Tuesday, May 28, 2013

አባይ ተፈጥሯዊ አቅጣጫውን ቀየረ


























አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 20 ፣ 2005 (ኤፍ. ቢ .ሲ) ለታላቁ  የኢትዮጵያ  ህዳሴ ግድብ  ግንባታ  አመቺነት  የአባይ  ወንዝን ተፈጥሯዊ  አቅጣጫ  የማስቀየር  ስራ ሲከናወን  ቆይቷል ።
ይህ  ስራ  ተጠናቆ ዛሬ ወንዙ  በይፋ ተፈጥሯዊ አቅጣጫውን ቀይሯል ።
የወንዙን  ተፈጥሯዊ አቅጣጫ  የማስቀየሩን  ተግባር ይፋ ለማድረግ  በተዘጋጀ ስነ ሰርዓት ላይም የተገኙት የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ  ሚኒስትርና  የትምህርት ሚኒስትር አቶ ደመቀ  መኮንን  እለቱ አባይን  በፈለግንበት መስመር የምናስኬድበት ቀን  ብለዋል ።
“ስር በሰደደ ድህነታችን ምክንያት በፈለግነው ሳይሆን እሱ ባሰኘው መንገድ ሲፈስ ቆይቷል” ያሉት አቶ ደመቀ ፥  “አሁን አባይን በመዳፋችን ውስጥ እንዲገባ  አድርገናል” ነው ያሉት  ።
አባይ እጣ  ፈንታው በእጃችን እንዲሆንና  በታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ እኛ  በመራንበት እንዲጓዝ ማድረጋችን የኢትዮጵያንና  የአፍሪካን ህዳሴ የሚያመላክት መሆኑንም  ተናግረዋል ።
እንደ አቶ ደመቀ ንግግር እለቱም  ከግንቦት 20 ጋር  መገናኘቱም  ልዩ  ትርጉም ያለው ይሆናል ።
በዚህ  ታሪካዊ እለት  ከአገሪቱ ማህፀን ፈልቆ ኢትዮጵያን የበይ ተመልካች ያደረገው አባይ በኢትዮጵያ  መዳፍ ላይ መውደቁ  እለቱን የድርብርብ ታሪክ ባለቤት ያደርገዋልም ነው ያሉት ።
ምክትል  ጠቅላይ  ሚኒስትሩ እንዳሉት ፥ የዚህ  ታላቅ  ፕሮጀክት ጠንሳሽ አቶ መለስ ዜናዊ የተሰዉለት ዓላማ  የጠራ መሆኑንና  የመላውን ህዝብ ድጋፍ ማግኘቱንም ያረጋገጠም ሆኗል ።
አገራዊው ደስታ ሙሉ የሚሆነው  ግድቡ ስራ ሲጀመር በመሆኑም  ህዝቡ ድጋፉን እንዲቀጥል ጠይቀዋል ።
በግድቡ  ግንባታ  ሂደት  አራት አበይት  ክንውኖች አሉ ያሉት የኢፌዴሪ የውሃና  ኤኔርጂ ሚኒስትር አቶ ዓለማየሁ የተገኑ ደግሞ ፥  ዛሬም በይፋ የተከናወነው  የወንዙን ተፈጥሯዊ አቅጣጫ  የማስቀየር ስራ  አንዱ ነው ብለዋል ።
የወንዙ ተፈጥሯዊ አቅጣጫ  መቀየር የአይችሉም አመለካከትን  በከፍተኛ  ደረጃ የሚያከስምና  ኢትዮጵያ ወንዙን ማልማት እንደምትችል የሚያሳይም ነው።
አቅጣጫውን ማስቀየር ለምን አስፈለገ ?
ወንዙ  የሚገኘው ግድቡ በሚገነባው  መሃል ላይ ሲሆን ፥  ወንዙ እየፈሰሰ  ግድቡን መገንባት የማይቻል በመሆኑ ነው  ተፈጥሯዊ  አቅጣጫውን ማስቀየር ያስፈለገው ።
አቅጣጫ  የማስቀየሩ ስራ በግንብታው  ሂደት  አስቸጋሪ ስራ መሆኑን  የሚናገሩት  የኢትዮጵያ  ኤሌክትሪክ ሀይል  ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ምህረት  ደበበ  ፥ ስራውም  እጅግ  ከፍተኛ ጥረት  ውጤት መሆኑን  አመልክተዋል ።
የግድቡ ፕሮጀክት ዋና ስራ  አስኪያጅ  ኢንጂነር ስመኘው በቀለ በበኩላቸው ፥ የወንዙን  አቅጣጫ  የማስቀየሩ  ስራ ከተያዘለት ጊዜ በሁለት ሳምንት  ቀደም ብሎ መጠናቀቁን  በመጠቆም ይህ ስራዎች ከተያዘላቸው  ጊዜ  ቀደም ብለው  በፍጥነት  እየተከናወኑ መሆናቸውን እንደሚያሳይ ነው  ያመለከቱት ።
በአሁኑ  ወቅትም የታላቁ  የኢትዮጵያ  ህዳሴ  ግድብ ግንባታ 21 በመቶ መጠናቀቁ  ተመልክቷል ።
 www.fanabc.com







No comments:

Post a Comment