥሩ ካልሆነ ሲጀመር ድርድር ውስጥ አልገባም፡፡ ‹ስክሪፕቱ› ምርጥ ከሆነ ግን ለመሥራት ዐይኔን አላሽም፡፡ ዋናው ‹ስክሪፕቱ› ነው፡፡››
አንዳንድ ብለን ከጠቀስናቸው እንዲህ ባይ ተዋንያን አብዛኞቹ ግን የሚሠሩት ፊልም ወይም ቴአትር የቆየ ስማቸውን የሚያድስ ሳይሆን የሚንድ፣ የሰጠናቸውን አንቱታ የሚያረዝም ሳይሆን የሚያሳጥርና የሚያረክስ ሆኖ መገኘቱ፣ ‹‹እነዚህ ሰዎች ያወሩት ስለምን ነበር?›› ያሰኛል፡፡ /ኧረ ሙሉ ‹‹ስክሪፕት›› አንብቦ የሚተውነው ተዋናይ እጅግ በጣም ጥቂት ነው አሉ ! …ሕም !/
ለነገሩ አብዛኞቹ የጥበብ ሰዎች በጥሩ ፎቶ እንጂ በጥሩ ንግግር አይታሙም፡፡ /ጎበዝ፤ እንዘንላቸው እንጂ! ንግግሩን ከየት ያመጡታል?/ ልብ ብለን ከተከታተልናቸው የሚነግሩን ነገር ከሠሩት ፊልም ወይም ቴአትር የተወሰደ ቃለ ንባብ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለሆነም አንድ ተዋናይ፣ ‹‹አየህ ለእኔ ሕይወት ማለት…›› ብሎ መናገር ሲጀምር መጠርጠር ይኖርብናል ማለት ነው፡፡
ጨዋ ተዋናይ፣ ‹‹አሁን ስለ ራሴ ከነገርኩህ ውስጥ ከስሜ፣ ከዕድሜዬ፣ ከሰፈሬና ከልጆቼ እናት ስም ውጪ የሰጠሁህ ቃለ መጠይቅ፣ ‹‹ይጮኻል ደሙ›› በሚል ርዕስ ከሠራሁት ፊልም ላይ የወሰድኩት ነው፡፡›› ብሎ ምንጭ ይጠቅሳል፡፡
ኧረ ‹‹ታዋቂዎቻችን›› እንደ ስማችሁ ጥሩ ሥራና ጥሩ ንግግር ምረጡ፡፡ ‹‹ያምራል ብለው ከተናገሩት እና ያምራል ብለው ከሠሩት ይከፋል ብለው የተዉት ይሻላልና፡፡››

No comments:

Post a Comment